Wednesday, 31 July 2024 00:00

"ከተገፉ ህዝቦች ጀርባ የተገፋ ታሪክ አለ"

Written by  በነቢል አዱኛ
Rate this item
(1 Vote)

በታሪክ ሃዲድ ስንጓዝ፣በዘመን ኬላ ወደ ኋላ፣ መርምረን መርጠን ለመያዝ፣እውነትን ከሃሰት በኋላ፣
ማንበብ ማጥናት አለብን፤የሰው ልጆች በጠቅላላ።
፨ በአለም ላይ በጣም በርካታ ታላቅ ታሪክ የሰሩ ሰዎች አልፈዋል። የአብዛኛዎቹንም የህይወት ገጽ፣ ያበረከቱትን አስተዋጽዖ ተምረናል። አንብበናል። በዛውም ልክ ታላቅ ታሪክን ሰርተው ፍኖተ ህይወታቸው ለሁሉም በልኩ ያልደረሰላቸው አሉ። አውቆ በማጥፋት፣ በመሸፋፈን፣ በመቀያየር ታሪካቸው የተቀበረባቸው ሞልተዋል። ሃገር እየተለየ፣ ጎሳ እየተመረጠ፣ ዕምነት እየታየ ያልሆኑትን ሆነዋል፤ የሆኑትን አልሆኑም የተባሉ ብዙ ናቸው። ለምሳሌ፦ ምድረ አውሮፓ በጨለማው ዘመን(Dark age) ላይ በነበረበት ጊዜ በምስራቁ አለም እስከዛሬ ያልተደገሙ ታላላቅ ስልጣኔዎች ነበሩ። ሳይንቲስቶች፣ ኬሚስቶች፣ ዶክተሮች፣ ፕርፌሰሮች፣ ፊዚስቶች ወዘተ ... የነበሩበት፤ በአንድ ንጉስ(ኸሊፋ) አገዛዝ ለ400 አመታት በፍትሃዊነት ስትተዳደር የነበረች የስልጣኔ፣ የፍልስፍና፣ የታሪክ መናገሻና የብዙ ሳይንሶች መመስረቻ የነበረች የስልጣኔ ምሳሌ የሆነች የኢስላም ወርቃማው ዘመን(Golden age) ማሳያ ባግዳድ ነበረች። በ1258 በሞንጎሎች ወረራ ግን እንዳልነበር ሆነች። ወዲህ ደሞ የመስቀል ጦርነት ከተነሳ ኋላ የእነዚያ ሊቃውንት ስም እየተሻረና እየተሰረዘ፣ ኋላቀር እና ስልጣኔ የማያውቁ የሚል ታፔላ ተለጥፎላቸው ስማቸው ከሽብር ጋር እንጂ ከሳይንስ ጋር እንዳይጠራ የተደረጉ ህዝቦች አሉ። መሀመድ አሊ(ቡርሃን) እንደሚለው፦ "በምድራችን ጠበብት ዝርዝር ውስጥ ሙስሊም ሊቃውንት ሲካተቱ ማየት - ላዘነበለው የአለም የታሪክ ፍልስፍና ህመም መሆኑ እሙን ነው።"(6ቱ የሃዲስ ሊቃውንት ቅጽ 2 - 67)
፨ አለም ላይ አንስታይን፣ ኒውተን፣ ሮጀር ቤከን፣ ረኔ ዴካርት ሲባል ሁሉም እንዲያውቃቸው፣ ነገር ግን የነዚህን 'ፈጠራ' ውጤት ለመጀመሪያ ጊዜ መሰረት የጣሉት ኢብኑ ሃይሰም፣ አል-ኸዋሪዝሚ፣ አል-ቤሩኒ፣ ጃቢር ኢብን ሃያን እንዳይጠቀሱ ተደርገዋል።
"ከተገፉ ህዝቦች ጀርባ የተገፋ ታሪክ አለ።" (መሀመድ አሊ/ቡርሃን)።
