“ሰው አዎንታዊ አስተሳሰብን መተግበር ሲጀምር፡- ክፋትን፤ተንኮልንና ምቀኝነትን ያስወግዳል፡፡ የራሱ ያልሆነ ነገር
መመኘትን፤ በማይጠቅም ነገር ላይ መጠመድን/ጊዜ ማባከንን ያቆማል፡፡ በአጠቃላይ የማይጠቅሙ፤ ጊዜውን በከንቱ
የሚያባክኑ፤ ጤናውን የሚያውኩ፤ ግንኙነቱን የሚያበላሹ ሃሳቦችንና አመለካከቶችን ከውስጡ ያወጣል፡፡--
በአንድ ወቅት አንድ ታዋቂ ት/ቤት በትምህርት ዘመኑ መጨረሻ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና ለመስጠት የሽልማት መርሃ ግብር አዘጋጅቶ፣ የተማሪ ወላጆችንና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ግለሰቦች ጋበዘ፡፡ በእለቱ በርካታ ታዳሚዎች በአዳራሹ ተገኝተው፣ የመርሃ ግብሩን መጀመር በጉጉት ይጠባበቃሉ፡፡ ከዚያም የመድረክ አጋፋሪው ብቅ ብሎ የሞላውን አዳራሽ ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከቀኝ ወደ ግራ በአይኑ ካማተረ በኋላ፣ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፎና የእለቱን መርሃ ግብር አስተዋውቆ ሲጨርስ፣ የትምህርት ቤቱን ርእሰ መምህር ወደ መድረክ ጋብዞ ወደመጣበት ተመለሰ፡፡
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ርእሰ መምህሩ በደማቅ ፈገግታቸው መድረኩን አሞቁት፡ ርእሰ መምህሩ ደስታ፤ እርካታ፡ ተስፋና አዎንታዊነት ይነበብባቸው ነበር፡፡ ቀጥሎም ታዳሚውን አመስግነው ለእለቱ በተመረጡ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን ከሰነዘሩ በኋላ፣ በቀጥታ የሽልማት መርሃ ግብሩን ለመጀመር የተማሪዎች ስም ዝርዝር የያዘውን ማስታወሻ ገለጡና የአንድ ተማሪ ስም ተጠራ፤ ይህ ተማሪ በሁሉም የትምህርት አይነቶች ከመቶ መቶ በማምጣት የመጀመሪያው ተሸላሚ በመሆኑ ስለ እርሱ ጉብዝናና ጥንካሬ ተናግረው ሽልማቱንና ሰርተፊኬቱን ሰጡት፡፡ በዚህን ጊዜ አዳራሹ በጭብጨባ፣ በፉጨትና በጩኸት ተናወጠ፡፡
ዳይሬክተሩ ለጥቂት ደቂቃዎች ቆም ብለው ሁካታውን ከተመለከቱ በኋላ የሚቀጥለውን ተሸላሚ ለመጥራት ማስታወሻቸውን ሲገልጡ ጩኸቱ ትንሽ ጋብ ማለት ጀመረ፤ ከዝርዝሩ መሃል የአንድ ተማሪ ስም ሲጠራ የተጠራውን ተማሪ ማንነት ለማየትና የሚባለውን ለመስማት ሁሉም ጸጥ አለ፡ የስም ጥሪውን ሰምቶ የወጣ ተማሪ የለም፤ ታዳሚውም በጸጥታ ሂደቱን ይከታተላል፡፡ የተማሪው ስም ለሁለተኛ ጊዜ ተጠራ፤ አሁንም ብቅ ያለ አልነበረም፤ ተመልካቹ ግራ ተጋባ፤ ለሦስተኛ ጊዜ ተደገመ ፤ በዚህ ጊዜ አንድ የደነገጠ የሚመስል፣ ፊቱ በላብ የራሰና መራመድ ያቃተው ተማሪ ከአንድ ጥግ ተነስቶ እየተንገዳገደ መድረክ አካባቢ ከደረሰ በኋላ መራመድ አቅቶት ቆመ፡፡ ርእሰ መምህሩ በፍቅርና በስስት እየተመለከቱት ወደ እርሳቸው እንዲቀርብ ምልክት አሳዩትና ወደ መድረኩ ወጣ፡፡
