ባለፈው ሳምንት እኔና ባለቤቴ ልጆቻችንን ይዘን ለጥቂት ቀናት እረፍት ወደ ሃዋሳ ተሻግረን ነበር- ለመዝናናት። እንደሚታወቀው ሃዋሳ ከአገራችን ምርጥ ከተሞች ተጠቃሽ ናት፡፡
አየሯ ምቹ ነው፡፡ ውብ መልክአ ምድር የታደለች ናት፡፡ በሃይቆች ተከባለች፡፡ በዚያ ላይ እንደ ኃይሌ ሪዞርት ዓይነት ባለ 4 ኮከብ ምርጥ ሆቴሎች ታንጸውላታል፡፡ ቢያንስ ሁለት ሆቴሎች እንግዶቻቸውን በመኪና ከአየር ማረፍያ እንደሚቀበሉና እንደሚሸኙ አይተናል፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎች እንደሚኖሩ እንገምታለን፡፡
በዚህች አጭር ማስታወሻዬ፣ እኔና መላው ቤተሰቤ በሃዋሳው ኃይሌ ሪዞርት የቀናት ቆይታችን የገጠመንንና ያስተዋልነውን ለመመስከር እወዳለሁ፤ ሊመሰከርለት ይገባልና፡፡ እርግጥ ነው ሁሉም የኃይሌ ሪዞርቶች በእንግዳ አቀባበላቸውና መስተንግዶአቸው የሚታሙ አይደሉም፤ ይልቁንም ለብዙዎቹ የአገራችን ሆቴሎች በአርአያነት የሚጠቀሱ እንጂ፡፡ ይሄ ደግሞ እንደው በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን ብዙ የተለፋበት ነው፡፡ ልብ በሉ፤ ኃይሌ በብቃት የሰለጠኑ የሆቴል ባለሙያዎች በአገሪቱ እንደሌሉ ሲገነዘብ መፍትሄ ነው ብሎ የወሰደው እርምጃ፣ የሆቴል ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም መክፈት ነው፡፡ ለዚህ ነው አሁን 10 በሚደርሱ ሪዞርቶቹ ተመሳሳይ (ደረጃውን የጠበቀ) የእንግዳ አቀባበልና መስተንግዶ ማቅረብ የቻለው፡፡ እርግጠኛ ነኝ የራሱን የሰለጠነ ባለሙያ እጥረት ለማሟላት የከፈተው የሆቴል ማሰልጠኛ ተቋሙ፣ የአገርንም የሆቴል ባለሙያ እጥረት ይቀርፋል፡፡ ኃይሌ ሲከፍተውም ለአገርም ጭምር አስቦ እንጂ ለራሱ ሆቴሎች ብቻ እንደማይሆን መገመት ይቻላል፡፡
ወደ ኃይሌ ሪዞርት ሃዋሳ ስንመጣ፣ ከህንጻው አሰራርና ህንጻው ካረፈበት መልክአ ምድር ይጀምራል - ውበቱና መለያው፡፡ እያንዳንዱ ነገር በጥንቃቄና በዕውቀት መሰራቱን መመስከር ይቻላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሆቴሉ ሰራተኞች የተሰጣቸው ሥልጠና ቀላል እንዳልሆነ መስተንግዷቸውና አገልግሎት አሰጣጣቸው ይናገራል፡፡
የመስተንግዶ ባለሙያዎቹ ብቻ ሳይሆኑ፣ ጠቅላላ የሆቴሉ ሠራተኞች (የምግብ ዝግጅት ባለሙያዎቹ፣ የእድሳትና ጥገና ሰራተኞቹ፣ ሴኩሪቲዎቹ እንዲሁም ሃውስ ኪፐሮቹና አትክልተኞቹን ጨምሮ) እንግዶችን አይተው በዝምታ አያልፉም፤ ወዳጃዊ የአክብሮት ሰላምታ ይሰጣሉ፡፡ ግራ የገባው ወይም አንዳች ነገር የቸገረው እንግዳ ከገጠማቸው ከመቅጽበት ደርሰው ለመርዳት ይተጋሉ፡፡
በሆቴሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ እስካላችሁ ድረስ በፈገግታ የተሞላ የአክብሮት ሠላምታ የማይሰጣችሁ አንድም ሠራተኛ አታገኙም። በዚህም የተነሳ ፈፅሞ ባይተዋርነትና እንግድነት አይሰማችሁም፤ የሆቴሉ እንግዳ ብትሆኑም። ባለፋችሁ ባገደማችሁ ቁጥር ፈገግታና ሰላምታ በሽበሽ ነው፤ በኃይሌ ሪዞርት፡፡ ምግቡም ቢሆን ግሩም ነው፤ ጣዕሙ--ዓይነቱ---መጠኑ አጥጋቢ ነው፡፡
በመስተንግዶው፣ በምግቡ ወይም በመኝታ ክፍል አገልግሎቱ አሊያም በሌላ ቅር ከተሰኛችሁ ደግሞ መፍትሄው ቀላል ነው፤ ከናንተ የሚጠበቀው ቅሬታችሁን ለቅርብ ሃላፊ ማቅረብ ብቻ ነው። አትጠራጠሩ፤ ፈጣን ምላሽ ታገኛላችሁ። ያውም አጥጋቢ ምላሽ፡፡
