Monday, 22 July 2024 20:07

ቅመም ሠፈር

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(0 votes)

ጠሐይ ገራገር ዘሃዎቿን ከምድር ብብት ሥር ሰግስጋ በስልት ትኮረኩራለች፤ በመልስ ምት ምድር ፍክትክት ብላለች…
…የአንደኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ተከታትላ የተመለሰቺው እሌኒ፣ በእናቷ ትዕዛዝ የጌሾ ጠላ ትቸበችባለች። ቅመም ሠፈር ነው ቤታቸው፤ የአዲዮ ኤሼሺኖ (ኤሼሺኖ - ቃሉ ካፊቾ/ካፊኖኖ ሲሆን ትርጉሙ ጭሰኛ ማለት ነው) የነበሩ የእሌኒ አባት የወየበ ፎቶ-ግራፍ፣ በነተበ የብረት ፍሬም ተጣብቆ እንደ ዘመነ መሳፍንት ወንጀለኛ ከደሳሳ ቤታቸው ግርግዳ ላይ ተሰቅሏል።        
ጠላሞች፣ ባሞጨሞጨ ዓይናቸው የደጉን ሰው ፎቶ እያዩ ለማንኛውም ሰው ቀላል የሆነውን የከንፈር መምጠጥ ዕርዳታቸውን ይለግሳሉ። ሙት ወቃሽ መሆን ውግዝ ነውና ለአመል ቢጤ…‹‹አውራ ሞዴል›› ይላሉ፤  አንኮላቸውን ስበው ጠላ ይቃርማሉ፤
*  *  *
እሌኒ ስድስት ኪሎ ግቢ እንደደረሳት ለእናቷ ስትነግራቸው ቆጣሪያቸው ነበር የዞረው…
‹‹አቅሜን እያወቅሽ ስድስት ኪሎ ዘለሽ ገባሽ? የዘመኑ ልጆች አቅማችሁን እንኳን አታውቁም›› ተነፋረቁ፤
ነገሩ ሲዘልቃቸው፡-
‹‹የዘመን ያለህ፣ ሠፈርም እንደ ብቅልና ዳጉሳ ሚዛን ላይ ተጭኖ ይመዘን ጀመር?›› በሸራፋ ጥርሳቸው ያፈነገጠች ሳቅ ሳቁ።
ሸራፋ ጥርሳቸው ታባብላለች። ባለቤታቸው በደጉ ጊዜ ‹ወርቅ ላስተክልልሽ› ሲሏቸው ‹ፈጣሪዬ ምን ነፍጎኝ ነው ወርቅ እጥርሴ የማስቀበቅበው?› ብለዋል ይባላል…
…በሸራፋ ጥርሳቸው ታግዘው ያልተቀኘ ዜማ ያለው ሳቅ ያመነጫሉ። ሳቃቸው ባይቀኝም ለዛው እንደ ሸንኮራ ደም ሞልቶ የሚፈስስ ነውና ለጆሮ የተለየ ዓይነት ጣዕም አለው፤ አነሳሱና አወዳደቁ የአራራይ ስልት ታክሎበት መንፈስ ያለመልማል።
በተረት፣ ተረት መጻሕፍት እንዳሉ ድንቃይ ሰዎች፣ ሳማና ቆንጥር እሾክ ብቻ ሲያበቅል የከረመ ማሳ እሳቸው በረገጡት ማግስት ስንዴ ያበቅላል፤ ነዳጅ ፍልቅ-ፍልቅ ይልበታል አሉ። ወላ ዝናብ ለረጅም ወቅት ላይጥል የሚችለው፣ የእሌኒ እናት ‹የሰማይ ግት ይንጠፍ› ብለው ከተራገሙ ብቻ ነውም ይባላል።
