Wednesday, 07 August 2024 07:28

ታሪክ፣ የታሪክ ጸሐፍትና ተቀባዮች

Written by  ስንታየሁ ገ/ጊዮርጊስ
Rate this item
(1 Vote)

1. እንደ መግቢያ
ባለፈው ጽሑፌ የጎልያድ ታሪክ ሲታመንበት ከነበረው፣ ወደተቀየረው የታሪክ ወዝ፣ በሳይንሳዊ መላምትና ምርምር እንዴት ሊለወጥ እንደሚችል አጫውቻችኋለሁ፡፡ የታሪክ ጸሐፍትንና አንባቢዎችን ባህሪያት አስመልክቶ፣ ያለኝን ሃሳብ የማነሳላችሁ መሆኑን አሳውቄ ማሳረጌንም አስታውሳለሁ፡፡ ይህን ጽሑፍ ያቀረብኩት፣ በጨረፍታ የነካካሁትን የታሪክ አጻጻፍ ሂደት በመጠኑ አስፍቼ በማቅረብ ውስጣችሁን መኮርኮር ስለፈለግሁ ነው፡፡
ብዙ ብሔረ-ሰቦች ባሉበት አገር ውስጥ የአንድ ብሔረ-ሰብ ታሪክ ብቻውን ተነጥሎ ሊነገር ይችል እንደሆነ እንጂ፣ ሌሎች ብሔረሰቦችን ሳያካትት/ሳያሳትፍ የተከናወነ የጋራ ታሪክ ሊኖር ይችላል ብዬ ፍጹም አላምንም፡፡ ታሪክ በጣም ብዙ ሕዝብ የተሳተፉበት/የሚሳተፉበት ድርጊት ነው፡፡ በእርግጥ አንድ ሰውም ታሪክ ሊጻፍለት ወይንም በራሱ ታሪክ ሊሆንም ይችላል፡፡ ያተኮርኩት በህዝብ ታሪክ ላይ መሆኑን ግን ልብ በሉልኝ፡፡
ታሪክ ተከናውኖ ያበቃለት/ያለፈ ሂደት ብቻ አይደለም፡፡ ያለፈውን ክንዋኔ ዛሬ ላይ ሆነን የምናይበት/የምናውቅበት መዘክርም ነው፡፡ ዛሬ እየተጻፈ የሚገኝ ክንዋኔ፣ ነገ ላይ ያለፈ ታሪክ በመሆን በማስታወሻነት ይመዘገባል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከአንድ ሰዓት በፊት የተከናወነ ድርጊት እንኳን በራሱ ታሪክ ሊሆን ይችላል - ያንን ያለፈ ሰዓት መመለስ ስለማይቻል፡፡ ተከናውኖ ባለፈ ጉዳይ ላይ ግን መነጋገርና መወያየት ይቻላል፡፡ ውይይቱ የሚጠቅመው፣ ስህተት ካለበት በሚቀጥለው ጊዜ ለማረም፣ መልካም ክንውን ከሆነም ከምሳሌነቱ ለመማር ነው፡፡ ሌላ ተአምር የለውም፡፡
የሰው ልጆች ድርጊት እስካልቆመ ድረስ ታሪክ አያቆምም፡፡ ታሪክ የድርጊቶች ሂደት ነው፡፡ ያ ድርጊት ግን በጊዜ፣ በቦታ፣ በዓይነት … ወዘተ ሊለያይ ይችላል፡፡ የሚጻፈው ክንዋኔ/ድርጊት የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚ፣ የሃይማኖት፣ የባህል፣ የልማት/ስልተ-ምርት፣ የቅርስ፣ የግጭት/የጦርነት ታሪክን በአንድነት ወይም በተናጠል የሚያንጸባርቅ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ውስጥ የሕዝቦች መነሻ/ፍልሰት፣ ባሕርያት፣ ግጭት፣ አንድነት፣ ልዩነት (የቋንቋ፣ የባሕል፣ የሃይማኖት፣ የአስተዳደር፣ ወ.ዘ.ተ) በቦታና በጊዜ መዘርዘራቸው አይቀርም፡፡ የተማሩትና ደፍረው ስለ አንድ አገርና ሕዝብ/ሕዝቦች ታሪክ የሚጽፉት (ቀለምን ከወረቀት አዋድደው በመጽሐፍ የሚያቀናብሩት) ግን በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የታደሉ ናቸው፡፡
የታሪክ ጸሐፊና ተመራማሪ ዐቢይ ሥራ/ተግባር፤ በመረጃ ላይ ተመስርቶ ታሪክን በጽሁፍ ማስቀረት/መጻፍ፣ በመረጃ ላይ ተመስርተው የተጻፉ ሌሎች ታሪኮችን ማስታረቅና፣ በታሪክ የተሳተፉ ሕዝቦችን ማቀራረብ፣ እንዲሁም ማዋሀድ ይመስለኛል (አብሮነት ከሚያስገኘው የጋራ ጥቅም አንጻር)፡፡ በእርግጥ አንድ ታሪክ ይሁን ተብሎ ሕዝብን ለመነጣጠያነትም ሊጻፍ ይችላል፡፡ ከማቃቃር ጋር ሲነጻጸር ማስታረቅ ከባድ ተግባር ነው፡፡ ብዙዎች አውቀውም ሆነ (የራሳቸውን ወገን ሚና ከፍ ለማድረግ በአድልኦና ለፖለቲካ ጥቅም ሲሉ) ሳያውቁ (ነገ በሚመጣው ትውልድ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ ቀድመው ሊያገናዝቡ ባለመቻል) ሊያቃቅር በሚችለው የሃይማኖትና የፖለቲካ (የጦርነት ጀግንነት ታሪክ) ላይ በማትኮር የሚጽፏቸው ታሪኮች በአንጻራዊነት በርክተው ይታያሉ፡፡ ታሪክን እንደ ሃይማኖት ማስፋፊያና የፖለቲካ ጥቅም ማግኛ መሣሪያ አድርጎ መመልከት በስህተቶች እንዲታጨቅና አድሏዊም እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
አንድ የታሪክ ጸሐፊ የእርሱ ብሔረ-ሰብ በታሪክ ውስጥ ያደረጋቸውን አስተዋጽኦዎች እያጎላና የሌላውን እያኮሰሰ፣ የበላይ የሚያደርገውን የታሪክ ዳራ ብቻ እየመረጠ ቢጽፍ፣ ትውልዶችን ወደ ማያባራ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ንትርኮች ውስጥ የሚያስገባ አውድ መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ታሪክን የፖለቲካ ሥልጣን ማማ ላይ መወጣጪያና የበላይነትን ማግኚያ መሣሪያ ለማድረግ ትኩረት ማድረግ፣ ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ ጥቅምን አያስገኝም፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ብዝኃነት ባለባት አገር ውስጥ የሚኖርን ሕዝብ ታሪክ መጻፍ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግ ሥራ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሕዝብ በታሪክ ላይ እምነት ከሌለው፣ በመንግሥቱም ላይ እምነትን ያጣል፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ፣ እንዲሁም በሕዝብና በሕዝብ መካከል መተማመን መኖሩ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ታሪክ መጻፍ ማስተዋልን የሚሻው አንዱም ለዚህ ነው፡፡
