Monday, 29 July 2024 20:13

የ“ደማቆቹ” መንደርደሪያ

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

የህይወትን እውነተኛ ገፅታ በአጭር የፈጠራ ታሪክ አማካኝነት ማቅረብ አስቸጋሪ ጉዳይ ነው። ግን ደግሞ የሰው ልጅ ታሪክ ሳይናገር የኖረበት ዘመን የለም። እንደ ጦርነት እና እንደ በሽታ፣ ወይንም እንደ ርሃብ እና ብልፅግና አንድ ጊዜ የሚመጣ እና ሌላ ጊዜ የሚሄድ ነገር አይደለም። ታሪክ መንገር ለሰው ልጅ የማይለወጥ ማንነቱ ነው። ታሪክ መንገር የህልውና ጉዳይ ነው። ከሰው ልጅ ጋር አብሮ የኖረ፣ ከዘመናት ተሞክሮው ጋር አብሮት ያደገ ነገር ነው።
በሰው ልጅ የዝግመተ ለውጥ ሂደት የሚያምኑት፣ የልብ ወለድ ተረክ ወይንም ተረትን መናገር ከዋሻ ዘመን ጊዜ ጀምሮ ተከትሎት የመጣ መሆኑን ይገልፃሉ። እንዲያውም የባሰበት የዚህ ፅንሰ ሃሳብ አቀንቃኝ (ዩቫል ኖህ ሃራሬ) የሰው ልጅ ጦጣ መሰል የዝርያ መሰሎቹን በልጦ ብቸኛ ሆኖ በህልውና መቀጠል የቻለው፣ በሚናገራቸው እና በሚያስተላልፋቸው ታሪኮች ምክንያት ነው ይላል። ይሄ አሁን የላቀ ንቃተ ህሊና ባለቤት ሆኖ ምድርን በብቸኝነት በመቆጣጠር እየናኘበት ያለው የሰው ልጅ (ሳፒየን)፣ ይኼንን ማድረግ የቻለው በተረት እና በታሪኮች አማካኝነት ነው ማለቱ ነው።
የዝግመተ ለውጥ እምነትን ለጊዜው እንተወውና፣ ሃሳቡን በጥበብ መነፅር አሻሽዬ አይቼ ለራሴ መጠቀሚያ እገዛዋለሁ። ስለዚህ አጭር ታሪክ ወይንም ተረት የመናገር እና የማስተላለፍ ጉዳይ ድንገት በዘመናት ሂደት አዲስ ስልጣኔ ሆኖ የመጣ ሳይሆን ከማንነታችን ጋር ጠብቆ የታሰረ ነገር ነው። የሰው ልጅ ለሰው የሚያስተላልፈው ውድ መልዕክት ሁሉ የታሪክን እና የተረትን ቅርፅ ዞሮ ዞሮ መንተራሱ የማይቀር ነው።
የዘመናዊ አጭር ልብ ወለድ ማንነት ግን ወይንም “ሮማንቲክ ቴል” የሚባለው ግን ከአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ላይ መነቃቃት የጀመረ፣ አውሮፓዊ የጥበብ እና የአመለካከት እንቅስቃሴ ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ይነገራል። በዚህ ዘመን ዋዜማ ላይ የነበሩት የመጀመሪያዎቹ ደራሲዎች (እንደ ኤ.ቲ. ደብሊው ሆፍማን እና እንደ ሉድዊግ ቲክ) የልብ ወለድ መዋቅራቸው ልል ሴራ ያላቸው፣ “ሁኔታዊ” የሆኑ፣ የጠበቀ አንድነትን ያላዳበሩ ታሪኮችን ለአንባቢያን ያቀርቡ ነበር። የነዚህ ተረክ ገፀባህሪዎች ሲበዛ ምናባዊ እና በደራሲው አምሮት እጅግ ተጋነው የሚቀርቡ፣ ከተጨባጩ እውነታም የተፋቱ ነበሩ።
