“ዕውቀትን ከአንቀልባ እስከ መቃብር ፈልጉ”
“ጎረቤቱ ተርቦ እርሱ ጠግቦ ያደረ አማኝ አይደለም።” ይህ የነብዩ ሙሃመድ አስተምህሮና የእስልምና ሃይማኖት መተዳደሪያ ነው። “አንድ ሰው ለሌላ ሰው ካላዘነ አላህም ለርሱ አያዝንም።”(ነብዩ ሙሃመድ) እንዲህ የኾነውን የእስልምና አስተምህሮ በመካድ በአለም ላይ የተነዛ ሃሰተኛ ወሬ አለ፤ በበርካታ ሰዎች የታመነ። “ኢስላም ጦርነት ነው። ጂሃድ ነው። ፀረ-ስልጣኔ፣ ፀረ-ፍልስፍና እና ፀረ-ሳይንስ ነው” የሚል፤ በአውሮፓውያንና በአሜሪካ የተነዛ። የሃይማኖቱ ስም’ም ‘ሰላም’ ከሚል ቃል የመጣው እስልምና፤ ሽብርተኝነት የአስተምህሮው ተቃራኒ ነው።
ታዲያ እንዴት “አሸባሪ” የሚል ሃሰተኛ ወሬ ሊነዛበት ቻለ? “አጥፍቶ ጠፊ” የሚል ነገር ከየት መጣ?
(ማስታወሻ፡- በዚህ ጽሁፍ የተጠቀሱት የቀን አቆጣጠሮች በሙሉ በአውሮፓውያኑ -እ.ኤ.አ ነው፡፡ )
፨ በ2008 አ.ል በነጃሺ ማተሚያ ቤት የታተመውና በመሀመድ አሊ(ቡርሃን አዲስ) የተዘጋጀው፣ በ200 ገጾች የተቀነበበው “ኢስላም ወርቃማው የሳይንስ ማዕከል” የተሰኘው መጽሐፍ፤ ለነዚህ ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ ከታሪክ ማስረጃ ጋር ያቀርባል። መጽሐፉ በአራት ‘ማሳያዎች’ ተከፍሏል። ማሳያ 1,2,3,4። መሃመድ አሊ፤ በአለም ላይ የተንሰራፋውን ኢ-ኢስላማዊ አስተሳሰብ የሞገተበት ነው - መጽሐፉ፡፡ ይልቁንም የመጀመሪያው የሳይንስ(ፊዚክስ፣ ጂኦግራፊ፣ ኬሚስትሪ፣ አስትሮኖሚ) መስራቾች ሙስሊም ሳይንቲስቶች እንደኾኑ ከመረጃ ጋር ያቀርባል። ታላቅ ስልጣኔ ከነበራቸው እነ ሮማ(3 ወይ 4 ክ/ዘመን) እና ግሪክ ስልጣኔ (5 ወይ 6 ክ/ዘመን) የበለጠ ኢስላም ታላቅ ስልጣኔ ነበረው።
- ኢስላም ከ8ኛው ክ/ዘመን እስከ 16ኛው ክ/ዘመን ድረስ 800 ዓመት የዘለቀ ስልጣኔ ነው የነበረው። ከነብዩ ሙሃመድ ዘመን ጀምሮ እስከ አባሲይ ዘመን መቋጫ ድረስ ሳይበጣጠስ፣ በአንድ ኸሊፋ ስርአት እየተመራ ቆይቷል። ከዚያም እንደ መጀመሪያው ጠንካራ ባይሆንም፣ በኦቶማን ቱርኮች አማካይነት እስከ 1923 ድረስ ዘልቋል። ይህን የመሰለ የስልጣኔ ታሪክ በየትኛውም ዘመን አልታየም።(ገጽ-197)
- “የኢስላም ስልጣኔ በሁለት ዋና ዋና ከተሞች ላይ በተመሳሳይ ጊዜ የፈነጠቀ አስደናቂ ጥበብ ነበረው። ከምስራቅ ባግዳድ፤ ከምዕራብ የስፔኗ ኮርዶቫ።”(164)
፨ ሁሉም ት/ቤት ገብቶ የተማረ ሰው እንደሚያውቀው፣ በየትኛውም መምህርም ሆነ መጽሐፍ ላይ ኢስላም የሳይንስ መስራች እንደሆነና ሙስሊም ሳይንቲስቶች እንደነበሩ አይነገርም። በተቃራኒው ስለ እስልምና የሚነገረው፣ ከእስልምና መመሪያ ውጭ፣ ‘አውሮፓ’ ሰራሽ የሆነ አሉባልታ ነው። “አንዲትን ነፍስ ያጠፋ፣ የሰው ዘርን በጠቅላላ እንዳጠፋ ነው።” የሚለውን የቁርዓን አስተምህሮ ሳይሆን፤ “አውሮፓ የበላይ መሆን አለባት። የሁሉም ስልጣኔና ሳይንስ መስራች እሷ ናት። ምስራቁ አለም ኋላቀርና ከምዕራቡ የሚማር ነው።” የሚለውን አስተሳሰባቸውን ለማንሰራፋት እንዲመቻቸው፣ ሽብርተኛና ፀረ-ሳይንስ ይላሉ።