2. የታሪክ ባሕሪ
በታሪካዊ ሂደቶች ውስጥ መሳተፍ፣ ታሪክን መጻፍ፣ ታሪክን በትምህርት ቤት መማርና የተጻፈን ለማወቅ ማንበብ የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ታሪኩን ጸሐፊው ወይንም አንባቢው ታሪኩ በተከናወነበት ጊዜ/ዘመን የኖረ ወይም ያልነበረ ሊሆን ይችላል፡፡ ድርጊቱ ሲከናወን የነበረ ታሪክ ጸሐፊ ወይም አንባቢ የተከናወኑትን ድርጊቶች በቅርብ ርቀት የመስማት፣ የማየትና በድርጊቱ ውስጥም የመሳተፍ ዕድሉ ይኖረዋል፡፡ ባልነበሩበት የታሪክ ምዕራፍ ወቅት የተጻፈን ታሪክ ማንበብ ግን፣ በሌሉበት ድርጊት ውስጥ ራስን አስቀምጦ/ሰይሞ ታሪኩ በተከናወነበት ጊዜ የነበረውን ሂደት በአዕምሮ/በዐይነ ህሊና መመልከት/መቃኘት ነው፡፡
“ማየት ማመን ነው” እንዲሉ፣ ከታሪክ መጽሐፍ ታሪክን ያነበቡ ሁሉ ድርጊቱን ካዩት ወይንም ከተሳተፉበት እኩል በታሪኩ ሊያምኑ ወይም ሊመሰጡ ያለመቻል አዝማሚያን ቢያሳዩ የማይጠበቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ “ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸውና” ያልነበሩ፣ ነገር ግን ያነበቡትን ታሪክ የራሳቸው አድርገው የሚቀበሉና የሚያምኑም ብዙ ናቸው፡፡ ያም የሚጠበቅ ነው፡፡
ታሪክ በባሕርዩ (እንደ ሃይማኖት ሁሉ) ሳያዩ ማመንን የግድ ይላል፡፡ የተጻፈ ታሪክን ለማመን ያሉበትን ብሔረ-ሰብ ሚና፣ ባህሉን፣ የአኗኗር ስርዓቱንና ሥነ-ልቡናውን በአወንታዊም ሆነ በአሉታዊ ጎኑ ማወቅንም ይጠይቃል፡፡ በታሪክ አጻጻፍ ላይ በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ሳይንተራሱ ለራስ ወገን ማድላት ተአማኒነትን ማሳጣቱ አይቀርምና ሚዛናዊ መሆን የግድ ነው፡፡ አለያ ታሪኩን ጸሐፊውም ሆነ ታሪኩ በራሱ ባዶ ይሆናሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የታሪክ ጸሐፍት የሚወድቁት የራሳቸውን ወገንና አስተሳሰብ/እምነት እስከደገፈ ድረስ ለመረጃ ግድ የሌላችውና ያነበቡትን (ወይንም ጻፉ የተባሉትን) እንደወረደ ተቀብለው የሚያቀብሉ በመሆናቸው እንደሆነ አልጠራጠርም፡፡ ካላቸው የማቃቃር ፍላጎት (ፖለቲካ) ተነስተውም፣ በራሳቸው አሳሳች ተረክ ላይ ተመስርተው በመጻፍ ታሪክን ሊያጠለሹም ይችላሉ፡፡ አሳሳች ታሪክ ከተሳሳተ ተረክ ሊመነጭ ይችላል፡፡
ከታሪክ ፀሐፊዎች መካከል ታሪኩ በሚከናወንበት ወቅት የሌሉቱ፣ ሌሎች የጻፏቸውን መነሻና ማጣቀሻ እያደረጉ ከሚጽፉ ውጭ በራሳቸው አዲስ ነገር አይፈጥሩም፤ ወይም በወቅቱ ስላልነበሩ ቀጥታ የዐይን እማኝ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሊያደርጉ የሚችሉት የተጻፉት የታሪክ መጻሕፍት በመረጃ ላይ የተመሰረቱ መሆን አለመሆናቸውን መመርመርና፣ በነዚያም ላይ ተመስርተው የሚጽፉትን የታሪክ መጽሐፍ በተሻለ የታሪክ ትንተና መሠረት ላይ ለማዋቀር ጥረት ማድረግ ነው፡፡ ተዛብቷል (ሚዛኑ አጋድሏል) የሚሉትን የታሪክ መስመር፣ ታሪኩ ከተጻፈበት ዘመን አንድ በሆነ፣ በተመሳሰለ ወይም በተቀራረበ ሁኔታ ውስጥ ብቻ ሁነው ለማጥናት (ለመተንተንና የታሪኩ ባለቤት ላይ ለማስመር) መሞከራቸው ግን አግባብ ሊሆን ይችላል፡፡
ታሪክን የማጥኛና የመጻፊያ ሳይንሳዊ ዘዴዎች ቢኖሩም፤ ታሪክ በምርምር (በቤተ-ሙከራ ውስጥ ሆኖ በመመራመር ለማለት ነው) የሚገኝ ሳይንስ አይመስለኝም፡፡ በሳይንሳዊ ምርምር (በመረጃ ላይ ተመስርተው ታሪክን በሚገባ በመፈተሽ) የነበረውን ታሪክ እውነታ የበለጠ ለማጠናከር ወይንም ለማሻሻል በመቻል የአስታራቂነትን ድርሻ መወጣት ይቻል ይሆናል ብዬ ግን አምናለሁ፡፡ ታሪክ የአንድ ወቅት ድርጊት ነውና (የማይቆም ሂደት መሆኑን ከማመን ጋር)፣ ከተከናወነበት ወቅት ጋር ያለፈ ሂደት መሆኑን መለወጥ ግን አይቻልም፡፡ ታሪክ በራሱ አይጨምርም፣ አይቀንስም፤ እንዲሁም በራሱ አያድግም፡፡ የተጻፈ ከሆነ ያለው በመጽሐፍና ድርጊቱን በሚገልጡ ሐውልቶች፣ በቦታ፣ በቅርሶች፣… ውስጥ ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ የድርጊቱ ጣመን በሌሎች ዘመንና ትውልዶች ባሕል፣ ሃይማኖት፣ አስተምህሮ፣ አመለካከት/ርዕዮት፣ … ሂደት ውስጥ ቀስ እያለ የመትነንና ሽታው/ትንፋጉ በጥሩ/በጎ መዓዛ ለማወድም ይሁን በመጥፎ ሽታ ለመሰንፈጥ የሚያስችል ባሕርያት ያሉት ይመስለኛል፡፡