እንደዚሁ አይነት የተዝረከረኩ ታሪኮችን አሜሪካዊያኖቹም ደራሲዎች (እንደ ናታኔል ሃውቶርን፣ ዋሽንግተን ኧርቪንግ እና ኤድጋር አለን ፖ’ም) መጀመሪያ ላይ ያቀርቡ ነበር። ነገር ግን በተለይ እነዚህ ሶስት ደራሲዎች ቀስ በቀስ አዲስ አይነት ቅርፅን እያዳበሩ መጥተዋል። ይሄም አዲስ የአጻጻፍ ዘይቤ እና ቅርፅ፣ በተሻለ ስያሜ እጦትም “ዘመናዊ አጭር ልብወለድ” ተብሎ መጠራት ጀመረ።
የዋሽንግተን ኧርቪንግ “ሪፕ ቫን ሪንክል” የተሠኘ ድርሰት በዚህ አዲስ ቅርፅ ውስጥ የሚካተት ነው። ቀድሞ ከነበረው ምትሃታዊ ታሪክ ይልቅ፣ ሴራው የተጨመቀ፣ አንድ የትኩረት ማዕከል ያለው እና የታሪኩን ትኩረት በሙሉ ሰብስቦ ወደ አንድ ነጠላ ውጤት የሚያመጣ ነው።
ኤድጋር አለን ፖ “The philoslophy of composition” በሚል ባስቀመጠው ንድፈ ሃሳባዊ መግለጫ ለዚህ አዲስ ቅርጽ ማብራሪያ ሰጥቷል ፡- የሚነገረው ታሪክ ወደ አንድ የትኩረት ነጥብ በሃይል መሰብሰብ መቻል እንዳለበት ይገልፃል። ለታሪኩ የማያስፈልገው ዝባዝንኬ ሁሉ፣ ከአብይ ሴራውና በወሳኝነት ታሪኩን ከሚነዱት ገፀባህሪያት በስተቀር መወገድ እንዳለባቸው ያሳስባል። ጥንታዊው የአሪስጣጣሊስን የድራማ መሰረታዊያን ድንጋጌን ከ ፖ እሳቤ ጋር ማነጻጸር ይቻላል።
ፖ የተናገረው፣ ሴራው ዋናው ነገር ስለመሆኑ ነው። ደራሲዎች በአብዛኛው የታሪኩን መጨረሻ ከወሰኑ በኋላ ወይንም በዛ የስሜት መጠንሰሻ ላይ ተመርኩዘው ከዛ ባሻገር ያለውን ሌላውን ነገር ያለ ምንም ጥንቃቄ አዝረክርከው የሚፅፉ ከሆነ ስህተት ነው ይላል።
ስብከትን መስበክ፣ ማስተማር እና ማሳወቅ፣ የአጭር ልብ ወለዱ ግብ ተጻራሪ ጉዳዮች መሆናቸውን ነው የ ፖ መንገድ የሚያስገነዝበው። በዚህም አንድ ዋና ትኩረትን ወይንም ነጠላ ውጤትን መፍጠር (“Single effect”) ዋነኛው ነገር ነው ብሎ የጥበብ አቋሙን ገለፀ። ከረጅም የፈጠራ ልብ ወለድ እና ከኖቬላ አጭር ልብ ወለድ የሚለየው በእጥረቱ እና ሴራው የጠነከረ ውህድ በመሆኑ እንደሆነ ገለጠ። በዚህም የአቋም መሰረት የራሱን አጫጭር ልብ ወለድ ፈጠራዎች ማቅረብ ጀመረ። ውበቱም ያለው እዚህ ላይ ነው ባይ ነው። እጥረቱ እና አንድ ግብን ለመምታት ካለው ውስን ትኩረቱ ጋር ውበቱ ጥብቅ ቁርኝት አለው ይላል። ይኼን ለማሳካት ደግሞ ለታሪኩ ሴራ ደራሲው ታማኝ መሆን አለበት።