ቅር ያለኝ ግን ለሸራፋቸው የወርቅ ጥርስ ያለማበጀታቸው ነበር፤ እሌኒ የእናቷን የወርቅ ጥርስ በጠቋሚ ጣቷ እያሻሸች፣ ወርቅ የመግዛት ፍላጎቷን ወርቅ በመንካት ትወጣው ነበር። እሌኒ ጋግርታም አይደለችም፤ የቅመም ሠፈር ቅመም ነች። ቅመም ሠፈር ጉልት ትላላካለች።
ወደ እንጀራ ሻጭ አጨንቁራ…
‹‹እንጀራውን ስንት አልሺኝ?›› ትላታለች፤
‹‹አምሥት፣ አምሥት ብር››
‹‹አምሥት አልሺኝ? የዛሬው እንጀራ ዓይን የለውም፤ አምሥት ብር ነው ለማለት ዓይን ያለውን ስታመጪ አይሻልም?››
በተቀዛቀዘው ገበያ መሀል ሳቁ ይደራል፤
ሻጭ ትበሳጫለች…
‹‹ሴትነት ጋግሮ መብላት ነዋ››
‹‹ይኼንን የጠፈጠፍሽው ዳቦ ነው ብለሽ ነው ወይስ እንጀራ?››
‹‹ይኼንን እውር ገዝተን ሄደን ዓይኑን በስትኪኒ ልናወጣው ነው?›› /ሌላ ገዢ/
የቅመም ሠፈር ጉልት ታውካካለች፤
ሻጭ ጥርሷን ትነክሳለች፤
‹‹ይኼ የሚቆረሰው በቢላ ነው፣ ይቅርብን››
‹‹ይቅርብን››
የእንጀራ ዋጋ ጠይቀው ሽንቆጣ ይከፍሏታል። ሻጯ ትተክናለች።
ቅመም ሠፈር ከልክ በላይ ደጋግ የሆኑ እናቶችን የታደለች ሠፈር ናት። የሠፈሩ እናቶች በደግነት አብርሃምን ያስቀናሉ። እንደውም አብርሃም ተመልሶ ቢመጣ ‹‹የቅመም ሠፈር እናቶችን ደግነት ከእኔ ሲያስተያዩት የእነሱ በስንት ጣዕሙ!›› የሚል ይመስለኛል። እንደ ልማዴ ‹‹እናት ሠፈር›› ብትባል ጥሩ ይመጣል እላለሁ።
በመንደሩ ውስጥ ራሱን ለታመመ ዳመከሴና አንድ ኩላሊት ይዘው የሚመጡ እናቶች ብዙ ናቸው። ካላመንክ ቅመም ሠፈር ዘመድ ካለህ ቤቱ መጥተህ ራስህን ታመምና ሞክር።
ራስህን እንዴት መታመም እንዳለብህ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ልነግርህ ቃል እገባለሁ። በእርግጥ የላቤን ማግኘት እንዳለብኝ አውቃለሁ፤ ያም ሆኖ ግን አስፈላጊ ከሆነ ከእኔ ለምታገኘው አገልግሎት ክፍያውን እሸፍናለሁ።
አንተ ብቻ ለመታመም ፈቃደኛ ሁን። ከዚያ ጠይቀኝ፤ ይኼውልሃ ምላሹ፡- የቀን ወጪህን ደምረህ ስታበቃ ያለጥርጥር ራስህን መታመምህ የማይቀር ነው፤ ግድ የለህም፣ ራስህን ብቻ ሳይሆን ወገብና እግርህንም ትያዛለህ፤ የለት ወጪህን መደመር ዓይንህን ጨለማ፣ ጉልበትህን ቀጤማ ያደርገዋል።
ስለ ደግነት ሲወሳ፣ በአንድ ወቅት አንድ የማውቀው የመንደሩ ኮከብ ኳስ ነራች ሜዳ ውስጥ ከብጤዎቹ ጋር ሲራገጥ አስከፊ የቁርጭምጭሚት ጉዳት ገጥሞት የአልጋ ቁራኛ ቢሆን ጊዜ ሊጠይቁት የመጡ አንድ እናት…
