Saturday, 27 July 2024 21:45

ጎልያድና ታሪኩ በሳይንሳዊ መላምት ዐይን

Written by  ስንታየሁ ገ/ጊዮርጊስ
Rate this item
(1 Vote)

 1. መንደርደሪያ፡ በዚህ ዘመን ላሉት የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፍት
በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ሰዎችን (ምሁራንን?) ከማያግባቧቸው ጉዳዮች አንዱ ታሪክ ነው፡፡ በአንጻሩ የታሪክ ጸሐፊዎችን በአመዛኙ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር፣ ከአንድ ዓይነት መረጃ ተነስተው የየራሳቸውን ወዝ አላብሰው ታሪክን ሊጽፉ የሚችሉ መሆናቸው ነው፡፡
ታሪክን ያነበቡ ሰዎች፣ ካነበቧቸው መጻሕፍት ተነስተውና፤ የተለያዩ መረጃዎችን ትንተና ዋቢ በማድረግ፣ ይህኛው የታሪክ አጻጻፍ ጥሩ/ትክክል ነው፤ ይህኛው ደግሞ ጥሩ/ትክክል አይደለም በማለት ሊከራከሩ ይችላሉ፡፡ ክርክሩ ከቆሙበት ቦታ አንጻር የሚያደርጉት ከመሆን አልፎ ለሁለቱም ወገን ዳኝነትን ለማስፈን አይረዳቸውም፡፡ በታሪክ ክርክር ውስጥ መረጃ እንጂ የታሪኩ ወዝ አይረታም (ረ ይላላ)፡፡ እንደ ሁኔታው ግን የተጻፈው ታሪክ ሊያካርርና ወደ ቅራኔ ሊያስገባ ይችላል፡፡ ታሪክ የሚያጣላው በጽሑፉ የተመለከተው መረጃና ትንታኔው እኔን/ቡድኔን በስርዓት አልገለጠም፣ አሳንሶኛል፣ ወይንም ለሌላው ቡድን አድልቷል የሚል ስሜት በውስጣችን ጎልቶ ስለሚሰማን ነው፡፡
ታሪክ ፀሐፊዎች ከመረጃ የወጣ (የተጣመመ መረጃን መሰረት ያደረገ) ታሪክን ሲጽፉና እርስ በእርስ ሲቃረኑ፣ በመጀመሪያ የተጣሉት የታሪክ ፀሐፊዎቹ ናቸው፡፡ ያሏቸውን መረጃዎች ይዘው በጠረጴዛ ዙሪያ በመቀመጥ፣ የጻፉትን ለምን እንደጻፉ የአመለካከታቸውን ዳራ ማስረዳትና ጽሁፎቻቸውን አስታርቀው ራሳቸውም እርስ በእርስ መታረቅ ያለባቸው ጸሐፊዎቹ ናቸው፡፡ እርስ በእርስ ታርቀው ሲያበቁ አንባቢንና የታሪክ ተማሪን/ተከታይን ያስታርቁ፡፡ ይህን ለማድረግ ታሪክ ፀሐፊዎች ተሰባስበው ተከታታይ ጉባኤዎችን በማድረግ፣ አንድ “የኢትዮጵያ ታሪክ” ጽፈው ቢያቀርቡ መልካም ይመስለኛል፡፡ እስከ አሁን የነበረው ታሪክ ሁሉ ጥሩ/ትክክል አይደለም ማለት ግን አይደለም፡፡ አሁንም በታሪክ ዙሪያ የሚጠይቁ ሰዎች በርካታ በመሆናቸው ነው ይህን እንድል የገፋፋኝ፡፡ ታሪክ ኢትዮጵያውያንን ለመለያየት ምክንያት እንዳይሆን መላ ይበጅለት ለማለት ነው፡፡ የታረቀ የታሪክ ጸሐፊ በሌለበት፣ የታረቀ ታሪክና ሕዝብ ማግኘት ሊከብድ ይችላል፡፡
በዚህ ሂደት፣ ሁላችንም ካለመጠራጠር የምንቀበለው የኢትዮጵያ ታሪክ (የጦርነት ታሪክን ብቻ ሳይሆን የኤኮኖሚውን፣ የባህሉን፣ የአንድነቱን፣… ያቀፈ ታሪክ) ይኖረናል ማለት ነው፡፡ በታረቀ ታሪክ ላይ ተመስርቶ አጠቃላይ አገራዊ እርቅን ማድረግ ቀላል ነው፡፡ አገራዊ እርቅን መፍጠር በየትኛውም መልኩ ወሳኝ ሂደት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ያልታረቀ ታሪክና ያልተግባቡ (ያልታረቁ) የታሪክ ጸሐፊዎች ባሉበት ሁኔታ የሚካሄድ የእርቅ ሂደት የማያዳግም የእርቅ ሂደት መሆን የሚሳነው ሊሆን ይችላል ብዬ እሰጋለሁ፡፡ “አለባብሶ ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንዲሉ፡፡
በጥቅሉ፣ በአንድ ታሪክ/ድርጊት ላይ ሁለት ዓይነት (ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል) የአጻጻፍ እይታዎች/ስልቶች/ምርምሮች ሊኖሩ መቻላቸውን አምናለሁ፡፡ ታሪክን ሁሌም አዎንታዊና አሉታዊ ጎኑን በጥንቃቄ ዳስሰው፣ አዎንታዊነትን ተላብሶ ሕዝብን እንዲያስማማ ማድረግ ይገባል፡፡ በአሉታዊ የፖለቲካ ጎኑ ከታየ ታሪክ አብሮ አያኗኗርም፡፡ ታሪክን ከግል ወይንም ከቡድን ጥቅም አኳያ የመጻፍ አካሄድ ሊኖር መቻሉን አልጠራጠርም፡፡ ይሄ አጻጻፍ አሉታዊ ስለሆነ ጥንቃቄን ይሻል፡፡
2. ታሪክና ወዙ  
አንድ የታሪክ ጸሐፊ በመረጃ ላይ ከተመሰረቱ የታሪክ ድርጊቶች በመነሳት መቼ? የት? በማን? እንዴት? ለምን? ሊሆን ቻለ ብሎ ሊጠይቅና ሳይንሳዊ ትንተናን አክሎበት ሊጽፈው ይችላል፡፡ በመረጃ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ድርጊቱ ባይለወጥም፣ የታሪኩ ወዝ ግን ሊለወጥ ይችላል፡፡ የታሪኩ ወዝ ሲለወጥ፣ ቀደም ሲል ታምኖበት የነበረው “ደረቅ” ታሪክም በአንጻራዊነት “ወዙ ይለወጣል”፡፡ ወዙ ሲለወጥ ደግሞ በአንዳንዶች ዘንድ የቀድሞ ተአማኒነቱ ሊሸረሸር ይችላል፡፡ ለዚህ አባባል ማስረጃነት የዳዊትንና የጎልያድን ታሪክ በምሳሌነት አሳያለሁ፡፡ ታሪኩን የወሰድኩት “David and Goliath” ከተሰኝ፣ ማልኮም ግላድዌል (Malcolm Gladwell) በ2013 እ.ኤ.አ ከጻፈው መጽሐፉ ውስጥ ነው፡፡ የራሴን ትንተና እና  ከመጽሐፍ ቅዱስ የወሰድኳቸውን አንዳንድ መረጃዎች ተጠቅሜአለሁ፡፡
በእርግጥ ማልኮም በዳዊትና በጎልያድ ታሪክ ውስጥ ሊያመለክት የሞከረው፣ ትንሽ ነገር የራሱ ጥቅም/ብርታት እንዳለውና፣ ትልቅ/ግዙፍ ነገርም የራሱ ጉዳት/ድክመት እንዳለው ለማሳየት ነው፡፡ ማልኮም በጽሑፉ ውስጥ በጥቅሉ ሊያሳይ የሞከረው ጉዳይ፣ ትንሽ ቢመስልም (ለምሳሌ፣ ወንጭፍ)፣ በተካንንበት ነገር በአግባቡ ከተጠቀምንበት ግዙፉን ኃይል እናሸንፍበታለን የሚለውን ስልታዊ የአስተሳሰብ መስመር  ነው፡፡
እኔ ለማሳየት የምሞክረው ግን (የማልኮም ሃሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ) ታሪክን በሳይንሳዊ የምርምር ስልት/መንገድ በማየት (የታሪክ መረጃዎችን ሳይቀይሩ)፣ ወዙን ለመቀየርና መጀመሪያ ታሪኩ ሲከናወን የታየበትን አቅጣጫ/እምነት “መለወጥ” እንደሚቻል ነው፡፡ በእርግጥ ታሪኩ የተከናወነ ድርጊት በመሆኑ “እውነቱን” መለወጥ አይቻልም (የተጻፈው ታሪክ እውነት ነው ብለን እስካመንን ድረስ)፡፡
እንግዲህ፣ የዳዊትና ጎልያድ “የጦርነት ታሪክ” ሲጻፍ ሁለት ጽንፎችን ሊይዝ እንደሚችል ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛውን ሃይማኖታዊ፣ ሌላኛውን ሳይንሳዊ  በማለት ልክፈለው፡፡ ሌላም አቅጣጫ ሊኖረው ይችላል - ፍልስጥኤማውያን ጀግናቸው ስለነበረው ጎልያድ በራሳቸው መንገድ የሚተርኩለት፡፡ እስቲ የዳዊትንና ጎልያድን የታሪክ አውነታ በሁለቱም የአተራረክ መንገድ እንመልከት፡፡