በዚህ መነፅር አጭር ልብ ወለድ አሁን የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ካየን በኤድጋር አለን ፖ ብያኔ የሚፃፉ ልብወለዶች ወይንም እሱ የሚጽፋቸው አይነት ልብወለዶች የዲቴክቲቭ፣ ምስጢር እና የተደበቀ ነገርን መግለጥ ወይንም የሆረር ልብወለድ ከመሆን ውጭ አማራጭ አይኖራቸውም። “Six stories of fear” በመባል የሚታወቀው የዚህ ደራሲ መድበል እነዚህን ባህርያት ያሳያል።
አሁን ዘመን ላይ ባለው ብያኔ፣ ዘመናዊ አጭር ልብ ወለድ ማለት እንደ ስሙ አጭር፣ በአንድ ቁጭታ ተነቦ ማለቅ የሚችል፣ በውስን ገፀባህሪያት አማካኝነት ታሪኩ ከመነሻው እስከ መደምደሚያው አንድ ትኩረትን ይዞ የሚዘልቅ ማለት ነው። በቸኮለ የተረክ ጥበብ፣ ውበትን እና የመግለፅ ብቃትን ሳያጓድል አንዳች ግጭትን መሰረት አድርጎ በታሪኩ ሂደት ለውጥና እልባትን ወይንም ያልነበረ እንቆቅልሽን ገልጦ የሚያልቅ ታሪክ ሁሉ በአጭር ልብወለድ ውስጥ ሊካተት የሚችል ነው።
ማንኛውም አይነት የጥበብ ዘውግ የሚዳኘው ለውበት ካለው ተጠሪነቱ አንጻር ነው። ልዩ ሆኖ፣ በአይነቱ ብቸኛ፣ በአንድ ከያኒ ወይም በዘመን መንፈስ ሊገኝ የሚችል፣ ውድ እንቁ የመሆኑ ምክንያትም በቲዎሪ ብቻ ተገልፆ “እንዲህ እና እንዲያ ሲሆን” ተብሎ ከመደንገጉ የሚመነጭ ነው ማለት አይቻልም። ለዚህኛው ወይንም ለዛኛው ቲዎሪ መጥኖ በመገኘቱ አይደለም ለተሰየመለት ሳጥን ብቁ የሚያደርገው። ዋናው ሳጥን ውበት ነው። ጋሪው ከፈረሱ ሊቀድም አይችልም። የደራሲው ፈጠራ ቲዎሪውን ሊከተልም ላይከተልም ይችላል። ልክ የፅጌሬዳ አበባው የተክሉ ሁለንተናዊ ውበት ጫፍ ሆኖ እንደሚፈካው። ከቅጠልም፣ ከዛፉም፣ ከስሩም ለተለየ፣ ከአገልግሎትም ውጭ ለሆነው ውበቱ ጥንቅቅ ያለ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም። ወቅቱ ነው፣ ልዩ ነው፣ ራሱ ከራሱ ጋር አመጣጥኖ የተቀመመ ነው፣ ደማቅ ነው… ከማለት ውጭ ምንም ምክንያት ማቅረብ አይቻልም። አልማዝ ከከሰል ለምን እንደተለየ ከመታመቅ ውጭ ሌላ ምክንያት ማቅረብ እንደማይቻለው።
ዘመናዊ አጭር ልብ ወለድ ምን ማለት እንደሆነ መግለፅ ያስቸግራል የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ። ቢያስቸግርም ግን በእርግጠኝነት እነዚህ የሚከተሉትን አይደለም።
