የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አሕመድ ሞአሊም ፋቂ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ከሁለት ወራት በፊት በቱርክ አመቻችነት ድርድር አላካሄዱም ሲሉ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ባለፈው ረቡዕ ሃምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም፣ በኳታር ዶሃ የሶማሊያ ዲያስፖራ ኮንፈረንስ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ “አል አረቢ አል ጃዲድ” ከተሰኘ የዜና አውታር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።
“ከኢትዮጵያ ጋር ድርድር አላካሄድንም። ነገር ግን እነርሱ አሁን እያደረጉ ካሉት አደገኛ አካሄድ እንዲመለሱ የሚያሳምን ንግግር ነው በእኛ በኩል የተደረገው። ከሶማሌላንድ ጋር ያደረጉትን ስምምነት እንዲያቋርጡ ነግረናቸዋል፡፡” ብለዋል፤ ሚኒስትሩ ለዜና አውታሩ።
“ከኢትዮጵያ ጋር ድርድሮች አልተደረጉም። ያደረግናቸው ውይይቶችም እንደ ድርድር የሚቆጠሩ አይደሉም” ነው ያሉት አህመድ፡፡
በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መካከል የተደረገውን ስምምነት “ሕገ ወጥ” ሲሉ ያጣጣሉት የሶማሊያው ሚኒስትር፤ “ኢትዮጵያ ወራሪ አገር ነች። መሬታችንንና አገራችንን ማስከበር አለብን። ስምምነታቸው ሕገ ወጥ በመሆኑ፣ መሬት ላይ መተግበር የለበትም” ሲሉም በሃይለቃል ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ለዜና አውታሩ፣ ሁለቱ አገራት ድርድር አላደረጉም ቢሉም፤ ከወራት በፊት የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያ በቱርክ ድርድር እንደሚያደርጉ የሚገልጽ መረጃ በቀድሞው ትዊተር (ኤክስ) ገጹ ላይ አስፍሮ ነበር። ይህን መረጃ ግን ብዙም ሳይቆይ ከገጹ ያስወገደው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ በምትኩ “የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቱርክ አደራዳሪነት ለሚደረገው ንግግር አንካራ ገብተዋል” ሲል መግለጹ አይዘነጋም፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ቀደም ብለው ወደ ቱርክ አቅንተው የነበር ሲሆን፣ የሶማሊያው አቻቸው እርሳቸውን ተከትለው መግባታቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ የተካሄደውን ይህን ውይይት ተከትሎም፣ የሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ሞአሊም፣ አገራቱ ልዩነታቸውን በሰላማዊ ንግግር ለመፍታት መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሊያ “በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ባለው ማዕቀፍ” ልዩነታቸውን ለመፍታት ሁለተኛውን ዙር ድርድር፣ በፈረንጆቹ አቆጣጠር መስከረም 2 ቀን 2024 ዓ.ም በአንካራ ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ነበር፣ የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን የገለጹት።
እ.ኤ.አ. በ2011 ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ሞቃዲሾን መጎብኘታቸውን ተከትሎ፣ የጸጥታ ሃይሎች በማሰልጠንና የልማት ዕርዳታዎችን በማቅረብ ቱርክ፣ የሶማሊያ መንግስት የቅርብ አጋር ሆናለች። ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ከስምምነት ላይ ከደረሱ ከወር በኋላም፣ ቱርክና ሶማሊያ የ10 ዓመት የወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።
Published in
ዜና