Sunday, 28 July 2024 00:00

የአሜሪካ የምርጫ ድራማ!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(1 Vote)

 ለወትሮው ድራማ የበዛበት የአሜሪካ ምርጫ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ቀድሞው አላምርለት ብሏል። ድራማ አንሶት አይደለም። እንዲያውም ከልክ አልፏል፤ እንዲያውም መረን ለቋል ቢባል ይሻላል እንጂ። ምርጫዎች በቅጡ ወደ እልባት አልደርስ ማለት ጀምረዋል። “በጨዋ ደንብ” ያልተጠናቀቀ ድራማ ምን ይሉታል? አሁን ደግሞ ነገሩ የባሰበት ይመስላል።
መንቀሳቀስና መናገር የከበዳቸው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከስንትና ስንት ውትወታ በኋላ፣ ጫና ሲበዛባቸው  “ከምርጫው ወጥቻለሁ” ብለዋል። ታመው አልጋ ላይ ስለነበሩ በደብዳቤ ነው ስንብታቸውን የገለጹት።
ከዚያ በፊት ደግሞ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ላይ በግድያ ሙከራ በጥይት ተመቱ። በያዝነው ሳምንት ደግሞ፣ የፕሬዚዳንትና የባለሥልጣንት የደህንነት ጥበቃ ዳይሬክተር ከሥልጣን ለቀቁ ተባለ።
የምርጫ ድራማው ቅጥ አላጣም ትላላችሁን? የጆ ባይደን ሁኔታ እንደ ኮሜዲ ይመስላል። ግን የሚያሳዝን ነገርም አለው። ዕድሜና እርጅና ሲመጣ በጸጋ ማስተናገድ እንጂ ምን ማድረግ ይቻላል? በትራምፕ ላይ የተካሄደው የግድያ ሙከራ ደግሞ በጣም ያስደነግጣል።
በጣም አስገራሚው ደግሞ፣ የግድያ ሙከራውን እንደ መቀለጃ ለማየት የሞከሩ ፖለቲከኞች መኖራቸው ነው። ምን ይህ ብቻ! “ከተኮሰ አይቀር አስተካክሎ ለመምታትና ኢላማ ላለመሳት በደንብ መለማመድ ነው” የሚል አስተያየት የሚጽፍ ፖለቲከኛ አልጠፋም። ለዚያውም የምክር ቤት አባል! የአሜሪካ ፖለቲካ የዚህን ያህል ተበላሽቷል? ወደ ትራጄዲ እየተንደረደረ አይመስልም?
መጨረሻው የማያምር የምርጫ ድራማ!
የምርጫ ዘመቻ ፈዛዛና ደንዛዛ ከሆነ፣ “ችግር አለ” ማለት ነው። በረብሻ አገር የሚናወጥና ቀውጢ የሚፈጠር ከሆነም አደጋ ነው። የአሜሪካ የምርጫ ድራማ፣ “ያልፈዘዘና ያልተቀወጠ ምርጫ ነው” ቢባል፣ አዎ በአብዛኛው እንደዚያ ነው። ወይም እንደዚያ ነበር ማለት ይቻላል። ዛሬ ዛሬ ግን…
ዛሬም ቢሆንኮ ደህና ነው። አዝማሚያው ግን… ግርግር እየበዛበት ነው። ቢሆንም ግን…
የምርጫ ዘመቻው ውካታና ትርምስ ቢበዛበት እንኳ፣ መጨረሻ ላይ በወጉ ከተጠናቀቀ ችግር አይኖረውም፤ አይደለም? የአሜሪካ ምርጫ በጨዋ ደንብ ሲጠናቀቅ ነው የምናውቀው። እንደዚያ ዐይነት ታሪክ አለው።
ባለፉት ስምንት ዓመታት እንዳየነው ግን፣ የአሜሪካ ምርጫ እንደ ቀድሞው አልሆን ብሏል።