ያለፈን ድርጊት በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ መመርመርና ማነጻጸር መቻሉ (ቻ ይጥበቅ) እሙን ነው፡፡ እንደ አዲስ ግኝት ለመተረክ ሳይሆን፤ ያለፈውን ድርጊት ወይም ታሪክ ለማጠናከር ወይም በመረጃ አስተካክሎ ለትውልድ ለማስቀረት - ለትምህርት እንዲሆን፡፡ ታሪክ የሚጠቅመው፣ ካለፉ መልካም ከሆኑና ካልሆኑ ድርጊቶች ለመማር ነው፡፡
ከመልካም ታሪክ ጥሩውን ለመውሰድና በጎ ያልሆነውን ደግሞ ላለመድገም ታሪክን ማወቅ ያገለግላል፡፡ አንድን ታሪክ፣ አንዱ ብሔረ-ሰብ ከሌላው ይበልጣል ወይንም ያንሳል (በጥቅሉ የእኔ ይበልጣል) ለማሰኘት በዘ-ፈቀደ የሚጠቀሙበት የትንተና ጽሑፍ አድርገው ከወሰዱት፣ የጋራ እምነት ይሸረሸራል፡፡ የታሪክ ጸሐፍት ጥንቃቄ ማድረግና፣ የሚጽፉትን ታሪክና የራሳቸውን ባሕሪያት መፈተሽ ያለባቸውም ለዚህ ይመስለኛል፡፡
3. የታሪክ ጸሐፍት ባሕሪ
ታሪክን መጻፍ በጣም ከባድ ነው፡፡ ክብደቱ የሚያመዝነው ግን ጽሑፉ ላይ አይመስለኝም፡፡ የታሪክን ሂደትና ተሳታፊዎቹንም ተረድቶ “እውነተኛ” የታሪክ ማስረጃዎችን በመመልከት ካለአድልኦ (ለማንም ሳይወግኑ ሚዛናዊ በመሆን) መተንተኑ ላይ ይመስለኛል፡፡ የጸሐፊው ሚዛናዊነት ወሳኝ ነው፡፡ ጸሐፊው ልክ እንደ ታሪኩ ሁሉ በተለያዩ አቅጣጫዎች ጥያቄን በሚያነሱ ታሪክ አንባቢዎች (ለታሪካቸው በሚቆረቆሩና ታሪክንም በሚመረምሩ) ዘንድ ይገመገማልና ፍጹም ሆኖ ለመገኘት ይጥራል (ይህ ለራሱና ለትውልድ ታማኝ የመሆን ሕሊና/ባሕሪ ለተላበሰ ጸሐፊ የሚባል ነው)፡፡ አንድ ታሪክን የሚጽፍ ግለሰብም ይሁን ቡድን ግን ፍጹም መሆን ይሳነዋል፡፡ ፍጹምነት ከባድ በመሆኑ ጭምር ነው ታሪክን መጻፍም ሆነ መተቸት የሚከብደው፡፡ ታሪክ የተከናወኑ የድርጊት መረጃዎችን አሰባስቦ “ሚዛናዊ በመሆን” መጻፍ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ታሪክን ለመጻፍ የግድ የታሪክ ምሁር መሆን ብቻውን በቂ አይመስለኝም፡፡
ድርጊቱ (ታሪክ)፣ ትክክለኛ መረጃ (“fact”) ያለው በመሆኑ በራሱ የሚለወጥ ነገር የለውም፡፡ የሚለወጠው ነገር መረጃውን የምንመለከትበት፣ የምንተረጉምበትና የምንተነትንበት አቅጣጫና፤ አንባቢው ወይም ታሪኩን ተቀባዩ ትውልድ በባሕሪ የሚለያዩ መሆናቸው ብቻ ነው፡፡ የታሪክ እይታ እንደ ዘመኑ/ትውልዱ ሊለዋወጥ የመቻል አዝማሚያን ይከተላል በማለት አምናለሁ፡፡ ትውልድና ታሪክ ይለዋወጣሉ - ፖለቲካም እንደዚያው ተለዋዋጭ ነው፡፡ እኔ እንኳን ሦስት መንግሥታትን በማየት ትውልድና ታሪክ ለመለዋወጣቸው የዐይን ምስክር ነኝ፡፡
ሁለት የታሪክ ጸሐፊዎች አንድን መረጃ ተመልክተው በሁለት ዓይነት (ከሁለትም በላይ ሊሆን ይችላል) የአጻጻፍ ወዝ ሊጽፉት ይችላሉ፡፡ ድርጊቱን ሲመለከቱት አንዱ ያየውን ሌላኛው አላየ ሊሆን ይችላል፡፡ አይቶም የሚያስብበት አቅጣጫ ሊለይ ይችላል፡፡ ወይንም እያንዳንዱ ለራሱ ያዳላል፡፡ ያም ቢሆን “የድርጊቱን/መረጃውን እውነተኝነት” አይቀይረውም፡፡ሁሉም ያዩትን/ያገኙትን መረጃ ሊለውጡት አይችሉም፡፡ ከለወጡት ስሕተት ሠርተዋል፤ የታሪኩን ሚዛን አቃውሰዋል ማለት ነው፡፡
በጽሁፍ የሰፈረ መልካምም ይሁን መልካም ያልሆነ ድርጊት ሁሉ ለትውልድ የመተላለፍ እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ያለንበት ዛሬ፣ ራሱንም ሆነ ያለፈውንና መጪውን ለማየት/ለማገናኘት እንደ ድልድይ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የዛሬው ክንዋኔ ነገ ላይ የትናንት (ያለፈ) ታሪክ ነው፡፡ እያንዳንዱ በጊዜ/ዘመን የተከናወነ ድርጊት በራሱ ሊቆም የሚችል ቢሆንም፣ የአንዱ ድርጊት ሌላውን ማስከተሉ የግድ የሚያደርገው ግን ትውልድ የማያቋርጥ ሂደት በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ የታሪክ ጸሐፊውም የትውልዱ አባል በመሆኑ ባሕሪው እንደትውልዱ ዓይነት፣ አመለካከት/ርዕዮት፣ የመንግሥት አስተዳደር (ፖለቲካ) እና የኤኮኖሚ ዕድገት ደረጃ፣ … ሊቀረጽ የመቻሉ እውነት አያከራክርም፡፡ ትውልድ “የማይደርቅ” ፈሳሽ ጅረት/ወንዝ ነው፡፡ ታሪክ እንደትውልድ ሁሉ የማያቋርጥ ሂደት/ፍሰት ያለው ክንዋኔ ነው፡፡ ታሪክን የሚጽፍ ጸሐፊ (ትውልድ) ያለፈውን ሁሉ እንዳልነበረ በመቁጠርና ካለፈው ሳይማር፣ አዲስ ታሪክን መጻፍ ቢችል፣ ማነጻጸሪያ-አልባ ድርሰት ይሆንበታል፡፡ ያለፈውን መጥፎ ታሪክ ላለመድገም፣ ታሪክን ከስሩ ማወቅ፣ ማጥራትና ማነጻጸር የጸሐፊው ባሕሪ መሆኑ የግድ ነው፡፡