”ይህ ተማሪ“ አሉ ርእሰ መምህሩ እጃቸውን ትከሻው ላይ ጣል አድርገው ስሙን እየጠሩ፤ ”በሁሉም የትምህርት አይነቶች የወደቀ በመሆኑ በትምህርት ቤታችን ታሪክ የመጀመሪያው ተማሪ ነው፤ ነገር ግን በትህትናው ከሁሉም ተማሪ ይበልጣል፤ እንደሱ ያለ ትሁት ተማሪ በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ አጋጥሞኝ አያውቅም“ ካሉ በኋላ “እመኑኝ፤ በሚቀጥለው አመት ጠንክሮ ይሰራል፤ ጎበዝ ተማሪ ይሆናል ፤ጥሩ ውጤት ያመጣል” በማለት የተዘጋጀለትን ሽልማትና ሰርተፊኬት ሰጡት፤ ይህም ያልተለመደ ድርጊት በመሆኑ ታዳሚውን አስደመሙት፡፡
የወደቀ ተማሪ ይገሰጻል፤ ይዘለፋል፤ ይገለላል፤ መጠቋቆሚያም ይሆናል፡፡ እኚህ ሰው ግን ባዳበሩት አዎንታዊ እይታ፤ በተማሪው መውደቅ ላይ ሳይሆን ውስጡ ባለው ጥንካሬ ላይ በማተኮር ችግሩ እንዲፈታ፤ ጥንካሬው ጎልቶ እንዲወጣና ነገ ትልቅ እንዲሆን አበረታቱት፤ ሸለሙት፤ ተስፋው እንዲለመልም አደረጉት፡፡ እንደተባለውም ተማሪው በሚወዳቸው ትምህርቶች ላይ በማተኮርና ጠንክሮ በመሥራት ከጎበዝ ተማሪዎች ጎራ መሰለፍ ጀመረ፤ ስኬታማ ሆነ፤ ብሎም የሂሳብ፤ የፊዚክስና የስነፈለክ ቀመሮችን ለአለም ያበረከተ ትልቅ ሳይንቲስት ሆነ፡፡
“እኔ አዎንታዊ ስሆን ጥቅሙ ለኔ ብቻ ሳይሆን በዙሪያዬ ላሉ ሁሉ ነው”
[ Harvey Mackay ]
የሰው ልጅ አዕምሮ በየደቂቃውና በየሰከንዱ የተለያዩ ሃሳቦችን፤አመለካከቶችንና ስሜቶችን ማፍለቅ የሚችል ፈጣን ኃይል ነው፤ ሰዎች አዕምሯቸውን ተጠቅመው በፈለጉት መልክ የፈለጉትን ነገር መስራት፤ በፈለጉት ስኬት ላይ መድረስ፤ እራሳቸውን ፤ማህበረሰባቸውንና ብሎም ሃገራቸውን ማሳደግ ይችላሉ፡ ይሁን እንጂ አዕምሮ ሁለት (መጥፎና ጥሩ) መስመሮችን ዘርግቶ የሰዎችን ምርጫ ይጠብቃል፡፡ ሰዎች አዕምሮአቸውን በአዎንታዊ መንገድ የሚያለማምዱ ከሆነ ለጥሩ ሥራ/ ለስኬት፤ለእድገት ይጠቀሙበታል፤ አሊያም ደግሞ ለመጥፎ ነገር / ለጥፋት ፤ ለውድቀት ይጠቀሙበታል፡፡ ስለዚህ ሰዎች አዕምሯቸው ከሚያፈልቅላቸው መልካም ነገሮች ሁሉ ተጠቅመው እራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን በመጥቀም፤ ለውጥ ለማምጣትና ከጥፋት ለመዳን ወይም ለማዳን፤ ወደ ምድር የመጡበትን ዓላማ አሳክተው ለመሄድ አዕምሯቸውን በአዎንታዊ እይታዎች ማለማመድ ይኖርባቸዋል፡፡
አዎንታዊ አስተሳሰብ ምንድነው?
በሰው ልጅ የእለት ተእለት የህይወት እንቅስቃሴ ውስጥ ሰዎች የህይወት ፈተናዎችን በአዎንታዊ እይታ በመቅረብና አመለካከትን በማሻሻል፣ ደህንነትና ሰላምን ማስፈን የሚችሉበት፤ ፍቅርን፣ መተሳሰብን፣ መደጋገፍን፣ መረዳዳትን ማሳደግ የሚችሉበት፤ ስኬትን ማምጣት የሚያስችል ለትውልድ የሚተርፍ ለሃገር እድገት የሚበጅ መልካም ሥራዎችን ማከናወን የሚስችል በብሩህ አስተሳሰቦችና እምነቶች ላይ ትኩረት የሚያደርግ የአዕምሮ አስተሳሰብ ነው፡፡ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ የበጎ ሰው ተሸላሚው አምባሳደር ዘውዴ ረታ በአዎንታዊ አስተሳሰብ ዙሪያ ሲናገሩ፤ ደካማነትንና ስንፍናን አስወግዶ ለስኬት የሚያበቃ የቅኖች መንገድ ነው ብለው ነበር፡፡ በመሆኑም በማንኛውም ጊዜና ሰዓት በአለም ላይ የሚተገበሩ ክንውኖችን፣ ልምዶችንና የሚፈጠሩ ክስተቶችን በጥሩ ጎን በማየት፤ ከሚፈጠሩ ችግሮችና እንቅፋቶች ትምህርት በመውሰድና በተሻለ ጥቅም ላይ በማዋል ግላዊ ፤ ማህበራዊና ሃገራዊ እድገት ማምጣት የሚያስችል የመልካም እሳቤ ሰፊ ጎዳና ነው ማለት ይቻላል፡፡
አዎንታዊ አስተሳሰብ የሕይወትን በጎ ገጽታና የሌሎችን መልካም ነገር ማየት መቻል፤ በራስ የመተማመን ስሜትን ማዳበር፤ ከችግሮች መማርና ችግር ፈቺነትን መላበስ ብሎም እራስን፤ ቤተሰብን፤ ማህበረሰብንና ሃገርን መለወጥ የሚያስችል የይቻላል ኃይልን መጎናጸፍ ቢሆንም፡ በሌላ መልኩ አዎንታዊ አስተሳሰብ ሕይወት ጭራሽ መጥፎ ጎን የላትም ብሎ ማሰብ፤ የሕይወትን መጥፎ ገጽታዎችን ላለማየትና ላለመስማት መወሰን/ እራስን ማሸሽ ወይም ግዴታ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማስወገድ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ችግሮችን እንደየ አመጣጣቸው ተቀብሎ ለመፍትሄው መስራት፤ ወደ በጎ መቀየር፤ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉትን ለይቶ በመልካም ሥራ ላይ ማዋል፤ በሌሎች ውስጥ ያለውን ምርጥ ነገር ማየት መቻልና እራስንም ሆነ ሌሎችን በአዎንታዊ እይታ መመልከት ማለት ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአዎንታዊ አስተሳሰብ መገለጫዎች በርካታ ቢሆኑም ለዚህ ጽሁፍ ይጠቅማሉ ተብለው ከተወሰዱት ውስጥ፡-
ከእራስ ጋር ፤ ከአካባቢ ማህበረሰብና ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶና ተግባብቶ መኖር፤
የእራስንም ሆነ የሌሎችን የእለት ተእለት የሕይወት እንቅስቃሴ ፤ አስተሳሰብና አመለካከት፤ በበጎ መመልከት፤
በሕይወት ጉዞ ላይ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችንና ችግሮችን እንደየ አመጣጣቸው ተቀብሎ አዎንታዊ ምላሽ መስጠትና ከችግሮቹ መማር፤
የችግር ፈቺነትን ባህሪይ መላበስ፤
ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ፤
በሌሎች ውሰጥ ያሉ ጥሩ ፤ጥሩ ነገሮችን መመልከት መቻል፤
