Saturday, 03 August 2024 21:27

ወንጀል እና ሥልጣን (ማኪቬላዊ አስተምህሮ

Written by  በደረጄ ጥጉ (የአለም አቀፍ ህግ መምህር)
Rate this item
(1 Vote)

ይህ ፅሁፍ መነሻውንና የመርሁን ማጠናከሪያ ምሳሌዎች የወሰደው ከእውቁ የዘመናዊው ፖለቲካ ፍልስፍና ፈር-ቀዳጅ ጣልያንያዊው ፈላስፋ ኒኮሎ ማኪቬሌ ነው፡፡ ማኪቬሌ በወጣትነቱ የተሃድሶ ከተማ  ተብላ የምትጠራው የጣልያኗ ፍሎረንስ ከተማ አስተዳዳሪ ነበር፡፡ በሮም ፖሊቲካ ውስጥ በነበረው ቀጥተኛ ተሳትፎና በአስተዳዳሪነቱ በነበረው ሚና በ1512 እ.ኤ.አ ሎሬንዞ ዲሚዲቺ ዳግም ስልጣኑን ሊይዝ አበቃ፡፡ ከአስተዳዳሪነቱ በመገለሉ በፖለቲካው ውስጥ የነበረው የጎላ ድርሻ ከሰመ፤ ስራ ፈትም ሆነ፡፡ በዚህ የስራ ፈትነት ጊዜው ነው በመጠን ትንሽ በይዘት ግን ትልቅ የሆነችውን The Prince የተሰኘችውን መፅሐፉን የደረሰው፡፡ The Prince ማኪቬሌ ሀሳቡንና ምናቡን ተጠቅሞ አምጦ የወለደው የበኩር ስራው ነው፡፡ መታሰቢያም አድርጎ ለአዲሱ ንጉስ ሎሬንዞ ዲሚዲቺ በስጦታ አበረከተው፡፡ በዚህ ዝነኛ መፅሐፉ ምክንያትና በውስጡም አቅፎ በያዛቸው እንግዳና ባይተዋር  የፍልስፍና ሀሳቦቹ ምክንያት በፍልስፍናው ሰፈር ማኪቬሌ የዘመናዊ ፍልስፍና አባት የሚል የክብር ስምን አቀዳጀው፡፡ ሶቅራጠስ ፍልስፍናን ከሰማይ ወደ ምድር አወረደ እንደሚባለው፣ ማኪቬሌም በፖለቲካና ስነምግባር መሃል ለዘመናት ፀንቶ የቆየውን የትስስር ገመድ በጠሰው፡፡ የማኪቬሌ ንድፈሃሳብና ትወራው ማህበረሰብ ተስማምቶ በተቀበላቸው የስነምግባር እሴቶች ላይ አልቆመም፡፡ ለፖለቲካና የፍልስፍናው አለም አዲስ የሃሳብ መንገድን አስተዋወቀ፡፡ ለዘመናት ጸንቶ በቆየው አስተምህሮ ጥሩ መሪ የሚያስብለው ወሳኙ መለኪያ ጥሩ ምግባርን መላበስ ነው፡፡ ጥሩ መሪ ጥሩ ምግባር እንዲኖረው ይጠበቃል፡፡ የጥሩ ምግባር ባለቤት የሆነም መሪ ከጠቢብ ይቆጠራል፡፡ በማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች ወጥና ሃቀኛ ውሳኔዎችን ይወስናል ተብሎ ይታመናል፡፡ እንዲህ አይነት መሪ የአስተዳደር መሰረቱን የሚጥለው ማህበረሰቡ በተስማማባቸው የሞራል መርሆዎች ላይ ነው፡፡ ለማኪቬሌ ግን ይህ አይነት እምነት በግብሩ ነቢባዊ እንጂ ገቢራዊ አይደለም፡፡ ማኪቬሌ በመፅሐፉ እንዳሰፈረው፤ እሱ በነበረበት ዘመን ሞራሊቲ ተደላድሎ ከተቀመጠበት የሰገነት ወንበር ወርዶ አፈር ከድቼ በልቶ ነበር፡፡ የሮምን ፖለቲካ መርምሮ በደረሰበት ድምዳሜ ሞራሊቲ ምንም ሳይሆን የስልጣን ደንቃራ ነው፡፡ በድምዳሜው ላይ ተመርኩዞ  ነው  በጥሩ ሰውና በጥሩ መሪ መሃል ያለውን ልዩነት ያነፀረው፡፡ ጥሩ መሪ ግዛቱን ለመምራት ጥሩ መሆን አይጠበቅበትም፡፡ በዚህና ይህን በመሰሉት ባይተዋር ሃሳቦቹ የተነሳ ማኪቬሊ በፍልስፍናው መንደር  አዲስ የክርክር ርእስን ለመቀሰቀሰ በቃ፡፡