የምርጫ ዘመቻ ድራማ፣ ባልተጠበቁ ውዝግቦች ይሟሟቃል። አፈትልከው በሚወጡ የቅሌት ወሬዎች አማካኝነት ይጦዛል። ደግሞም ይበርድለታል። ወሬዎች እየዋሉ ሲያድሩ እየነፈሰባቸው፣ በትኩስ ቅሌቶች እየተተኩ፣ እነሱም ወረት እያለፈባቸው፣ “ጉድ ነው” የሚያስብሉ አዳዲስ ወሬዎች ይፈጠራሉ።
ድራማው እንዲህ እየጦዘና እየረገበ፣ ወደ ግራና ወደ ቀኝ እያዘነበለ ይገሠግሣል። ይጋልባል።
የአንዱ ተፎካካሪ ተስፋ ሲደምቅ ቆይቶ በድንገት ሲደበዝዝና ሲጨልም፣ በስንት ጭንቅና መከራ እንደገና ሲያንሰራራና መንፈሱ ሲፈካ… ብዙም ሳይቆይ እንደገና በአወዛጋቢ ጥያቄዎች እየተጠለፈ ይንደፋደፋል። መውደቅና መነሳት ይፈራረቅበታል። የተስፋና የጭንቅ ውጣ ውረድ እንደ አዋዋሉ አያድርም። እንደ አመጣጡ አይዘልቅም።
እናም… የተፎካካሪዎች የብልጫ ልዩነት እየጠበበ ውድድራቸው “አንገት ለአንገት” እየተናነቀ ልብ አንጠልጣይ ይሆናል። ተወዳዳሪዎች ስንዝር በማትሞላ ርቀት ነው የሚበላለጡት። በአሜሪካ ምርጫ ላይ በ10 በመቶ ብልጫ ማሸነፍ የማይታሰብ ሆኗል። ለግማሽ ምዕተ ዓመት አልታየም። ማንኛውም ተፎካካሪ በምርጫ ካሸነፈ በትንሽ ነው። ከተሸነፈ ለትንሽ ነው። ለማሸፍም ለመሸነፍም ቅርብ ናቸው።
በቅንጣት ልዩነት እየተበላለጡና ቦታ እየተለዋወጡ ወደ መጨረሻዋ ሰዓት ይንደረደራሉ። ማን እንዳሸነፈ እስኪታወቅ ድረስ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ደግነቱ፣ በምርጫው ማን እንዳሸነፈ የሚታወቀው በዚያው ዕለት ነው።
ተሸናፊው ፖለቲከኛ መድረክ ላይ ወጥቶ ለደጋፊዎቹ ምስጋናውን ይገልጻል። ለአሸናፊው ደግሞ “እንኳ ደስ ያለህ” የሚል መልእክት ያስተላለፋል። ለወግ ያህል እንጂ በንዴት ሁለመናው መንገብገቡና እርር ድብን ማለቱ አይቀርም። “ደስታው ለኔ በሆነ!” በሚል ከንቱ ስሜት መብሰልሰሉ አያጠራጥርም።
በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ተሸናፊ መሆን… በቀላሉ የማይሽር ቁስል ነው። የሌሎች አገራት የምርጫ ዘመቻ በጥቂት ሳምንታት፣ ቢበዛ ደግሞ በሁለት በሦስት ወራት ተጀምሮ የሚጠናቀቅ ነው።
የአሜሪካ የፕሬዚዳንት ምርጫ ግን፣ የሁለት ዓመት ሩጫና ወከባ ነው። በአንድ ቀን ውስጥ አራት አምስት ከተሞች ላይ የምርጫ ቅስቀሳ ለማካሄድ ሲጣደፉ ይውላሉ። ማታ የገንዘብ ድጋፍ ሲያሰባስቡና ታዋቂ ሰዎችን ሲያግባቡ ያመሻሉ። በወጉ ሳይተኙ በማግስቱ ደግሞ ወደ ሌሎች ከተሞች።
ዛሬ ዛሬ የምርጫ ዘመቻ፣ የብዙዎችን ኪስ የሚያራቁት አክሳሪ የልመና ሩጫ ሆኗል ቢባል የተጋነነ አገላለጽ አይደለም። በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ምትክ፣ ሰሞኑን የዲሞክራቲክ ፓርቲ እጩ ተፎካካሪ በመሆን ወደ ፍልሚያው ዘው ብለው የገቡት ካማላ ሀሪስ፣ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ ከደጋፊዎች አሰባስበዋል።