አጭር ልብ ወለድ አንድን ገጠመኝ ብቻ የሚተርክ (Anecdote) አይደለም። አፈ ታሪክ አውሪ፣ ገድል ዘካሪ፣ የሀገረ ሰብ ታሪክ (folktale) ማሸጋገሪያ አይደለም። አጭር ልብ ወለድ በእንስሳት አማካኝነት ተወክሎ የሚቀርብ አስተማሪ ታሪክ (fable) አይደለም። ተአምራዊ ታሪክ፣ ሃይማኖታዊ የማስተማሪያ ምሳሌ (Parable)፣ ድንቃይ እና አስማታዊ ታሪክ (fairy tale) አይደለም። አጭር ልብ ወለድ በዝርው ቢቀመጥም ወግ (Essay) አይደለም። ወይንም ለምዕመናን በጉባኤ የሚዘጋጅ ስብከት (Sermon) አይደለም።
የአንድን አጋጣሚ ምስል በግርድፉ ለመንገር የሚጠቅም ፅሁፋዊ ንድፍ (Sketch) አይደለም። የአንድ ሰው ግለ ታሪክ ወይንም የሀገር ታሪክ አጭር ልብ ወለድን አይወክልም። እንደ “አንድ ሺ አንድ ሌሊት” አይነት ተረቶች መናገርም የአጭር ልብ ወለድ ልዩ መገለጫው አይደለም።
እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው ሁሉ ታሪክን ወይንም ተረክን ከሰው ወደ ሰው የማሸጋገሪያ፣ ራሳቸውን የቻሉ፣ የየራሳቸው ግብ ያላቸው መንገዶች ቢሆኑም፣ ዘመናዊ አጭር ልብ ወለድን በተለያየ መንገድ ዝርያው ሆነው ቢመስሉትም፣ ሙሉ ለሙሉ አንደኛውም ሌላኛውን ነው ማለት አይቻልም። በአጋጣሚ አጭር ልብ ወለዱ ከተዘረዘሩት መሃል አንደኛውን ተንተርሶ ወይንም ተወራርሶ ሊገኝ ይችላል። የእነዛኛዎቹ ኢላማ አንድ ከሆነ፣ የአጭር ልብ ወለድ ግን አሸን የግብ አማራጭ ሊኖረው ይችላል። ብዙ አማራጭን ሲጠቀልል የውበትነቱ ንጥረ ነገር ከፍ እያለ ይመጣል። ብዙ አላማ ያለውን ነገር በአንድ አላማ መጥራት የግድ ካስፈለገ አላማው ውበት ነው። የሁሉም ነገር መጠቅለያው ማዕቀፍ።
ውበት አንዱ ነው፤ ዋናው ነው። የነጠረውን ውበት፣ ብቸኛ እና በውድነቱ አምሳያ (የአልማዝ ደርዘን) የሌለውን፣ ልዩ የደራሲው ተሰጥኦ እና አሻራ በአጭር ታሪክ አማካኝነት የሚገኝበት ነው። እድለኝነትም አለው። ማግኘት (ለደራሲው) ፣ መገኘት (ለሚደርሰው ነገር)፣ መገናኘት (ደራሲው ወደ ተደራሲው - በአጭር ልብወለዱ አማካኝነት) እድል ያስፈልገዋል።