የመጀመሪያው፣ “በሃይማኖት መስመር የተገነባው” የታሪክ አመለካከት ነው - በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኘው የእሥራኤላውያን ታሪክ፡፡ ሁለተኛው፣ በመጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው ያው ታሪክ ሆኖ በሳይንሳዊ መንገድ ለመተንተን/ለማየት የተሞከረው ነው፡፡ እንደ መንደርደሪያ በመጀመሪያው (“በሃይማኖት መስመር በተገነባው”) ልጀምር፡-
3. የዳዊትና ጎልያድ የፍልሚያ ታሪክ፡ ሃይማኖታዊ ወዝ
በጥንታዊት ፍልስጥኤም እምብርት የሚገኝ ሽፍላህ የሚባል አካባቢ ነበር፡፡ ይህ ሥፍራ የይሁዳ ተራራዎችን በምሥራቅ በኩል በከበቡ ወጣ ገባ ጉብታዎችና ሸለቆ፣ እንዲሁም በምዕራብ በኩል የሜዲትራንያንን ባህር አካልሎ በሚገኝ ለጥ ያለ ሜዳ (ዝቅታ ሥፍራ) የሚገኝበት ነበር፡፡ ሥፍራው ልብን የሚማርኩ የወይን ማሳዎችና የስንዴ እርሻዎች እንዲሁም እጣንና ከርቤ የሚገኙባቸው ጫካዎች ያሉት ድንቅ ቦታ ነበር፡፡ ቦታው በብዙ መልኩ ስትራተጂካዊ ሥፍራም ነበር፡፡ ይህ የታሪክ አገላለጽ መልክዓ ምድራዊ እውነት ነው፡፡ ዛሬ በተገለጸው መልኩ ላይኖር ይችላል (እዚህ የተገለጸው ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት በታየበት ሁኔታ ነው)፡፡
ሥፍራውን ለመቆጣጠር ለምዕተ ዓመታት በርካታ ጦርነቶች ተደርገውበታል፡፡ ሥፍራው ከሜዲትሬንያን ወለል ተነስቶ ሽቅብ ወደ ይሁዳ ከፍታማ ኮረብታዎች የሚያመራ ከመሆን አልፎ፤ ወደ ሄብሮን፣ ቤተልሄምና ኢየሩሳሌም መተላለፊያ ቁልፍ በር ነበር፡፡ የኤላ ሸለቆ አዋሳኝ የነበረ፣ ዋናውና ስትራተጂካዊ የሆነው አኼሎን የተሰኘው ሸለቆ ደግሞ በሰሜን በኩል ይገኝ ነበር፡፡ የኤላ ሸለቆ በ12ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የክርስትና ጦርነት (ክሩሴድ) የተደረገበት በመሆኑ ብዙ ጊዜ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህም የታሪክ እውነት ነው፡፡
ከዚያ አንድ ሺህ ዓመታት ቀደም ብሎ መቃብያን ከሶሪያ ጋር ጦርነት ያደረጉበትና በዘመነ ብሉይም የተበታተነው የአይሁድ/እሥራኤል ግዛት በፍልስጥኤማውያን ሠራዊት ላይ ድል ያገኘበት ሸለቆ ነበር፡፡ ፍልስጥኤማውያን ባህሩን አካልሎ ባሉት ሥፍራዎች ላይ ሰፍረው የነበሩ ሲሆን፣ እሥራኤላውያን ደግሞ ተራራማውን ሥፍራ ይዘው በንጉሥ ሳኦል ይተዳደሩበት የነበረበት ዘመን ነበር፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት በአሥራ አንደኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ፍልስጥኤማውያን የኤላ ሸለቆን አካልሎ ባለው የምሥራቁ ክፍል ቀስ እያሉ መስፈር ጀምረው ነበር፡፡ ዋና ዓላማቸው በቤተልሔም አቅራቢያ የነበረውን የተራራማውን አንድ ክፍል በመያዝ የንጉሥ ሳኦልን መንግሥት ሁለት ሥፍራ ለመክፈል ነበር፡፡
ፍልስጥኤማውያን በጦርነት የተፈተኑና አደገኛ የሆኑ የእሥራኤላውያን ጠላቶች ነበሩና፤ ንጉሥ ሳኦል ስጋት ገብቶት ሠራዊቱን ሰብስቦ ከተራራው በመውረድ ጦርነት ሊገጥማቸው ተዘጋጀ፡፡ እሥራኤላውያን በሰሜን በኩል በፍልስጥኤማውያን ትይዩ ድንኳናቸውን ተክለው ይጠባበቁ ጀመር፡፡
