ካሊጉላ ከአባቱ ጀርማኒከስ እና ከእናቱ አግሪፒያ ሮም አጠገብ በምትገኝ አንቲየም በምትባል ትንሽ ከተማ በ12 A.D ተወለደ፡፡ ቤተሰቡ ካፈራቸው ስድስት ልጆች ሦስተኛው ነው፡፡ አባቱ ጀርማኒከስ በሮም ታሪክ በጣም የታወቀ የጦር መሪና ስመ ገናና ጀግና ሲሆን፤ እናቱ አግሪፒያ የመጀመሪያው የሮም ንጉስ የልጅ ልጅ ናት፡፡ ካሊጉላ የዘር ሃረጉ ከንጉሳውያን ቤተሰብ ይመዘዛል፡፡ የካሊጉላ አባት በጊዜው የሮም ንጉስ የነበረው የቲበርየስ የልብ ወዳጅ ነበር፡፡ ቲበርየስ ጀርማኒከስን በቤተመንግስቱ ባለሟሉ አድርጎት ለብዙ አመታት አብረው ኖረዋል፡፡ የጠበቀ ወዳጅነት ቢኖራቸውም በኋላ ላይ በተፈጠረ የፖለቲካ አቋም ልዩነት ግንኙነታቸው ጥላ አጠላበት፡፡ ቲበርየስ ጀርማኒከስን እንደ ስልጣን ባላንጣው ቆጠረው፡፡ ጀርማኒከስ በድንገት ሞተ፡፡ ጠልፎ መጣል የሮማውያን የጊዜው ስልት ነበርና ቲበርየስ ሳልቀደም ልቅደም ብሎ ጀርማኒከስን መርዞ እንደገደለው ይገመታል፡፡
የሮማውያን የጥንት ታሪክ በሚስጥርና በእንቆቅልሽ የተሞላ ነው፡፡ ለዚህም ነው በታሪክ ዘገባቸው ውስጥ ተብሎ ይገመታል (ወይም ይጠረጠራል) እየተባለ በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው፡፡ በታሪካቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ አግሪፒያ ግን የባሏ ገዳይ ቲበርየስ እንደሆነ አመነች፡፡ አግሪፒያ ሀይለኛ ሴት ነበረችና በባሏ ህልፈት ንጉሱን ቀጥተኛ ተጠያቂ አደረገችው፡፡ “የባሌ ገዳይ ማንም ሳይሆን አንተ ነህ፤ ከአንተ ራስ አልወርድም፡፡ ፍትህን እሻለሁ” እያለች ስሞታዋን በሴናተሮቹ ፊት አሰማች፡፡ ምን ያደርጋል! ሁሉ በእጁ ከሆነ ንጉስ ተካስሶ የት ሊደረስ? ንጉስ እራሱ ህግ አይደል፡፡ ንጉስን ለማን ይከሱታል? ቲበሪየስ አግሪፒያን ከሁለት ወንድ ልጆቿ ጋር በግዞት እንድትኖር ፈረደባት፡፡ ብዙም ሳይቆይ አግሪፒያ ከሁለት ልጆችዋ ጋር የሞት ቅጣት ተወሰነባት፡፡ ካሊጉላ ከግዞትና ከሞት የተረፈው እድሜው ገና ልጅ ስለነበረ ነው፡፡ ቲበርየስ ካሊጉላን በራሱ ቤተመንግስት አስቀመጠው፡፡ ቆየት ብሎ ካሊጉላ ከቲበርየስ እናት ጋር እንዲኖርና በዚያው እንዲያድግ የቲበርየስ እናት ወዳሉበት ተላከ፡፡ ከተወሰኑ አመታት በኋላ ማለትም በ31 A.D ካሊጉላ ካፕሪን ወደተባለች ደሴት ከቲበርየስ ጋር በቤተመንግስቱ እንዲኖር ተመልሶ ተላከ፡፡ ቲበርየስም ዳግመኛ በቤተመንግስቱ በሚገባ ተንከባክቦ አሳደገው፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ካሊጉላ በእናትና አባቱ ላይ ብሎም በሁለት ወንድሞቹ ላይ የደረሰውን ግፍ እንደማያውቅ ሆኖ እና በቤተሰቡም ላይ ምንም የተፈጠረ ነገር የሌለ እስኪመስል ድረስ በፍፁም ታዛዥነትና ታማኝነት ኖረ፡፡ በቲበርየስ ላይ በውስጡ ይዞት የነበረውን ጥላቻውን ደብቆ ኖረ፡፡ ይህ ስልት ህይወቱን አተረፈለት፡፡