ለማኪቬሌ የሁሉ ነገር ማጠንጠኛው ፖለቲካ ነው፡፡ ሰውስ በተፈጥሮው ፖለቲካዊ እንስሳ አይደል፡፡ በአስተዳዳሪነቱ ዘመን በቅርበት እንደታዘበው፤የተሃድሶና የጥበብ ከተማ የነበረችው ፍሎረንስ ለስልጣን ባቆበቆቡ ቡድኖች ምክንያት ውበቷ ተገፎ የስልጣን የጦር ቀጠና ሆነች፡፡ በዚህም በጣም ያዝን ነበር፡፡ ለቁጭቱ እልባት ለመስጠት ለፍሎረንስ ያስፈልጋታል ብሎ ያሰበውን ያስተዳደር አይነት ስራዬ ብሎ ማጥናት ጀመረ፡፡ አንድ ከተማ እንዴት በልኡል በጥሩ ሁኔታ መመራት አለባት የሚለውንም በደንብ አጠና፡፡ በዚህ ጥልቅ ጥናቱ  ታግዞ የሚከተለው ድምዳሜ ላይ ደረሰ፤ ፖለቲካ ከሞራሊቲ የላቀ ስፍራ እንዳለውና ፖለቲካና ስነምግባር ትስስር እንደሌላቸው፡፡ ለማኪቬሌ የባህሪ ፀጋ ለመሪው ስኬትን አያጎናፅፈውም፡፡ የስኬት መወጣጫውና መዳረሻው ሃይል ነው፡፡ ልኡላን ስልጣናቸውን የሚያፀኑት የሞራል ሰው በመሆን ሳይሆን፤ ሃያል ሆኖ በመገኘት  ነው፡፡ በዘመኑ እንዲህ አይነት አስተምህሮ ታላቅ የሃሳብ አመፅ ተብሎ ይፈረጃል፡፡ እንደ ማኪቬሌ እምነት፤ ሀይል በፖለቲካ መድረክ ዋናውን ሚና ይጫወታል፡፡ ሀይል (ስልጣን) በራሱ እሴት እስከሆነ ድረስ ከሌሎች የማህበረሰብ እሴቶች የላቀ ዋጋ አለው፡፡ የማኪቬሌ ወርቃማ ህግ ይህ ነው፡፡ በዜጎች ልብ ውስጥ ፍርሃትን መዝራት፡፡ ለአንድ ልኡል ከመወደድ ይልቅ መፈራት ይሻለዋል ይለናል፡፡ ማኪቬሌ የፖለቲካውን እውነት  በቅርበት መረዳቱና በቀጥታ ተሳትፎ የቀሰመው እውቀት የፖለቲካ ፍልስፍናውን የቢሆን ሳይሆን ተጨባጭና እውናዊ አደረገለት፡፡ የሮምን የፖለቲካ ታሪክ በሚገባ መርምሮና መዝኖ ያሰናደው ግሩም ድርሳን በመሆኑ የፖለቲካን ሀሁ ለቀሰመ ድርሳኑ ውስጥ የሰፈሩት መርሆዎችና ስልቶች ተጨባጭ መሆናቸውን ይረዳል፡፡ መነሻውን እውነት ላይ በማድረጉ የሃሳቦቹ እውነተኛነትና ተግባራዊነት ላቅ ያሉ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ ድንበር ሳይገድበው የፖለቲካውን አለም ጠልፎ የመጣል ዘዴና የወንጀልና የሸርን ውስብስብ መልክ በማሳየቱ በፖለቲከኞችና በፍልስፍናው አለም ሰዎች ዘንድ እንደ አንድ ቅዱስ መፅሐፍ ሲጠቀስ ይኖራል፡፡ ምፀት ቢመስልም ስልጣንን አልሞ የሚፋለም ፖለቲካኛና የፖለቲካ ቡድን በሙሉ የትግል እንቅፋት ነው ብለው ስለሚያምኑ  በትግል ወቅት የሚያወግዙትና የሚነቅፉት መፅሐፍ  ቢሆንም፣ ድል ቀንቷዋቸው ስልጣንን ሲጨብጡ ግን ካለበት አድነው  እንደ ቅዱስ መመሪያ መፅሐፍ  የሚያነቡት ድርሳናቸው ያደርጉታል፡፡ ማኪቬሊ በመፅሐፉ ያስተላለፈው መልእክት በአጭሩ፤ አንዴ በእጅ የገባ ስልጣን እንዴት ፀንቶ መቆየት እንዳለበትና በምንም መንገድ መታጣት እንደሌለበት ነው፡፡ ታጋዮችን እርር ድብን የሚያደርጋቸው ዋናው ምክንያትም ይህ ነው፡፡
የፖለቲካ ስልጣን በተለያዩ መንገዶች በእጅ ይገባል፡፡ በደም ውርስ፤ በግልበጣ፤ በንግርት፤ በብልጠትና ጀግንነት፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዋና ትኩረት ወንጀል በመፈፀም ስልጣን እንዴት ይያዛል የሚለው ነው፡፡ እንግዳ ቢመስልም ወንጀልን ፈፅሞ የስልጣን ካባን መጎናፀፍ ይቻላል፡፡ በአለም ላይ ሆኖ ያየነውም በአብዛኛው ከዚህ እውነት የራቀ አይደለም፡፡ ከጥንት እስካሁን ባለው ዘመናዊ አለም ከእያንዳንዱ የስልጣን ወንበር ጀርባ አንድ አይነት ወንጀል አለ፡፡ በአፍሪካ፤ በላቲን አሜሪካ በእስያና በተወሰኑ የአውሮፓ ክፍሎች