አብዛኛው ገንዘብ ለማስታወቂያ የሚውል ነው። ተቀናቃኛቸውን ለማጥላላት እንደ መርፌ እንደ ስለት የሚዋጉ ማስታወቂያዎችን በቲቪ እና በኢንተርኔት ቀንና ማታ ያለ ፋታ ማሰራጨት የተፎካካሪዎች ዋና ሥራ ሆኗል። “ብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላሮችን የሚፈጁ እልፍ ማስታወቂያዎች” በምድረ አሜሪካ ይገኛሉ።
ችግሩ እየከፋ የሚመጣው ደግሞ፣ ተቀናቃኝን ከማጥላላት ከማንቋሸሽ ባሻገር፣ ውንጀላና ዛቻ ማዘውተራቸው ነው።
ከሁለት ሳምንት በፊት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ከምርጫው ላለመውጣት ያካሄዱትን የሞት ሽረት “ሩጫ” አይታችሁ ይሆናል። ከዕድሜ ጋር እርጅናው እየከበዳቸው፣ በቅጡ መንቀሳቀስና መናገር እየከበዳቸው ቢመጣም፣ ብርታታቸውን ለማስመስከር ለአንድ ሳምንት ያህል በአምስት በስድስት ከተሞች የምርጫ ዘመቻ ለማካሄድ ሞክረዋል።
የጆ ባይደንን ንግግር ለመስማትና ድጋፋቸውን ለማሳየት የተሰበሰቡ ነዋሪዎች፣ በማጨብጨብና ፕሬዚዳንቱን የሚያሞግሱ መፈክሮችን እየደጋገሙ በመጮህ አልረኩም። ዶናልድ ትራምፕ በብዙ ቦታዎች እየተከሰሱና እየተፈረደባቸው እንደሆነ ጆ ባይደን ሲናገሩ ደጋፊዎች በጩኸት ደስታቸውን ገለጹ።
ባይደን በዚህ አላበቁም፣ የትራምፕ ክሶችና ወንጀሎች ብዙ ናቸው አሉ። ዶናልድ ትራምፕ “የወንጀል ማዕበል” ናቸው ሲሉ ሰይመዋቸዋል። የጆ ባይደን ደጋፊዎች ደስታቸውን አልቻሉትም። “የወንጀል ማዕበል” የሚለውን አገላለጽ ወደውታል። ከዚያም “እሰረው! እሰረው!” እያሉ መጮኽ ጀመሩ። “Lock him up!”
ጆ ባይደን የደጋፊዎችን ጩኸት ለማስቆም ቢያመነቱም በይሁንታ አልፈውታል።
በእርግጥ፣ ጆ ባይደን ከምርጫው ላለመውጣት ያካሄዱት ወከባ ብዙም አልጠቀማቸውም። እንዲያውም ድካም በርትቶባቸው፣ ለመንቀሳቀስም ለመናገርም በጣም ከብዷቸው፣ በዚያ ላይ ጉንፋን ይዞኛል ብለው ሲያስሉ መሰንበታቸው ያነሰ ይመስል “ኮቪድ” ተጨምሮባቸው፣ አልጋ ላይ ለመዋል ተገደዋል።
የባይደን የምርጫ አዝማሚያ ያላማራቸው የዲሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች፣ ፕሬዚዳንቱ ከምርጫው እንዲወጡ በቀንና በማታ ከመወትወት አልፈው ጸብ ጸብ የሚሸቱ ቃላት መሰንዘር ሲጀምሩ፣ ጆ ባይደን ከአልጋ ተነስተው የመከራከር ዐቅም አልነበራቸውም።
ወዳጆቼና አጋሮቼ በሚሏቸው ፖለቲከኞች ክህደት እንደተፈጸመባቸው በማመን “ቆሽታቸው” እርር ብሏል። “ሰይጣን አይስማ። የቆሽት በሽታስ አይጨምርባቸው)። ለማንኛውም እጅግ ቢናደዱም፣ ከምርጫው ለመውጣትና በምትካቸው ምክትል ፕሬዚዳንቷ ካማላ ሀሪስ በዋና መሪነት እንዲፎካከሩ ድጋፌን እሰጣለሁ ብለው በደብዳቤ አስነግረዋል።
