ዶናልድ ሆል የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ፣ንባብን በተመለከተ በተለያዩ ዘውጎች ሸንሽነው በየራሳቸው ጎጥ ያስቀምጧቸዋል። ታዲያ እንደ እርሳቸው አባባል፤ ሁሉም ዐይነት ንባባት አንድ ዐይነት አይደሉም። እንደየ ዘውጋቸው ማጣጣም፣ አጽንኦትና ትኩረት መስጠት ይጠይቃሉ። ለምሳሌ ያህል ፍልስፍናን ነጠል አድርገው በዝግታ የሚመነዠግና የሚጣጣም እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ከየምድባቸው የሚጠይቁት ጥንቃቄም መጠበቅ እንደዚሁ ሳያዳልጠን ጠንቅቀን የምንራመድበት ጎዳና እንደሆነ ሳይጠቁሙ አያልፉም።
እኔም የዛሬው ንባቤና የጭብጤ ትኩረት እስካሁን ከነካኋቸውና ካየኋቸው የጥበብ ሥራዎች፣ የግጥም ዜማና ስልቶች ዐይነት አይደሉም። ሕይወታችንን ጀርባ ልጠው የገረፉ፣ገና የወደፊት የሕይወት ጉዟችንና ግባችን ላይ ዐይናቸውን ያፈጠጡ ዘላለማዊ ትርጓሜዎችና ሽሽግ ሕልሞች ነው። መነሻዬና መድረሻዬም በቅርቡ የታተመውና “ከግዙፉ ማታለል ጀርባ ያለው እውነት” በሚል ርዕስ ሻሎም ዓለማየሁ በተባሉ ጸሐፊ የተጻፈው መጽሐፍ ነው።
መጽሐፉን ቀደም ብዬ ባየውም፣አጀማመሩ ላይ አስደናቂ፣አስደንጋጭና ፈታኝ ሁነቶችና ቀጣይ መንፈሳዊ ትንበያዎች ይኖራሉ ብዬ አልገመትኩም። በተለይ የመጽሐፉ መነሻ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፈ ሔኖክ በመሆኑ ከጥናቶችና የፖለቲካው ዐለም ሀዲድ ላይ ፉርጓቸውን ያግተለትላሉ ብዬ አላሰብኩም ነበር። በኋላ ግን ገጹ እየጨመረ ሲሄድ የማነብበው ነገር እያስገረመኝ፣እያስደነቀኝና እያስፈራኝም መጣ።
ነገሩን እንደዋዛ እንዳላየውም፣በዚህ ምድር ላይ፣በሆነ ሀገር፣በሆነ ጊዜ ተወልደው ኖረው፣ጥናት አጥንተው፣አንዳንዶቹም ቡድን መሥረተው የነበሩ ሰዎች መሆናቸውን ስገነዘብ፣ መቋጫ በሌለው መገረም ውስጥ ገባሁ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕውቀቴ ያን ያህል የጠነነ ባይሆንም፣ የተወሰኑትን መጻሕፍት የማነብበት፣የዳራና የዐውድ ልየታ ጭላንጭል አለኝ ብዬ ስለምገምት ፍተሻዬን በግርምት ቀጠልኩ።
መጽሐፉ መሠረት ያደረገው ከእግዚአብሔር መገኛ ራሳቸውን ያገለሉ መላዕክት ከሰዎች ልጆች ጋር የተዳቀሉበትንና ወደ ዐመጻ ግባቸው ለመድረስ የሄዱባቸውን መንገዶችና ረቂቅ ስልቶች ነው። ይህንን የረቀቀ ሥራ ሲሠሩም መናፍስቱ ብቻቸውን ሳይሆን በምድር ላይ ባሉ የሰው ልጆች፣ተቋማትና የፖለቲካ መሪዎች በመጠቀም ነበር። ታዲያ የመጽሐፉ ደራሲ፣እነዚህ ከምድራችን ውጭ ያሉና ራሳቸውን ከሰው ልጆች ጋር ያዳቀሉ ፍጡራን (አልያንስ)ከሰው ልጆች ጋር የብዙ ሺህ ዐመታት ግንኙነትና ታሪክ ያላቸው መሆናቸውን ጉዳዩን በሚመለከት ሠፊ ጥናት ያጠኑትን ዘካርያስ ሲችንና ጓዶቻቸውን ዋቢ አድርገው ያስረዳሉ። ለዚህም ማስረጃው ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ሳይሆኑ፣ከሺህ ዐመታት በፊት እንደተጻፉ የሚታመኑት የድንጋይ ላይ ጽሑፎችም ናቸው።
በመጽሐፉ ውስጥ እንደተጠቀሰው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ በይሁዳ መልዕክት ላይ “መኖሪያቸውንም የተውትን” የሚለውን ሀሳብ የጠቀሰው በብዙዎች ዘንድ የሚታመነውና በኢትዮጵያ ገዳማት በግዕዝ ቋንቋ ተጽፎ በ1773 በጀምስ ብሩስ አማካይነት ከተገኘውና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀምበት 81 አሐዱ ውስጥ የተካተተው የሄኖክ መጽሐፍ በዝርዝር ሁኔታ አስቀምጦታል። በዚህም መሠረት፣ ከሰማይ የወረዱት መላዕክት ቁጥራቸው 200 ሲሆን፤ ኤርሞን በሚባል ተራራ እንደሰፈሩ፣ዋና ዐላማቸውም ከሴት ልጆች ጋር መዳቀል ነው።
መጽሐፉ ገጽ 30 ላይ በቀጥታ ከመጽሐፈ ሄኖክ ምዕራፍ 2 ቁጥር 1-23 ላይ፦
“የሰው ልጆች ከበዙ በኋላ እንዲህ ሆነ። በእነዚያ ወራት መልከ መልካሞችና ደመ-ግቡዎች ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው። የሰማይ ልጆች መላዕክትም እነሱን አይተው ወደዷቸው። እርስ በእርሳቸውም “ኑ ለእኛ ከሰው ልጆች ሴቶችን እንመረጥ፥ለእኛም ልጆችን እንውለድ” አሉ። አለቃቸው የሆነ ስማዝያ “እኔስ ይህ ሥራ ይሠራ ዘንድ ምናልባት አትውደዱ እንደሆነ እፈራለሁ። የዚህችም ታላቅ ኃጢአት ፍዳ ተቀባይ እኔ ብቻ እሆናለሁ።” አላቸው።
እንግዲህ በመጽሐፉ ውስጥ ለሚታዩትና አሁን በዐለማችን ላይ ላሉ ቀውሶች ምክንያት ናቸው የሚባሉት እነዚህ በጥቂቱ ያየናቸው አማጺ መላዕክትና ከእነርሱ ጋር የተዳቀሉ የሰው ልጆች ናቸው። እነዚህ ከሰው ልጆች ጋር የተዳቀሉ ፍጡራን፣ አሁን አሁን ተልዕኳቸውን ለመፈጸም በየተቋማቱ መሰግሰጋቸውን መጽሐፉ ይናገራል። መጽሐፉም ፎቶግራፋቸውን ዋቢ በማድረግ ከሌላ ዐለም ከመጡ ፍጡራን ጋር ግንኙነት አድርገው የወለዷቸውን ልጆች ይዘው ወደ አደባባይ ብቅ ያሉት እናቶች የሚያሳዩትን ምስል ፣በተጨማሪም ባደጉ ሀገራት ካሉ ተቋማት ጋር ያደረጉትን ስምምነትና ውል በማስረጃ አስደግፎ አስቀምጧል። በተለይ በአሜሪካ ከፕሬዚዳንቶች ጋር ሳይቀር በአካል መገናኘታቸውን የሚያሳዩ ሰነዶች ተገኝተዋል።