4. አራቱ የታሪክ ጸሐፍት
ታሪክ አራት ዓይነት ፀሐፊዎች ሊኖሩት ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ የመጀመሪያው የራሱን በራሱ (በውስጡ ያለፈበትንና ያየውን በራሱ አነሳሽነት) “እውነተኛ”ታሪክ/ድርጊት ተመልክቶ የሚጽፈው ነው፡፡ ሁለተኛው፣ የሌላውን (እንዲጽፍ የተነገረውን) “እውነተኛ” ታሪክ/ድርጊት የሚጽፈው ነው፡፡ ሦስተኛው፣ በተለያዩ የታሪክ ጸሐፊዎች በተለያዩ ጊዜያት የተጻፉና በወቅቱ የተገኙ የታሪክ መጻሕፍትን/መዛግብትን አገላብጦ፣ አነፃፅሮ፣ አጥንቶና መርምሮ የሚጽፈው/የሚያጠናቅረው፣ ታሪክን በቅንነት የማስተላለፍ የሥራ ሂደት ውስጥ የሚሳተፈው ነው፡፡ አራተኛው፣ የተለያዩ ታሪክ ጸሐፊዎች የጻፉትን (ከሌሎች ታሪክ መጻሕፍት) አንብቦና መርምሮ፣ የራሱንና ያለበትን ቡድን አመለካከት (narrative) የሚደግፍለትን መርጦ በማውጣጣት (ወገናዊ በሆነ ሁኔታ) የሚጽፈው ነው፡፡
አራተኛው ወገን ከሦስቱ ጸሐፍት የሚለየው፣ ጭፍን ወገንተኛ በመሆንና መረጃን እያዛባ ታሪክን (በተለይ መልካም መልካሙን ለራሱ በማድረግ ሊሆን ይችላል) ለአንድ ወገን ብቻ ለመስጠት የሚጥር መሆኑ ላይ ነው፡፡ ከላይ የገለጠኳቸውን አራት የታሪክ ተመራማሪዎች/ጸሐፊዎች/አጠናቃሪዎች አንድ በአንድ እንያቸው፡፡
የመጀመሪያው ጸሐፊ፣ በውስጡ ያለፈበትን “እውነተኛ”ታሪክ የሚጽፈው፣ ዝንባሌው ወይንም ትምህርቱ በመሆኑ አውቆ ለማሳወቅ፣ የነበረበትን ትውልድና የፖለቲካ ሥርዓት ከማስቀጠል አኳያ ካለው ፍላጎት ተነስቶ በራሱ አነሳሽነት እርሱና ትውልዱ በውስጡ ያለፉባቸውን ድርጊቶች/ክንዋኔዎች ሊጽፍ ይችላል፡፡ በውስጣቸው በማለፉ ምክንያት ያየውን፣ አብረው በድርጊት ከተሳተፉት ሰዎች የተመለከተውን/የተረዳውንም ይጽፋል፡፡ በወቅቱ በራሱ ውስጥ ከሚመላለሰው የግንዛቤ ጣሪያ ተነስቶ በሌሎች ተበረታትቶና የሌሎችን ሃሳብ አርዓያነት ተመርኩዞም ይጽፋል፡፡ የዚህ ክፍል ፀሐፊ ዓላማው/ፍላጎቱ የጊዜ/የዘመን ክንዋኔዎችን ማስፈርና ለቀጣይ ትውልዶች በማስታወሻነት ማስቀመጥ ይመስለኛል፡፡ አንድ ሰው በመጀመሪያ ታሪክ መጻፍ ሲጀምር ይህን ዓላማ ይዞ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ የታሪክ አነሳስ/አጻጻፍ እንደዚያ ብቻ ሆኖ ቢገኝ እመርጣለሁ፡፡
ይህ ታሪክ ከእውነት (ትክክለኛ ድርጊት) ጋር እጅግ የቀረበ ግንኙነት ያለው ይመስለኛል፡፡ የጸሐፊው የግሉና አብረውት በታሪኩ/በድርጊቱ የነበሩት የጊዜው ሰዎች ትምክህት (ego) ብዙም ሳይጋነን ሊኖርበት እንደሚችል ግን እገምታለሁ፡፡ ሰው ከማጋነን/ትምክህት ነፃ የመሆን አቅሙ ደካማ ነው፡፡ ከተለያዩ የታሪክ መጻሕፍት አጻጻፍ ስነሳ፣ እንደ መጀመሪያው የታሪክ ጸሐፊ ዓይነት በፍጹምነት ይገኛል ብዬ ለማመን ይቸግረኛል፡፡ መረጃዎችን በቅንነት ለማየትና ለመተንተን የሚሞክሩ የታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚኖሩ ግን እገምታለሁ፡፡
የሁለተኛው ዓይነት ታሪክ ጸሐፊ፤ በሥራው፣ በዕውቀቱ ወይንም በያዘው ሥፍራ ምክንያት ተመርጦ ወይም ተቀጥሮ (በክፍያ ወይም ዳረጎት ተሰጥቶት) የአንድን ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ሥርዓትና የሥርዓቱን መዋቅሮች (ላዕላይና ታህታይ) እንዲጽፍ ሊደረግ ይችላል፡፡ የዚህ ክፍል ፀሐፊ የሌሎች ሰዎች ፍላጎትና ተፅዕኖ ሊያርፍበት የሚችል መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በላዕላይ መዋቅሩ የሚገኙ “የገዢ መደቦች”፣ የሃብት ባለቤቶች፣ የእምነት ተቋማት የእነርሱን ሚና ጎላ አድርጎ እንዲያሳይና በዚያ ሳቢያ የሚያገኟቸው ጥቅሞች እንዲቀጥሉ ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎችን እንዲያሰፍር ተጽዕኖ ሊያሳድሩበት እንደሚችሉም እገምታለሁ፡፡ ፀሐፊው ራሱም የዚያ ሕብረተሰብ/ትውልድ አካል በመሆኑም በጋራ የሚጋራው ጥቅም/አመለካከት ተጽዕኖ ሊኖርበት እንደሚችል መጠርጠርም ይቻላል፡፡ ታሪክ ፀሐፊው ያየውን የሚጽፍ በመሆኑ “አውነተኛ መረጃ” ያለው ይሁን እንጂ የፖለቲካና የሃይማኖት ተፅዕኖ ያረፈበት ስለሚሆን አድሏዊ (ሚዛን የጎደለው) ለመሆን እንደሚገደድ አያጠራጥርም፡፡ ጸሐፊው በግሉ ሌሎችን ለመጉዳት ይሁን ብሎ የሚያደርገው ነው ለማለት ቢከብድም፤ በዚህ የታሪክ አጻጻፍ የሚጎዱና የሚጠቀሙ ሌሎች ክፍሎች ሊኖሩ መቻላቸው ግን እሙን ነው፡፡