ቲበርየስ የቀረው እድሜ አጭር መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሞት ሳይቀድመው ወራሴዎቹን በጊዜ አዘጋጀ፡፡ ካሊጉላን እና የእህቱ ልጅ ጂሜሎስ የዙፋኑ እኩል ህጋዊ ወራሾች እንደሆኑ ለሮማውያንና ለሴናተሮቹ አሳወቀ፡፡ ከ6 ዓመታት በኋላ ቲበርየስ ከዚህ አለም በሞት ሲለይ የካሊጉላ ወዳጅና ቀኝ እጅ የነበረው ማክሮ፣ ካሊጉላ ብቸኛው የዘውዱ ወራሽ የሆነበትን መላ አበጀለት፡፡ የአባቱን የከበረ ስም በማንሳት በሴናተሮቹ ልብ ውስጥ ጨመረው፡፡ ካሊጉላ የሴናተሮቹንና የሹማምንቱን ይሁንታ ያገኘው በአባቱ የጀግንነትና የከበረ ስም ታግዞ ነው፡፡ ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው አባቱ በሮማውያን ዘንድ ታላቅ የጦር ጀግና የነበረና በሴናተሮቹም የተወደደ ሰው ነበር፡፡ ሴናተሮቹ የአባቱ ምትክ እንደሚሆን ስላመኑ ወደ ስልጣን እርካብ እንዲወጣ በብዙ አገዙት፡፡ ስልጣኑን ከሌላው ህጋዊ ወራሽ ነጥቆና ቀድሞ በእጁ አስገባ፡፡ እንዲህ ሲያዩት ቀላል ይምሰል እንጂ ወደ ስልጣን ያደረገው ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ቢሆንም የማክሮ እና የሴናተሮቹ ትብብር እንቅፋቶችን አስወገደለት፡፡ የስልጣን መንበሩ ላይ በ24 አመቱ ጉብ አለበት፡፡ የሚገርመው ነገር ካሊጉላ ስልጣኑን በእጁ ካስገባ በኋላ የመጀመሪያውን የሞት ቅጣት ያሳረፈው በወዳጁ ማክሮ ላይ ነበር፡፡ በስልጣኔ ላይ እንቅፋት ይሆናሉ የሚል ጥርጣሬ ስላደረበት ባለውለታውንና ወደ ስልጣንም እጁን ስቦ ያወጣውን ማክሮ እና ዋራሴውን ጂሜሎስ በአሰቃቂ ሁኔታ ገደለ፡፡
ካሊጉላ በ24 አመቱ የንግስና ስልጣንን ያለምንም ተቀናቃኝ ጠቅልሎ ያዘ፡፡ ስልጣን ላይ ሲወጣ ለሮማውያን ብዙ ቃል ገብቶ ነበርና በህዝቡ የተወደደ መሪ ለመሆን በቃ፡፡ በወጣትነቱ ዋናውን የሃገሪቱን ስልጣን ሲቆናጠጥ ህዝቡ በተስፋና በጋለ ድጋፍ ነበር የተቀበለው፡፡ ለሮማውያንና ለወታደሮቹ ቸርና ለጋስ መሪ ነበር፡፡ በቸርነቱ ላይ አንደበተ ርእቱ ተናጋሪና የጦር ንድፍ ስትራቴጂስትም ብለው የሙገሳ ካባ ደረቡለት፡፡ በቲቤሪየስ ዘመን ህዝቡ ላይ አረብቦ የነበረውን የፍርሃትና የጭንቅ ደመና ካሊጉላ በቸርነቱ ገፈፈው፡፡ በቲቤሪየስ አመራር ዘመን ተማሮ የነበረውም ህዝብ፣ የነፃነትን አየር መተንፈስ ጀመረ፡፡ ለዚህ ያበቃቸውን ንጉስ ካሊጉላ አወደሱት፡፡ ካሊጉላ በቀላሉ በህዝቡ ተወዳጅ ለመሆን በቃ፡፡ በአፍላነቱ እድሜ ወደነፈሰበት የሚነፍስ ማንም እንደፈለገ የሚያሾረው አይነት ሰው ነበር፡፡ ስልጣኑን በእጁ ሲያስገባ ካሊጉላ ሌላ ሰው ሆኖ ብቅ አለ፡፡ አይደለም ማንም እንደፈለገ ሊያደርገው ቀና ብሎ የሚያየውም ጠፋ፡፡ እሱ የበላይ ሌሎች የበታች፤ እሱ ተናጋሪ ሌሎች አድማጭ፤ እሱ ብቸኛ መሪ ሌላው ተመሪ ሆኖ አረፈው፡፡
የፖለቲካ አስተዳደሩን ለእሱ እንዲስማማው አድርጎ ዘረጋው፡፡ እርምጃዎቹን በደንብ የተከታታሉ ሮማውያን ስልጣኑ ላይ ልጓም ካልተበጀለት ካሊጉላ ፍጹም አምባገነን እንደሚሆን ገመቱ፡፡ እነዚህ አስተዋዮች ካሊጉላን እብደት እንደሚጫወትበት ቀድመው የተረዱ ነበሩ፡፡ የካሊጉላ እብደት መቼም የራሱ የሆነ ነው፡፡ መመለክ ይፈልግ ነበር፤ ከህግ ውጪ ነበር፤ ለሰው ልጅ ምንም አይነት ክብር አልነበረውም፡፡ ፍጹም ጨካኝ ንጉስ ነበር፡፡ ይሆናል ተብሎ ሊደረግ አይደለም ሊታሰቡ የማይችሉ ጭካኔዎችን ፈፅሟል፡፡ ለምሳሌ የወሲብ ስሜቱን ካረካ በኋላ በወሲብ የተገናኛቸውን ሴቶች ገድሏል፡፡ በህይወቱ የፈረደ ካልሆነ በቀር ይህን መሰል ነውሩን ማን ደፍሮ ተው ብሎ ይናገረው፡፡ አይደለም በተቃውሞ የቀረበውን፣ በበጎ ምክር አስተያየት የሰጡትንም አስወግዷል፡፡ እንደልቡ የነበረ ንጉስ ነው፡፡
በመጀመሪያዎቹ ስድስት የስልጣን ወራት ለወታደሮቹ የተለያዩ ገፀበረከቶችን በመለገስ ችሮታውን አሳይቷል፤ ህዝቡን ከከባድ የታክስ ቀንበር ነፃ አውጥቶታል፤ በግፍ ለታሰሩት ምህረት አድርጓል፤ በግዞት ላይ የነበሩትን በምህረት እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ እንዲህ አይነት መልካም የነበረው የህይወቱ ገፅ ብዙም አልዘለቀም፡፡ በሂደት እንደታየው ጭንብልና ለስድስት ወራት ብቻ ታይቶ የጠፋ የማስመሰል ወጋጋን ነበር፡፡ በንግስናው ዙፋን ላይ ቂጥጥ ካለበት ከስድስት ወራት በኋላ ያለው ካሊጉላ፣ ፍፁም ሌላ ሰው ሆኖ በፖለቲካው መድረክ ላይ ብቅ አለ፡፡ የምናብ ፈጠራና ተውኔታዊ የሚመስለውና በትራጄዲ የተሞላው ዘመኑ ከዚህ ይጀምራል፡፡ ስልጣኑን ከተቆናጠጠ ስድሰት ወራት በኋላ ያለው ታሪክ የካሊጉላን ንክነቱንና እብደቱን ያሳበቁበት ነበሩ፡፡ ምክንያቱ በውል ባይታወቅም በዚህ ወቅት ካሊጉላ አንድ አይነት የአእምሮ መቃወስ ደርሶበት ነበር፡፡ ወፈፌነቱ ከጀመረው በኋላ ፍጹም ዋልታ ረገጥ ባህሪዎቹ አደባባይ ወጡ፡፡ ኮሚክና ጨካኝ ባህሪዎቹን አምጦ የወለደበት እብደቱ በሮማውያን ታወቀ፡፡ ወይ ይገድላል ካልሆነ በጭካኔ ይገርፋል፡፡ የቲቤሪየስ የእህት ልጅና የስልጣን ወራሼ የነበረውን ጂሜሎስ ሲገድል አያቱ ፍፁም ልታምን ያልቻለችውና የምትቀበለው ስላልነበር እራሷን ገደለች፡፡ የእሷን ራሷን መግደል ካሊጉላ ከቁብ አልቆጠረውም፡፡ እንደውም በታወቀበት ንግግሩ፤ “ማንኛውንም ነገር የማድረግ ህጋዊ መብት አለኝ፤ ውሳኔዬም ፍጹም ነው” ሲል በአያቱ ህልፈት ምንም እንዳልተሰማው አሳወቀ፡፡
የአለም ታሪክ ካሊጉላን የወርቃማው አባባል፣ “ስልጣን ያባልጋል እና ፍጹም ስልጣን ፍጹም ያባልጋል” የሚለው መለኪያ ሚዛን አድርጎ ሳይረዳው አይቀርም፡፡ ወፈፌነቱና የጨበጠው ስልጣን ተዳምረው ካሊጉላን ፍፁም አምባገነን አደረጉት፡፡ በወፈፌነቱና ለራሱ በነበረው የተጋነነ ግምት ካሊጉላ ፍጹም ጨካኝ አምባገነን ሆነ፡፡ ስልጣኑ ላይ ክትትል፤ ቁጥጥርና ተጠየቅ አልነበረበትምና እንደልቡ ሆነ፡፡ በሮማውያን የታሪክ ድርሳናት እንደተዘገበው፤ “አስታውሱ፤ በማንም ላይ ምንም የማድረግ መብት ያለኝ ሰው ነኝ” ባይ ነበር፡፡ ከአምላክ ጋር ትከሻ ለትከሻ መለካካት ይፈልግ ነበርና፣ ሮማውያን እንደ አምላካቸው እንዲያመልኩት አዘዛቸው፡፡ ለሴናተሮቹና ለሮማውያን በተደጋጋሚ ህያው አምላክ እንደሆነም ተናግሯል፡፡ ፈላስፋው ሴኔካ በከተበው ማስታወሻ፣ አንድ ኮሚክ ነገር ሰፍሮ እናገኛለን፡፡ ይኸውም ካሊጉላ በቤተመንግስቱና በዚያው አቅራቢያ በቆመው የጁፒተር ማስታወሻ ሀውልት መካከል የዋሻ ድልድይ እንዲሰራ አደረገ፡፡ ይህን ያደረገው ለምንም ሳይሆን አማልክቶቹን በዛ ለመገናኘት ስለፈለገ ነበር፡፡ አማልክትን መስሎ ለመታየት ኮሚክ የሆኑ የሴት አልባሳትን ለብሶ ይታይ ነበር፡፡ ድንቅ ተዋናይ ነኝ ብሎ ያስብ ስለነበር ሴናተሮቹን በውድቅት ከእንቅልፋቸው እየቀሰቀሰ ትወናውን ይጋብዛቸው ነበር፡፡ አምላክ ነኝ የሚለው ቕዠቱ የእብደቱን ጫፍ ነክቶም ነበርና፣ ሀውልቱ ከሮም በተጨማሪ በእየሩሳሌም እንዲቆምና አይሁዳውያንም እንዲያመልኩት ትእዛዝ ሰጣቸው፡፡ ሌላው ኮሚክ ነገር ካሊጉላ የሚወደውን ፈረሱን ከሴናተሮቹ የተሻለና ታማኝ ነው ብሎ ስላመነው፣ ቅንጡ ቤቱን ለመኖሪያው እንዲሆነው ለቀቀለት፡፡ ጠባቂና አገልጋይ ባሪያዎችም መደበለት፡፡ በኋላም ፈረሱ የሴኔቱ አባልና ሹመኛም ሆነ፡፡ የካሊጉላን ኮሚክ የሆኑትንና የወፈፌነቱን ማሳያዎች እንዘርዝር ካልን ማብቂያ የለውም፡፡