ፍልስጥኤማውያን ደግሞ በኤላ ሸለቆ ደቡባዊ ክፍል የጦር መንደር ከትመው እሥራኤላውያን ከተራራው ወርደው እንዲገጥሙዋቸው ይጠባበቁ ነበር፡፡ የሁለቱም ሠራዊት ማዶ ለማዶ ይተያያሉ፡፡ ማናቸውም ለመንቀሳቀስ ግን አልደፈሩም፡፡ መፋጠጥ ብቻ ሆነ፡፡
በመጨረሻ ፍልስጥኤማውያን ትዕግሥታቸው አለቀ፡፡ በዚህ ጊዜ ዋናውን ተዋጊያቸውን ጎልያድን ወደ ሸለቆው እንዲወርድ በማድረግ ፍጥጪያውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በድል ለማጠናቀቅ ወሰኑ፡፡ በመሆኑም፣ ወደ እሥራኤላውያን መንደር በመቅረብ፣ “አንድ ሰው መርጣችሁ ወደ እኔ ላኩ፡፡ እርሱ እኔን በውጊያ ካሸነፈ፣ እኛ ለእናንተ ባሮች እንሆንላችኋለን፡፡ እኔ በውጊያ ካሸነፍኩት ግን እናንተ ባሪያዎቻችን ትሆናላችሁ፡፡” እያለ ይጮህ ነበር (በመጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ምዕ 17፡ 8-10  እንደተጻፈው)፡፡
ጎልያድ ግዙፍ ነበረ፡፡ ስድስት ክንድ ከስንዝር ቁመት ነበረው፡፡ በራሱ ላይ የናስ ቁር የደፋና ጥሩር የለበሰ ነበር፡፡ በመላ አካሉም መከላከያ ነበረው፡፡ እግሮቹ የናስ ገምባሌ ነበራቸው፡፡ ጦር፣ ሰይፍና ጋሻም ታጥቆ ነበር፡፡ ከእሥራኤላውያን ወገን አንድም ደፍሮ ሊገጥመው የተንቀሳቀሰ አልነበረም፡፡ ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ጎልያድ የተጻፈ ታሪክ ነው፡፡
በእሥራኤል ወገን ደግሞ፣ ስሙ ዳዊት የተባለ ወጣት እሥራኤላዊ እረኛ ከቤተልሔም ተነስቶ ለታላቅ ወንድሞቹ ስንቅ ለማቀበል በጦር መንደሩ ውስጥ ይገኝ ነበረ፡፡ ፍልስጥኤማዊውን ለሚገድል ሰው፣ ቤተሰቦቹን እጅግ ባለጠጋ እንደሚያደርጋቸው፣ ልጁንም እንደሚድርለትና ያባቱን ቤተሰብ ከግብር ነፃ እንደሚያወጣቸው፣ ቀደም ሲል ንጉሥ ሳኦል የተናገረውን ዳዊትን ጨምሮ ሁሉም ሰምተውታል፡፡ እሥራኤላውያን ጎልያድን ለመግጠም የነበረባቸውን ፍርሃትም ዳዊት ተመልክቷል፡፡
ፍልስጥኤማዊው ተዋጊ ጎልያድ፣ እሥራኤላውያንን ሲገዳደር ዳዊት ሰማ፡፡ ጎልያድ የሚናገርውን ሲሰማ ወደ ንጉሥ ሳኦል ፊት በፈቃደኝነት ቀርቦ በውጊያ ሊገጥመው እንደሚፈልግ ገለጠለት፡፡ ንጉሥ ሳኦልም ፊቱ የቆመውን ለግላጋ ወጣት ተመልክቶ፤ “አንተ ልጅ ስለሆንክ ከዚህ ፍልስጥኤም ጋር ለመግጠም አትችልም፡፡ እርሱ ከልጅነቱ ጀምሮ በጦርነት ያደገ ነው፡፡” አለው፡፡ እረኛው ዳዊት ግን ፤ “እኔም የአባቴን በጎች ስጠብቅ በጎችን ነጣቂ አንበሳና ድብ ሲመጡብኝ ከኋላቸው ተከትዬ በመሄድ ከጉሮሮዋቸው አስጥላቸው ነበር፡፡” ብሎ በልበ ሙሉነት መለሰ፡፡ ንጉሥ ሳኦል ምርጫ አልነበረውም፡፡
ንጉሥ ሳኦል ያሰበው ግን ዳዊት በተለመደው መንገድ (የእጅ በእጅ ግጥሚያ) ጎልያድን እንደሚገጥመው ነበርና ሰይፉን አስታጠቀው፣ ጥሩር አለበሰው፣ በራሱም ላይ የናስ ቁር ደፋለት፡፡ ዳዊት ግን ያልለመደው ስለነበር ገና አንድ ሁለት እርምጃዎችን እንደተራመደ ደከመው፡፡ በላዩ ላይ ያለበሱትን ሁሉ አወልቆ በትሩን በእጁ ያዘ፡፡ ወንጭፉም በእጁ ነበር፡፡ ከወንዝ አምስት ድቡልቡል ድንጋዮችን መርጦ በእረኛ ኮረጆዎቹ ውስጥ ከተተ፡፡ ከዚያም፣ ከተራራው ቁልቁል እየተንደረደረ ጎልያድ ወደ ነበረበት ሸለቆ ወረደ፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የተተረከ ነው፡፡
