• አዲስ አበባ ፈካ፣ ጸዳ፣ ነቃ ነቃ ያለችበት ዓመት ነው 2016።
• ከተማዋ ቀንና ሌሊት በሥራ የተጠመደችበት ዓመትም ነው
በጥበብ ካልተጉ 18091 ሺ ፕሮጀክቶችን መሥራትና አሳምረው ለውጤት ማድረስ፣ ጀምረው መጨረስ አይችሉም።
ዓመቱን ሙሉ በብርቱ ተምረው ከሠሩ ነው የፈተና ውጤት የሚያምረው፤ የወደፊት ተስፋ የሚፈካው፤ መንፈስ የሚነቃቃው። እንቁጣጣሹም ከተማውም የሚደምቀው።
የሌሎች አድናቂና የዳር ተመልካች ሆነን የምንቀርበት ምክንያት የለም የሚል የእልህ ስሜት ውስጣችን ሲያነሣሣ፣ በዚህም ሌት ተቀን ስንሠራ፣ በሙያ ፍቅርና በብርቱ መንፈስ ስንጥር ነው፣ ኑሮም አገርም በበጎ የሚቀየረው።
ደግሞም መልካም የሥራ ውጤት ሲያዩ የብዙዎች መንፈስ እየተነቃቃ ስሜታቸውንም እንደሚገልጹና ለሥራ እንደሚነሣሡ፣ የፒያሣ-አራት ኪሎ የኮሪደር ልማት የተመረቀ ጊዜ አይተናል። ይሄው በጎ መንፈስ በሌሎቹ የኮሪደር ልማት የምረቃ አጋጣሚዎችም ተመሳሳይ በጎ መንፈስ እየተደጋገመ ሲደምቅ ተመልክተናል።
ከተረጂነትና ከውርደት መላቀቅ ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ አኩሪ ታሪክ የሚመጥን አዲስ ተጨማሪ ታሪክ የማይፈጠርበት ምክንያት የለም። ወደ ዕድገትና ወደ ብልጽግና በመገሥገሥም አዲስ አበባ የሥራ መዲና፣ ኢትዮጵያ የስኬት ምሳሌ ተብለው እንዲጠቀሱ ማድረግም ይቻላል። እንደሚቻል ብቻ ሳይሆን፣ እውን እንደሚሆን ከንቲባዋ ሲገልጹ… ሌላ ምሥጢር የለውም፤ ሠርተን አገራችንን እንለውጣለን በማለት እንደተናገሩ እናስታውሳለን።
ዘንድሮ የተሠሩና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችም የዚህ ግሥጋሤ ጅምርና ምስክር ናቸው ማለት ይቻላል።
አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች በአካልና በግላጭ ደምቀው የሚታዩ ሥራዎች ናቸው። ከቅርብም ከሩቅም በርካታ ሺህ የከማዋ ነዋሪዎች ከየአካባቢያቸው እየመጡ የዐድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምን ጎብኝተዋል። በኮሪደር ልማት የተስፋፉና የተሻሻሉ መንገዶችን፣ አምረው የተሠሩ የእግረኛና የብስክሌት መስመሮችን፣ በዛፎችና በመብራቶች ደምቀው የተዋቡ አካባቢዎችን እየተዘዋወሩ አይተዋል። ዘና ለማለት ልጆቻቸውን ይዘው ጎራ ማለት ሲያዘወትሩም ታዝባችሁ ይሆናል። “የከተማዋን የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ሪፖርት በአካል እንደመመልከት” ልትቆጥሩት ትችላላችሁ።
በእርግጥ ሁሉንም ፕሮጀክት ሁሉንም የሥራ ውጤት እየዞርን የመጎብኘትና የመመልከት ዕድል ይኖረናል ማለት አይደለም። ግን ችግር የለውም። ከንቲባ አዳነች አቤቤና የቢሮ ኀላፊዎች ሰሞኑን ለከተማዋ ምክር ቤት ያቀረቡትን ዓመታዊ የሥራ ሪፖርት ዐጠር ዐጠር አድርገን መቃኘት እንችላለን።
ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል
ከግንባታው ግዙፍነትና ፍጥነት ጋር፣ በውበቱና በታሪካዊነቱ የተደነቅንበትና የኮራንበት የዓድዋ ድል መታሠቢያ ሙዚየም፣ የዓመቱ ማሳያ ዓርማ ነው። ግንባታው ሲጠናቀቅና ሲመረቅ ታስታውሳላችሁ። ድንቅ ነው።