፨ በመጽሐፉ ማሳያ አንድ ላይ እንደቀረበው፣ መላው አለም የፊዚክስ ሊቁን አይዛክ ኒውተንን ያውቀዋል። የ’ኒውተን ህግ’ የሚባለውንም ፈጣሪና አባት ኒውተን እንደሆነ ነው የሚያውቀው። እንጂ ኢብን አል-ሃይሰም ስለሚባለው የመጀመሪያው ፊዚስት የሚያውቅ የለም። ቢሰሙ እንኳ ‘ለማመን የሚከብድ ተራ ወሬ ነው’ መባሉ አይቀርም፡፡ “አይዛክ ኒውተን ‘የኒውተን ህግ’ አባት አይደለም ማለት እብደት ይመስላል። ነገሩ ከሰዎች ጆሮ ቢደርስ ጆሯቸው ማዠቱ አይቀርም።”(35) ይለናል። አውሮፓውያኑ፣ አል-ሃዜን ወይም አል-ሃሲን ብለው የሚጠሩት፤ ሁለተኛው ፔተሎሚ እያሉም የሚያሞካሹት(38) ኢብን አል-ሃይሰም፣ ዒራቅ ባስራ መንደር ... በ1643 ከተወለደው አይዛክ ኒውተን፣ 670 ዓመት በፊት በ965 ወይም በ354 አመተ-ሂጅራ ተወለደ። በሳይንስ ታሪክ የሳይንስ አላባን በመጠቀም የመጀመሪያው ሰው ነው። በፊዚክስ መጽሐፍ ላይ የምናገኛቸው የስኔል ህጎች የሚባሉት ከስኔል ከአምስት መቶ አመት በፊት የፈጠረው ኢብን አል-ሃይሰም ነው። በስኔል ህጎች የምናገኛቸው ሃሳቦች፣ በኢብን አል-ሃይሰም መጽሐፍት በዝርዝር የተቀመጡ ናቸው። ፕሮፌሰር ሮበርት ኢሊየት የሚባሉ ሰው እንደገለጹት፤ “አል-ሃዜን የኦፕቲክስ(አስትሮኖሚ፣ የካሜራና የማይክሮስኮፕ) ሳይንስን በተመለከተ እጅግ የመጠቀ ዕውቀት ነበረው። በ7 ቅጾች ያዘጋጃቸው መጻሕፍት በምዕራቡ አለም አስተሳሰብ.. በተለይ በሮጀር ቤከንና በኬፕለር ላይ ከፍተኛ ጫና ነበራቸው።” ይላሉ።(38)
- ኢብን አል-ሃይሰም ለነ ስኔል ጆን ፒቻም፣ ዮሃንስ ኬፕለር፣ አይዛክ ኒውተን፣ ሮጀር ቤከን፣ ረኔ ዴካርት እና ሌሎችም ሃሳቦች መሠረታቸው ነው።(42) ከመጻሕፍቱ መሃል 23 ያህሉ በሂሳብና አስትሮኖሚ ፅንሰ ሃሳቦች ላይ ያተኩራሉ። 14 ያህሉ የኦፕቲክስ ፊዚክስን ይመረምራሉ። ከዚህ በተጨማሪ በሌሎች የዕውቀት ዘርፎች(በሃይማኖት ጉዳዮችና በጥበብ ስራዎች) ላይ የሚያትቱ ይገኙበታል(46)። እሱ የጻፋቸውና በአውሮፓውያን የተተረጎሙ በርካታ መጻሕፍቶች አሉት። ለአብነት ያህል... Book of optics, Doubts about plotomy, The model of the motions, Treaties on light. . .ወዘተ ይጠቀሳሉ።(41) ይህንን በጥልቅ ማብራሪያ ቡርሃን በማሳያ አንድ ይገልጽልናል።
፨ እያንዳንዱ ሙስሊም ግለሰብ በቀን ለ5 ጊዜ የመስገድ (ስግደት የመፈጸም) ግዴታ አለበት። ለዚህም “የጸሃይን መጥለቅ፣ ምሽት፣ ንጋት፣ እኩለቀንና ከሰአት በኋላ ያሉ ጊዜያት ለስግደቱ የተቀመጡ ጊዜያት ናቸው። በዘመናችን አላርም ሞልተን እንደምንጠቀመው፣ ያ ዘመን ቴክኖሎጂው አልነበራቸውም። የጸሃይን እንቅስቃሴና የብርሃን አቅጣጫን መረዳት ነበር - አማራጩ።”