ማየት የሚችልበትን የታሪክ ማጦዣ አተራረክ ተተግኖ… እሱ ብቻ መግለፅ የሚችለውን… ከዛው ከተለመደው ነገር ውስጥ… አዲስ መልክ አውጥቶ መስጠት መቻል እድለኝነትን ይጠይቃል። መወለድ፣ መኖር፣ ማየት እና መግለፅ መቻል። በዘመናት ውስጥ የማይሻር የሰው ልጅ መንፈስ ውድ አበርክቶት ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርገው ነገር አንዱ ውበት ነው። ውበት እድለኝነት ነው። እድለኝነት ነው ማለት ግን አቦ ሰጡኝ ማለት አይደለም። አቦ ጥበብን እና ፈጠራን አይሰጡም። ኪነት “ሆነ-ብዬ” (Deliberate) ነው። ሆነ ተብሎ የሚከወን። ሆነ-ብዬ እድለኝነት።
ሁለተኛው፣ በስድ የፅሁፍ ቅርፅ የተፃፈ መሆኑ በግጥም እና በስድ ጽሁፍ መሃል ያለውን ጥምረት እና ልዩነት ድንገት በአንድ አምጥቶ፣ አጋብቶ ያሳያል። በሴራ የማምሪያ ጎዳና፣ ከመነሻው እስከ መድረሻው፣ በተለያየ የታሪክ አማራጭ እና ጭብጥ፣ ልብ እንዲያስር አድርጎ የማቅረቢያ ይሄ ዘዴ፣ እንደ አበባ በሂደት እየፈካ የሚሄድ ነው። መነበብ ተጀምሮ ተነቦ እስኪያልቅ። ተነቦ ካለቀ በኋላ ደግሞ… መጣባት ጀምሮ የእድሜ ልክ ስንቅ እስኪሆን። እንደ ስኬታማ ውበት አጭር ልብ ወለድም ፈክቶ የሚቀጥል እንጂ ከዘመን ጋር የሚረግፍ ወይንም የሚወይብ አይሆንም። ከሆነ ደማቅ አይደለም።
ሦስተኛው፣ አንድ ስሜትን ወይንም መነካትን የሚፈጥርበት ማህተም ነው። ይኼ ደግሞ አይን አዋጅ ሊሆንበት ገበያ እንደወጣ ሸማች በእውነታ ላይ ትኩረት አጥቶ የሚመላለሰውን ሁሉ በአንድ ታሪክ አማካኝነት ቀልጦ እንዲያያዝ ያደርገዋል። አንዴ አንብቦ ከደነገጠበት በኋላ እድሜ ዘመኑን እውነታን የሚተረጉመው ከዛ አጭር ታሪክ አንፃር ይሆናል። ደማቅ ታሪክ በቀላሉ አይገኝም።
የአጭር ልብ ወለድ ሃይለኛ የመምረጥ አቅሙ የተመሰከረለት ነው። ስለዚህም፣ ከየትኛውም አይነት የስድ ፅሁፍ ዝርያ፣ ቁጥብ እና የሚመርጠውንም በጥንቃቄ ሳያዝረከርክ ለግቡ የሚያውል ብልሃተኛ ተራኪ ያደርገዋል። ምናልባትም፣ ከግጥም በስተቀር በመምረጥ እና በመጭመቅ አቅም ሌላ የሚስተካከለው የለም።
ግጭት የትኛውንም ሴራ የሚነዳው ሃይል ነው። ደራሲው ከመረጠው ግጭት እና ከገፀባህሪዎቹ ሳይማከር ሴራውን ወዳሰኘው፣ እንዳሰኘው የሚጠመዝዘው የመጫወቻ መሪ ነገር አይደለም።
“አይመስልም” ለሚል ጥርጣሬ በፍፁም በር ከፍቶ ሳይሰጥ፣ መሰልቸት እና የትኩረት ማጣትን ሳያመጣ፣ ሳይዝረከረክ፣ ለፍፃሜ ሳይቸኩል፣ በገለፃ ብዛት አንባቢ እና ድርሰቱን ሳያደክም፣ በነባራዊው አለም ላይ የሚታወቀውን እውነት የታከከ መስሎ፣ የራሱን አሳማኝ ድምዳሜ ለመፍጠር እንቆቅልሽን ፈጥሮ፣ ወይንም ቀድሞ የተፈጠረውን አንስቶ የፈታ መስሎ፣ በሃሳብ እና ስሜት እየተከተለ የሚነጉደውን አንባቢና አድማጭ ልብ የማሰር ሂደት ነው።