ከሰኞ ወዲህም ካማላ ሀሪስ “የዲሞክራቲክ ፓርቲ እጩ ተፎካካሪ” ሆነው የምርጫ ዘመቻ ጀምረዋል (የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይነታቸው ገና ባይጸድቅም። የፖርቲው ጉባኤ ከዐሥር ቀን በኋላ ነው የሚካሄደው።)
የሆነ ሆኖ ካማላ ሀሪስ ሰሞኑን ባካሄዱት የምርጫ ዘመቻ ደጋፊዎችን ሰብስበው ሲናገሩ፣ የሕግ ባለሙያ አቃቤ ሕግ ሆነው እንደሰሩ በማስታወስ፣ ዶናልድ ትራምፕ ወንጀለኛ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል። እንደነሱ ዐይነት ሰዎችን አውቃቸዋለሁ፤ እየከሰስኩ ሳስፈርድባቸው ነው የኖርኩት ብለዋል - ካማላ ሀሪስ። ከደጋፊዎች ያገኙት ምላሽ ሌላ አይደለም። “Lock him up!” የሚል ነው።
ያው ካማላ ሀሪስ ተቀናቃኛቸውን ዶናልድ ትራምፕን እንዲያሥሩ ነው የተሰብሳቢው ጩኸት።
እንዲህ ዐይነት ጩኸት ድሮ ድሮ እንደ ጊዜያዊ ስሜትና እንደ ቀልድ ነበር የሚቆጠረው። ዛሬ ዛሬ ግን ነገሩ የምር እየሆነ መጥቷል።
ተቀናቃኝን የማሠር ጩኸት ለመጀመሪያ ጊዜ እጅግ እየገነነና እየተዘወተረ የመጣው የዛሬ 8 ዓመት ነው። የዶናልድ ትራምፕና የሂላሪ ክሊንተን ፉክክር ታስታውሱ ይሆናል።
ያኔ የክስ ጣጣ ያመዘነው ወደ ሂላሪ ክሊንተን ነበር። በኮምፒዩተር ውስጥ የነበሩ የመንግሥት ሰነዶችን ለመሰወር ሞክረዋል፤ ከክስ ለማምለጥ የኮምፒዩተር ዕቃዎችን አውድመዋል እየተባለ ተወርቶባቸዋል። ምርመራም እየተካሄደ ነበር።
ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ፣ “ሴረኛዋ ሂላሪ ክሊንተን ወንጀለኛ ናት” እያሉ በየሄዱበት ሁሉ ለደጋፊዎች መናገር ያስደስታቸው ነበር። ደጋፊዎች ይህንን ተቀብለው፣ “እሠራት፣ እሠራት” እያሉ ይጮኻሉ። መጥፎ ነገር ተለመደ ማለት ነው።
የሆነ ሆኖ ትራምፕ በምርጫው አሸነፉ። ወግ ነውና የጨዋ ደንብ ነውና፣ ሂላሪ ክሊንተን በዚያው ዕለት “እንኳን ደስ ያለህ” ብለው የምርጫውን ውጤት መቀበላቸውን አሳይተዋል። እየተናነቃቸውም የአገሬውን የምርጫ ወግ አክብረዋል። ግን ምን ዋጋ አለው?
ብዙም ሳይቆይ፣ ሂላሪ ክሊንተን “ትራምፕ ሕገወጥ ፕሬዚዳንት ነው” ብለው መናገር ጀምረዋል። ይሄ የአሜሪካ ምርጫ ወግ አይደለም። በጭራሽ!
ሕገወጥ ፕሬዚዳንት?
ከምር ሕገወጥ ባለሥልጣንን ምን ያደርጉታል? ማባረር? ከስልጣን መጣል? እስከ መፈንቅለ መንግሥት ባይደርስም፣ በሕጋዊ አሠራር ትራምፕን ለማባረር ብዙ ተሞክሯል። ከእልፍ ውንጀላዎች መካከል፣ አንድ ሁለቱ ትንሽ ቁምነገር ቢኖራቸውም፣ አብዛኞቹ ግን ከአሜሪካ የማይጠበቁ በጣም  ከንቱ የፖለቲካ ድራማዎች ናቸው።
ይሄ ያነሰ ይመስል፣ ዶናልድ ትራምፕ በተራቸው በምርጫ ሲሸነፉ ደግሞ፣ ከሂላሪ ክሊንተን የባሰ ለአሜሪካ የሚያሸማቅቅ ቅሌት ፈጽመዋል። ጆ ባይደን በምርጫ ሲያሸንፉ፣ ዶናልድ ትራምፕ በወጉ “እንኳን ደስ ያለህ” ብለው አልተናገሩም። ምርጫው ተሰርቋል የሚል ጨዋታ ነው ያመጡት።