መሪዎች ስልጣን ላይ የወጡት በምርጫና በህዝባዊ ቅቡልነት ሳይሆን ወንጀልን ፈፅመው ነው፡፡ ወይ ይገድላሉ ካልሆነም መፈንቅለ መንግስት ያደርጋሉ፡፡ ወይም ሁለቱን፡፡ እንደ ማኪቬሊ እምነት፤ ይህ ስልት ከእጣ ፋንታ (ንግርት) ጋር ምንም አይነት የሃሳብ ዝምድና የለውም፡፡ እጣ ፋንታ ሌላ፣ በወንጀል ታግዞ ስልጣን መጨበጥ ሌላ፡፡ ወንጀል በማሕበረሰብ እሴት መነፅር ሲታይ ኢ-ሞራላዊ ቢሆንም፣ እንደ ማኪቬሊ እምነት ግን የራሱ ፀጋዎች አሉት፡፡ እነዚህን ፀጋዎች ወረድ ብለን እናገኛቸዋለን፡፡
ማኪቬሌ ስልጣንን በወንጀል ድርጊት ታግዞ መያዝ የሚለውን ስልት በሁለት ጠንካራ ምሳሌዎች ያብራራዋል፡፡ አስረጅ ምሳሌዎቹ የተገኙት ከጥንትና ከዘመናዊው የሮም የፖለቲካ አለም እውነት ነው፡፡ ሮም መቼም በእንዲህ አይነት ምሳሌዎች የታደለች ነች፡፡ ጠልፎ መጣልና ጭካኔ በነሱ ልክ የተሰፋ ነው የሚመስለው፡፡ ማኪቬሌ ሮማዊ ነውና ምሳሌዎቹን የሚያቀብለን ከዛው ካደገበት የሮም የፖለቲካ ባሕል ነው፡፡ በመፅሐፉ እንዳሰፈረው፤ ምሳሌዎቹ በራሳቸው በቂና ገላጭ ስለሆኑ ስለ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ገፃቸው ማብራሪያ በመስጠት ጊዜውንና የአንባቢን ህሊና ማሰልቸት አልፈለገም፡፡ አንባቢ ለራሱ አንብቦና አገናዝቦ የራሱን ፍርድ ይስጥ ነው የሚለን፡፡
በሮማውያን ዘንድ ወጣቱ ሲሲሊያዊው አጋቶክለስ የሚታወቀው በተራ ሰውነቱ ብቻ ሳይሆን ከዝቅተኛው የማህበረስብ መደብ የተገኘ በመሆኑም ጭምር ነው፡፡ አባቱ የታወቀ ሸክላ ሰሪ፤  እናቱ የቤት እመቤት ነበሩ፡፡ እራሱን አምጦ ለንግስና እስኪያበቃ ድረስ ከድህነት ጋር አብሮ ኖረ፡፡ ንጉስ ኃይለስላሴ፤ ከታላቅ ወይ ከታናሽ መወለድ ቁም ነገር አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ ራስን ለታላቅ ቁምነገር መውለድ ነው እንዳሉት፣ አጋቶክልስም እራሱን አምጦ ወለደ፡፡
አጋቶክልስ የተዛባውንና ኋላቀሩን የባህል አመለካከት ጥሶ ራሱን ለታላቅ ስልጣን ለማብቃት ቻለ፡፡ ከአመታት በኋላ ለሚኖርባት የሲራክስ ግዛት ንጉስ ለመሆንም በቃ፡፡ በሮም ፖለቲካ ላይ ባሳደረው ተፅእኖ  በሮማውያን ዘንድ ትልቅ የፖለቲካ ምሳሌ ሆኖ ለመጠቀስም ቻለ፡፡ ይህ የሸክላ ሰሪ ልጅ ለስልጣን ባደረገው ጉዞ ነውጠኛነቱ ወንጀለኛነቱ ጎልቶ ይጠቀሳል፡፡ ባህሪውና ሲያደርግ የነበራቸው ድርጊቶቹ በሙሉ በወንጀለኛነት ስሙን በደማቁ ፃፉት፡፡ የአካል ብቃቱን ያጎለበተበት ስፖርት ወዳድነቱ በወንጀል ታግዞ ድል አድራጊ እንዲሆን እንዳስቻለው ይጠቀስለታል፡፡ በአካል ብቃቱ ላይ ጭራሽ ፍርሃት የሚባል የማይነካካው መሆኑ ቀስበቀስ በወታደራዊውና ፖለቲካዊው መስክ ሥልጣንን በቀላሉ እንዲጨብጥ   አገዘው፡፡