(61) ስለዚህም የሰላት ወቅት መድረሱን ለማወቅ ኮከቦችንና የጸሃይን ጨረር በመመልከት፣ “ሂሳባዊ አስትሮኖሚና ትሪጎኖሜትሪ ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ መነሻ ነበር።” ከዚህ በተጨማሪ ሰላት ሲሰገድ ወደ መካ (ካዕባ) አቅጣጫ መቅጣጨት ያስፈልጋል። ቦታውን ለይቶ ማወቅ ግዴታ ነው። ማንኛውም አማኝ ለፈጣሪው ሲሰግድ ፊቱን ወደ ካዕባ አቅጣጫ ሰጥቶ ነው። ከቦታው ዝንፍ ማለት የለበትም። በዚህም ምክንያት ስፌሪካል ጂኦሜትሪን በማጥናት ፈልስፈዋል። የኢስላማዊ የዘመን አቆጣጠር (ሂጅራ) ለማወቅ (የረመዳንን ወር ለመጾም ወሩ መች እንደኾነ ለመረዳት ጨረቃንና ከዋክብትን በመመልከት) አስትሮኖሚ ታስቧል። ይህንንና ሌሎችን በማሳያ ሁለት ያብራራል፡፡
፨ ከጥንታዊ የስልጣኔ መገኛዎች አንዷ የኾነችው ህንድ ዛሬ ላይ የምንጠቀምባቸውን ቁጥሮች (ከ0-9 ያሉት) የፈጠረች አገር ናት። በ500 አ.ል የተፈጠሩ ሲኾን ወደ አለም እንዲሰራጭ ያደረገው ታላቁ የሂሳብ ሊቅ ጃዕፈር ሙሃመድ ኢብን ሙሳ አል-ኸዋሪዝሚ ነው።(81) እነዚህ ቁጥሮች ብዛታቸው አስር ሲሆን፤ የዳበረ የሂሳብ ስሌት እንዲጎለብት መሰረት ጥለዋል። ሌሎቹ የቁጥር መወከያ ዘዴዎች ኋላቀር ናቸው። ለምሳሌ 38 የሚለውን ቁጥር በአውሮፓዎች ግኝት XXXVIII ተብሎ ነው የሚጻፈው። ይህም ለስሌት በጣም አስቸጋሪ ነው።(78)
-የአል-ኸዋሪዝሚ ስራዎች ዛሬ ድረስ ተግባራዊ የሆነውን የሂሳብ ትምህርት መገንባት ችለዋል። ‘አልጎሪዝም’ የሚለው ቃል በሂሳብ ትምህርት የታወቀ ነው። የሂሳባዊ ስሌት ሎጂካዊ አሰራር ማለት ነው። ይህም መጽሐፉ ወደ ላቲን ሲተረጎም አል-ኸዋሪዝም አል-ጎሪዝም በሚለው ተለውጧል። ሌላው የአል-ኸዋሪዝሚ ግኝት አል-ጀብራ ይባላል። ይህም የተወሰደው የአል-ኸዋሪዝሚ መጽሐፍ ከሆነው ‘ኪታቡል ጀብር ወል-ሙቃበላ’ ከሚለው ነው። ከዚህ ውጭም በጣም በርካታ ግኝቶች እንዳሉት ከማስረጃ ጋር በማሳያ ሦስት መጽሐፉ ይተርካል።
፨ ይህን እና ሌሎች ግኝቶችን (በፍልስፍና፣ ህክምና፣ ኬሚስትሪ ወዘተ) ሙስሊሞቹ እንዴት ሊያውቁ ቻሉ? በ1076 የተወለደው በእንግሊዝ የመጀመሪያው ሳይንቲስት እንደኾነ የሚነገርለት አዴላርድ፣ በየሃገራቱ እየዞረ፣ ሙስሊም ሳይንቲስቶችን እየፈለገ ለምን ተማረ? በ1114 የተወለደው ጣሊያናዊው ጄራርድስ ለምን የሙስሊም ዩኒቨርሲቲዎች እየሄደ ተማረ? ሙስሊሞች ከየት አመጡት? ከጋሊሊዮ ታሪክ ወዲህ ባሉት ጊዜያት ሳይንስ ባለበት ሃይማኖት ላይደርስ የተማማሉ መሰለ። በዚህም ሃይማኖት የሳይንስ ፀር ነው ተብሎ ስለታሰበ እስልምናም(በኢስላም ላይ የተሰራ ሌላ ታሪክ ቢኖርም) ከሳይንስ ጋር ስሙ አይነሳም።
- ሃይማኖቱ በራሱ እውቀትን መፈለግና መማርን ነው የሚያስተምረው። ቁርዓን ላይ በተለያዩ አንቀጾች እንደሚናገረው፤ እንደ ግሪኮች ፍልስፍናዊ ሳይንስ (Speculative science) አሻግሮ፣ ሙከራ ሳይንስ (Experimental science) ነው የሚያስተምረው። ማንኛውንም አይነት እውቀት መፈለግ ግዴታ አድርጓል። “የሚያውቁና የማያውቁ እኩል ናቸውን?” “ከተንቀሳቃሾች ውስጥ መጥፎዎቹ አላዋቂዎች ናቸው” የሚሉ እና ሌሎችም ብዙ ማወቅ ግዴታ መኾኑን የሚገልጹ አንቀጾች አሉ። በሃዲስም ነብዩ ሙሃመድ “ዕውቀትን መማር በያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው!”