የሁለተኛው ዓይነቱ የታሪክ አጻጻፍ የፖለቲካ (ሃይማኖትን ጨምሮ) ሥልጣንና የሃብት ሚዛን ያጋደለለት ሥርዓትና ቡድን እየነገሠ (እየገነነ) ሲመጣ የተለመደ አሠራር በመሆን የዘለቀ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ አብዛኛው በኢትዮጵያና በዓለም ላይ ያሉት የታሪክ አጻጻፎች ወደዚህ ያደሉ ይሆናሉ ብዬም አስባለሁ፡፡ የዚህ ዓይነት አጻጻፍ ለምን? መቼ? በማን? የት? ተጀመረ የሚሉት ጥያቄዎች ናቸው በታሪክ ተመራማሪዎች መመለስ ያለባቸው፡፡
ኢትዮጵያን በተመለከተ፣ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን እየጠየቅን በጥሞና (ረቺና ተረቺን ለመፍጠር ሳይሆን በጋራ ሆኖ እውነትን ለማንጠርና ተስማምቶ የጋራ ታሪክን ለማበልጸግ) መወያየት መልካም ይመስለኛል፡፡ በዚያውም፣ በታሪክ አጻጻፍና አተናተን ረገድ የሚጋጩትንና የሚስማሙትን ከዋቢ የታሪክ መጻሕፍት በመሰብሰብ የተጋጩት ለምን ተጋጩ (የጸሐፊው ችግር/አድሏዊነት ወይስ የመረጃ እጥረት)? ብለን በመጠየቅ አንድ የሚያስማማ ታሪክንና የታሪክ ምዕራፍ ብንከፍት ይበጅ ይመስለኛል፡፡ “የታሪክ ድርሳናት” መስተካከል አለባቸው በማለት የሚያምኑ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በርካቶች ናቸው፡፡
ሦስተኛው የታሪክ ጸሐፊ፣ “ምሁርና የታሪክ ተመራማሪ” እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ፍላጎቱ፤ ለመጻፍ ካሰፈረው/ካስቀመጠው ርዕስ አንጻር ተነስቶ፣ ታሪክ/ድርጊት “የተመሠረተበትን እውነት” መፈለግና የተከናወኑ ድርጊቶችን እያመሳከረ በጽሑፉ ውስጥ ማስፈር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በማንኛውም ክፍል የተጻፉና በወቅቱ የተገኙ የታሪክ መጻሕፍትን አነፃፅሮ፣ መርምሮና አጥንቶ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ ድርጊቶችን (የተፈጸሙ ታሪኮችን) የሚጽፍና ሚዛንን ለመጠበቅ የሚጥር በመሆኑ ፍላጎቱ እውነተኛ ድርጊቶችን መፈተሽና ለትውልድ ማስተላለፍ ነው - በዚያውም ራሱን ለማሳደግ (ለትምህርት ደረጃ)፡፡ እውቅና እና ዝናን በመሻትም ሊሆን ይችላል፡፡
ዝናን መሻት የሰው አንዱ ድክመት በመሆኑ፣ ከዚህም አንጻር ጸሐፊው ሊቃኝ ይችል ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በዚህ ላይ የሠሩ በርካታ የታሪክ ምሁራን በሌላው ዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ይህ ክፍል እንግዲህ፣ አንድ ድርጊት እንዴት ሆነ? ለምን ሆነ? ድርጊቱ የትና መቼ ተከናወነ? እነማን በሥፍራው ነበሩ? ታሪኩ ሲጻፍ ምን ነባራዊ መረጃ ጎድሎት ነበር? (መጋነን አለመጋነኑን ጭምር) በማለት ሊጠይቅና የተለያዩ የታሪክ መረጃዎችን በመንተራስ የቀደመው ታሪክ ፍሰቱን ጠብቆ እንዲነበብና የተሻለ የታሪክ እይታን ለማጎልበት ጭምር የሚሞክር ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲያም ሆኖ የጸሐፊው የግል እምነትና አመለካከት (የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚ፣ የሃይማኖት፣ የባህል፣…) በጽሁፉ ውስጥ ሊንጸባረቁ አይችሉም ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ በምርምሩ አዲስ ነገርን የማሳየት ፍላጎትም ስለሚኖረው፣ ቀደም ያልታዩ በርካታ መረጃዎችን በማቅረብና “የታሪክ ምሁርነቱንም ለማስመስከር” የራሱን ጥረት ማድረጉ የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህ በአብዛኛው ለትምህርት ልህቀት መረጃ እንዲሆን በሚደረጉ ጥናቶች (Research Papers or Thesis) አማካኝነት የሚንጸባረቅ ሊሆን ይችላል፡፡
ጸሐፊው በራሱ የፖለቲካ አዝማሚያና በሌሎች ተጽእኖ ምክንያት የሚጽፈው የታሪክ ምርምር ጽሑፍ ሚዛናዊነቱን ሊያጣ ይችላል፡፡ የታሪኩ የሚዛን እጦት ሲረጋገጥ ግን ሚዛንን እንዲጠብቅ ከሌሎች የታሪክ ተመራማሪዎች (ምሁራን) ጋር በጥሞና መወያየት ይበጃል፡፡ ሁሉም የታሪክ ጸሐፊ እኔ የጻፍኩት ትክክል ነው ብሎ የመቆም/የመሞገት አዝማሚያ የሚይዝ በመሆኑ፣ ውይይቱ ቀላል እንደማይሆን መገመት አይከብድም (የጽሑፉ ይዘት በአስተማማኝ መረጃ ውድቅ ከተደረገ በምርምር ጽሑፉ የተገኘ ማዕርግና የዕውቅና ደረጃም ጥያቄ ውስጥ ስለሚገባ ጭምር ጸሐፊው ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል አይሆንም)፡፡ ይሁን አንጂ፤ ውይይቱን መረጃዎች ላይ ብቻ እንዲያተኩር በማድረግ ታሪክንና ጸሐፊውን ማስታረቅ ቀላል ይመስለኛል፡፡