የንግስና መንበር ላይ ጉብ ከማለቱ በፊት እራሱንና ባሕሪውን በመከላከያ ውስጥ በመሳተፍ ሞረደው፡፡ ጀግና በዛም ላይ ሃይለኛ በራስ መተማመን የተጎናፀፈ ወታደር ነበርና ወታደራዊ  አዣዡ የሲራከስ አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመው፡፡ አጋቶክለስ ግን በትንሽ ስልጣን ውስጡ የሚረካ አልነበረምና ላቅ ያለውን ስልጣን መመኘት ጀመረ፡፡ እራሱን ማንገስ፡፡ የሚገርመው ነገር ይህን የልቡን መሻት ለማንም ትንፍሽ አላለም፡፡ በውስጡ ሰውሮ ያዘው፡፡ በዚህን ጊዜ ብቸኛ ምኞቱ የነበረው የግዛቷ ሃያል መስፍን መሆን ነበር፡፡ በወታደራዊ አዣዡ የተሠጠው የግዛት አስተዳዳሪነት ሹመት አስተማማኝ እንዳልሆን ስላመነ ስውር አላማውን ከሌሎች ሰውሮ በጉልበቱና በሃይሉ ሊያፀናው ፈለገ፡፡ መሾምን ሳይሆን እራሱን በራሱ ያነገሰ መስፍን መሆን ነበር የፈለገው፡፡ በፖለቲካ ውስጥ ውለታና ይሉኝታ አደገኛ የውድቀት ወጥመዶች እንደሆኑ ከተግባር የተረዳ ሰው ነበር፡፡ ብልህ ከሌላ ሰው ውድቀት ይማራል እንደሚባለው እሱም ይህን ከሌሎች ውድቀት ተምሯል፡፡ የዋህ በመሆን ከተሞኙት አንዱ መሆን እንደሌለበት ለራሱ በሚገባ አስገነዘበ፡፡ ውለታና ይሉኝታ የተባሉትን የሰው ባህሪዎች ከራሱ አራቀ፡፡ አጋቶክለስ ይሉኝታ ሲያልፍም የሚነካካው አልነበረም፡፡ ከፊቱ ለሚጠብቀው የስልጣን ፍልሚያ  የሚያስፈልጉ ስልቶችን ጠንቅቆ ለየ፤ ለዛም በሚገባ ተዘጋጀ፡፡ ድል ማድረግና አሸናፊ ሆኖ መወጣት ጓድን መግደል የሚጠይቅ ቢሆን እንኳን ማስወገድ እንዳለበት በደንብ ተረዳ፡፡ ተጠቀመበትም፡፡ በስልጣን ጉዳይ ሁለቴ ማሰብ እራስ ላይ አደጋ መጥራት ነው፡፡ አጋቶክለስ የመጨረሻ ዝግጅቱን መልክ ካስያዘ በኋላ ይህን የህይወቱን የመጨረሻ ግብ ለብቸኛ ወዳጁ የካርቴዢያው ሀሚልካር ሹክ አለው፡፡ ሁለቱ የጦር መሪዎች በተለያዩ የጦር አውዶች አብረው ተካፍለዋል፡፡ በመጨረሻም በሲሲሊ በተደረገ ውጊያ ሀሚልካር ከሚመራው ጦር ጋር ሆኖ አጋቶክልስን አጅቦታል፡፡ በብዙም ረድቶታል፡፡ የልብ ወዳጅም ነበሩ፡፡
አጋቶክለስ በአንድ ማለዳ  የሲራከስን ህዝብ፤  ወታደራዊ አዛዡንና የሴኔት አባላትን ለአንድ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራቸው፡፡ ህዝቡም ሴናተሮቹም ጥሪውን ተቀብለው በማለዳ በስብሰባው ቦታ ተገኙ፡፡ የስብሰባው ጉዳይ ቀድሞ አልተገለጸም ነበርና የህዝቡም የሴናተሮቹም ግምት የነበረው አጋቶክለስ በማለዳ ለስብሰባ የፈለጋቸው ለአንድ አንገብጋቢ ለሆነና የመንግስታቸውን አስተዳደር ለተመለከት ጉዳይ ምክክር ለማድረግ ነበር፡፡ ጉዳዩ ግን እነሱ እንደገመቱት ሳይሆን ሌላ ነበር፡፡ የስብሰባውን አስፈጊነት ከራሱ ከአጋቶክለስ በቀር ማንም አያውቀውም፡፡ እቅዱ ምንም ሳይሆን አጋቶክልስ ቀድሞ ተዘጋጅቶበት በነበረው የማጥፋት እቅዱ ሴናተሮቹንና የከተማዋን ቁልፍ ሰዎች ማስወገድ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ለወታደሮቹ የአይን ጥቅሻ ምልክት ሲሰጣቸውና  የሴናተሮቹና የግዛቲቱ ባለፀጋዎች  ሲረሸኑ አንድ ሆነ፡፡ እነሱን በዚህ አይነት አረመኔያዊ መንገድ ካስወገደ በኋላ የግዛቲቱን አጠቃላይ የማስተዳደር ሃላፊነት የራሱ አደረገ፡፡ እራሱን በራሱ ለንግስና አበቃ፡፡ ከዚህ በኋላ አጋቶክለስ እራሱ መንግስት ሆነ፡፡ ጨካኝና አረመኔ መሆኑን ሁሉም ያውቅ ነበርና ቅሬታም ሆነ ተቃውሞን በግልፅ ለማሰማት የደፈረ አንድ እንኳን አልነበረም፡፡ በፍርሃት ቆፈን ተይዘው ምንም አይነት ውስጣዊ ተቃውሞ ሳያደርጉ ለተወሰኑ አመታት በፍፁም ታዣዥነት