በዐለማችን የባንክና ፋይናንስ ተቋማትን የተቆጣጠሩት የሮዝ ቻይልድ ቤተሰቦች ሚና፣ ከተለያዩ ሁነቶችና ዐለም አቀፍ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የእጃቸውን ርዝመት ያሳያሉ። እነዚህ ቤተሰቦች የፌደራል ሪዘርቭ ሲስተምን ጨምሮ የአሜሪካ ተቋም ውልድ የሆኑትን የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት(IMF)በማቋቋምና ከአሜሪካ መንግሥትና አለፍ ሲልም ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ይልቅ ሌሎች ከበርቴዎች እንዲዘውሩት የሚያደርጉና በታዳጊ ሀገራት ላይ እንደፈቃዳቸው ጠንካራ ጫና የሚፈጥሩ ናቸው።
ይህ ቤተሰባዊ ቡድን ላይ የተንጠለጠለ ተቋም፣ ተጽዕኖው ከፍ ያለና ለአሜሪካ መንግሥት ጭምር ዶላር በማተም በወለድ እስከማበደር የዘለቀ አቅም ያለው ነው። ምሥረታው በ1913 ዓ.ም በአሜሪካ ተፈጥሮ የነበረውን ቀውስ ለመፍታት ቢሆንም፣ ወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዋዜማ በመሆኑ ሥልጣናቸውን ይዘው ተቋሙን በመደገፍ ፊርማቸውን ለማኖር ለተስማሙት ተወዳዳሪና 28ኛው ፕሬዚዳንት ውድሮ ዊድሰን ለውድድሩ የሚያስፈልጋቸውን ሙሉ ወጭ በመሸፈኑ ከምርጫው በኋላ ሥልጣን በጨበጡት ፕሬዚዳንት ሁኔታዎች ተመቻችተውለታል። ይህም ሁነት ተቋሙ እስከዛሬ ለሚፈጽማቸው ተግባራት በሁለት እግሮቹ የቆመበት ወሳኝ ምዕራፍ ነበር። ከጎኑም በሌላ ክንፍ በውጭ ጉዳዮች ዐለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለሆነው መሠል ተቋም መፈጠር አሜሪካዊው ከበርቴ ሮክፌለርም ነበሩበት።
የዳሰሳዬ መነሻ የሆነው መጽሐፍ ዐቢይ ርዕሰ ጉዳይ የሆኑት ከሰው ልጆች መኖሪያ ውጭ ያሉ ፍጥረታት(ኤሊዬንስ) ዐለማችን ላይ ከፍተኛ ቀውስ በፈጠሩት ሁለቱ የዐለም ጦርነቶች እጃቸው እንዳለበት መጽሐፉ ጠቅሶ፣በተለያዩ ጊዜያት ከሰው ልጆች ጋር ካደረጓቸው ስምምነቶች አንዱ ከጀርመኑ ናዚ ጋር ያደረጉት መሆኑን ይጠቅሳል። በዚህም ጀርመኖች በወቅቱ ከዘመኑ የቴክኖሎጂ አቅም በላይ የሆኑና የላቁ የጦር መሳሪያ ንድፎችን በቀጥታ ማርያ ኦርሲክ(Marib Orsic) በተባለች ተወካያቸው በኩል አግኝተዋል።
ይሁንና ጀርመን በመሸነፏ ምክንያት የሶቪየትና የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ባደረጉት አሰሳ በወቅቱ ሁለቱ ሀገራት ከነበራቸው የቴክኖሎጂ አቅም በላይ የሆነ ሥራ የሚሠሩ ሳይንቲስቶች ስለነበሯት ሁለቱ ሀገራት በማባበያ ወደ ሀገራቸው ወስደዋቸዋል። ይህንን መጽሐፉ ገጽ 117 ላይ እንዲህ አስፍሮታል፦