ጸሐፊውና ታሪክ ከታረቁ ሕዝብም በታሪኩ ዙሪያ የመታረቅ እድሉ በጣም ሰፊ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ ጥንቃቄ የሚሻው ጉዳይ ግን የታሪክ ሽሚያ እንዳይኖር መሥራቱ ላይ ነው፡፡ ያ ደግሞ የታሪክ ዕውቀትን፣ ጥበብንና “ሆደ ሰፊነትን” (መከባበርንና በመርህ ላይ የተመሠረተ መቻቻልን) የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡
አራተኛው ክፍል ሌላው የጻፈውን አንብቦ/ተመልክቶ/መርምሮ/ተመርኩዞ የሚስማማውን መርጦ የሚጽፈው ነው፡፡ የራሱንና ያለበትን ቡድን አመለካከት (narrative) የሚደግፍለትን ከተጻፉ የታሪክ ድርሳናት ውስጥ መርጦ በማውጣጣት የራሱን “እውነተኛ” ታሪክ የሚጽፍ ክፍል ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ (አራተኛው) ክፍል ከሌለ ታሪክ የሚነሳ አይደለም፡፡ መነሻን ይይዛል፡፡ የሚደግፉትን የታሪክ መረጃዎችም ያሰባስባል፡፡ ይህ ክፍል በአብዛኛው የተጎጂነት ሥነ ልቡናን የተላበሰና፣ እኔና ቡድኔ አሁን ላለንበት “የተጎጂነት” ሁኔታ ተጠያቂዎቹ ሌሎች ናቸው (ታሪክ ጸሐፊዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የገዢ መደቦች ወይንም ብሔረሰቦች) የሚል ዝንባሌን የሚያቀነቅን “የምሁር” ክፍል ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡
አራተኛው ክፍል መነሻው የታሪክ እውነትን መፈለግ ሳይሆን፣ ተጎጂነቱን የሚያመለክቱ ጥቃቅን ጉዳዮችን ወይንም ተረኮችን በመልቀም የፖለቲካ አስተሳሰቡን ማራመድና በሌሎች ተጠቂ ሆኖ የነበረ መሆኑን አጉልቶ በማስቀመጥ ተከታዮችን ማበራከት ነው፡፡ ባልነበረበት የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ራሱን በመሰየም ድርጊቶችን ለመበየንና ሌላውን “በዳይ” ራሱን “ተበዳይ” አድርጎ በማቅረብ፤ ቢችል ራሱን የሚያጎላበትን፣ አለያም ሌላው ስለእርሱ የሚወነጀልበትን ምዕራፍ እያሰላሰለ “ተረክ የሚያራባ” ክፍል/ጸሐፊ ይመስለኛል፡፡
አራተኛው ክፍል ቀደም ሲሉ በልዩ ልዩ ሰዎችና መንግሥታት (በሚኖርበት ሕብረተ-ሰብም ይሁን ከዚያ ውጭ ባሉ ጸሐፊዎች) የተጻፉ “የታሪክ መዛግብትን” በማውጣጣት የራሱን “የተጎጂነት” ታሪክና የሌሎችን “ጎጂነት” በጽሑፉ ውስጥ ለማጠንከር እየመረጠ የሚጽፍ ክፍል ነው (ይህ ክፍል ለዝና በቋመጡ ከእርሱ ውጭ ባሉ ሌሎች የታሪክ ጸሐፍትም ሊታገዝ ይችላል)፡፡ አራተኛው ዓይነት የታሪክ ጸሐፊ የታሪክን አመጣጥና የትውልድን ሂደት ሳይሆን የተነሳለትን “የተጎጂነት” መፈክር የሚደግፉለትን የታሪክ ክንዋኔዎችን በመፈልፈል/በመምዘዝ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ይህ ክፍል ጂኦግራፊያዊ እውነታዎችን እንኳን ወደ ራሱ አመለካከትና አሰማመር ለመቀየር ጥረት የሚያደርግ ሊሆን ይችላል፡፡ በእኔ አመለካከት የዚህ ዐይነቱ ታሪክ ጸሐፊ እጅግ አደገኛ የሆነውን መስመር የሚከተልና በትውልዶች መካከል ሊታረም የሚያዳግት የታሪክ አረም የሚዘራ መሆኑ ይሰማኛል፡፡
አራተኛው ክፍል፤ ተከናውኖ ባለፈ ታሪክ ላይ እርቅን፣ መከባበርንና መቻቻልን ለማምጣት ሳይሆን፣ ጠባብ የፖለቲካ ዓላማን በማራገብ ታሪክን ለመለወጥ የሚጥር ክፍልም ይመስለኛል፡፡
በአንድ የታሪክ ሂደት ውስጥ የእርሱ/የቡድኑ “ጉዳት” በታሪክ ውስጥ መከሰቱ እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ እርሱም በራሱ ለራሱ ውድቀት አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል፡፡ ምናልባትም ሙሉው የረጅም ጊዜ የታሪክ ማህደራት የሚመሰክሩት የርሱን ሌሎችን “መጉዳት/መተንኮስ” ሊሆንም ይችላል፡፡ ይህ አራተኛው ክፍል የሚፈልገው ግን የራሱን “ተጠቂነት” የሚያሳዩ ታሪካዊ ዳራዎችን ብቻ በመሆኑ እየመረጠ በማውጣጣት ለምስክርነት/ዋቢነት ከሚጠቀምባቸው በስተቀር “ለታሪክ ደንታ” (ከታሪክ የመማር ደንታ) የለውም፡፡ የአራተኛው ዓይነት የታሪክ ጸሐፊ ደንታው የራሱን ነጥብ ማስቆጠርና የርሱን የታሪክ አመለካከት (narrative) የሚያስተጋቡ ተከታዮችን ማፍራት ነው፡፡ ግቡ፣ የፖለቲካ ዓላማውን በተከታዮቹ አማካኝነት እውን ማድረግ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ፣ እንዲህ አይነቱ የታሪክ መረጣና “የተጎጂነት” ስነ-ልቡና ላይ የተመሠረተ የታሪክ አጻጻፍ አየጎመራ የመጣው፣ ከኮሚኒስታዊ መርሆ ጋር ተያይዞ “የነፃነት/የራስን እድል በራስ የመወሰን ጥያቄ” የአብዮታዊ መስመር እየሆነ መምጣት ከጀመረበት (ጨቋኝና ተጨቋኝ መደብ የሚል የትግል መስመር መቀንቀን ከጀመረበት) ጊዜ አንስቶ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡
በእርግጥ በኢትዮጵያ ሁኔታ የዚህ ዓይነት ታሪክ አጻጻፍ ተከስቷል? መቼ ተጀመረ? በእነማን? የትኞቹ የታሪክ መጻሕፍት ናቸው ለዚህ በዋቢነት ሊቀርቡ የሚችሉት? በማለት ጠይቆ በታሪክ ተመራማሪዎች ሊመለሱ እንደሚገባ አምናለሁ፡፡
በሌላ በኩል ይህ አራተኛው ክፍል በተቃራኒው ሆኖ ሊጽፍም ይችላል (ማለትም፣ ሁሉም በታሪክ የተከናወኑ መልካምና አኩሪ ተግባራት በርሱ ቡድን የበላይነትና ግንባር ቀደምት ጥረት የተከናወኑ አድርጎ በመጻፍ የሌላውን አስተዋፅኦ ሊያኮስስ በሚችል መልኩ)፡፡ የተጻፈ ታሪክን በራሱ አመለካከት ለመለወጥ በሚያስችለው መልኩ ተዘጋጅቶበት ሊያቀናብረውም ይችላል፡፡ ታሪክን ተአማኒነት የሚያሳጣው አራተኛው ዓይነት ጸሐፊዎች ሲበራከቱ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ዓይነትና ሌሎች ጥያቄዎችንም እየጠየቅን፣ የታሪክን አጻጻፍና አተረጓጓም ችግሮችን ሁሉ በጋራ ባየናቸው አቅጣጫዎች በጋራ እየፈታንና እየተማመንን መሄድ ለጋራ የአብሮነት ታሪክ የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ፣ ሁሉም የታሪክ ጸሐፊዎች ከግልና ከቡድን ጥቅም በሚመነጩ መድልኦዎች (prejudices) ላይ ተመስርተው አይጽፉም ብሎ ለመደምደም አይቻልም፡፡ ለራስ ማዳላት የሰው ተፈጥሯዊ ዝንባሌ/ድክመት መሆኑም እሙን ነው፡፡ የሚለያየው ልኬቱ/መጠኑ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ነገር አንጻራዊ ነውና፣ ፍጹም የሆነ ነገር በዓለም ላይ ለማግኘት ይከብዳል፡፡ ያንን ማጤን ወደ ሚዛናዊነት ያቃርባል፡፡
5. ሦስቱ ታሪክን ተቀባዮች/ተማሪዎች/አንባቢዎች
ታሪክን የሚጽፍ ማንኛውም ክፍል የጻፈውን ታሪክ አምኖ በመቀበል [የአመለካከቱ መሠረታዊ ከፍል በማድረግ] ለመኖር የሚጥር እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ እርሱ የጻፈውን ታሪክ የሚያነቡት/የሚማሩት/ የሚመረምሩት/የሚቀበሉት ሰዎች/ቡድኖች ግን የተለያዩ መሆናቸው እሙን ነው፡፡ አጥርቶ ለማየት እንዲመች፣ የተጻፈ ታሪክን ተቀብለውና አምነውበት የሚኖሩቱን (በመማር፣በማንበብ/በመስማት አምነው የሚያሳምኑትን) በሦስት በመክፈል ላመላክት፡፡
የመጀመሪያው ክፍል፣ የፀሐፊውን እምነትና ታሪክ የሚጋራ ክፍል በመሆኑ የተጻፈለትን ወይንም የተማረውን/ያነበበውን ታሪክ አምኖና ተቀብሎ የሚኖረው ነው፡፡ ይህ ክፍል፣ ከእኔ ታሪክ ውጭ ያለው ሌላው ታሪክ (በጽሑፍ የሰፈረም ይሁን ያልሰፈረ ትውፊት) ሁሉ ትክክል አይደለም ብሎ ሊያምንም ይችላል፡፡ የእኔ ነው ብሎ አምኖ የተቀበለው ስለሆነ አያስገርምም፡፡ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ የተጻፈን ታሪክ ተምሮ/አንብቦ እኔንና እኔን መሳዮችን አይገልጥም በማለት የሚያስብ ክፍል ነው፡፡ ይህ ሁለተኛው ክፍል በተማረው/ባነበበው ታሪክ ለማመንም ሆነ ተቀብሎ ለመኖር የሸፈተ ልብ ያለው እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ኑሮ ሲሳካለት ታሪክን “ተቀብሎ” የሚኖር፣ ሳይሳካለት (ወይንም የበለጠ የሥልጣን/የተሰሚነት/የጥቅም ሥፍራን ሲሻ) ደግሞ “ታሪክን የሚያጥላላና የልዩነትን ቀዳዳ እየፈለገ የታሪክ ቅራኔን የሚያሰፋ” በመሆን ሊኖር ይችላል፡፡
ለሁለተኛው ክፍል የሚጥመው ታሪክ፣ ጥቅሙንና የበላይነቱን ሊጠብቅለት የሚችለው አጻጻፍ ብቻ ነው፡፡ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ጥቅም ከሌለው (ጥቅሙ በጉልህ ካልታየው) ማማረሩን ይቀጥላል፡፡ በጋራ ታሪኩ ውስጥ በያዘው (አለኝ ብሎ በተረዳው) ድርሻ ላይ የራሱን ለይቶ በማውጣት ይህ የእኔ ድርሻ ነው ብሎ ከማቀናጀትና፣ በሌሎች መልካም የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ እየተሳተፈ ድርሻውን ከማሳደግ ይልቅ ማማረርን የሚወድ ነው፡፡ ይህ ክፍል ምናልባት ከአራተኛው ታሪክ ጸሐፊዎች ጋር የተቀራረበ ሥነ-ልቡናዊ አመለካከት (ባሕሪ) ያለው ይመስለኛል፡፡ ሦስተኛው ታሪክን የሚቀበል/የሚማር/የሚያነብ ክፍል ደግሞ፣ በጋራ ታሪኩ ውስጥ በያዘው (አለኝ ብሎ በተረዳው) ድርሻ የማይረካና የእርሱ ታሪክ የበላይ እንዲሆን ለብቻው የተለየ ታሪክ ለመጻፍ የሚፈልግ ክፍል ነው፡፡ ራሱ ከሚያምንባቸው መረጃዎች ውጭ ሌሎች ተጨባጭ መረጃዎችን፣ እሱን የማይጠቅሙ እስከሆኑ ድረስ፣ የማይቀበል ክፍል ይመስለኛል፡፡ ይህም ከአራተኛው ታሪክ ጸሐፊዎችና ከሁለተኛው ዓይነት የታሪክ ተቀባዮች/አማኞች ተርታ አብሮ የሚታይ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡
ታሪክን የሚጽፉትም ሆነ የሚያነቡት/የሚቀበሉት ክፍሎች የየራሳቸውን እውነት የሚኖሩ እንደሆኑ እገምታለሁ፡፡ ሁሉም ደግሞ የየቡድናቸው “ልሂቃን” (ምሁራን) ይመስሉኛል፡፡ ችግሩ ያለው በአንድ “የጋራ እውነት” ላይ ተስማምተው አንድን የጋራ ታሪክ በማመን ተቀብሎ በስምምነት ለመኖር አለመቻል ይመስለኛል፡፡ የግድ ሁሉም አንድ ወጥ ታሪክ ይኑረው ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ሁሉም ልዩነቱንና አንድነቱን አውቆና ልዩነቶችን አክብሮ በአንድነቱ ላይ ግን እንደ አንድ ሆኖ መሥራት ይጠቅማል፡፡ መቼም ቢሆን አንድ ትክክል (sound) አእምሮ ያለው ሰው ወይም ቡድን ተወያይቶ እውነትን ከሐሰት ውስጥ አንጥሮ ማውጣት አያዳግተውም፡፡
ከዚህ ዋና ጉዳይ ስነሳ፣ በዘመናት መካከል ታሪክን በመልካምም ይሁን በማጣመም የሚጽፉና ልዩነቶችን የሚያሰፉት የየቡድኑ/የየክፍሉ “ልሂቃን” (ምሁራን) እንደሆኑ ለአፍታም እንዳልጠራጠር እገደዳለሁ፡፡ ችግሩ፣ በየቡድኑ የሚገኙት ግለሰቦች ራሳቸውን በልሂቅ ሥፍራ አስቀምጠው “የእኔ ብቻ ይደመጥ” ፉክክር ውስጥ የገቡና እርስ በእርስ እንኳን መደማመጥ የማይችሉ መሆናቸው ነው፡፡ መማር/ማወቅ መደማመጥን ይቀንሳል ልበል? በስፋት በማየት የታዘብኩት ያንን ነው፡፡
አንድ የተጻፈ ታሪክ ድክመት ሊኖረው ይችላልና እኛም (ልሂቃን) ድክመት አለብን ብለው ለመስማማት አለመቻላቸው ዋናው ችግራቸው ይመስለኛል፡፡ “ልሂቃን” (ምሁራን)፣ የእኛ ሃሳብ ብቻ ትክክል ነው የሚል እልህ አለባቸው፡፡ እልህ የጋራ ታሪክን ይንዳል እንጂ አያንጽም፡፡ ሌሎች ታሪክን ተቀባይ የሆኑ የየቡድኑ አባላት (“ልሂቅ” (ምሁር) ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ) የየግል “ልሂቃኖቻቸውን” እየተከተሉ የሚሄዱ ናቸው - እንደሚያገኙት ጥቅም (ጥቅም ደግሞ እንደ ባህሉና አመለካከቱ በዓይነትና በመጠን የሚለያይ ጉዳይ ነው)፡፡ ምክንያታዊነትን ገንዘቡ ያላደረገ፣ ወደ ነዱት የሚነዳ ትውልድ አይግጠማችሁ፡፡
በጥቅሉ፤ የጥቂት ፀሐፊዎችን የትምህርትና የፖለቲካ አቋም፣ የቋንቋና የፈለቁበትን ማህበረሰብ መሠረት በማሰብ፣ በታሪክ ለማመን መቸገር ወይም ላለማመን መወሰን የእውቀት ደርዝ አይደለም፡፡ የተጻፉ ታሪኮችን ማንበብ ስለራሳችን አንድነትና ልዩነት የማወቅ አንዱ እርምጃ ነው፡፡ ያነበበ አንድነቱንና ልዩነቱን መረዳት ይችላል፡፡ እኔ መርጦ በማመን ላይ ሳይሆን፣ ሁሉንም በመረዳት ላይ ነው ማተኮር የምሻው፡፡ ሁሉን መረዳት ከጽንፈኛ አስተሳሰብ ይታደጋል - ሚዛናዊ ያደርጋል፡፡ መካከለኛው ዓይን የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ይመስለኛል፡፡ በጽንፍ በሚያዩ ሁለቱ ዐይኖቻችን እስከ ዛሬ ያየናቸውን ሁሉ አይተናል - የተንሸዋረሩ እይታዎች ይበዛሉ፡፡
6. ታሪክ ለምኔዎች
እኔ እየኖርኩኝ ያለሁት ዛሬን ነው፤ ስለዚህ ታሪክ ምኔ ነው የሚሉ ብዙዎች ሊኖሩም ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩልም አሁን ሊያደርጉት በሚፈልጉት ድርጊት ላይ፣ ያለፈው ታሪክ (ድርጊት) ገደብ ያስቀመጠባቸው የሚመስላቸው ቢኖሩም ምንም አያስደንቅም፡፡ ታሪክ ለንፅፅር የሚጠቀሙበት የትዝታ ምዕራፍ እንጂ፣ የአሁንን ድርጊት የሚገድቡበት መሠረታዊ የእምነት መርህ/ዶግማ አይደለም፡፡ የተፈጸመ ድርጊትን አይቀይሩትም፡፡ ተከናውኖ አልፏል፡፡ ነገር ግን ታሪክ የሚቀጥል ድርጊት ከመሆኑ አንጻር፤ መልካሙን ወስዶ እየተጠቀሙበት፣ መጥፎውን ደግሞ ማሻሻል፣ ማስቀመጥ ወይም መጣል እንደሚቻል ማወቅ አንድ የዕውቀት ደርዝ ነው፡፡ ይህ ተስኖን ይመስለኛል በየጽንፉ በመጓተት የምንጯጯኸው፡፡ ጩኸቱን ከፍ በማድረግ የሚቀባበሉት ደግሞ ታሪክ ለምኔ ባዮቹ ናቸው፡፡ መልካም መልካሙን የጋራ (የሕዝብ) ታሪክ በመያዝ መልካም ያልሆነውን ማረም እየተቻለ በታሪክ መቆዘምና መጣላት ሥፍራ ሊሰጠው አይገባም፡፡
መጥፎ ሽታን ወደ መልካም መዓዛ ለመለወጥ እንደሚቻል ይታወቃል፡፡ ይሁንና መጥፎ ሽታን ወደ መልካም መዓዛ የለወጠውን “ሽቶ” ሁሉም በእኩል አይወደውም (የሁሉም ሽቶ ቃና በሁሉም ሰው የሚወደድ ላይሆን ይችላልና)፡፡ የሰዎች ምርጫም እንዲሁ ይለያያል፡፡ ከዚህ አንጻር፣ በተለያዩ የታሪክ ፀሐፊዎች የተለያዩ የታሪክ አቀራረቦች ሲንጸባረቁና ቅራኔም ያለባቸው ሲመስል፣ ታሪክን አንብበው ለመረዳት በሚሞክሩት ሰዎች ዘንድም (እንደ ብሔረሰባቸውና እንደ ትምህርት ደረጃቸው) አንድን ታሪክ የመቀበል ወይንም ያለመቀበል “ችግር” ቢያጋጥም አያስደንቅም፡፡ ያም ሆኖ ግን፣ በራስ ላይ እየሳቁ አብሮ ለመኖር ታረክን የጋራ መሳቂያ/መደሰቻ/መደመሚያ እና የመታረቂያ አውድ አድርጎ መመልከት መልካም ይመስለኛል፡፡ እስቲ በራሳችን ላይ አብረን መሳቅን እንልመድ፡፡ በራስ መሳቅ ይፈውሳል፡፡

ታሪክ፣ የታሪክ ጸሐፍትና ተቀባዮች

Read 442 times