ከህይወት የተገኘ ህይወት ነው። ከእውነታ የነፀረ እውነት። ልብ ወለዱ በፊደል ላልፈጠረው ተጨባጩ የአለም እና የህይወት እንቆቅልሽ ታማኝ ሆኖ፣ የእውነታን ትርጉም ወደ አስፈለገው አመለካከት የመምራት አቅም አለው። ታሪክ መስሎ ፍልስፍናን ሊያስተምር ወይም ሊያምታታ ይችላል። ሃይማኖትን ሊሰብክ ወይንም ሊያስክድ ይችላል። ነገር ግን ይሄንን ለማድረግ ሆነ ብሎ ወጥቶ አይደለም።
ውበት ለመዝራት ወጥቶ አብሮ እምነትን ሊያሳጭድ ይችላል። ተራ ተረት መስሎ የማይደፈረውን በድፍረት ይመረምራል። ሚዛን ይመዝናል። ፈጠራ ነኝ ብሎ ከእውነትም በላይ ይሆናል። በአጭር ቆይታ እና በአጭር ታሪክ በሰው ትዝታ ላይ እንዳይረሳ ሆኖ እንደ ንቅሳት ይቀመጣል። ይኼም ከተራነት ወደ ውበትነት ደምቆ በበሰለ ጊዜ ብቻ የሚሆን ነው። የተዋጣለት ጥበብ በባህሪው እንደዛ ነውና!
¤¤¤
በዚህ የትርጉም መድብል ላይ ከወንጀል ታሪክ ጀምሮ እስከ ማጂካል ሪያሊዝም ተካተዋል። አንዱን የደራሲ ዘይቤ እና የታሪኩን ምርጫ ከሌላኛው ጋር ማመሳሰል አይቻልም። ከተቻለም በዚህ መድብል ውስጥ ተሰብስበው መገኘታቸው ብቻ ነው የሚያመሳስላቸው። እና በዚህ ተርጓሚ ፍላጎት መመረጣቸው። ግን “በአቦ ሰጡኝ” የተመረጡም አይደሉም፡፡ ቀድሞውንም ደምቀው የወጡ ደራሲዎችና ድርሰቶች ናቸው፡፡
ከምዕራብ እስከ ቅርብ ምስራቅ እና አፍሪካ የተገኙ ናቸው፡፡ ቢሆንም “ስብጥር” ለማሟላት ታስበው አልመጡም፡፡ ደግሞም መረሳት የለበትም ቋንቋው እንደሚወስነን። ምርጫ እንደሚወስነን። ወደ እንግሊዝኛ ባህር ገብተው ያገኘሁዋቸውን እና በእኔ መንጠቆ ላይ የተጣበቁትን ነው ያጠመድኳቸው። መንጠቆው እኔን እኔን ይላል፣ ባህሩ የእንግሊዘኛ ቋንቋን እና ተናጋሪዎቹን።
የመረጥኩት ዘመን ለዘመናዊ አጭር ልብ ወለድ ምርጥ ነበር ብዬ የማስበውን ነው። ይኼም ለአጭር ልብ ወለድ ማበብ ጉልህ አስተዋፅኦ ያደረገው የጋዜጣ ዘመን ነው።
በአንድ መድበል ሁሉንም ዋና ዋና “ደማቆች” ላካትት አልቻልኩም። አልሞከርኩም። ብሞክርም አይቻልም፡፡ ይኼም መጨረሻ ላይ በተርጓሚው ምርጫ የተቀናበረ መሆኑ የፈጠራ ባህሪ አለው። ለእኔ ቅርብ የሆኑትን ነው የመረጥኩት። ለእኔ ቅርብ የሆኑ ማለት እኔ የወደድኳቸው ማለትም ነው። ለማምጣት እኔን የተመቹኝን። ሌሎች ደማቆች አሉ። “እግዚአብሄር ቢፈቅድ እና ብንኖር” ሌሎቹንም እናመጣቸዋለን።
(”ደማቆቹ” ከተሰኘ ዛሬ የሚወጣ አዲስ የጸሃፊው መድበል የተወሰደ)

Read 572 times