በተለይ አሜሪካ ኦፕሬሽን ፔፐር ክሊፕ በተባለ ዘመቻ እስከ ዛሬ ድረስ የአሜሪካንን ኀያልነት የሚያሳዩ የሳይንስና የምርምር፣ በዋናነት የጦር መሣሪያና ተያያዥ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ባለቤት እንድትሆን ያስቻላት ከ1600 በላይ የናዚ ሳይንቲስቶችን ወደ ሀገሯ በማጓጓዟ እንደሆነ ማስረጃዎች ያሳያሉ።
እነዚህ ከሰው ልጆች ጋር ተዳቅለዋል የተባሉትና በቀጥታና በተዘዋዋሪ በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ተጽዕኖ በማሳደር፣ለቀጣይና ዘላቂ ዐላማቸው በምድር ላይ ካሉ ታላላቅ ሀገራት ጋር በትብብር በላቀ ቴክኖሎጂ ታግዘው ለሚሠሩት ሥራ የተሰጣቸው ሥፍራ የት ነው?..ለሚለው ጥያቄ “ከግዙፉ ማታለል ጀርባ ያለው እውነት” የተሰኘው የሻሎም አለማየሁ መጽሐፍ ያሰፈራቸው መረጃዎች እንደሚሉት፤ በአሜሪካና ከምድራችን ውጭ ባሉ ፍጡራን የጋራ ጥምረት የተለያዩ የምርምር ሥራ እንደሚሠራባቸው ከሚታመነው ሥፍራዎች አንደኛው የአንታርክቲክ የበረዶ ስፍራ ሲሆን፣በዚህ ሥፍራ ከመሬት ውስጥ በተገነባ ዘመናዊ የምርምር ጣቢያ ውስጥ በርካታ የዘረመልና የጦር መሣሪያ፤ እንዲሁም አርቴፊሻል ኢንተለጀንት የሆኑ ከሮቦት እጅግ የላቁና የሰውን ልጆችም በተለይ በወታደራዊ ባህርይ የሚልቁ ተንቀሳቃሽ ፍጡራን ጭምር ያካተተ ሰፋ ያለ የምርምር ሥራ እየተሠራ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህን መረጃ አግኝቻለሁ ባይዋም በምርመራ ጋዜጠኝነቷ፣ በዚሁ ዘርፍ በርካታ ጥናቶችን ያደረገችው ሊንዳ ሞልተን ናት። ሌላኛው በውቅያኖስ ውስጥ የምርምር ሥፍራዎችን እያደራጁ እንደሆነ በምርምር ሥራቸው ለማረጋገጥ የሚጥሩት ጌሪ ሄስተን የተባሉ ተመራማሪ ሲሆኑ፣እኒህ ሰው በእንግሊዝ የትራንስፖርት ፖሊስ ኀላፊነት፣ በአየር ኀይል አባልነት ለ24 ዓመታት ያገለገሉና ከምድራችን ውጭ ስላሉ ፍጡራን የሚያጠና ተቋምን በምክትል ፕሬዚዳንትነት የሚመሩ ናቸው።
የአዲስ ፍጡር ዝግጅት፦
መጸሐፈ ዳንኤል ምዕራፍ 2፥ቁጥር 43
“ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየሁ፥እንዲሁ ከሰው ዘር ጋር ይደባለቃሉ፤...” ይላል።
በተጨባጭ በምድራችን አሁን እንደሚታየው ደግሞ በተለይ በሠለጠኑት ሀገራት/አሜሪካ/በፈቃደኝነት ከምድራችን ውጭ ካሉ ፍጡራን ጋር በማዳቀል ተግባሩ ላይ የተሳተፉ አሜሪካዊ ሴቶች “ልጃችን” የሚሉትን ፍጡር ምስል ይዘው በአደባባይ ታይተዋል። እነዚህ ፍጡራን ለምን ይህንን መዳቀል ፈለጉት ለሚለው መልሱ የሚጀምረው፣ የሰው ልጅ ሆኖ የመጣውን መሲህ ዐላማ ለማሠናከል ከተደረገው ሙከራ ነው። በየዘመኑ ደረጃ በደረጃ የሚፈጽሙት ዐላማና ግብ ቢኖራቸውም፣ አሁን ባለንበት ዘመን በየኢኮኖሚ አውታሩና በመረጃና ደኅንነት ተቋማት ሳይቀር የሰው መሰል ፍጡራንን የአሁን ቁመና ለማምጣትና ከሰው ልጆች ጋር የተመሳሰለ መልክ ለመስጠት ከ50 እስከ 60 ዐመታት ሠርተዋል።