ካሊጉላ ሮማውያንን ለአራት አመታት ቁም ስቅላቸውን አሳይቶ ያለፈ ወፈፌ፤ ጨካኝና ፈሪ ንጉስ ነበር፡፡ ካሊጉላ በጭካኔውና ግብታዊ በነበሩት ውሳኔዎቹ የሽብርና የጭካኔ ምልክት ለመሆን የበቃ መሪ ነበር፡፡ ልክ እንደሌላው እብድ የሮም ንጉስ ኔሮ፣ ካሊጉላም ለሮማውያን የአራት አመታት የቁም ቅዠታቸው ነበር፡፡ አሁን ድረስ ሮም ካሊጉላን የምታስታውሰው በንክነቱ እንጂ በምኑም አይደለም፡፡ አይፍቁት ሆኖባቸው እንጂ ካሊጉላን ከታሪክ መዝገባቸው ቢፍቁት በወደዱ ነበር፡፡ እብድ የሚለው ቃል በልኩ የተሰፋና ለእሱ የተፈጠረ እስኪመስል ድረስ ካሊጉላ ሲነሳ እብደት፣ እብደት ሲነሳ ካሊጉላ አብሮ ይነሳል፡፡ መረን የለቀቀ ሰብእና፣ በሰው ስቃይ የሚደሰትና ከሰው ተፈጥሮ ውጪ የሆነ የወሲብ ስሜት ነበረው፡፡
አብዛኛዎቹ የሮም ታሪክ ፀሃፊያን በድርሳናቸው እንዳሰፈሩት፤ ካሊጉላ ግብረሰዶምም ነበር፡፡ ከግብረሰዶማዊነቱ በተጨማሪ ከገዛ እህቱ ድሩሲላ ጋር በወሲብ ይዳራ ነበር፡፡ አስገራሚና ክብረነክ ከሆኑት ድርጊቶቹ መሃል እህቱን ድሩሲላን በወሲብ መገናኘቱ ጎልቶ ይወሳል፡፡ ከእህቱ ጋር በወሲብ መገናኘቱ ሳያንሰው የሹማምንቱን ሚስቶች በሹማምንቱ ፊት በወሲብ ይገናኝ ነበር፡፡ በቤተመንግስቱ ውስጥ የሚያዘጋጃቸው የእርቃን ዳንስ ምሽቶች መዝናኛዎቹ ነበሩ፡፡ የወፈፌነቱ ሌላው ማሳያ የነበረው እህቱ ድሩሲላ ስትሞት ለዘጠኝ ቀናት የቆየ ብሄራዊ ሀዘን አወጀ፡፡ መሳቅ አይቻልም፤ በህብረት መዝናናት አይቻልም፡፡ ፀጉርና ፂም ማሳደግ የተከለከለ ሆነ፡፡ ይህን ተላልፎ የተገኘ በሞት ተቀጣ፡፡ የሚገርመው ነገር ካሊጉላ በእህቱ ቀብር ላይ አልተገኘም፤ በሮማውያን ዘንድ ልማድ የሆነውን የአስከሬን ሽኝትም አልታደመም፡፡ በዚህ የሃዘን ወቅት ካሊጉላ ቤተመንግስቱን ጥሎ ከሮም ውጪ በሌላ ከተማ ጸጉሩንና ጺሙን አሳድጎ ተቀመጠ፡፡ ባልተለመደ መልክ ለሀዘኑ መርሻ ምርጫው ያደረገው ቁማር መጫወትን ነበር፡፡ ቁማርና የተለያዩ አይነት ጨዋታዎችን በመጫወት የሃዘኑን ጊዜ አሳለፈ፡፡ ካሊጉላ እንዲህ እንዲህ አይነት ብዙ ንክ ባህሪዎችን የተላበሰ የሮማውያን ማፈሪያቸው ነበር፡፡
ካሊጉላ በታሪክ የሚታወሰው በጨካኝነቱ ብቻ ሳይሆን፣ በአንዳንድ ኮሚክ ነገሮቹም ጭምር ነው፡፡ በነዚህ ሁለት ዋልታ ረገጥ በሆኑ (ማለትም ኮሚክና አሰቃቂ በሆኑት) ባህሪዎቹ ሮም ብቻ ሳትሆን አለምም እንዳይረሳ አድርጋ መዝግባዋለች፡፡ ስለ እሱ ብዙ ተጽፏል፡፡ የህይወት ታሪኩና የመሪነት ዘመኑ ወደ ተውኔት ተቀይሮ ቀርቧል፡፡ አልበርት ካሙ ካሊጉላን ማእከል አድርጎ አንድ ጥሩ የፈጠራ መፅሐፍ ፅፏል፡፡