በራስ በመተማመን ለስኬትና ለለውጥ መትጋት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
አዎንታዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች፦ ጥሩ የአእምሮና የአካል ጤንነት፣ ጥሩ ግንኙነት፤ ጥሩ የመስራት፤ የመከወንና ውሳኔ የመስጠት ብቃትን የተጎናጸፉ፤ ጠንካራ በራስ የመተማመን ስሜት ያላቸው፤ ደስታንና ስኬትን ለማግኘት አዎንታዊ አስተሳሰብን በእለት ተእለት የሕይወት ጉዞአቸው የሚተገብሩ፤ ብሩህ እይታዎችን በማሳደግ በመልካም ነገሮች ላይ የሚያተኩሩ፤ የችግር መፍቻ መንገዶችን በመማር፤ በእራስም ሆነ በአካባቢ ማህበረሰብ ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን በመፍታት ለውጥ የሚያመጡ፤ በግልም ሆነ በሙያዊ ህይወታቸው የላቀ የስኬት ማማ ላይ የሚደርሱ እንደሆኑ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
የአዎንታዊ አስተሳሰብ ጥቅሞች፡-
አዎንታዊ አስተሳሰብ፡- አዕምሯዊ፤ ስነልቦናዊና አካላዊ ጤንነትን ከመጠበቅ፣ ግላዊና ማህበራዊ ግንኙነቶችን ከማጠናክር፤ የችግር አፈታት ክህሎቶችን ከማጎልበት፤ ስኬታማነትን፣ ሃገራዊ እድገትንና ሰላምን ከማስፈን ሂደት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ የአስተሳሰብ ሥርዓት ሲሆን፤ በእያንዳንዱ የሰው ልጅ የሕይወት ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ጥቅሞችን ያበረክታል፡፡
አዎንታዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች፡-
አዎንታዊ እሳቤዎችን ከአሉታዊ በመለየት አዎንታዊውን ተቀብለው አሉታዊውን በቀላሉ መሸኘት ስለሚችሉ በእራሳቸው የሚተማመኑ፤ ከያንዳንዱ የሕይወት ገጠመኝ እራሳቸውን የሚያስተምሩ፤ ክህሎታቸውን የሚያሳድጉ ብሎም እራስን፤ ህብረተሰብንና ሃገርን የመቀየር ትልቅ ሕልም ሰንቀው የሚጓዙ ናቸው፡፡
ሰው አዎንታዊ አስተሳሰብን መተግበር ሲጀምር ፡-
ክፋትን፤ተንኮልንና ምቀኝነትን ያስወግዳል፡፡ የራሱ ያልሆነ ነገር መመኘትን፤ በማይጠቅም ነገር ላይ መጠመድን/ጊዜ ማባከንን ያቆማል፡፡ በአጠቃላይ የማይጠቅሙ፤ ጊዜውን በከንቱ የሚያባክኑ ጤናውን የሚያውኩ፤ ግንኙነቱን የሚያበላሹ ሃሳቦችንና አመለካከቶችን ከውስጡ ያወጣል፡፡ በምትኩ ለራሱ፤ ለሌሎችና ለሃገር የሚጠቅሙ በጎ፤ በጎ ጉዳዮችን ለማሰብ፤ ፍቅርን ለመዝራት፤ ችግሮችን ለመፍታትና ለትክክለኛ ስኬት መሮጥ ስለሚጀምር ከጭንቀት፤ ከድብርትና ከብስጭት የጸዳ፤ ጤናማ፤ስኬታማ ለሃገርና ለወገን የሚጠቅም ይሆናል፡፡
አዎንታዊ አስተሳሰብን መመሪያው ያደረገ ሰው፡-
ትልቅ ሕልም ያለው ለስኬት የሚተጋ፤ እራሱን የሚያነቃቃና የሚያበረታታ፤ የይቻላልን ስሜት የተላበሰ ጠንካራ የተግባር ሰው በመሆኑ ስኬታማ ይሆናል፤ ከራሱ አልፎ ሃገርንና ወገንን ይጠቅማል፡፡
አዎንታዊ አስተሳሰብን ባህሪይው ያደረገ ሰው፡-