፨ ከተገፉ ህዝቦች ጀርባ ታሪክ የሰሩ ሰዎች ህይወት በ2007 በአል-ተውባ ማተሚያ ቤት በ2 ቅጽ በታተመው የመሀመድ አሊ/ቡርሃን - “6ቱ የሃዲስ ሊቃውንት” መጽሐፍ ላይ ተመስርተን፤ አንድ ሰው ስለ እስልምና ለማወቅ ከቁርአን ቀጥሎ የሚማርባቸውን 6 ቅቡል የሆኑ የሃዲስ ጥራዞች ያዘጋጁ ኢማሞች(ፕሮፌሰሮች) ታሪክን እንቃኛለን።
"ትናንት በዚያ ወርቃማ የኢስላም ዘመን ምሁራን የሚጠሩባቸው የማዕረግ ስሞች ሸይኽ፣ ዑስታዝ፣ ሃፊዝ፣ ፈቂህ፣ ኢማም ወዘተ... ያሉ ነበሩ። ያኔ ኢማም ተብለው የተጠሩትን የሙስሊም ምሁራን ታሪክ ስንፈትሽ በዛሬው መለኪያ ቢመዘኑ ሦስት አራት የዶክትሬት ማዕረግ እንደሚላበሱ ማሳየት ይቻላል።" (ቅጽ 2 - ገጽ 160)
፨ - ቁርዓን፦ ማለት በነብዩ ሙሀመድ ላይ በ23 አመት የነብይነት ዘመናቸው ሲወርድላቸው የነበረ መለኮታዊ የአላህ ቃል ነው።
- ሃዲስ፦ ማለት የቁርዓን አስረጂና ማብራሪያ፣ የነብዩ ሙሀመድ ንግግር፣ አስተምህሮ፣ ትዕዛዝ ነው።
፨ ሃዲስን ማጥናት ለምን አስፈለገ?
በነብዩ ሙሀመድ የነብይነት ዘመን ቁርዓን በርሳቸው ላይ በሚወርድበት ጊዜ ተከታዮቻቸው(ሰሀቦቻቸው) በተለያዩ ነገሮች(አጥንት፣ ቆዳ ወዘተ) ፅፈው ያስቀምጡ ነበር። ነብዩ ሙሀመድ ካለፉ በኋላም በመጀመሪያው ኸሊፋ አቡበከር ሲዲቅ ዘመን በሰሀቦች ርብርብ፣ ቁርአን በሚወርድበት ጊዜ ጸሃፊ በነበረው ዘይድ ኢብን ሳቢት ጥረት ቁርዓን ሙሉ ምዕራፉ በአንድ ተጠረዘ። በዘመኑ ሰሀቦቹ የነብዩ ሙሀመድን ንግግር(ሃዲስ) ፅፈው አላስቀመጡም። አንድም ከቁርአን እኩል ክብር እንዳይቸረው ብለው፣ አንድም ከቁርዓን ጋር እንዳይቀላቀል በማሰብ ሃዲስን የመዘገብና ከመለኮታዊ መመሪያዎች ማህደር ማካተት ባህል አልነበረም። ነገር ግን ከነሱ በኋላ ለመጡ ትውልዶች በየሃገሩ ተበታትነው ያሉት ሰሀቦች ቁርአንንም የነብዩ ሙሀመድ ትዕዛዝንም ማስተማር ጀመሩ። በጊዜው ተዘግቦ መቀመጡ ያን ያክል አስፈላጊ አልነበረም። ሃዲስን መማር የፈለገ ሰሀቦች ጋር ሄዶ መማር ይችላል። ነገሩ በዚሁ ቀጥሎ እያለ ሰሀቦች ካለፉ በኋላ ሙስሊሞችን በጦርነት ማሸነፍ ያቃታቸው ከሃዲያንና መናፍቃን በሌላ መንገድ ሙስሊሙን ለማጥቃት መላ ቀየሱ። የሌሉ እና ያልተባሉ ሃዲሶችን በመፍጠር "ነብዩ እንዲህ አሉ" ብለው ማሰራጨት ጀመሩ። በዕውቀት ያልገፉ ሙስሊሞች ላይም መደናገር ተፈጠረ። ይህንን የተመለከቱት ከሰሀቦች የተማሩ ሊቃውንት ኪታቦችን አዘጋጁ። ለምሳሌ፦ እነ ኢማም ማሊክ፣ ኢማም አህመድ፣ ኢማም አል-አውዛዒ፣ ሱፍያን አስ-ሰውሪ ይጠቀሳሉ። አምስተኛው ኸሊፋ ተብለው የሚታወቁት ዑመር ኢብን ዐብዱልዐዚዝ'ም ወደ ተለያዩ ምሁራን ደብዳቤ እየጻፉ ሃዲሶች ተሰብስበው በአንድ እንዲጠረዙ ያዝዙ ነበር። "ምሁራን አልፈው እውቀት ወደ ቀጣዩ ትውልድ ሳይተላለፍ ይቀራል የሚል ስጋት አለኝ፤ ስለዚህ የነብዩ ሙሀመድን ሃዲሶች ተከታትለህ ጻፍ። ጸጋን በምስጋና ዕውቀትን በመጽሐፍ አስራችሁ አስቀሩ።" ይሉ ነበር።