የጭካኝነት ስሜቱ ልጓም አልነበረውምና ትንሽ ትልቅ ሳይል ሮማውያንን ብሎም የሮም ሹማምንትን በግርፋትና በሞት ሲቀጣ ነበር፡፡ በስም መመሳሰል ብቻ ሕይወታቸው ያለፈው ብዙ ነው፡፡ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው አህያ፣ ፀጉራቸው የሚያማምሩትን የሮም ወጣት ወንዶች ፀጉራቸውን ይላጫቸው ነበር፤ ባስ ካለም አንገታቸውን ይቀላቸው ነበር፡፡ እንዲሾፍባቸው ከፈለገም ምላሳቸውን ቆርጦ መሳለቂያ ያደርጋቸው ነበር፡፡ ብዙ ቀሳውስትን ገድሏል፡፡ በአንድ አጋጣሚ ብቻ 160,000 ንፁሃንን እንደገደለ ተዘግቧል፡፡ በእሱ አጭር ሆኖም ዝንታለም በሚመስለው የአራት አመታት የንግስናው ዘመን፣ ሮም እግር ተወርች ተከርችማ ነበር፡፡ ሮም በስልጣኔዋና ለአለም ባበረከተችው በጎ አስተዋፆኦዋ እንደምትነሳው ሁሉ በካሊጉላም በኩል በክፉ ትነሳለች፡፡ የካሊጉላ እና የሌላው ወፈፌ ንጉስ የኔሮ ዘመን፣ የሮምን የጨለማውን ታሪክ ምእራፍ ይወክላሉ፡፡
ስር ድረስ ዘልቆ የገባ የስልጣን ጥም፤ ፍጹም አምባገነን፤ የተለየሁ ሰው ነኝ ብሎ ማመን፤ ከፈጣሪ ጋር የተለየ ግንኙነት ያለኝ እኔ ነኝ ማለት፣ የካሊጉላ መለያ ባህሪዎቹ ነበሩ፡፡ እርኩስ መንፈስ እንደሰፈረበት ሰው ካሊጉላን የሚመራው እንዲህ አይነት የእብደት ዛር ነበር፡፡ ጥሩ በማድረግ መታወስ ሳይሆን ዝነኛ ብቻ ሆኖ መታየት መሻቱን የሚያረጋግጥልን፣ ከላይ የሰፈረው በእየሩሳሌም ሀውልቱ ተቀርፆ እንዲመለክ፣ አይሁዶችን በቤተመቅደሳችሁ ሀውልት ቀርፃችሁ እንድታመልኩኝ እፈልጋለሁ ብሎ ማዘዙ ነው፡፡ ካሊጉላ ፍፁም ያልተረጋጋ ሰው ነበር፡፡ ከግድያውና ከጭካኔው በቀር በቅጡ ጀምሮ የጨረሰው አንድም በጎ ነገር የለውም፡፡ ሁሉንም ለማድረግ የታደልኩ ነኝ፤ ስለዚህ ሁሉንም ማድረግ እችላለሁ በማለቱ ከሴናተሮቹና ከልዩ ጥበቃ ጓዶቹ ጋር መቃቃር ጀመረ፡፡ ሊገመቱ የማይችሉት ባህሪዎቹ ጠላትን አፈሩበት፡፡ አወዳደቁንም አፋጠኑበት፡፡
በካሊጉላ ሰብእና ውስጥ ሁለት ተፃራሪ ባህሪዎችን እናገኛለን፤ አንዱ ኮሚክ ሌላው በስቃይ መደሰት፡፡ በስቃይ መደሰት መለያው የሆነው ታማኙና የቅርቡ የነበሩትን ሹማምንት ያለምክንያት በገፍ ሲገድል ነው፡፡ እጁን በደም ማጠብ የጀመረው የቅርቡ የነበሩትን ሹማምንት በመግደል ነው፡፡ ሁሉንም በፍርሃት ሸብቦ በዝምታ ልጓም አሰራቸው፡፡ ማንም ምንም ማድረግ የማይችልበት ጊዜ ነበር፡፡ አወዳደቁን ያፋጠኑለት እንዲህ አይነት ትርጉም አልባ ጭካኔዎቹና ግድያዎቹ ነበሩ፡፡ ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ በመጠቅለሉ ሴናተሮቹ ለስም ያህል ሹመት ቢኖራቸውም፣ ከካሊጉላ ተነጥሎ ሊጠራ የሚችል የስልጣን እርከንና አይነት አልነበረም፡፡ ሁሉም ትእዛዝን ከእሱ ይቀበላል ወይም የእሱን ትእዛዝ ያስፈፅማል፡፡ ከፈጣሪ ጋር የተለየ ግንኙነት አለኝ ብሎ ያምን