Monday, 22 July 2024 20:20

ምርኮኛው ባለቅኔ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“ባጠቃላይ፣ እናርጅና እናውጋ፣ ጌራወርቅ ሞጋች፣ አመራማሪ፣ ገሳጭና አስደማሚ ዐሳቦችን በምናቡ ሸምኖ በማቅረብ
ውስብስቡን ኑባሬንና ልቡናችንን ባላየነው አድማስ በርብረን እንድንገነዘብ ያደረገበት ሸጋ መድበል ነው፡፡ ይህ የፈጠራ ሥራ
በኪነት ሚዛን የከያኒውን ክህሎት መስክረን፣ ያለ ንፍገት ሥሙን በደማቅ ቀለም እንድንጽፍ የሚገፋ ነው፡፡--


እናርጅና እናውጋ (2015) በጌራወርቅ ጥላዬ የተጻፈ የግጥም መድበል ነው፡፡ መድበሉ መልከ ብዙ የሕይወት ገጾች በወርድና ቁመታቸው የተፈተሹበት ነው፡፡ በመድበሉ ውስጥ የቀረቡ ግጥሞች አጀንዳና ድምጸት መልከ ብዙ መሆኑ ደግሞ የገጣሚውን አቅም በግልፅ ያሳያል፡፡ ይህ ማለት፣ የጌራወርቅ ግጥሞች እንደ አንዳንድ ጥቂት ገጣሚያን ሥራዎች በተመሳሳይ ድምጸት ሥር የወደቁ፣ በተመሳሳይ ጭብጥ (recurrent subject) ዙሪያ የሚሽከረከሩ አይደሉም፡፡       
በእናርጅና እናውጋ የገጣሚው የቋንቋ ባለሟልነት፣ የምሰላ ክህሎት፣ የገለጻ ጠቢብነትና የምናብ ጥልቀት ተንፀባርቋል፡፡ በመድበሉ ውስጥ የቀረቡት ግጥሞች ምት ልክ ሆኖ መገኘትም ዜማው ስሙር እንዲሆን ረድቷል፡፡ ቀጥለው የቀረቡት ጥቂት ስንኞች ይህን ሐተታ በዋቢነት ያስረግጣሉ፡     
እንደ ደብር መርገፍ፣ እንደ ጸናጽሉ
ወዲህ ወዲያ ብዬ፣ ወዳንቺ ተመለስኹ
አፈር ለሚበላው ላፈር ጦም እያደርኹ፡፡
እህል ውኃ ከወሰደኝ፣ ካፍሽ አፋፍ የነጠቀኝ፣
ቢመልሰኝ ላንቺ ማጀት …
ልሣለምሽ እንደ ደብር፣ ልስገድልሽ እንደ ታቦት፤
በዐይኔ ቅንድብ አመልክቼ፣ በአኮቴት ሥመለከት፣
ካድባር - ካውጋር፣ ሳውጠነጥን ያንቺን ሕይወት …
መኖርሽ በኗሪሽ ውስጥ ጠፍቶ አየሁት፡፡
(ጌራወርቅ፣ 2015፡ገጽ 21)
ወይዘሪት እምዬ! መሆንሽ ምን ነውሳ …?
ቀባሪ እንዳጣ ሬሳ፣ በሰው እንደተረሳ፣
ዳዋ እንደወረሰው እንደ ገበሬ ማሳ፤
ምላሱ ከላንቃው እንደተጣበቀ፣
ገላው እንደልብሱ በላዩ እንዳለቀ፣
በወንጭፍ ድንጋይ ምት እንደተሰበረ እንደበኩር እሸት፣
ሞት እንደተጸየፋት፤ ኑሮ እንዳቀለላት፤ ደካማ አሮጊት፣
ጎታታ፣ ዳተኛ፣ እንደጉፋያ ከብት፣
በሚታየኝ ኹነት፣ ይሁን ያንቺ ሕይወት?
(ጌራወርቅ፣ 2015፡ገጽ 22-23)
ማሳ ሲሆን እንቅልፋችን፣
ስንፍናችን ፍሬ አፍርቶ፤