በማግሥቱ ውስጣችንን ዙሪያችንን ስንመለከት ግን… በደስታና በምስጋና ንግግሮች ፋንታ፣ እልፍ ጥያቄዎች እየተደራረቡ ይመጣሉ። “ታዲያ ሌሎች እልፍ ፕሮጀክቶችስ ለምን በፍጥነትና በጥራት ማጠናቀቅ አይቻልም?” የሚሉ ሐሳቦች በሚሊዮኖች አእምሮ ውስጥ ይፈጠራሉ።
ታሪካዊው ሕንጻ ተገንብቶ በእውን ሲመረቅ በማየታችን የደስታና የእርካታ መንፈስ ባይርቀንም እንኳ… በቦታው የእልህ ስሜቶች እየተወለዱ፣ “ሌት ተቀን በመትጋት፣ ተጨማሪ ታሪክ መሥራት”… እያሉ ይወተውቱናል።
ከዚያ ወዲህ ብዙ ሥራዎች ሲፋጠኑና ሲጠናቀቁ ብናይ ታዲያ ምን ይገርማል?
የዐድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታ ብዙ ልምድ አግኝተንበታል በማለት በዓመታዊ ሪፖርት የተናገሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የፕሮጀክት ክትትልና አመራር ልምድ አግኝተንበታል። የኮሪደር ልማት በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን ጠቅሞናል ብለዋል።
የኮሪደር ልማትም በተራው፣ የከተማዋን የኢኮኖሚና የሥራ ከማፋጠን፣ ለኑሮ ጽዱና የተዋበ አካባቢ ከመፍጠር በተጨማሪ በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ እንደመጣ ከንቲባዋ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።
ግንባታዎችን በጥራት የመምራት “ዲሲፕሊንና” በፍጥነት ለውጤት የማብቃት ተጨማሪ ልምድ አግኝተናል።
የሥራ ባህል ለማሳደግ ችለናል ብለዋል - ከንቲባዋ።
በሕዝባችን ዘንድ የልማት ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል። ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ልማቱ ወደ አካባቢያቸው እንዲመጣ ጥያቄ እያቀረቡ ነው ሲሉ ከንቲባዋ ተናግረዋል።
በእርግጥም ደግሞ የኮሪደር ልማት በሌሎች አካባቢዎችም እንደሚቀጥል ከንቲባዋ ሲገልጹ፣ ጥናት የተካሄደባቸውና ለሥራ የተዘጋጁ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ጠቅሰዋል።
በሌላ አነጋገር፣ 2016 ዓ.ም. እልፍ የፕሮጀክቶች ስኬት የተመዘገበበት ዓመት ሆኗል። ይህም በሪፖርት እየተዘረዘረ ቀርቧል። ነገር ግን፣ በዚህ ብቻ ረክቶ መቀመጥ የለም። እንዲያውም ለሚቀጥለው ዓመት አስበልጦ ለመሥራት መነሻና መንደርደሪያ ብርታት እንደሚሆን ከንቲባዋ ጠቁመዋል። “የአዲስ አበባ ልማት ሁሉንም ማኅበረሰብ ያቀፈና ማንንም ወደኋላ ያልተወ ነው” ብለዋል።
እንግዲህ የመጪውን ዓመት ለመገመት የዘንድሮውን ማየት ነው።
በመንግሥትና በበጎ አድራጎት ሥራ ከ18091 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች የተጠናቀቁበት ዓመት
በፍጥነት እየተጠናቀቁ ለአገልግሎት ከበቁት ግንባታዎች መካከል አንዳንዶቹ “ሜጋ ፕሮጀክቶች” ተብለው የሚጠቀሱ ናቸው።
የዓደዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም
ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል
ቃሊቲ - ቱሉዲምቱ - ቂሊንጦ መንገድ ተሻጋሪ ድልድዮች
3 ግዙፍ የገበያ ማዕከላት
የጉለሌ የተቀናጀ ልማት
የፒያሣ አራት ኪሎ፣ የሜክሲኮ ሳር ቤት የመሳሰሉ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች
እስቲ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶችን ለማየት ሌሎችንም አለፍ አለፍ እያልን ለመጥቀስ እንሞክር።
’’ለነገዋ ’’10 ሺ ሴቶችን እየተቀበለ ሥልጠና የሚሰጥ ማዕከል
የተሻለ ይገባታል
የሴቶች ተሃድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ተገንብቶ ሥልጠናዎችን መስጠት ጀምሯል። ዕምቅ ዐቅማቸውን እንዲጠቀሙ፣ ሕይወታቸውን እንዲመሩ፣ ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ፣ ችግር ሳይበግራቸው እንዲያንሰራሩ፣ ከራሳቸውም አልፈው ለሌላ እንዲተርፉ ነው የሥልጠናዎቹ ፋይዳ።
የማዕከሉ ትልቅነት ከዩኒቨርስቲ አይተናነስም። በአንድ ጊዜ 10ሺ ሴቶችን ተቀብሎ ሥልጠና የመስጠት ዐቅም አለው። ግን ከዚያም በላይ ነው። ጠለላና ከለላ ይሆናል። ማደሪያ ክፍሎች ተሟልተውለታል። ለልብስና ለምግብ አይቸገሩም። የሴቶች ህልምና ራዕይ፣ መተማመኛና አለኝታ፣ ሥንቅና ተስፋ ነው ማለት ይቻላል።
“ቀዳማይ ልጅነት
(የሕፃናት ማቆያ እንክብካቤና ትምህርት)
አዲስ አበባ ህጻናት የሚያድጉባት ምቹ ከተማ
“የቀዳማይ ልጅነት” በሚል ስያሜ የተጀመሩት ፕሮጀክቶች፣ ዋና ዓላማቸው የሕፃናትን የአእምሮና የአካል ዕድገት ላይ ያተኮረ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ግን፣ በመቶ ሺ ለሚቆጠሩ ቤተሰቦችና ወላጆች ትልቅ ድጋፍ ይሆንላቸዋል። ልጆችን ለጎረቤቶች አደራ እየሰጡ፣ ከአክስትና ከአያት ጋር እንዲውል እየወሰዱ፣ ወደ መደበኛ ሥራ መሄድ በዛሬ ዘመን አይቻልም። ብዙ እናቶች ልጆችን ማሳደግ ማለት፣ በመደበኛ ሥራ ጋር መለያየትና ቤት ውስጥ መዋል ማለት ይሆንባቸዋል።
“የቀዳማይ ልጅነት” በሚል ስያሜ እየተስፋፉ ያሉ የሕፃናት ማቆያ አገልግሎቶች፣ ለልጆች ዕድገት ብቻ ሳይሆን ለሴቶች ትልቅ ትርጉም አላቸው። ሕፃናት በተለይ እናቶች በየተሰማሩበት የሙያና የሥራ መስክ ላይ የዕድገት ጉዟቸው እንዳይስተጓጎል ጥሩ ዕድል ያገኙበታል።
አዲስ አበባ “ሕፃናትን ለማሳደግ ምርጧ አፍሪካዊት ከተማ” ትሆናለች ብለን እየሠራን ነው። ከ320ሺ ገደማ ሕፃናት “የቀዳማይ ልጅነት ትምህርትና እንክብካቤ” እንዲያገኙ ክትትልና ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል - ከንቲባዋ።
ለዚህም ነው ከ3680 በላይ የመዋዕለ ሕፃናት መምህራን ሠልጥነው ወደ ሥራ የተሰማሩት።
5200 የሕፃናትንና የእናቶችን ጤንነት እንዲሁም የልጆችን ዕድገት ቤት ለቤት እየተከታተሉ ምክር የሚሰጡ ባለሙያዎችም ተመርቀው ሥራ ጀምረዋል።
10800 ነብሰ ጡር እናቶች እና ሕፃናት የአልሚ ምግብ ድጋፍ አግኝተዋል።
ዋናው ጤና - የትልልቅ ሆስፒታሎች ግንባታ!