ስለነበር፣ በስልጣኑ ላይ ምንም አይነት ጥያቄ እንዲነሳበት አይፈቅድም ነበር፡፡ እሱ መሪ፣ ሌላው ተመሪ ነው፡፡ ካሊጉላ ስዩመ እግዚአብሄር መሆኑ ነው፡፡ ለነገሩ ተረቱስ “ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ” አይደል የሚለው፡፡ ንጉስን ማስቀየም ፈጣሪን ማስቀየም ነው፡፡ ማን ነው ደፍሮ ካሊጉላን የሚያስቀይመው፡፡ እብደቱን ያባባሰበት አንዱ ምክንያት ለራሱ የሰጠው እንደዚህ አይነት ግምት ነው፡፡ መለኮታዊ ሀይልን የተሞላሁ ነኝ ብሎ ማመኑ፡፡ ሁሉ በኩልሄ አይነት መሪ ነበር፡፡ በእያንዳንዱ ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበረው፡፡ እሱ ሳያውቅ የሚደረግ አንዳች እንኳን ጉዳይ አልነበረም፤የሞት ቅጣቶቹን ጨምሮ፡፡
ለዝና እና በታሪክ ፊት ህያው ሆኖ ለመታወስ የነበረው ፍላጎት የሰው አልነበረም፡፡ ሮም ጌጦቼና ማስታወሻዎቼ ናቸው ያለቻቸውን ቅርሶች አፈራርሷል፡፡ ፍፁም ተጠራጣሪ ከመሆኑ የተነሳ ሹማምንቱ የሚሰጡትን አስተያየት ከሸር ለይቶ አያየውም ነበር፡፡ በኋላ በኋላ ወፈፌነቱ ቀን በውኑ ሌት በህልሙ ያቃዠው ጀመር፡፡ ካሊጉላ በሁሉም መስክ ልቆ መታየት ይፈልግ ነበር፡፡ የተናገረው በሙሉ በጭብጨባና በኣድናቆት የሚጸናለት ሰው ነበር፡፡ ለንግግር ችሎታው ወደር አልነበረውም፡፡ በህዝብ ፊት ረዘም ላሉ ሰዓታት ንግግር ማድረግ ይወድ ነበር፡፡ የንግግሩ ይዘት ግን በአብዛኛው ትኩረቱ ሹማምንቱን በመሳደብና በመዝለፍ የተሞሉ ነበሩ፡፡ በዘመኑ ገናና የነበሩ ገጣምያንን፣ ጸሃፊያንንና ፈላስፎች መጻሕፍት ከያሉበት በመልቀም እንዲወገዱ አድርጓል፡፡ የሚገርመው ግን ለንግግሩ ማሳመሪያ የሆኑትን ጥቅሶች የተጠቀመው ከነዚህ ጠበብቶች መጻሕፍት ነበር፡፡ ለምሳሌ ከሆሜር “አንድ መሪ ይኑር እና አንድ ንጉስ” የሚለውን፤ “እስከፈሩኝ ድረስ ይጥሉኝ” ሲልም ማኪቬላዊ ሀሳቡን ከሆሜር በመዋስ ተናግሯል፡፡
ከህዝቡ ጋር የነበረው ግንኙነት የተመሰረተው በፍርሃት ላይ ነበር፡፡ ፍርሃትና ሽብርን በእያንዳንዱ ልብ በማስረጽ ሊመጣበት የሚችለውን ተቃውሞ ለጊዜውም ቢሆን የጋረደበት ጋሻው ነበር፡፡ በፍርሃትና በማርበትበት ገመድ ሮማውያንን ጠፍንጎ አሰራቸው፡፡ በሂደትም የጭካኔውን ሰይፍ በዜጎቹ ላይ ማሳረፍ ጀመረ፡፡ ለመግደል ከነበረው ፍላጎት የተነሳ የሮማውያን ጭንቅላት በአንድ አንገት ላይ እንዲቀርብለት እስከመመኘት ደርሶ ነበር፡፡