“ጎልያድ ዳዊትን አይቶ ናቀው” ይላል መጽሐፍ ቅዱስ፡፡  “ወደ እኔ ና፡፡ ሥጋህን ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጠዋለሁ” ብሎ ጮኸ - ጎልያድ፡፡ በዚህም በታሪክ አስደናቂ ሆኖ የተመዘገበው “ጦርነት” (ፍልሚያ) በጎልያድና በዳዊት መካከል ተጀመረ፡፡
ንጉሥ ሳኦልም ሆነ ጎልያድ የጠበቁት የተለመደውን የእጅ በእጅ ውጊያ ነበር፡፡ ዳዊት ግን በየዕለቱ የሚጠቀምበትንና እጅግ የተካነበትን ወንጭፍ ይዞ ስለነበር አንድ ድንጋይ ከኮሮጆው አውጥቶ በመወንጨፍ በግዙፉ ጎልያድ ግንባር ላይ ሰነቀረው፡፡ ከአንዲት ድቡልቡል ደንጊያ በስተቀር ሌላ አላባከነም፡፡ “ጦርነቱም” (ፍልሚያው) በዚያው ተደመደመ፡፡ የዳዊትና ጎልያድ የጦርነት/ፍልሚያ ታሪክ በሃይማኖት እይታ ሲቃኝ፣ ዋናው ጉዳይ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ተብለው የሚጠሩት እሥራኤላውያን ያገኙትን ድል በእግዚአብሔር ኃይልና በሕዝቡም ጥንካሬ መከናወኑን ማስመስከር ነው፡፡ ለዚህም ዳዊት ከተናገረው ለአብነት ልጥቀስ፡-
“ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል“፤
”…ሰልፉ የእግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔርም እናንተን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል”፤
…“አንተ ጦርና ጎራዴ ጋሻም ይዘህ ትመጣብኛለህ፡፡ እኔ ግን አንተ በተገዳደርከው በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ” በማለት ዳዊት የተናገራቸው ሁሉ ሃይማኖታዊ (በእግዚአብሔር ድንቅ ኃይል የመመካት) እንደሆኑና ለታሪኩ የእምነት መሠረቶች መሆናቸውን ማየት ይቻላል፡፡
በዚህ ረገድ፣ የተከናወነው ታሪክ እውነት ቢሆንም፣ እንዲያስተላልፍ የታቀደው ሃይማኖታዊ መልዕክት ደግሞ ፍጹም የተሳካ ነው - ድል ለዳዊትና ለወገኑ በመሆኑ፡፡
ታሪኩን የጻፉት ሕዝቦች ወገን የሆኑትና (እሥራኤላውያን) እንደ ሃይማኖት ታሪኩን የተቀበሉቱ ሌሎች (ክርስቲያን የሆኑ ሁሉ) በዚህ የታሪክ አካሄድ ሙሉ በሙሉ ያምኑበታል፡፡ ዳዊት አንድን ታላቅ የሆነ የፍልስጥኤም ተዋጊ በወንጭፍ መትቶ መግደሉንና የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራም በታሪኩ ውስጥ ዘወትር ያስታውሱበታል፡፡
በሃይማኖታዊው የታሪክ አካሄድ (አጻጻፍ) ምንጊዜም ዳዊት (እሥራኤላውያን) አሸናፊ፣ ፍልስጥኤማውያን ደግሞ ተሸናፊ ናቸው፡፡ ታሪኩ ሲጻፍ የተባለውንና የተከናወነውን “እውነት” አሰፈረ እንጂ ይህንን የስነ-ልቡና ሚዛን እንዲጠብቅ ሆን ተብሎ ለመጻፉ ማንም መረጃ ሊያቀርብ አይችልም፡፡ በዚያን ወቅት ክርስትናም በሃይማኖትነት አይታወቅም፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ታሪኩ የሚያስከብረው ወገን (እሥራኤላውያንና ክርስቲያን የሆነ ሁሉ) እንዳለ የሚቀበለው፣ በታሪኩ “የሚያፍረው ክፍል” (ፍልስጥኤማውያን) ደግሞ “እከሌ የጻፈው ታሪክ” በማለት የማይቀበሉት ሊሆን ይችላል፡፡
የጦርነትን/ፍልሚያን ታሪክ የሚያነብ ሰው፣ ሁሌም የራሱን ጀግና ከፍልሚያው መካከል መፈለጉ አይቀርም፡፡ የሽንፈትን ታሪክ ማንም አይወድም፡፡