‹‹ዕድሜ የፈጀን ፍቱቶች ሳለን ቦርቆ ያልጠረቃ ማቲ እንዲህ መያዙ አግባብ አይመስለኝም፤ ደሞ ሕመሙ ከጠናበት ምን ይደረጋል? እኔ እናቱ ይፈውሰው እንደሆን ደሜን ልለግስ ቃል እገባለሁ!›› ብለዋል ይባላል።
በጊዜው የታማሚው እናት በገመምተኛ አንደበት አጉረመረሙ…
‹‹እንዴት ነው ነገሩ? እኒህ ግሪሳ መሳይ ባልቴት ቤቴ የመጡት ልጄን ሊያፅናኑ ነው ወይስ ከእኔና ከእሱ ማን መታመም እንዳለበት ክፍለ ጊዜ ሊመድቡ?›› አሉ። ከዚያ ምላሽ አሰናድተው…
‹‹አዪ እርስዎ ሴትዮ! ሁሌ እንዳሳቁኝ ነው፤ ቁርጭምጭሚት እኮ ደም አያሻውም… አልሰሜ!›› ብለው አሳቁባቸው።
‹‹የርሶ ነገር… የማያውቁ ሰው መምሰል! ግራ እጁን የታመመ ሰው ቀኝ ኩላሊቱ በሚቀየርበት፣ እሾህ ለወጋው ወረንጦ ማቀበል ሲችሉ ትርፍ አንጀት በሚሉበት ዘመን መቼ ነው ነገር የሚዘልቅዎት? ዘምኑ እንጂ እቴ!›› አሏቸው።                      
ሌላ አጽናኝ በበኩላቸው…
‹‹እግሩን ከተሻለው የዛሬ ዓመት ከቻልኩ ጥንድ፣ ካልቻልኩ ነጠላውን ባለ ብሎን ታኬታ ልሸልመው እንሆኝ ቃሌን!›› አሉ።
ከፊሉ አስታማሚ ሳቀ።
‹‹እንግዲህ እጅዎ አጥሮ ነጠላውን የሚገዙ ከሆነ ለግራ እግሩ ቢሆን ጥሩ ነው!›› ሌላ እናት።
‹‹ግራ እግሩን ነው የታመመው ማለት ነው? እኔን እናትህን›› አንድ ሻካራ ድምጽ ከጥግ ተሰማ።
‹‹እንደዚያ የማደርገው ካልሰመረ ብቻ ነው፤ ካለልኝማ እኔ እናቱ ጥንዱን ብገዛለት ደስ ባለኝ››
‹‹አይቸገሩ፤ ግራውን ብቻ በቻሉት! ሰሞኑን አዲስ ተሰጥቶት ግራ እግሩን አይጥ ቸፍችፎት ቀኙ ሥራ ፈት ሆኗል… ስለዚህ ምትክ ይሆነዋል›› የታማሚው እናት ናቸው።      
ሠፈሩ ሲቆረቆር አንስቶ የነበሩ የስፌት መኪኖች ዛሬም ሕያው ናቸው። በቅርቡ ዳኪቦ ሱሪውን ሲያስለጥፍ አይቼአለሁ። የሚያሳዝነው ነገር የስፌት መኪኖቹ ከሰፊዎቹ ዕድሜ በላይ ያገለገሉ በመሆናቸው ትግል መፈለጋቸው ነው።    
*  *  *
በዕኩለ ሌሊት ገላን የሚያሽኮረምም ርጥብ ነፋስ በቦንጋ ሰማይ ላይ ከትሯል። የኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ደወል በረጅሙ ያቃጭላል። የፋሲካ በዓል ዋዜማ ነበር፤ ሻሞ እና መለኪያ ‹‹ፏፏቴ ሆቴል›› አንድ ጥግ ጭብጥ ብለው በበዓል ዋዜማ ሰበብ የቢራ ጠኔያቸውን ይወጣሉ። የቤቱ አስተዳዳሪ ጠይም ወጠምሻ ሰው ፈገግ እያለ እንግዶቹን ይጋብዛል፤ ተስተናጋጆቹ ፊት ላይ ፈገግታ ይነበባል፤ ሥራ እንዲህ ያለ መልካም ተጽዕኖ ሲፈጥር መልካም ነው። የእነሻሞ ሠፈሯ እሌኒ ከምትማርበት ዩኒቨርሲቲ ለፋሲካ በዓል እናቷ ዘንድ መጥታለች፤ ቅመም ሠፈር።