የተቃውሞ ሰልፍ በፓርላማው (በኮንግረስ) ሕንጻ ደጃፍ ተካሄደ። ግርግር ተፈጠረ። በኋላቀር ሀገራት ውስጥ የሚታይ የፖለቲካ ውጥንቅጥና ትርምስ በአሜሪካ የታየበት ዕለት ነው። ተቃዋሚ ሰልፈኞች ዐጥር ጥሰው ወደ ኮንግረስ ሕንጻ እየዘለሉ እየተንጋጉ ለመግባት፣ ከፖሊሶች ጋር ግብግብ ገጠሙ። “የጥር 6 ዐመጽ” እየተባለ እስከ ዛሬ ይወራል።
በእርግጥ፣ ሰሞኑን “የፍልስጥኤም ተቆርቋሪ፣ የእስራኤል ተቃዋሚ ነን” የሚሉ ሰዎች ወደ ኮንግረስ ሕንጻ ገብተው በየአቅጣጫው እየዞሩ እንደጮኹና እንዳስፈራሩ ተዘግቧል።  የመተላለፊያ አዳራሹን ዘግተው ለመቀመጥ ሲሞክሩም ታይተዋል። ደግነቱ በፖሊስ ተይዘው ከአዳራሹ ሲወጡ ብዙ አለማንገራገራቸው ጠቀመ። ነገሩ በሰላም በርዷል።
የሆነ ሆኖ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተበላሸ የመጣው የአሜሪካ የምርጫ ድራማ፣ በዚሁ የሚያበቃ አይመስልም። “ዶናልድ ትራምፕ ዐመጽን ቀስቅሰዋል” በማለት ዘወትር ክስ የሚደረድሩ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች፣ ዛሬ በተራቸው ዜጎችን ለዐመጽ ያነሣሣሉ።
“ትራምፕ የአሜሪካ የሕልውና አደጋ ናቸው። ዲሞክራሲን የሚያጠፉ የለየላቸው አደጋ ናቸው” በማለት ያለ ፋታ ይቀሰቅሳሉ። “ትራምፕ ካሸነፉ ዲሞክራሲ አይኖርም” ብለው አስፈሪ መዓት ያወራሉ።
ትራምፕ በፊናቸው፣ ባይደን ካሸነፉ አገር አይኖረንም ብለው ይቀሰቅሳሉ። ካማላ ሀሪስ ከተመረጡ አገራችን ትፈርሳለች፤ ከዚያ በኋሉ ምርጫም አይኖርም ብለው ያስፈራራሉ።
ጥያቄው ምንድነው?
“ተቃናቃኜ አገርን ያፈርሳል፤ ዲሞክራሲን ያጠፋል” ብለው የሚያስቡ ሰዎች እስከ መጨረሻዋ ጠብታ ይዋጋሉ፤ ይፋለማሉ እንጂ፣ “አገር አማን ነው፤ ነጻነት የተከበረ ነው” ብለው በሰላም ይነጋገራሉን?
አገር እንድትቀጥል ወይም አገር እንድትፈርስ እጣ ፈንታዋ በምርጫ ይወሰናል ብለው በሰላም ውጤቱን ይቀበላሉን? እንዴት ሊሆን ይችላል?
ምርጫ ሰላማዊ የሚሆነው፣ “የኔ ሐሳብ ከተቀናቃኜ ሐሳብ ይሻላል” ብለው የሚፎካከሩ ሰዎች ሲኖሩ ነው። አገር በማፍረስና አገር በመጠበቅ መካከል የምርጫ ፉክክር አይካሄድም፤ ጦርነት እንጂ።
ለጊዜው አብዛኛው አሜሪካዊ ለፖለቲከኞች ቅስቀሳ ሙሉ እምነት ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም። እንደዘበት ጨዋነትን እርግፍ አድርጎ እየጣለ ወደ ዐመጽ አይገባም - ለጊዜው።
ነገር ግን፣ የውንጀላና የዛቻ ፉክክር በጊዜ ለከት ካልተበጀለትና ካልተገታ፣ ፈጠነም ዘገየም አገሬው ቀስ በቀስ ወደ አስቀያሚ የፖለቲካ ቀውስ ማምራቱ አይቀርም።
የአሜሪካ ፖለቲከኞች ጩኸት ከአፍሪካ ፖለቲከኞች ጩኸት ጋር እየተመሳሰለ ከመጣ፣ የአገሪቱ ፖለቲካስ ከአፍሪካ አገራት ፖለቲካ ጋር እየተመሳሰለ መምጣቱ ያጠራጥራልን?

Read 750 times