በአገዛዙ ስር ኖሩ፡፡  በዜጎች ልብ ውስጥ የፍርሃት ክብሪት ለኮሰ፡፡ በዜጎች ልብ ውስጥ ፍርሃት ስር ሰደደ፡፡ ዜጎች ከፈሩህ ይከተሉሃልም፤ይታዘዙምሀል ይለናል ማኪቬሌ፡፡ ሰውን አንድ አድርጎ ህግን እንዲከተሉ የሚያደርጋቸው ፍቅር ሳይሆን፤ ዜጎች በውስጣቸው የሚያድርባቸው ቅጣትን የመፍራት ስጋት ነው፡፡ ስለዚህ ሳይወዱ በግድ ህግን መጣስ ይፈራሉ፡፡ በፍርሃት ሸብቦ መግዛት ቢችልም ከተወሰኑ አመታት በኋላ ግን ሁለት ያልተሳኩ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች ተደረጉ፡፡ ተሳታፊና ተባባሪዎች  ናቸው ያላቸውን በታወቀበት የማስወገድ ስልቱ ያለርህራሄ ጨፈጨፋቸው፡፡ ተቃውሞውን በጭካኔው አበረደው፡፡ ንጉስ ማድረግ የሚገባው ስልጣኑን የሚያፀኑለትን ብቻ መሆን አለበት፡፡ በጭካኔው የጨበጠውን ስልጣን አፀናው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ከራስ በላይ ንፋስ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ያለስጋት በስልጣን ላይ መሰንበት ነው፡፡ አጋቶክለስም ያደረገው ይህንን ነው፡፡ ይህንን ግርግር ሽፋን አድርጎ ከተማዋን ከተደቀነባት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አደጋ ለመከላከል ብቻ ሳይሆን  የተወሰኑትን ታማኝ ወታደሮች ከተማዋን በንቃት እንዲጠብቁ ትእዛዝ ሰጥቶ በቀረው ጦር የአፍሪካን ሰሜኑን ክፍል ወረረ፡፡ ከተማዋን ከተደቀነባት ከበባ ቢያድናትም ህዝቡን ግን ለአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ዳረገው፡፡ መከራን በህዝብ ላይ መጫን ሌላኛው መላ ነው፡፡ አይተው የማያውቁትን ፍዳ አዩ፡፡ በዚህን ጊዜ እሱ ብቻ ለሚያውቀው ግብ ህዝቡ ከእሱ ጋር አንድ አይነት ውል እንዲፈፅም አደረገው፡፡ ህዝቡ አጋቶክልስ ወደተቆጣጠራቸው የሰሜን አፍሪካ ክፍሎች እንዲዛወሩና ሲሲሊን ለእሱ እንዲለቁለት አደረጋቸው፡፡ ከተማዋን ለእሱ ትተው ከመከራ ለመሸሽ ተሰደዱ፡፡ ሲሲሊን የግሉ ርስት አደረጋት፡፡ አደጋን ያለ ፍርሃት የመጋፈጥ ችሎታው፤ በቀላላ ድል የማድረግ ጥበብና የአላማ ፅናት አጋቶክልስን ከማንም የበላይ ሆኖ እንዲወጣ አደረገው፡፡
በእኛም ሀገር የአጋቶክለስን ድርጊት የሚያስንቅ የጭካኔና የወንጀል ድርጊት በ1960ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በመንግስቱ ኃይለማርያም ተፈፅሟል፡፡ ከነበረኝ ስልጣን እየተንሸራተትኩ ከጨዋታ ውጪ እሆናለሁ ብሎ ያሰበው መንግስቱ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢነት ስልጣኑን ተጠቅሞ ሚኒስትሮቹንና የቢሮ ሀላፊዎችን የእድገት በህብረት ዘመቻን ለተመለከተ ጉዳይ ስብሰባ ጠራቸው፡፡ በዚህን ጊዜ መንግስቱ የነበረው ብቸኛ ስልጣን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢነት ነበር፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውም የማይመለከታቸውም  ሁሉም በቤተመንግስቱ ወደሚገኘው የመሰብሰቢያ አዳራሽ አቅንተው ስብሰባውን መታደም ጀመሩ፡፡ ስብሰባው ከመጀመሩ አፍታም ሳይቆይ መንግስቱ ጎን የተቀመጠው ስልክ ጠራ፡፡ መንግስቱ አነሳው፡፡ ስልኩን ወዲያ ዘጋው፡፡ ስልኩ ከጎንደር ነው፤ጎንደር አንድ አስቸኳይ አሳሳቢ ጉዳይ ተከስቷል እናንተ ቀጥሉ ብሎ ከስብሰባው አዳራሽ ወጣ፡፡ አምስት ደቂቃ ሳይሞላ የታጠቁ ወታደሮች ጠመንጃዎቻቸውን እንደወደሩ በሮቹን በርግደው ገቡ፡፡ ተሰብሳቢዎቹን እጅ ወደ ላይ አሏቸው፡፡ ይህን በጣም ረቂቅ የሆነ ስልት ያዘጋጀው መንግስቱ እራሱ ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር በቃልኪዳን ላንከዳዳ ተማምለናል ካላቸው ጓዶቹ ሁሉ ሰውሮት ነበር፡፡ የደርጉ ሊቀመንበር የነበሩትን ተፈሪ በንቲ ጨምሮ የደርጉ ዋና ዋና የነበሩትን እነ አለማየሁ ሃይሌንና ሞገስ ወልደሚካኤልን ጨምሮ ብዙዎች ተረሸኑ፡፡ ከዛም ዝነኛ የሆነውን ለምሳ ሲያስቡን ቁርስ አደረግናቸው የተባለውን ቀረርቶ በሬድዮ አስነዛ፡፡ የሃገራችን በደም የታጀበ ጉዞም በዛው ቀጠለ፡፡ መንግስቱም ያለማንም ተቀናቃኝ የሀገሪቱ ብቸኛ መሪ ለመሆን በቃ፡፡ መቶ ሃያ የነበሩት የደርግ አባላት ቀስ በቀስ ከፖለቲካው መድረክ ገለል ከተደረጉ በኋላ ደርግ ለስሙ ያህል ይጠራ እንጂ ደርግ በህይወት አልነበረም፡፡ የነበረው ፈላጭ ቆራጩ መንግስቱ ነበር፡፡ ይህን ማኪቬላዊ አስተምህሮ በደንብ ተጠቅሞበታል፡፡ ይደንቃል፡፡
የአጋቶክለስንና የኛውን መንግስቱ ድርጊትና ወደ ስልጣን ባደረጉት ጉዞ ላይ ለስልጣን ይረዱኛል ብለው የተከተሏቸውን ስልቶች በጥልቀት ለመረመረ፣ አጋቶክልስም መንግስቱም  ስልጣን ለመጨበጥ የበቁት በትንግርት እንዳልሆነ ይረዳል፡፡ ወደ ስልጣን ባደረጉት ጉዞ ወታደራዊ ክፍሉ በብዙ አግዟቸዋል፡፡ በተለይም አፋጣኝና ድንገተኛ የሆኑ እርምጃዎች በመውሰድ፡፡ የሁለቱም የስልጣን መንገድ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ከፊታቸው የተደቀኑትን ተግዳሮቶች በሚያስደንቅ ስልት አለፏቸው፡፡ ፈተናዎቹን በድል ተወጡ፡፡ እነዚህን መሰናክሎች አልፈው ነው ሁለቱም ስልጣንን በእጃቸው ያስገቡት፡፡ ወንጀልና ጥበብ ህብረት ፈጥረው በብዙ አገዙዋቸው፡፡ ስልጣናቸውም የፀናው በፈፀሟቸው የጭካኔ እርምጃዎች ነው፡፡ ንፁሃንን መግደል፤ወዳጆችን መክዳት፤ አጭበርባሪ ጨካኝና አረመኔ መሆን በሞራል ሚዛን ሲታዩ ጀግና ባያስብሉም፣ አጋቶክለስና መንግስቱ ግን በነዚህ ሁሉ ይታወቃሉ፡፡ እነዚህን ድርጊቶች መፈፀም ለአንድ መስፍን ስልጣንን እንዲቀዳጅ ያደርጉታል እንጂ ክብርን አያጎናፅፉትም፡፡ አንዱ ሲሞት ሌላው በስደት ይኖራል፡፡ ፍፁም ጭካኔያቸው ኢ-ሰባዊነታቸው ቁጥር ስፍር የሌላቸው ወንጀሎቻቸው በተከታታይ ትውልዶች ዘንድ ክብርን  እንዲቀዳጁ አላደረጓቸውም፡፡ ከታላላቆች ጎራም እንዲሰለፉ አላደረጋቸውም፡፡