ሳይንሳዊ ወደ ሆነው ወደ ሁለተኛው የታሪክ አተራረክ ልግባ፡፡
4. የጎልያድ ታሪክ፡ ሳይንሳዊ ወዝ  
ሁለተኛው የታሪክ አጻጻፍ የሳይንሳዊ መላምትን (ጥያቄዎችን አንስቶ መልስ ለመስጠት ሂደትን የፈተሸ/የመረመረ) የተላበሰ ነው፡፡ ሳይንሳዊ የሆኑ ጥያቄዎችንና ትንታኔን የተመረኮዘ የታሪክ ምርምር/አጻጻፍ ካለመነሻዎች አይነሳም፡፡
ጎልያድ ለመዋጋት ወደ ሜዳው ሲወርድ ከፊቱ የሚሄድ ጋሻ ያነገበ ሰው (ጋሻ-ጃግሬ) ነበረው፡፡ በጥንት ጊዜ ጋሻን ይዘው ከፊት የሚቀድሙ ሰዎች የሚያስፈልጉት ለቀስተኞች ነበር (ቀስትና ደጋን በሁለት እጆቻቸው ይዘው ስለሚራመዱ፣ ከፊት የሚመጣ ጠላትን የሚከላከሉበት ነፃ የሆነ ሦስተኛ እጅ ስላልነበራቸው)፡፡ ጎልያድ የእጅ በእጅ ውጊያን የሚያደርግ ተዋጊ ሆኖ ሳለ ለምን ጋሻ በያዘ ሌላ ሰው መታገዝ አስፈለገው? የሚለው አንዱ መነሻ ጥያቄ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ይህንን አንድ በሉ፡፡
ሌላው መነሻ ደግሞ ጎልያድ ዳዊትን “ወደ እኔ ና” ብሎ መጣራቱ ነው፡፡ ጎልያድ ጀግና የተባለ ተዋጊ ነው፡፡ በወቅቱ ከተለመደው የእጅ በእጅ የውጊያ ስልት አኳያ፣ ለምን ጎልያድ ወደ ዳዊት እየተፋጠነ አልሄደም? በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ እንደተጠቀሰው፣ የጎልያድ አካሄድ ዘገምተኛ/ቀርፋፋ እንደነበረ ነው፡፡ በጦርነት ጀግና ለተሰኘና ከፍተኛ ኃይል ላለው ተዋጊ ቀሰስተኛ የሆነ እርምጃ የሚጠበቅ አይደለም (በወቅቱ ከነበረው የውጊያ ዓይነትና ስልት አኳያ)፡፡ ይህንን ሁኔታ ደግሞ ሁለት በሉ፡፡
ሌላው የጥያቄ መነሻ ደግሞ ዳዊት ይዞት የነበረውን በትር እንዳየ ጎልያድ የተናገረው ቃል ነው፡፡ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” ብሏል ጎልያድ ዳዊትን፡፡ ይህ አባባል በእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈው “Am I a dog, that you come to me with sticks?” (1 Samuel 17: 43) ፡፡ “በትር” የሚለውን የአማርኛ ነጠላ ቃል በእንግሊዝኛው “sticks” (“በትሮች”) በማለት በብዙ ስለገለጠው ለጎልያድ የታየው አንድ በትር ብቻ ሳይሆን ከአንድ በላይ በትሮች ናቸው ብለው፣ እንዴት/ለምን? በማለት ከመጠየቅ ይነሳሉ - ለድርጊቱ ሳይንሳዊ ትንተና ለመስጠት የሚነሱቱ የታሪክ ተመራማሪዎች፡፡
ዳዊት የእረኛ ኮሮጆና በትር ይዞ ወደ እርሱ ሲሄድ ጎልያድ ስለ “በትሮች (sticks)” ብቻ መናገሩም ዙሪያ ገባውን የማገናዘብ ጉድለት እንደነበረበት ጠቁሟቸዋል፡፡ ወንጭፉን አላየም ይሆን? ወይንም ወንጭፉን እያየ ጥቅሙንና አገልግሎቱን አልተረዳ ይሆን? በአጠቃላይ ጎልያድን በዙሪያው ያሉትን ነገሮች የማጤን ችግር የተጫነው ግዙፍ ሰው አድርገው ይወስዱታል፡፡ እኒህን እንደ ሦስተኛ መንደርደሪያ ውሰዷቸው፡፡
ከላይ ከተመለከቱት ትንታኔዎች (ጥያቄዎችን ከሚጭሩ ሁኔታዎች) አንጻር፣ በርካታ የህክምና ኤክስፐርቶች የሚያምኑት ጎልያድ የጤንነት ችግር እንደነበረበት ነው (ልብ በሉ፤ በዚያን የታሪክ ወቅት የጎልያድን ጤንነት የመረመረው ማንም ሃኪም የለም፡፡ በታሪኩ ከተገለጹት ሁኔታዎች በመነሳትና አንዳንድ ህመሞች የሚያሳዩትን ባሕርያት በማመሳከር የሚደረግ የሳይንስ መላምትና ምርምር ነው)፡፡