በውጤቱም በበለፀጉት ሀገራት ኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂና ፈጠራ ተቋማት፣በወታደራዊ የምርምር ማዕከላት፣ የስለላ አደረጃጀቶች፣ በፖለቲካና በሃይማኖት ተቋማት ሳይቀር ተሰግስገዋል። በዘመናችን ሥራቸውንና ተግባራቸውን የሚጠቁመው ስያሜያቸውም እንደሚከተለው ይነበባል።
ኤክስትራ ቴሪቴሪያል፦ ከምድራችን ውጭ ያሉ ፍጡራንን በጥቅሉ የሚገልጽ መጠሪያ።
ሬፒቲሊያንስ፦ ከምድራችን ውጭ ካሉ ፍጡራን መሀል የአንዱ መጠሪያ።
ዩፎ፦ ከምድራችን ውጭ ያሉ ፍጡራንና እነርሱ የሚልኳቸውን ፍጡራን የሚያጓጉዙ መሣሪያዎች የወል መጠሪያ።
አብዳክሽን፦ አንድ ግለሰብ ከፈቃዱ ውጭ በማስገደድ የማይፈልገውን ነገር እንዲያደርግ ወይም ወደማይፈልገው ቦታ እንዲሄድ ማድረግንና ካለፈቃዱ የተገደደውን ግለሰብ የሚያመለክት ነው።
ቴሌፓቲክ፦ የምድራችን ሰዎች ከምድራችን ውጭ ካሉ ሰዎች ጋር ቋንቋን ሳይጠቀሙ፣በተመስጦ ውስጥ ሆነው ሀሳብ የሚለዋወጡበት መንገድ ነው።
ቻናሊንግ፦ በምድራችን ያሉ ግለሰቦች ከምድራችን ውጭ ያሉ ፍጡራን የግለሰቦችን አካል በፈቃዳቸው በመጠቀም መልዕክቶችን ለሰዎች የሚያስተላልፉበትን መንገድ የሚያመለክት ነው።
አጠቃላይ በመጽሐፉ የተጠቀሱትን ዐቢይ ጉዳዮች እንኳ ለማንሳት ውስኑ የጋዜጣ ገጽ ስለማይፈቅድ፣አንባቢያን ይህንን የትናንት ውስብስብ ሴራና የመጪውን ዘመን የሰው ልጆች ሥጋት ከመጽሐፉ በማንበብ፣እንደ ደራሲው ገለጻ በተለይ የሥላሴ አማኞች የሆኑት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣የካቶሊክና የወንጌል አማኞች የመጪውን ዘመን ሴራ በንቃት መጠባበቅ የሚገባቸው ጊዜ ላይ የደረሱበት አድማስ ይመስላል።
ከአዘጋጁ፡-
ደራሲና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አያሌ መጣጥፎችን አስነብቧል፡፡ በርካታ የሥነጽሁፍ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ትንተና አቅርቧል፡፡ ደረጀ በላይነህ ገጣሚና አርታኢም ነው፡፡ 12 ያህል መጻሕፍትን አሳትሞ ለአንባቢያን አድርሷል፡፡
Wednesday, 31 July 2024 07:06
“ከታላቁ ማታለል ጀርባ ያለው እውነት”
Written by ደረጀ በላይነህ
Published in
ጥበብ