ካሊጉላ ልክ እንደ 20ኛው ክፍለዘመን የአፍሪካ አምባገነኖች ቦካሳ እና ኤዲአሚን ዳዳ፣ ሰው በማሰቃየትና በመግደል የሚዝናና ነበር፡፡ በስልጣን ላይ የቆየው ለ4 አመታት ብቻ ቢሆንም ግፉ ግን ዝንታለም ይመስል ነበር፡፡ አምባገነን ሁሌም ፈሪ ነው፡፡ ፍርሃቱን ለመሸሸግ ጨካኝ ይሆናል፡፡ የትኛውም አምባገነን አይደለም ባለሟሎቹን ጥላውን አያምንም፡፡ የገዛ ፍርሃቱ ሲያባንነው ይኖራል፡፡ ካሊጉላ የልብ ወዳጁና የቅርቡ የነበረውን ፈላስፋው ሴኔካን ጭምር ገድሎታል፡፡ የካሊጉላ ዘመን ሮምን በፍርሃት ድቅድቅ ውስጥ ጨመራት፡፡ በአንዳንድ ነገሩ ከፍ ያለ በራስ መተማመን ያለው ሰው ቢመስልም፣ ከልክ ያለፈ ፍርሃትም ይጫወትበት ነበር፡፡ ጭካኔውን ያባባሰበት ይህ ከልክ ያለፈ ፍርሃቱ ነበር፡፡
ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች ድርጊቶቹ መረን ሲለቁና እብደቱም ሲባባስ፣ ሴናተሮቹ እና የልዩ ጥበቃ አባላት ካሊጉላን ማስወገድ እንዳለባቸው አመኑ፡፡ በአደባባይ ሳይሆን ውስጥ ለውስጥ በሚስጥር፡፡ በቃኸን ሊሉት እና እስከወዲያኛው ሊያስወግዱት ወጥመድ ዘረጉ፡፡ እንዴት እንደሚያስወግዱት የመጨረሻውን ምክክር ካደረጉ በኋላ ከስፖርት ሲመለስ ሳያስበው ጥቃት ፈፀሙበት፡፡ በአሰቃቂ ሁኔታም ገደሉት፡፡ ልጆቹና ሚስቱም የእሱ እጣ ደረሳቸው፡፡ ከሮም ታሪክ ውስጥ የእሱን ስም መፋቅ ስለፈለጉ ሀውልቱን ባለበት አፈረሱ፡፡ የመንግስቱንም አደረጃጀት ዳግም መገንባት ጀመሩ፡፡ ካሊጉላ የነገሰው ለአጭር ጊዜ ቢሆንም፣ ተፅእኖውን ግን በሮም ላይ በጉልህ አሳርፏል፡፡ ወፈፌነቱን የቀሰቀሰበት ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ካሊጉላና ድርጊቱ ግን በሮማን ታሪክ ውስጥ በመጥፎ የሚነሳ ንጉስ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
***
ከአዘጋጁ፡- ደረጄ ጥጉ፤ የመጀመሪያ ዲግሪውን በፍልስፍና ከአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ በ1998 ዓ.ም የወሰደ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ ከቻይና ዉሃን ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክ ኢንተርናሽናል ሎው በ2009 ዓ.ም አግኝቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ፍልስፍና እና አለም አቀፍ ህግ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡
Monday, 29 July 2024 19:58
ካሊጉላ - ወፈፌው ንጉስ
Written by በደረጄ ጥጉ (የአለም አቀፍ ህግ መምህር)
Published in
ህብረተሰብ