(ዑመር ኢብን ዐብዱልዐዚዝ ገጽ - 42)
ሆኖም ግን እነዚህ ኪታቦች እውነተኛ ሃዲስን(ሰሂህ የሆነ) ከሃሰተኛው ሙሉ ለሙሉ ተለይቶባቸው የተጻፉ አይደሉም። በዚህን ጊዜ  እውነተኛውን ከሃሰተኛው(ሰሂሁን ከደኢፍ) የሚለይበት አዲስ ማንፀሪያ ዘዴ ይዘው የመጀመሪያው የሃዲስ ሊቃውንት በመሆን ኢማም አል-ቡኻሪ መጡ።
፨ ኢማም ቡኻሪ፦ የኢማም ማሊክ እና የሃማድ ኢብን ዘይድ ተማሪ ከሆኑት ታላቁ አሊም እና ነጋዴ አባታቸው በሸዋል ወር በ13ኛው ቀን የሩሲያ ግዛት በነበረችው ኡዝቤክ ቡኻራ መንደር በ194 አመተ ሂጅራ(809 እ.ኤ.አ) ሙሀመድ ኢብን ኢስማኢል(ኢማም ቡኻሪ) ተወለዱ። ገና በህጻንነታቸው አባታቸውን ያጡት ቡኻሪ፤ በእናታቸው እንክብካቤ በማደግ ላይ ሳሉ ስድስት አመት ሳይሞላቸው የዓይናቸውን ብርሃን አጡ። በዚህ የተደናገጡት እናትም በዘመናቸው ወዳለው ዶክተር ቢወስዷቸውም መላ የለውም ተባሉ። በጣም አዝነውና ተሰብረው ለረዥም ሰአታት ጌታቸውን በመማፀንና በመለመን ያሳልፉ ገቡ። ብዙ ሌሊቶችን በእንባ ታጅበው ሲሰግዱ ያድራሉ። በዚህ ሁኔታቸው በርካታ ጊዜያትን ካሳለፉ በኋላ ጌታቸው ልመናቸውን መቀበሉን በመናም አሳይቷቸው - ነቅተው ወደ ልጃቸው ሲያመሩ የአይን ብርሃናቸው ተመልሷል። ከዚያም ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመለሱ።
፨ በአስር አመት ዕድሜያቸው ሙሉ ቁርአንን በቃላቸው ያዙ። ከቁርአን በኋላ አረብኛ ቋንቋን አጠኑ። ቀጥሎም ከኢማም ዙሃሊ ሃዲስን ተማሩ። በዕድሜ ትንሽ ቢሆኑም ከሌሎች በበለጠ በማስታወስ ችሎታቸውና በማስተዋል ብቃታቸው በሁሉም መምህራኖች የተደነቁ ነበሩ።
፨ በዘመኑ መምህራኖች(ሊቃውንቶች፣ ኢማሞች) ይኖሩ የነበሩት በተለያዩ የኢስላም ግዛቶች ውስጥ ነው። እናም አንድ ተማሪ መማር ሲፈልግ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጦ በፈረስ ወይ በግመል መምህሩ ያለበት ቦታ ይደርሳል። ይህ ዕውቀትን ፍለጋ ብቻ ተብሎ የሚጓዙት ጉዞ የ6ቱ ሊቃውንት እጣ ብቻ ሳይሆን በዚያ ዘመን የነበሩ ሌሎች ሰዎችንም የሚያካትት ነው። የዚህ ዕጣ ተቋዳሽ የነበሩት ኢማሙ ቡኻሪም ጓዛቸውን አሰናድተው በአስራ ስድስት