የተፈጸመውን ታሪካዊ ድርጊት በሳይንሳዊ መንገድ የመረመሩት ጸሐፊዎች፣ … የጎልያድ አጠቃላይ ሁኔታው “አክሮሜጋሊ (acromegaly)” በተሰኘ (ከፒቱታሪ እጢ በሚመነጭ ሕመም (a disease caused by a benign tumor of the pituitary gland) የጤንነት መታወክ የነበረበት ሰው እንደነበረ በሳይንሳዊ መላምቱ ይስማማሉ፡፡ እጢው የሰውን ያልተመጣጠነ የእድገት ሆርሞንን የሚያመነጭ ጭምር በመሆኑ ለጎልያድ እጅግ የገዘፈ ቁመና ምክንያት እንደሆነም ያስረዱበታል፡፡
“አክሮሜጋሊ” ከሚያስከትላቸው ችግሮች አንዱ እይታን የመጋረድ ችግር ነው፡፡ የፒቱታሪ እጢዎች እድገት ወደ ዐይን የሚሄደውን ነርቭ ስለሚጫኑት በ“አክሮሜጋሊ” የተጠቁ ሰዎች በአብዛኛው በተገደበ የዐይን እይታና በጥንድ ብዥታ የሚጠቁ ናቸው፡፡ ይህ በሕክምና የተረጋገጠ ሳይንሳዊ እውነት ነው፡፡  ጎልያድ ወደ ሸለቆው ሲወርድ በሌላ ሰው መንገዱን ይመራ የነበረውም ለዚያ ነበር ብለው ገምተዋል፡፡ በዝግታ ይራመድ የነበረ መሆኑም፣ በላዩ ላይ ከተጫኑት ከባድ የውጊያ እቃዎች/መሣሪያዎች በተጨማሪ፣ በዙሪያው ያሉትን ነገሮች በውል አጥርቶ የማያይ በመሆኑ ጭምርም ነበር ብለው ይደመድማሉ፡፡
ዳዊት ወደ እርሱ በመምጣት እየተጠጋዉ የነበረ ቢሆንም፣ “ወደ እኔ ና” በማለት ተጣርቷል - ጎልያድ፡፡ በዳዊት እጅ ስላለው ወንጭፍ ብዙ ያጤነው ነገር የነበርም አይመስልም፡፡ ለጎልያድ ያንን ያህል ግዝፈት የሰጠው ተፈጥሮ፣ ለድክመቱና ለውድቀቱ ታላቅ ምክንያት ነበር ብለውም አምነዋል፡፡
ዳዊት ያንን ግዙፍ ሰውነት በወንጭፍ ለመምታት ያንን ያህል ችግር አልነበረበትም፡፡ ርቀቱን መጥኖ ሲያበቃ፣ በተካነበት ወንጭፍ የጎልያድን ፍጻሜ በሞት ደመደመው፡፡ ዳዊት ጎልያድን በወንጭፍ እንደገደለው የሚተርከው ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስና በሌሎች የታሪክ ጽሁፎች የተረጋገጠ ነው፡፡
በሳይንስም ሆነ በሌላ ትንታኔ የታሪክን አካሄድ የሚመረምሩ ጸሐፍት አንድ ጉዳይ አስደንቋቸው ወይም ጉዳዩን ይበልጥ ለመመርመር ያ የታሪክ/ክንዋኔ ስለምን/እንዴት ሊሆነ ቻለ? ብለው በማጠየቅ ይጀምሩና የታሪኩ ጭብጥ የሆኑትን ድርጊቶች የሚተነትኑበትና ትምህርትም እንዲወሰድበት የሚጥሩበት መንገድ ሊኖር ይችላል፡፡ ትንታኔው ታሪኩን ፍጹም አይቀይረውም፡፡ የታሪኩን ወዝና አቅጣጫ (አንዳንድ የጭብጦችን ትንታኔ ጭምር) ግን ይለውጣል፡፡
ለምሳሌ፤ ከሃይማኖት አንጻር የዳዊትና ጎልያድ የፍልሚያ ታሪክ ዋና አላማ፣ የትንሹን የዳዊትን ጉብዝና ማሳየት ብቻ አይደለም፡፡ ማንም በወንጭፍ የተለማመደ ልጅ አነጣጥሮ ሊመታበትና ሊገድልበት ይችላል፡፡ የታሪኩ ዋና ሃይማኖታዊ ዓላማና ግብ የእግዚአብሔርን ቻይነትና በእርሱ ፍቃድ የተገኘውን ታላቅ ድል ማብሰርም ጭምር ነው፡፡