የአኗኗር፤ የአመጋገብ የአካሄድ፤ የአሰራርና የግንኙነት ዘይቤዎቹ ሁሉ ትክክለኛውን የአኗኗር ስልት ጠብቀው ስለሚጓዙ - የተስተካከለና አስተማማኝ አካላዊ ጤንነትንና ደስተኛነትን ይቀዳጃል፡፡ ከዚህም የተነሳ፡-
የተስተካከለ የጤንነት አቋም ይኖረዋል፤
ከፍተኛ በሽታን የመቋቋም / የመከላከል አቅም አለው፤
ረጅም እድሜ የመኖር እድሉ ሰፊ ነው፤
አደገኛ የሚባሉ የህመም አይነቶችን (የስኳር፤ ከፍተኛ የደም ግፊትና የልብ በሽታዎችን) የመከላከል ወይም የማቆም አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡
ይህን የአስተሳሰብ ስርዓት የተላበሰ ሰው፡-
ከእራሱ፤ ከአካባቢው ማህበረሰብና ከተፈጥሮ ጋር ጥሩ ግንኙነትን በመፍጠር ከሁሉም ጋር ተግባብቶና ተስማምቶ ይኖራል፡፡ በመሆኑም ፡-
ጠንካራና ደካማ ጎኑን በመለየት የጎደለውን ለመሙላት ብሎም ክህሎቱን ለማሳደግና የተሻለ ነገር ለመስራት እራሱን ያስባል፤ ከራሱ ጋር ይነጋገራል፤ እራሱን ይገመግማል ፤ምክርና ትችቶችን በፍቅር ይቀበላል፤ ውሳኔ ላይ ይደርሳል ፤ እራሱን ይቀይራል፡፡
ሰዎችን ያከብራል፤ በትህትና ይቀርባል፤ ያዳምጣቸዋል፤ ችግራቸውን ይረዳል፤ ይተባበራል፤ ተጋግዞና ተደጋግፎ በማደግ ያምናል፤ ያለውን እውቀት ለሌሎች ያካፍላል/ያስተምራል፤ ችግሮችን ለመፍታት ጠንክሮ ይሰራል፡፡
ተፈጥሮንና አካባቢን ይንከባከባል፤ ጽዱና የተዋበ አካባቢን ለመፍጠር ተግቶ ይሰራል፤ በዚህም ምክንያት ከእራሱ፤ ከተፈጥሮም ሆነ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተስማምቶና ተግባብቶ፤ በሰላምና በደስታ ይኖራል፤ ሌሎችንም ደስተኛ ያደርጋል፡፡
በአጠቃላይ የአዎንታዊ አመለካከት ዋነኛ ጠቀሜታ አእምሯዊ፤ ስነልቡናዊና አካላዊ ጤንነቱ የተሟላ፤ ጥሩ ግንኙነትን መተግበር የሚችል፤ መተባበርን፤ መደጋገፍንና መደማመጥን ባህሉ ያደረገ፤ችግር ፈቺነትን የተላበሰ ሙሉ ሰብእና እና ለትልቅ ሕልም የሚተጋ፣ ሰላሙ የተረጋገጠ ማህበረሰብ መፍጠር ሲሆን፤ ይህም በአንድ አገር ውስጥ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንና ሁለንተናዊ እድገትን ለማምጣት ቁልፍ መሳሪያ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ያስተምራሉ፡፡ ሰላም፤ ፍቅር፤ ስኬት፤ እድገት የሚባሉ ጉዳዮች መነሻቸው ግለሰብ ቢሆንም፣ ወደ ማህበረሰብ የማይዛመቱ ከሆነ እንደ ሃገር ለውጥ ሊያስመዘግቡ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ግለሰብ ያለ ማሕበረሰብ፤ ማሕበረሰብ ያለ ሕብረተሰብ /ሕዝብ፤ ሕዝብ ያለ ሃገር፤ ሃገርም ያለ ሕዝብ መኖር ወይም ማደግ አይችሉምና፡፡
በዚህ ምክንያት ነው እንግዲህ አዎንታዊ አስተሳሰብን ገንዘቡ ያደረገ ማህበረሰብ መፍጠር ወሳኝና በይደር የማይታለፍ ጉዳይ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን አጥብቀው የሚመክሩት፡፡
Saturday, 20 July 2024 21:12
የአዎንታዊ አስተሳሰብ ፋይዳ
Written by ሙሉእመቤት ጌታቸው
Published in
ህብረተሰብ