ሻሞ ውጭ፣ ውጭውን እያየ ጥቂት ተብሰለሰለ…  
‹‹ወቼው ጉድ›› እጁን በልብስ አጣቢ ስልት ወደ እላይ አንከረፈፈ፤
መለኪያ፣ የሻሞን አዝማሚያ ሲያጤነው አላምርህ ቢለው…
‹‹ምን ሆንክ?›› ሲል ጠየቀ።
ሻሞ ትንፋሹን ሰብስቦ ተንቀጨቀጨ፡-
‹‹እሌኒ በዚህ ደረቅ ሌሊት ከመሀል መንገድ ላይ ቁራጭ ቀሚስ ለብሳ--›› አልጎመጎመ፤ በከፊል ኀዘንና በከፊል ንዴት ተከፍሎ።
‹‹ቁራጭ ቀሚስ?››
ጥቂት ዝም ተባባሉ፤
‹‹እያትማ? ተነስ ተነስ…›› ወዘወዘው፤
ከመለኪያ ፊት ተመጣጣኝ ድንጋጤ ይነበባል…
…ያዘዙትን መጠጥ ሳይጨርሱ ሻሞ ባቀረበው ሀሳብ ተስማምተው ቤቱን ለቅቀው ወጡ። የወይዘሮ እልፌ ልጅ ግን እዚያው እመሃል አስፋልት ላይ መለመላዋን እንደ ቆመች ነበር።
አልፈዋት ሄዱ።
እሌኒ ድርሰት ላይ እንዳለች ሴት እንደ ብር እንክብል የሚያበራ ዓይን፣ እንደ ፏፏቴ የተንዠረገገ ጠጉር፣ ብልሃት የተሞላ የተረከዝ አጣጣል፣ የተቀኘ አንደበት፣ የሚያዋትት ከናፍር፣ የሚያጥወለውል ወዘና፣ ጥዑም ጠረን፣ ማራኪ ሽንጥና ሞንዳሌ ዳሌ የላትም። የእሷ ውበት እንቁ አዕምሮዋ ብቻ ነው። ሰብዕናዋ እንደ ባሕር የአዕምሮን ሠላም ያድሳል…
ሻሞ አስተዋይነቷንና ሰው አክባሪነቷን ይወድላታል። መንገድ ላይ ጥለዋት በመሄዳቸው ደራሽ ቁጭት ከአዕምሮው መሰግ ብሎ ይከነክነው ገባ። በአንድ በኩል ደግሞ እንግዳ ጠባይዋ ሳይታወቀው ሰውነቱን በላው። ባሉበት ቆሙ…
‹‹ቤት ማድረስ ይኖርብናል››
ሻሞ ፈርጠም አለ…
…ከቆመችበት ሲደርሱ አልነበረችም። ‹‹ፏፏቴ ሆቴል›› ሲደርሱ መድረክ ላይ ናት፤ ‹‹ጠይም ዘለግ ያለ፣ ጎራዴ ታጣቂ…›› እያለች፤ እሌኒ ፋሲካ ናት፤ ሻሞ ‹‹እሌኒ›› የተባለች በዓል ባስተዋለ ጊዜ ነፍሱ አስተሰረየች። መክሊትን ገሃድ አውጥቶ ማሳየት በዓል እንደሆነ ያምናል።
ቢራ አዝዘው በአግራሞት ይመለከቷታል፤ ሻሞ…
‹‹ጠይም ዘለግ ያለ፣ የሰፋው ደረቱ፤
ፍቅር አላፊ ነው፣ ባ‘ረገኝ እህቱ፤››
ማለቷን ግን አልወደደላትም።   
 
*  *  *
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር /ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።


Read 415 times