“የእግዚአብሔርን ሕዝቦች አምላካቸው ከጠላታው ታደጋቸው” የሚለው መልእክት የታሪኩ ትልቁ ዳራ ነው፡፡ እዚህ ላይ የዳዊት ድፍረት፣ የወንጭፍ አወነጫጨፍ ችሎታው በጠላቱ ላይ ያገኘው ድል ጥያቄ ውስጥ አይገባም፡፡ ሳይንሳዊው ትንተና ታሪኩን ሊቀይረው ባይችልም የታሪኩን ወዝና አቅጣጫ ግን ቀይሮታል፡፡ አንድ በአምላኩ የተማመነ ዳዊት የተባለ ትንሽ ልጅ ትልቁን ጦረኛ (ጀግና) በወንጭፍ መትቶ ድል አደረገው ከሚለው ሃይማኖታዊ የታሪክ ወዝ ወይንም አቅጣጫ፤ በህመም ምክንያት ግዙፍ ከሆነና ምንም ቅልጥፍና የሌለው “በሽተኛ ተዋጊ” ሰው፣ በቆመበት እንዳለ በድንጊያ ተመትቶ እንደ ወደቀ ወደ ሚያሳይ ሳይንሳዊ የታሪክ ወዝና አቅጣጫ ተቀይሯል፡፡
ጎልያድ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል አስፈሪ/ጨካኝ አውሬ (monster)፣ ጭራቅ (giant) በሚሉ መዝገበ ቃላት (Thesaurus) የተገለጠ መሆኑ፣ ሃይማኖታዊውን የታሪክ ወዝ አጉልቶ ለማሳየትም ሊሆን ይችላል ወደ ሚለው ሃሳብም ይወስዳችኋል፡፡ ላይሆንም ይችላል፡፡ የእኔ ግምት ነው፡፡ በሳይንሳዊ መላምት የታገዘው የታሪኩ ትንተና ክፍል፤ ዳዊት በወንጭፍ የገደለው ጎልያድ የተሰኘው ፍልስጥኤማዊ ጀግና የነበረ ተዋጊ ሳይሆን፣ በሽተኛ የሆነ ግዙፍ ማስፈራሪያ ሰው ነበር (ከሌሎች ሰዎች ሁሉ የገዘፈ ስለነበር ብቻ ማንም ሰው እጅ ለእጅ ውጊያ ከእርሱ ጋር ለማድረግ ከባድ ነበረና) ወደ ሚለው የታሪክ ወዝ እንዲያመራ አድርጓል፡፡
የታሪኩ ወዝ ከመለወጡ በስተቀር በትክክል የተከናወነ ድርጊት ስለነበር አንድ ዳዊት የተሰኘ ትንሽ ልጅ (በኋላ የእሥራኤል ንጉሥ የሆነ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው)፣ ግዙፍ የሆነውን ጎልያድ የተሰኘ ፍልስጥኤማዊ ተዋጊ በወንጭፍ መግደሉ እውነትና ሊለወጥ የማይቻል ድርጊት ነው፡፡ እኔ እንኳን ክርስቲያን ከመሆኔ የተነሳ በአጻጻፌ ውስጥ ለዳዊት እንዳደላሁ ሊሰማችሁ ይችላል፡፡ አይሰማችሁ፡፡
እንግዲህ ታሪክ እንዲያና እንዲህ እያለ ነው ወዙና አቅጣጫው አየተለወጠ ሊሄድ የሚችለው፡፡ ከዚህ አንጻር ግንዛቤን በመውሰድ፣ የታሪክ ጸሐፍት አርስ በእርስ ታርቃችሁ ታሪክን አስታርቁ፡፡ አንባቢም ታርቆ፣ በእርቅ የታረቀ ታሪኩን እንደየዝንባሌው ያንብብ፣ ይረዳ፣ ይግባባ፡፡
ስለታሪክ ጸሐፍት፣ ተማሪዎች፣ አንባቢዎች፣ ጥቅል የታሪክ ተከታዮችን ጠባይ በተመለከተ ሌላ ጊዜ ሌላ እይታ ይዤላችሁ ብቅ የምል ይመስለኛል፡፡ ሰላም፡፡
ከአዘጋጁ፡-
ጸሃፊው ስንታየሁ ገብረጊዮርጊስ ወልደሐዋርያት፤ BSc በእርሻ ኤኮኖሚክስ፣ MSc  በኤኮኖሚ ፖሊሲና ፕላኒንግ ያገኙ ሲሆን፤የዶክትሬት ድግሪያቸውን በባሕሪያዊ ኤኮኖሚክስ (Behavioral Economics) ማጥናት ጀምረው አላጠናቀቁም፡፡ በተማሩት ዘርፍም፣ በሲአርዲኤ በድኽነት ቅነሳ ስትራቴጂ ኦፊሰርነት፣ በኢትዮጵያ ግራጁዌት ስኩል ኦፍ ቴዎሎጂ በዲቨሎፕመንት ኦፊሰርነት፣ በዓለም ባንክ ፕሮጄክት የዘር ሥርዓት ልማት ፕሮጄክት (SSDP)የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ስፔሻሊስት ሆነው አገልግለዋል።
ጸሃፊው በአማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅተው ያልታተሙ በርካታ መጻሐፍት ያላቸው ሲሆን፤ ”በቀልና ፍትህ“ የተሰኘ የትርጉም ሥራቸው በቅርቡ ለንባብ በቅቷል፡፡ ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ወይም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 554 times