Saturday, 27 July 2024 21:40

በጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት የሟቾች ቁጥር 500 ሊደርስ እንደሚችል ተጠቆመ

Written by  በሚኪያስ ጥላሁን
Rate this item
(7 votes)

 • “ከ15 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ ናቸው”
                               
          በደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ ዞን፣ በተከሰተው ተከታታይ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሟቾች ቁጥር 500 ሊደርስ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ)፣ የአካባቢው ባለስልጣናትን ዋቢ በማድረግ አስታወቀ።  አሁንም ድረስ በናዳ ሥር ተቀብረው  የጠፉ ሰዎችም ማፈላለጉ የቀጠለ ሲሆን ባለፉት ቀናት በተደረጉ የፍለጋ ጥረቶች በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥር 260 መድረሱ ተገልጿል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ ዞን፣ ገዜ ገፋ ወረዳ፣ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ባለፈው እሁድና ሀምሌ 14 እና ሰኞ ሀምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በተከሰተው የመሬት መንሸራተት፣ በናዳ ስር ተቀብረው የጠፉ ሰዎችን የማፈላለጉ ሥራ የአካባቢ ባለስልጣናት ነዋሪዎችን በማስተባበር እያከናወኑ ነው ተብሏል።
የአካባቢው ማሕበረሰብ በናዳው ስር ተቀብረው የሚገኙትን ዜጎች ለማውጣት ቁፋሮውን እያካሄደ ያለው በእጅ መቆፈሪያ መሳሪያዎች ሲሆን፤ የቁፋሮ መሳሪያዎችን ወደ ቦታው ለማስገባት ባለው ጭፈቃማ ሁኔታ ሳቢያ አስቸጋሪ መሆኑ ተገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከትላንት በስቲያ ባወጣው ሪፖርቱ፣ ከ15 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም ለተጨማሪ የመሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭ ናቸው ብሏል። ከነዋሪዎቹ መካከል 5 ሺህ 293 የሚሆኑ በእርግዝና እና በማጥባት ላይ ያሉ ሴቶች፣ እንዲሁም 1 ሺህ 320 የሚሆኑ ህጻናትን ከአካባቢው በማራቅ ወደተሻለ አካባቢ እንዲጠለሉ የማድረግ የዕቅድ ስራው ተገባዷል ብሏል፤ድርጅቱ።
 የፌደራል መንግስት ከክልልና ከወረዳ ባለስልጣናት ጋር በመተባበር አሁንም ለተጨማሪ የመሬት መንሸራተት ተጋላጭ ከሆነው አካባቢ ነዋሪዎቹን ወደ ሌላ ቦታ ለማዛወር እየተሰራ መሆኑን ተመድ ጠቁሟል።
በአካባቢው ከተቋቋመው የአስቸኳይ አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል ጋር በመተባበር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ አካላት በቦታው በመገኘት እገዛ እያደረጉ እንደሚገኙም ነው የተነገረው።
 የመሬት መንሸራተት አደጋውን ተከትሎ፣ የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ድጋፋቸውን ለተጎጂዎች እያደረሱ መሆኑ ተነግሯል። የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በዚሁ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ግምቱ 45 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚሆን የገንዘብና የህክምና ግብዓት ያካተተ የአስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ ወደ ቦታው መላኩን ገልፀዋል።
“ለወገን ቀድሞ መድረስ ቀዳሚ ተግባራችን ነው” ያሉት ከንቲባዋ፤ የጉዳቱን ልክ በአካል ለማየት የከተማዋ አስተዳደሩ አመራሮች ባለፈው ሐሙስ ወደ ስፍራው ማቅናታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ኢንጂነር) እና የክልሉ ልኡካን በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን አደጋው በደረሰበት ስፍራ በመገኘት ያጽናኑ ሲሆን፤ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ወገኖችና ለተጎጂዎች በመጀመሪያ ዙር በጥሬ ገንዘብ 5 ሚሊዮን ብር እና በዓይነት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።
በተመሳሳይ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደረሰው የመሬት ናዳ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡ የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ በበኩሉ፣ በአደጋው ለተጎዱ ዜጎች የሚሆን የዕለት ደራሽ ምግብ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ በተጨማሪም፣ አንድ አምቡላንስና አስቸኳይ እርዳታ የሚሰጡ የሐኪሞች አባላት ቡድን ወደ ቦታው መላኩን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል፣ ባለፈው ሐሙስ በካፋ ዞን፤ ዴቻ ወረዳ፤ ሞዲዮ ጎምበራ ቀበሌ መንደር 3 በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ፣ 3 የአንድ ቤተሰብ አባላትን ህይወት መቅጠፉን የዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ አስታውቋል።


Read 986 times