ኩራት ሲሆን ብልግናችን፣
ትዕቢታችን አፍ አውጥቶ፤

ገድል ሲሆን ውርደታችን
 ታ’ምር አይሆን ውድቀታችን፡፡

ለፍቅር ልብ ባንረታ፣
እንደ በሬ ጥልን ጠምደን፣
ለጦርነት ስንበረታ፤
ቀን ይነሣል፤ ዘመን ወድቆ፣
ሲደናበር ጊዜ ቃዥቶ፡፡

ለከንቱ አውድማ፣
… በባዶ ባድማ፤
ስንደክም ለሥጋ፣
ክረምት አልፈን በጋ፤
ነፍሳችን ብንገፋው፣ አድርገን እንዳይሆን
ካልተፈጠረ አነስን፣ ከሞተ ሰው ሳይሆን፡፡
(ጌራወርቅ፣ 2015፡ገጽ 94)
ጌራወርቅ ሥጋና ደምን ዘልቀው ስሜትን የሚሸነትሩ ቅኔያትን በመከየን የተካነ ልኂቅ ነው፡፡ የሐዘን ትካዜው የነፍስ ቅኝትን ያደፈርሳል፡፡ የፀፀት ኑዛዜው ልብ ያደማል፡፡ የፍቅር እንጉርጉሮው ማዕበሉ ያላጋል፡፡ የቁጭት እሮሮው ረመጡ ያጋያል፡፡ የኂስ ሾተሉ ኅሊና ያቆስላል፡፡ የመፃኢው ጊዜ ትንቢቱ በፍርሃት ያርዳል፡፡ ደም አንተክታኪ ሽለላው ፍም ያስጨብጣል፡፡
ጌራወርቅ ከሌሎች ባለቅኔዎች በበለጠ የውበት ምርኮኛ ነው፤ የፍቅር ተማላይ፡፡ የውበት ምርኮኛነቱ በሴት ቁንጅና ይገለጣል፡፡ በግጥሞቹ ውስጥ በምናብ ሥሎ ያቀረባቸው ሴቶች በአካል ቁመናቸው አምሣለ አማልክት ናቸው፡፡ ባለቅኔው በፍቅር ምርኮ ልደርላችሁ፣ ሠልጡኑብኝ የሚላቸው፣ ክሱት ምግባራቸውን እያወሳ የሚያወድሳቸው ሴት ገጸባሕርያትም እንከን የለሽ ሰብዕናን የተሸለሙ ናቸው፡፡ የሚከተሉት ስኝኞች ለእዚህ ዐሳብ ዋቢነት የቀረቡ ናቸው፡   
የሚያስፈራስ! እንደመሸበር
የሚያስፈራስ! እንዳለማፈር
የሚያስፈራስ! እንደ ሲኦል መንገድ
አንቺን ለይቶ! ዐይቶ! አለመውደድ፡፡
            
ዐይንሽ አስደንባሪ፣ አፍንጫሽ አቀበት
ይጥላል ከንፈርሽ የጥርሶችሽ ውበት፤
መልክሽ እንቆቅልሽ ባገር የሚፈታ!
አንደበትሽ ቅኔ ግጥም በአንድምታ!
ልብሽ የመለኮት ምሥጢር የሚረታ!
አትገኝም እንጂ በዕድሜ ልክ ሱባዔ፣
አንቺን ያገኘ ነው፣ ፍቅር ማስመስከሪያ! የገነት ጉባኤ፡፡

ታምኖ እንደኖረ በጌታው ቤት ሲኖር
ለንጉሡ አስከሬን እንደሚሞት አሽከር፤
አልታደለም እንጂ አንቺን ሰው ሊያፈቅር!
አልመጠነም እንጂ ሰው አንቺን ለማፍቀር!
ተመርጦ! ተለይቶ! አንቺን ሰው ቢያፈቅር?!
ለጥላሽ ይሞታል እንኳን ላፍሽ ከንፈር፡፡
(ጌራወርቅ፣ 2015፡ገጽ 92-93)

እንኮይ የእንኮይ መሥክ መሣይ አበቄለሽ
ንጋት እያየሁሽ እጠላለሁ ሲመሽ፤
ወተት፣ ያጓት ፍሬ በሚያስንቀው ጥርስሽ
ሳልጠጣው፣ ሳልጎርሰው ብገድፍ በፈገግታሽ
ምን - ትዋብ? ስላቸው፣ ተዋበች እያሉ
ባርብ አፈር አልኩኝ ለቁንጅናሽ ቃሉ፡፡
(ጌራወርቅ፣ 2015፡ገጽ 102)
ዘቢብ - ዕጣን - ጧፍ ነው የደጅሽ አምኃ
አልማዝ የሚፈሰው ቀለመ ወርቅ ውኃ፡፡
አፍሽ ሥላሣየኝ የልብሽን ጸዳል
ገዳሙ፣ ገዳሙ ልበልሽ ሥራውባል
የሽፋልሽ ጽድቀት ከኃጢያት ያነጻል
የወደደሽ ወዶ ከሞት ይታረቃል፡፡  
(ጌራወርቅ፣ 2015፡ገጽ 103-104)
እናርጅና እናውጋ እንደ ሀገር የተጣባንን ክፉ ደዌ በጥልቀት የሚዳስሱ፣ የዘመኑን መልክ የሚያሳዩ ግጥሞች የቀረቡበት መድበል ነው፡፡ በመድበሉ ገጣሚው የተንሻፈፈ አመለካከታችንን ኮንኖ፣ የእዚሁ እኩይ አመለካከታችን ዳፋ መጥፎ መሆኑን ነግሮናል፡፡
ባጠቃላይ፣ እናርጅና እናውጋ፣ ጌራወርቅ ሞጋች፣ አመራማሪ፣ ገሳጭና አስደማሚ ዐሳቦችን በምናቡ ሸምኖ በማቅረብ ውስብስቡን ኑባሬንና ልቡናችንን ባላየነው አድማስ በርብረን እንድንገነዘብ ያደረገበት ሸጋ መድበል ነው፡፡ ይህ የፈጠራ ሥራ በኪነት ሚዛን የከያኒውን ክህሎት መስክረን፣ ያለ ንፍገት ሥሙን በደማቅ ቀለም እንድንጽፍ የሚገፋ ነው፡፡
***
ከአዘጋጁ፦መኮንን ደፍሮ ልብ ወለድ ጸሐፊ፣ ገጣሚ እና የሥነ ጽሑፍ ኀያሲ ነው፡፡ የባችለር እና የማስተርስ ድግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍና አግኝቷል፡፡ በተማረው የሙያ መስክ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ፍልስፍና አስተምሯል፡፡ ጸሐፊው ወደ ፊት ለህትመት የሚበቁ የተለያዩ የልብ ወለድ፣ የኢ-ልብ ወለድ እና የግጥም ሥራዎችን አዘጋጅቷል፡፡


Read 522 times