        ሌላው ምሳሌ ደግሞ በአሌክሳንደር ስድስተኛው ዘመን የተከሰተው ነው፡፡ የፌርሞው ኦሊቬርቶ ወላጆቹን በልጅነቱ በሞት ያጣና በአጎቱ እጅ ያደገ ልጅ ነበር፡፡ ወላጆቹን በልጅነቱ በሞት ቢነጠቅም ሳደግስ አይጣላም እንደሚባለው እናት በሆነ አጎት እጅ አደገ፡፡ አጎቱ ጆቫኒ ሲበዛ ደግና መልካም  ሰው ነበር፡፡ ኦሊቬርቶን በሚገባና በሚያስፈልገው  ሁሉ ተንከባከቦ ለቁም ነገር አበቃው፡፡ ኦሊቬርቶ በወጣትነት እድሜው ከስመጥሩው የጦር መሪ ፓውሎ ቪቴሊ ስር ሆኖ ሀገሩን በወታደርነት አገለገለ፡፡ በእሱ ሰር ሆኖ ታላላቅ የመሪነት እርካቦች ላይ ለመወጣጣትም ቻለ፡፡ ፓውሎ ሲሞት ቪቴልዞ ተካው፡፡ አሁንም በቪቴልዞ ስር ሆኖ ሀገሩን በወታደርነት ማገልገሉን ቀጠለ፡፡ ብልህ፤ ጀግናና ፍርሃት የሚባል ያልፈጠረበት ስለነበር በአጭር ጊዜ ውስጥ የቪቴልዞ ከፍተኛ የጦር መሪ ሆነ፡፡ ብቁ ነኝ ብሎ ስለሚያምን ከሌሎች ትዕዛዝን የማይበቀል ነበር፡፡ የፖለቲካ ስልቱን አደራጀ፡፡ በህዝቡ ውስጥ ለመጎዝጎዝ የቻለው ስለከተማዋ የነዛው የሚያሳዝን ወሬ ነበር፡፡ ርእስ ከተማችን በባርነት ስር ወድቃለች፤ ማራኪነቷም አብቅቷል ሲል የህዝቡን ብሶት ቀሰቀሰው፡፡ በንግግሩ የተነሳ ሀዝቡን በቀላሉ የራሱ ማድረግ ቻለ፡፡ በንግግሩና ቪቴሊ በተባለ ወዳጁ እገዛ ፌርሞን  በእጁ አስገባ፡፡ ከተማዋን ከተቆጣጠረ በኋላ ለአጎቱ ለጆቫኒ የሚከተለውን ደብዳቤ ላከለት፡፡ “ከምወዳት ከተማ ከወጣሁ ብዙ አመት ሆነኝ፡፡ ናፍቆቱ ሊገድለኝ ነው፤ከተማዪን መጎብኘት እፈልጋለሁ፡፡” በክብር ወደናፈቃት የትውልድ ከተማው ተመለሰ፡፡ መቶ የሚሆኑ አጃቢዎቹን አስከትሎ ዋና ከተማዋ ደረሰ፡፡ ይህ አልበቃውም፡፡ ጆቫኒ ለክብሩ የክብር አቀባበል እንዲያዘጋጅለት ተማፀነው፡፡ ልጅህ እኮ ነኝ፤ ክብሩ ለኔም ለአንተም ነው አለው፡፡ ጆቫኒም ተንከባክቦ ያሣደገው ነውና አንድም ነገር ሳያጓድል በሚገርም ሁኔታ በታላቅ ክብር ተቀበለው፡፡ ነዋሪውም በላቀ አጀብ በሆታ ተቀበለው፡፡ አጎቱ ጆቫኒ በራሱ ማረፊያ በክብር አስተናገደው፡፡ ኦሊቬርታ የወደፊት እቅዱን በሚስጥር አዘጋጀ፡፡ አጎቱ ጆቫኒንና የከተማዋን ዋና ዋና ሰዎች የእራት ግብዣ አሰናድቶ  በክብር እንዲታደሙለት ጋበዛቸው፡፡ ግብዣውንም ታደሙ፡፡ የእራቱ ግብዣ ካበቃ በኋላ ኦሊቬርታ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የውይይት ርእስ ከፈተ፡፡ የአሌክሳንደርን ታላቅነት የልጁንም ሴዛር ታላላቅ ገድላት በአድናቆት አወሳ፡፡ ጆቫኒና ሌሎችም  በነዚህ ጉዳዮች ላይ አስተያየት መስጠት ሲጀምሩ፣ ኦሊቬርቶ ከተቀመጠበት እመር ብሎ በመነሳት እንዲህ አይነት ጉዳዮች የትም የሚወሩ ሳይሆን ሰወር ባለ ስፍራ  ለሚስጥርነቱም ሲባል በግል እንዲሆኑ ለአጎቱ አሳሰበው፡፡ ጆቫኒንና ታላላቆቹን ሰዎች ቀድሞ ወዳዘጋጀው ወደ ሌላኛው ክፍል ይዟቸው ገባ፡፡ ገብተው ሲቀመጡና የኦሊቬርቶ ወታደሮች ከተደበቁበት ወጥተው ጆቫኒንና ሌሎችን ሲገድሉ አንድ ሆነ፡፡ ከዚህ በእርድ ከተሞላ ግድያ በኋላ ኦሊቬርቶ ፈረሱ ላይ ጉብ አለ፡፡ በከተማው መሃልም በድል አድራጊነት መንፈስ ጋለበ፡፡ የአስተዳዳሪውን ቤተ መንግስት በከበባው ውስጥ አደረገ፡፡ የቀድሞው መንግስት ባለሟሎች ከመሞት መሰንበት ብለው እጃቸውን ሰጡ፡፡ ኦሊቬርቶ ራሱን አዲሱ መስፍን በማለት አንግሶ አዲስ መንግስት መሰረተ፡፡ ወደፊት ስጋት ይሆኑብኛል ብሎ የሰጋቸውን በግድያ አስወገደ፡፡ ስልጣኑን በሚገባ አጠናከረ፡፡ አዲስ ማህበራዊና ወታደራዊ አደረጃጀትን ዘረጋ፡፡ በዚህ ሳያበቃ ተፅእኖውን በጎረቤት ሀገሮች ላይም አሳደረ፡፡
