Saturday, 27 July 2024 21:41

”የጉራጌ የክልልነት ጥያቄን ወደ ዓለም አቀፍ ፍ/ቤት ልንወስደው እንችላለን”

Written by  በሚኪያስ ጥላሁን
Rate this item
(6 votes)

ከጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ጋር በተገናኘ፣ በአገር ውስጥ ፍርድ ቤት የሚሰጠውን ውሳኔ ከተመለከተ በኋላ፣ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የመውሰድ ዕቅድ እንዳለው ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ አስታወቀ፡፡ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጀሚል ሳኒ፣ ፓርቲያቸው እስከመጨረሻው ድረስ ሕጋዊና ሰላማዊ በሆኑ መንገዶች ብቻ መንቀሳቀሱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡  
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጉራጌ የክልልነት ጥያቄን በተመለከተ የሰጡት ምላሽ፤ “ሕዝቡን ያስቆጣ፣ ያሳዘነና ቅሬታን የፈጠረ ጉዳይ ነው። ሕዝብን መናቅ የታየበትም ነው።” ያሉት አቶ ጀሚል፤ “ይህም ሕገ መንግስቱን በትክክል ያለመረዳት ይመስለኛል።” ብለዋል።
 “አንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ራሱን እንዲያስተዳድር ሲፈቀድለት፤ በግለሰቦች ይሁንታ ወይም ጠያቂው ባለው የልብ ስፋትና ጥበት ሳይሆን ሕገ መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት መሆን ነበረበት” ሲሉም ሞግተዋል።
የጉራጌ ሕዝብ ፍላጎት በውይይት “ይገለጻል” ማለት እንደማይቻል የሚናገሩት አቶ ጀሚል፤ “የሕዝቡ ጥያቄ ጉራጌ ዞን ‘ክልል ይሁንልኝ’ የሚል እንጂ አማራ፣ አዲስ አበባ አሊያም ኦሮሚያ... ላይ ክልል ‘ይሰጠኝ’ የሚል አይደለም።” ብለዋል፡፡  
“ከረሜላ በመወርወር የሚሸነገልና የሚታለል ማሕበረሰብ በአሁኑ ሰዓት የለም። ‘ልብህ ጠባብ ነው፣ ሰፊ ነው’ በማለት ሳይሆን፣ ትክክለኛ ማሕበረሰቡ የጠየቀውን ፍላጎቱን መረዳት ይገባል” ብለዋል፤ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው።
“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚያነሷቸው ሃሳቦች መረጃ እንደሌላቸው ነው የተረዳነው” ያሉት አቶ ጀሚል ሳኒ፤ “የክልልነት ጥያቄውን የፓርቲው ጥያቄ አድርገው ነው ያቀረቡት። ይህም የተሳሳተ ነው። በዚህም ጥያቄውን አድበስብሰው አልፈውታል” ሲሉ አስረድተዋል።
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ነፍጥ ያነሱ ወገኖች ድምጽ እንኳን እየተሰማ እንደሚገኝ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊው ጠቅሰው፣ ፓርቲያቸው እንደ አንድ ፓርቲ፣ አባላቱም እንደ አንድ የጉራጌ ተወላጅ፣ የጉራጌ የክልልነት ጥያቄን ሰላማዊና ሕጋዊ አማራጮች ተጠቅመው ለማስኼድ እንደሚጥሩ ተናግረዋል።
“ሰላማዊ የክልልነት ጥያቄን ለማራመድ በፍርድ ቤት የመሰረትነው ክስ አለ። ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔ ካላስደሰተንና ይግባኝም ጠይቀን አመርቂ ውጤት ካላገኘን፣ በሌላ መንገድ እንቀጥላለን። የአገር ውስጡን ስንጨርስ ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የመውሰድ እንቅስቃሴ ይኖራል።” ብለዋል፤ አቶ ጀሚል ለአዲስ አድማስ።
ባለፈው  ሰኞ ሃምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ባያደረጉት ውይይት ላይ ጎጎትን ወክለው የተገኙት አቶ መሐመድ አብራር፣ የጉራጌ የክልልነት ጥያቄን በተመለከተ “ግልጽ የሕገ መንግስት ጥሰት ተፈጽሟል” ያሉ ሲሆን፣ በሕዝቡ ዘንድ የክላስተር ምክረ ሃሳብ “ውድቅ” መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የጉራጌ ዞን ሕዝብ ከጠ/ሚኒስትሩ ግልጽ ምላሽ እንደሚሻም ጠቁመዋል።
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ በጉራጌ ዞን ከሕብረተሰቡ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመው፣ “ክላስተሩን ያዋቀርነው ሕዝቡን በማወያየት ነው” ብለዋል፡፡ ሕዝቡ የክልልነት ጥያቄው ምላሽ እንዲሰጠው በጉጉት እንደማይጠብቅም ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
“ጉራጌ ልቡ ትልቅ ነው። ልቡ የተዘረጋ ነው። በሰፈር የታጠረ አይደለም። ግን ልቡን ለማጠር የሚሞክሩ ፖለቲከኞች አሉ።” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ለዚህም የጉራጌ ሕዝብ በተለያዩ ክልሎች ተዘዋውሮ የሚኖር መሆኑን በማስረጃነት አቅርበዋል።
 “የክልልነት ጥያቄ የፓርቲ ጥያቄ ነው? ወይስ የሕዝቡ? የሚለው መፈተሽ አለበት” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ለጉራጌ የሚያስፈልገው መልካም የስራ ዓውድ፣ መልካም ፖሊሲዎች፣ ሰርቶ ሲያተርፍ በሕግ አግባብ ከመንግስት ጋር መነጋገር፣ ልጆቹንና ራሱን ማበልጸግ ነው። እርሱ ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን።” ብለዋል።
ጎጎት ከምስረታው ጊዜ አንስቶ ጫና እንደነበረበትና በዚህ ወር ግን ከእነዚህ ጫናዎች አንጻራዊ ነጻነት ማግኘቱን  ለአዲስ አድማስ የገለፁት አቶ ጀሚል፤ “ነገር ግን አሁንም ስጋት አለብን፤ አባላቶቻችን፣ አመራሮቻችንና ደጋፊዎቻችን በወልቂጤና በቡታጅራ፣ እንዲሁም በሌሎች የጉራጌ ዞን ከተሞች፣ በአዲስ አበባም ጭምር ታስረዋል።” ብለዋል።
ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ፣ መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም፣ መሥራች ጉባዔውን በማካሄድ ወደ እንቅስቃሴ የገባ ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል;፡፡  

Read 1500 times