ከ2.6 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች በጤና ተቋማት አገልግሎት እንደተስተናገዱና አገልግሎት እንዳገኙ ዓመታዊው ሪፖርት ይገልጻል። ብዙዎቹ ተመላላሽ ታካሚዎች ናቸው። በየጊዜው እየተስተናገዱ ሕክምናቸውን ይከታተላሉ፤ የጤና አገልግሎት ያገኛሉ። ለተመላላሽ ታካሚዎች የተሰጡ የአገልግሎት መስተንግዶዎች በአጠቃላይ ከ13 ሚሊየን ይበልጣሉ።
ከ190 ሺህ በላይ እናቶች የቅድመ ወሊድ ክትትል የጤና አገልግሎች እንዳገኙና በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች እንደጨመረ ገልጸው፣ በዚህም ምክንያቶ የእናቶች ሞት እንደቀነሰ ተናግረዋል።
የጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎት በመስፋፋቱ፣ ከመቶ ሺህ ወሊዶች ውስጥ በእናቶች ላይ የሚያጋጥመው የሞት አደጋ ከ34 በታች ሆኗል። ለታዳጊ አገራት በዓለም ጤና ድርጅት የወጣውን መስፈርትና በአገራዊ ራዕይ የተዘጋጀውን ግብ ለማሳካት ተችሏል። ግን በዚህ አያበቃም። የእናቶች ጤንነትና ደህንነት ይበልጥ እየተሻሻለ እንደሚሄድ አያጠራጥርም።
የሆስፒታሎችና የጤና ጣቢያዎች አገልግሎት እየተስፋፋ ቁጥራቸውም እየጨመረ ነው። የዘውዲቱ መታሰቢያና የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታሎች፣ እንዲሁም የራስ ደስታ ዳምጠውና የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታሎች ነባር ዐቅማቸውና አገልግሎታቸው እንዲስፋፋ፣ ተጨማሪ ሕንጻዎች እየተሠሩ ነው፤ የሙያ መሣሪያዎች እየተሟሉ ነው። የሕንጻዎቹ ግንባታ ከ50 በመቶ አልፏል።
ሦስት አዳዲስ ጤና ጣቢያዎች በአዲሱ ዓመት አገልግሎት እንዲጀምሩ እየተዘጋጁ ነው።
ሁለት ትልልቅ ሆስፒታሎችም እየተገነቡ ግማሽ ላይ ደርሰዋል። በሚቀጥለው ዓመት አገልግሎት ለመስጠት ይበቃሉ ብለዋል የጤና ቢሮ ኀላፊ ዶ/ር ዮሐንስ።
በኮልፌ ቀራኒዮ የተጀመረው የዘመናዊ ሆስፒታል ግንባታ 68% እንደደረሰ የገለጹት የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ሆስፒታሉ 520 በላይ ክፍሎችና 423 አልጋዎች እንደሚኖሩት ተናግረዋል።
ንፋስ ስልክ ላፍቶ ሆስፒታልም ከትልልቆቹ መካከል የሚመደብ ነው። ግንባታ ወደ ስድሳ በመቶ ደርሷል። 520 ክፍሎችና 370 አልጋዎች ይኖሩታል ብለዋል - ከንቲባዋ።
ትውልድን መገንባት - የተማሪዎች ውጤት ዘንድሮ ተሻሽሏል።
የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር ዘንድሮ ከ626 ሺህ በላይ፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር ከ232 ሺህ በላይ ማድረስ ችለናል ብለዋል - ከንቲባዋ።
“የመዋዕለ ሕፃናት” ትምህርት ሲታከልበት፣ የተማሪዎች ቁጥር ከ1 ሚሊዮን 175 ሺህ በላይ ሆኗል።
ከበጎ አድራጎት የገንዘብ፣ የዐይነትና የሙያ ድጋፎችን ለማሰባሰብ በተደረገው ጥረት 6.4 ቢሊዮን ብር ተገኝቷል። ይህም ተማሪዎችን ለማገዝ ጠቅሟል። በተማሪዎች ምገባ 780 ሺህ በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ መመገብ ችለዋል። የተማሪዎች የደንብ ልብስ፣ የትምህርት ቁሳቁስና የመምህራን የሥራ ልብስ ተሟልቶ እንደቀረበም ተገልጿል። ደብተር፣ ስክርቢቶ፣ የትምህርት ቤት ልብስ ለልጆች ማሟላት የስንትና ስንት ቤተሰብ ራስ ምታት እንደነበረ ማን ሊረሳው ይችላል? ወላጆች ይመሰክራሉ።