አመታቸው ወደ መካ አቀኑ። የሃጅ ስርአታቸውን ከፈጸሙ በኋላም እናታቸውና ወንድማቸው ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ ቡኻሪ እዚያው ቆዩ። በመካ እየተዘዋወሩም ከተለያዩ መምህራኖች በርካታ ዕውቀት ቀሰሙ። ከሁለት አመት በኋላም ወደ መዲና በማቅናት ሲማሩ ከቆዩ በኋላ፣ እዚያው እያሉ በ18 አመታቸው ትልቅ መጽሃፍ ጻፉ። በዘመኑ በኢስላም አገዛዝ ስር የሆነ ሃገር ውስጥ ማንኛውም ሰው በፈለገው ሰአት መግባትም መውጣትም መኖርም ይችላል። ለኋለኛው ዘመን የሃዲስና የእስልምና ታሪክ ተመራማሪዎች ሁሉ ትልቅ መሰረት የሆነ መጽሐፍ በታዳጊነት ዕድሜያቸው ሰሩ። ታሪኹል ከቢር የሚሰኘው ይህ ድንቅ መጽሃፋቸው፤ የ40 ሺህ ሃዲስ ተራኪዎችን ማንነትና ታሪክ የያዘ ትልቅ መጽሐፍ ነው።
፨ ከመዲና በኋላ ወደ በርካታ ሃገሮች በመዘዋወር ከብዙ መምህራን  ጋር እየተገናኙ ተምረዋል። ባልክ፣ ኒሻፑር፣ ራኢ፣ ባስራ፣ ዋሲጥ፣ ሃማስ፣ ደማስቆ፣ ባግዳድ ወዘተ የሚጠቀሱ ናቸው። ከበርካታ መምህራንም ተምረዋል። "ሃዲስን ከ1000 በላይ ሰዎች ጋር ተምሬ ፅፌያለሁ።" ብለዋል። በርከት የሚሉ የታሪካቸው አጥኚዎች፣ ከ1080 የማያንሱ መምህሮች ጋር ዘልቀው መማራቸውን ይጠቁማሉ። ባግዳድ ላይ ከታላቁ የፊቅህ(የኢስላማዊ ህግጋት መርማሪ) ኢማም አህመድ ኢብን ሃንበል ዘንድ ተምረዋል። (የመምህራኖቻቸው ዝርዝር በቅጽ 1 መጽሐፍ፤ ከገጽ 48-53 አለ።)
፨ ትልቁን የሃዲስ ኪታባቸውን <ሰሂህ አል-ቡኻሪ> የተሰኘውን የሃዲሶች ስብስብ ጥራዝ ለማዘጋጀት ራሱን የቻለ የሃዲስ ማንፀሪያ ዘዴ አዘጋጅተዋል። እኚህ በአለም የኢስላም ታሪክ ቁጥር አንድ የሃዲስ ምሁር (ሳይንቲስት)፤ በሃዲስ ዘገባ ከሳቸው በፊት ሌሎች በርካቶች ያዘጋጇቸው ጥራዞች ቢኖሩም የሳቸውን ያክል የጠራ እና ሰሂህ(ዕውነተኛ) ሃዲሶች ያሉበት አይደለም። ይህን ከ16 አመት በላይ የፈጀባቸውን ኪታብ ለመጻፍ ያበጁት ማንፀሪያ - ሃዲስን ሰሂህ ነው ብለው ከመዘገባቸው በፊት ሃዲሱን የሚነግራቸው ሰው ምን አይነት ባህሪይ እንዳለው ያጠናሉ። የህይወት ታሪኩንም ማወቅ አለባቸው። ለዚያም ነው ታሪኩል ከቢር የተሰኘ ትልቅ የሃዲስ ዘጋቢዎች የህይወት ታሪክ ያለበት መጽሐፍ ማዘጋጀታቸው። እናም ሃዲስ የሚነግራቸው መምህር ከዚህ በፊት ውሸት ወይንም ማንኛውም አይነት የስነ-ምግባር ጉድለት ካለበት ሃዲሱን ሰሂህ ነው ብለው አይቀበሉትም። ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚነሳ ታሪክ አላቸው። አንድ ጊዜ ሃዲስን ከሚያውቅ መምህር ለመማር ለአንድ ወር ያክል ተጉዘው ከሰውየው መኖሪያ ይደርሳሉ። መምህሩ ቤቱ ውስጥ ፈረሱ አልያዝ ብሎ አስቸግሮት እየታገለው ነው። በመጨረሻም ባዶ እንቅብ በማሳየት ፈረሱን አታሎ ያዘው። ነገር ግን ኢማም ቡኻሪ ይህን በሚመለከቱ ጊዜ "እንስሳትንስ ቢሆን ማታለል በጎ ስራ ነው?" ብለው ተናደው ሳይጠይቁት በመጡበት ተመለሱ።(ቅጽ 1 - 43)
፨ ሌላው ሃዲስ በሚዘገብበት ጊዜ የሃዲሱ አስተላላፊዎች ሰንሰለት እየተቆጠረ፣ "እገሌ ከእንቶኔ እንደሰማው..." እየተባለ እስከ ነብዩ ሙሀመድ ድረስ መድረስ አለበት።
"በጊዜው የታወቁና የታመኑ ሊቃውንት ቢያስተምሯቸውም ከነርሱ የተቀበሉትን ሃዲስ እንዲሁ በተአማኒነት ፈርጀው አልዘገቡም። ይልቁንም መምህሮቻቸው ከየትና ከማን እንደሰሙ፤ የሰሙትን ይዘው የዘጋቢውን ታሪክ ማጥናት ይጀምራሉ። እናም በሰንሰለቱ ውስጥ ከተጠቀሱ ሃዲስ አስተላላፊዎች መካከል አንዱ ብቻ እንኳ በህይወቱ የሚዋሽ ወይም በዕምነቱ ደካማ መሆኑን ከተገነዘቡ የሃዲሱን ሰሂህነት ደረጃ ወይም ሳይዘግቡ ይተዉታል። ይህ ማንፀሪያ በአለማችን ሊቃውንት ስራ ውስጥ ይገኛል ብሎ ለማሰብ እጅግ ይቸግራል።" (ቅጽ 1 - 63)
፨ ከ600 ሺህ ሃዲሶች ውስጥ ተአማኒ ያሏቸውን 7000 ሃዲሶች በማካተት ከሰሩት <ሰሂህ አል-ቡኻሪ> ሌላ 'አዳቡል ሙፍረድ፣ አፍአሉል ኢባድ፣ ኪታቡል ሂባ፣ ጁዝ ረዕፉል የዲን' እና ሌሎችም ከ22 በላይ መጽሐፎችን ጽፈዋል።(ቅጽ 1 - 70) በሰሂህ አል-ቡኻሪ ኪታባቸው ላይም 82 የሚደርሱ ማብራሪያዎች ተሰርቶበታል።
፨ "ቡኻሪ በታሪክ ድንቅ ሊቅ መሆናቸውን ያስመሰከሩት ገና በ18 አመታቸው በጻፉት የታሪክ ጥራዝ ነው። በሃዲስ ጥናት ዘርፍም አዲስ መንገድ እስከ ማስተዋወቅ በደረሰ የዕውቀት ምጥቀት የታወቁ ነበሩ። በኢስላማዊ ህግጋት(ፊቅህ) ላይም የነበራቸው ምልከታ ከወሰን የሰፋ ነበር። እናም ቡኻሪ ቢያንስ በታሪክ፣ በስነ-ሃዲስ እና በፊቅህ ዘርፍ ታላላቅ ስራዎችን የሰሩና አዲስ መንገድ ያሳዩ ሰው በመሆናቸው በሦስት ዘርፎች ትልልቅ ማዕረጎች እናላብሳቸዋለን። ይህንን ታላቅ ማንነት ወዲህኛው ዘመን ካለ ፕሮፌሰር ጋር ማነጻጸር ይቻላል።" (ቅጽ 2 - 160)
፨ ከፍተኛ የማስታወስ ብቃት የነበራቸው እና ድንቅ መምህር የነበሩት ታላቁ ፕሮፌሰር ኢማም ቡኻሪ፤ በ256 አ.ሂ(871 እ.ኤ.አ) በሰመርቀንድ በ62 ዓመታቸው አረፉ።


Read 640 times