“ዕውቀትን ከአንቀልባ እስከ መቃብር ፈልጉ” እያሉ ያስተምራሉ። ሰሃቦቻቸውንም(ተከታዮቻቸውንም) እንዲማሩ ወደ ተለያየ ሃገርም ይልኩ ነበር። በዚህም ምክንያት የሃይማኖታቸውን ትዕዛዝ ለመወጣት እነዚህ ሳይንቲስቶች ተፈጠሩ። ይህንን እና ኢስላም ለዘመናዊ ሳይንስ የዋለው ውለታ በምን ምክንያት እንደተፋቀ፣ በቁርዓን ውስጥ የተጠቀሱትን የሳይንስ መረጃዎች በማሳያ አራት ይብራራሉ።
፨ ታዲያ ይኽ ሁሉ ስልጣኔ የነበረው ኢስላም፤ አሁን ለምን እንደዚህ አይነት ስም ተሰጠው? ለሚለው ባግዳድን በጥቂቱ እናንሳ።
- ባግዳድ ከ750-1258 ለ400 ዓመታት በአባሲይ መንግሥት በፍትሃዊነት ስትመራ ቆይታለች። ማይክሮ ባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ፣ ህግ፣ ፊሎሶፊ፣ ቲዎሎጂ፣ ሜዲስን፣ ፋርማኮሎጂ፣ ታሪክን ያስተማረች ናት (172)። የመጀመሪያው ሙስሊም ዶክተር - ኢማም አል-ራዚ፣ የመጀመሪያው የሂሳብ ሊቅ - አል ኸዋሪዝሚ፣ የመጀመሪያው ኬሚስት - ጃቢር ኢብን ሃያን፣ የመጀመሪያው ታሪክ ተንታኝ - አጥ-ጦበሪ፣ የመጀመሪያው የሙስሊም ፈላስፋና ሳይንቲስት - አል-ኪንዲ’ን ያበቀለች ከተማ ነበረች - ባግዳድ።
፨ በ13ኛው ክ/ዘመን የቻይና ወራሪዎች(ሞንጎሎች) ባግዳድን አወደሙ። ከአራት መቶ ሺህ በላይ መጻሕፍት ተቃጠሉ። ተዘረፉ። ተጣሉ።(173)
- ወታደሮች በከተማዋ ላይ ለአርባ ቀናት ቆዩ። በአርባ ቀናት አንድ ሚሊዮን ህዝቦች ተገደሉ። በርካታ የተውሂድ፣ ተፍሲር፣ ሃዲስ፣ ባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ፣ ስነ-ፈለክ መጻሕፍት ባህር ውስጥ ተጣሉ፤ ባህሩ መጻሕፍቱ በተጻፉበት ቀለም ወደ ጥቁርነት እስኪለወጥ ድረስ። ታዋቂው የታሪክ ዘጋቢ ኢብን አሲር እንደሚሉት፤ “ከኪታቦቹ(መጽሐፍቶቹ) ብዛት የተነሳ ባህሩን ሞልተው ድልድይ በመሆን ፈረሰኛን አሻገሩ።” ይላሉ። ያ ጊዜ ለአውሮፓውያን የስልጣኔ፣ ለኢስላም የውድቀት ዘመን ነበር። በስፔንም በ1609 ከ350 ሺህ በላይ ሙስሊሞች ተጨፍጭፈዋል። ከሃገር ተባረዋል።
፨ በአጠቃላይ መሀመድ አሊ(ቡርሃን አዲስ) ሰፊና ብዙ ሊያነጋግር እንዲሁም ሊጻፍበት የሚችል መጽሐፍ አዘጋጅቷል ማለት እንችላለን።
Sunday, 21 July 2024 00:00
ወርቃማው ሳይንስ
Written by በነቢል አዱኛ
Published in
ህብረተሰብ