አሁን ይህችን ማስታወሻ ለመከተብ ሰበብ የሆነኝን አንድ የኃይሌ ሪዞርት ሃዋሳ አስገራሚ ገጠመኝ ላጋራችሁ፡፡ ነገሩ የተከሰተው የመኝታ ክፍላችንን ተከራይተን እንደገባን ነው፡፡ እስካሁንም ድረስ ባላወቅነው ምክንያት (ምናልባት ተዘንግቶ ሊሆን ይችላል) ወደ መኝታ ክፍላችን ስንገባ የተለመደው የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ሳይደረግልን ቀረ፡፡ በሆቴሉ አሰራር መሰረት ወደ ክፍላችን ስንገባ፣ የፍራፍሬ ጭማቂዎች ሊቀርብልን ይገባ ነበር- የእንኳን ደህና መጣችሁ የቤቱ ግብዣ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ቅሬታችንን በቀጥታ ለሆቴሉ አስተዳደር አቀረብን።
ቅሬታችን ታዲያ እንደ ብዙዎቹ የአገራችን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጆሮ ዳባ ልበስ አልተባለም። ወዲያው ነው ምላሽ የተሰጠን፡፡ በሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ የተፃፈና የተፈረመ የይቅርታ ደብዳቤ - የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ከተሞላ ቅርጫት ጋር መኝታ ክፍላችን ድረስ መጣልን፡፡ ይቅርታና ካሣ እንደማለት ነው፡፡
ከሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ በእንግሊዝኛ የተፃፈልንን የይቅርታ ደብዳቤ (ለኢትዮጵያውያን በአማርኛ ቢሆን ይመረጥ ነበር) በግርድፉ ተርጉሜ ታነቡት ዘንድ ከዚህ በታች አቅርቤዋለሁ፡፡
በዚህ አጋጣሚ የሃዋሳው ኃይሌ ሪዞርት አስተዳደር፣ ለቅሬታችን ለሰጠን በአክብሮት የተሞላ ፈጣን ምላሽ በራሴና በቤተሰቤ ስም ከልብ ላመሰግንና ላደንቅ እወዳለሁ። ከዚህ በኋላ እኔና ቤተሰቤ፣ ኃይሌ ሪዞርት፣ ቁጥር አንድ ምርጫችን እንደሚሆን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
በነገራችን ላይ ጀግናው አትሌታችን ኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ እንደ ሩጫው ሁሉ፣ በሆቴል ኢንዱስትሪውም ሪከርድ እየሰበረና ታሪክ እየሰራ መሆኑን እያስተዋልን ነው! ለራሱም ለአገሩም፡፡ ሌሎች የአገራችን ሆቴሎችና በአገልግሎት ዘርፉ የተሰማሩ ሁሉ ከኃይሌ ሪዞርት ብዙ ሊማሩ እንደሚችሉ ሳልጠቁም አላልፍም። እነሆ ደብዳቤው፡-
ለውድ ወ/ሮ ሃና ጎሳዬ፡-
በኃይሌ ሪዞርት ሃዋሳ ቡድን ስም፤ ለገጠማችሁ ችግር ልባዊ ይቅርታ ልጠይቅ እወዳለሁ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ለተከሰቱት አጠቃላይ የአቀባበል ክፍተቶች ይቅርታ እንጠይቃለን፤ እርስዎ ከጠበቁን በታች በመሆናችንም በጣም አዝነናል። በመሆኑም፤ ይህ ሁኔታ ዳግም እንደማይከሰት ልናረጋግጥልዎ እንፈልጋለን፡፡
በሁኔታው በእጅጉ እያዘንኩ፤ ይህችን ትንሽዬ የፍራፍሬ ግብዣ ይቀበሉኝ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ። በሃይሌ ሪዞርት ሀዋሳ ባደረጋችሁት ቆይታ ሊፈጠርባችሁ የሚችለውን የተዛባ ምስል ለማንጻት ላደርግ የምችለው ትንሹ ነገር ይህ ነው።
የዋና ሥራ አስኪያጁ ስምና ፊርማ
Published in
ህብረተሰብ