በእርግጥ መጻሕፍት አቅርቦትም ወጪው ቀላል እንዳልሆነ የከተማዋ የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ተናግረዋል። እንደ አዲስ የተዘጋጁትን የመማሪያ መጻሕፍት ለሁሉም ተማሪዎች ለማዳረስ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር በጀት ይጠይቃል። ቢሆንም ለሁሉም ተማሪዎች ማዳረስ ተችሏል። የትምህርት ጥራት ከመማሪያ መጻሕፍት ውጭ አይታሰብምና። ደግሞስ ከንቲባዋ፣ “ትልቁ ሥራችን የትውልድ ግንባታችን ነው” ብለው የለ!
ዘንድሮ የተማሪዎች ውጤት መሻሻሉ ደግሞ ይበል የሚያሰኝ ነው።
ከሳምንት በፊት በይፋ የተገለጸውን የ8ኛ ክፍል የፈተና ውጤት በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በፈተናው 50 ነጥብና ከዚያ በላይ ውጤት ያገኙ ተማሪዎች ብዙ ናቸው።
በቀን የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች 82.4 በመቶ ያህሉ፣ በቀን የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ደግሞ 96 በመቶ ያህሉ ከ50 ነጥብ በላይ ውጤት በማግኘት አልፈዋል ብለዋል፤ሃላፊው።
ከ290 ሺህ በላይ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል አግኝተዋል
የጤናውም፣ የትምህርቱም፣ የኮሪደር ልማቱም… ሁሉም ፕሮጀክቶችና ጥረቶች፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ “ነዋሪዎች ሠርተው ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያግዙ ናቸው” ማለት ይቻላል።
የኢንቨስትመንትና የንግድ ፈቃድ አመዘጋገብን በዘመናዊ አሠራር በማሻሻል ፈጣን አገልግሎት መስጠት፣ ገበያን ማረጋጋት፣ የማምረቻና የገበያ ማዕከላትን መገንባትና ማዘጋጀት… እነዚህና ተመሳሳይ ጥረቶች በሙሉ፣ የነዋሪዎች የመተዳደሪያ ሥራ እንዲሳካና አዳዲስ የሥራ ዕድሎች በብዛት እንዲፈጠሩ የሚጠቅሙ ናቸው።
በእርግጥ ደግሞ፣ ዘንድሮ ለ330 ሺህ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ከማከናወን በተጨማሪ፣ ለ78 ሺህ ያህል አዲስ ንግድ ፍቃድ እንደተሰጠ የከተማዋ የንግድ ቢሮ ኀላፊ ገልጸዋል።
1919 የኢንቨስትመንት ፈቃዶች ታድሰዋል። 2619 አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶችም ተሰጥተዋል።
ከ7500 በላይ ኢንተርፕራይዞች የ2.5 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት እንዳገኙ ያወሱት ከንቲባ አዳነች፣ ቀድሞ ከተሰጠው ብድር 2.6 ቢሊዮን ብር ማስመለስ እንደተቻለ ጠቅሰዋል። 466 አምራች ኢንዱስትሪዎችም የመሳሪያ ሊዝ ተጠቃሚ ሆነዋል።
በትልልቅ ኢንቨስትመንቶችና በፕሮጀክቶች፣ በአነስተኛና በመካከለኛ ተቋማት አማካኝነት በአጠቃላይ ከ290 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንዳገኙም ተጠቅሷል። 50 መቶ ያህሉም ሴቶች ናቸው ተብሏል።
Published in
ባህል