አጋቶክልስ ያን ሁሉ ቁጥር ስፍር የሌለው ወንጀል በንፁሃን ዜጎችና በሹማምንቱ ላይ ከፈፀመ በኋላ ከዜጎቹ ጋር እንዴት በሰላም ለመኖር ቻለ ብሎ አንባቢ ሊገረም ይችላል፡፡ ሌሎች ደካሞች ግን በክፉ ባህሪያቸው የተነሳ አይደለም በቀውጢው ጊዜ በሰላሙም ጊዜ እንኳን ማስጠበቅ አልቻሉም፡፡ የአጋቶክልስን ጥበብ አልታደሉማ፡፡ ለዚህ እንቆቅልሽ ምላሹ ጭካኔን በአግባቡ ወይም በመጥፎ ሁኔታ ተግባራዊ ሆኗል የሚለው ነው፡፡ እንደ ማኪቬሌ እምነት፤ ጭካኔ በአግባቡ ስራ ላይ ውሏል የሚባለው ( ጭካኔ በዚህ መንገድ መገለፅ ከቻለ) ለአንዴና እስከ ወዲያኛ ተግባር ላይ እንዲውል ሲደረግ ነው፡፡ አንድ ልዑል ውሳኔዬ  ልክ ነው ብሎ ካመነ  ከወሰነው ውሳኔ ንቅንቅ ማለት የለበትም፡፡ መጥፎ ማድረግ ተገቢ በሆነበት ቦታ ሁሉ መጥፎን ማድረግ፡፡ ሁኔታው የሚጠይቀውን በሙሉ ማድረግ፡፡ እንደሚነፍሰው የፖለቲካ አየር ልዑሉም ድርጊቱ ተለዋዋጭ መሆን አለበት፡፡ አጭበርባሪ ሆኖም ግትር ግን መሆን የለበትም፡፡ የወቅቱንና የሁኔታውን አስፈላጊነት  ማወቅ አለበት፡፡ የልዑሉም የስልጣን ደህንነት በእዚህ ላይ የተመሰረተ ይሆናል፡፡ በዚህ መንገድ የዘለቁ በሰውም ሆነ በመለኮታዊ እገዛ አጋቶክልስ እንዳደረገው ስልጣናቸውን የሚያበጃጁበት መላን ያገኛሉ፣ ሌሎች ግን በስልጣን ላይ ለመቆየት አይችሉም፡፡ ስለዚህ ልብ ማለት የሚያስፈልገው አዲስ ንጉስ የአገሩን ስልጣን በእጁ ሲያስገባ፣ በዜጎቹ ላይ ማድረግ የሚገባውን መከራና ጉዳት መለየትና በሚገባ መፈፀም አለበት፡፡ ይህን በማድረግ ሰውን በፍርሃት ሸብቦ መያዝ ይችላል፡፡ በፍርሃት በመያዛቸው አእምሮአቸው ምንም አይነት ሴራን አያስብም፡፡ ረግቶ ይቀመጣል፡፡ ህዝቡም በቀላሉ የእሱ ታዣዥ ሆነ ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ በተቃራኒው የሚያደርግ ግን ቢለዋውን በራሱ አንገት ላይ ያሳርፋል፡፡ በዜጎቹ ሊተማመን አይችልም ይለናል ማኪቬሌ፡፡ የወንጀልን ሀይልና እገዛ ከተረኩ መረዳት ይቻላል፡፡ ወንጀል የራሱ ፀጋዎች አሉት የሚያስብለውም ከላይ የሰፈረው አይነት ድርጊት ሲያነፅረው ነው፡፡
በመጨረሻም ማኪቬሌ አወዳሽ እንዳለው ሁሉ አምርሮ ወቃሽም አላጣም፡፡ የሴጣን ሀዋርያ፤የእኩይ ድርጊት መምህር ሲል የ16ኛው ክፍለዘመን ፈላስፋው ሊዮ ስትሮውስ ፈርጆታል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ደረጄ ጥጉ፤ የመጀመሪያ ዲግሪውን በፍልስፍና ከአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ በ1998 ዓ.ም የወሰደ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ ከቻይና ዉሃን ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክ ኢንተርናሽናል ሎው በ2009  ዓ.ም አግኝቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ፍልስፍና እና አለም አቀፍ ህግ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡

Read 569 times