የአጭር አጭር ልብወለድ
እንደ ወትሮው ለዕለት ጉርሴ ተጣድፌ የወጣሁት ወፍ ጭጭ ሳይል ነው፡፡ ጎኔን ከማሳርፍባት ጭርንቁስ ጎጆዬ ተስፈንጥሬ፣ ከሥራ ገበታዬ ለመከተት፤ ብዙ ርቀቶችን ማቆራረጥ ይጠበቅብኛል፡፡ ለሰዐት እንደሚሮጥ አትሌት፣ በላይ በላይ ሳልተነፍስ የደረስኩበት ቀን ትዝ አይለኝም፡፡ ይኼ ሁሉ ግራ ቀኝ መወዝወዝ፣ ጎተራን ለማደላደል ነው፤ያውም በመናኛ ፈረንካ፣ይኹና፡፡
እንደ እናት ክንድ፣ እቅፍ ድግፍ አድርጋ፣ ከሥራ ገበታዬ የምትከተኝ ባለፉርጎዋ አውቶቢስ፣ ዛሬ አለጠባይዋ የውሃ ሽታ ሆናለች፡፡ ከሥራ ሰዐት መግቢያ ጥቂት መሽረፉ፤ በሥጋ ኮንክሪት ለተሞላው ዱለኛው አለቃዬ፣ ሽመል ማቀበል ነው፡፡ ዳግም ከተላተምኩት፤ ቆሜ የምሄድ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ቀደም እየተረገፈገፈ፤ እላዬ ላይ ለመፈርስ ተገልግሎብኛል፡፡ አሁን በቀጭን ገመድ ላይ እንደሚራመድ አስማት ሠሪ፣ ምንም አይነት ስህተት እንድሰራ አይፈቀድልኝም፡፡ ለእንጀራ ገመዴ ዋስትና ብቸኛው መላ፤አስማተኛ መሆን ነው፡፡
ሰዐቱ እየነጎደ ነው፡፡ ባለፉርጎዋ አሁንም ብቅ አላለችም፡፡ በሥጋት ተወጥሬ ወዲህ ወዲያ በመንከላወስ ላይ ሳለሁ፣ ድንገት አንዲት ከርካሳ ግልገል ሚኒባስ፣ ከፊት ለፊቴ ገጭ አለች፡፡ ሆድ ዕቃዋን ከፍታ፣ አላፊ አግዳሚውን ወደ እልፍኟ መጋበዝ ጀመረች፡፡ ኪሴ ውስጥ ያለው ፈረንካ አያወላዳም፡፡ የባለፉርጎዋ አስቤዛ ነው፡፡ ልጨክንበት ወሰንኩ፡፡ ምርጫ የለኝም፤ ከቢጤዎቼ ጋር በአንድነት ተደምሬ፤ ሚኒባሷ ላይ ተሰቀልኩ፡፡
ሚኒባሷ እየተንፏቀቀች፣ የአዲስ አበባ መግቢያ ደጃፍን ለመሳለም ተቃርባለች፡፡ ከትውልድ ከተማዬ የተሰደድኩት በምክንያት ነው፡፡ ኑሮ እጅ ወደ ላይ ብሎ ቢማርከኝ፤ከፉ ቀንን እንደ ቅዝምዝም ጎንበስ ብዬ ለማሳለፍ፤ እልፍ አልኩኝ፡፡ ቤት ኪራይ ሽሽት፤ስንፏቀቅ ስንፏቀቅ፤ ድንገት ራሴን ከአዲስ አባባ ማዶ አገኙሁት፡፡
“ሹፌር ድምጹን ቀንሰው፣እንዴት እናውራ?” አለች ከጎኔ የተቀመጠችው ባለቃጭል ድምጽ ጉብል፡፡ ልብ አንተርክክ ጠይም አሳ መሳይ ናት፡፡
“ይሄን የመሰለ የውብት አድባር እስካሁን እንዴት ዘነጋሁት? ጤባ ነኝ፤” አልኩኝ ለራሴ፡፡
ጤባ የምትለው ቃል፣ ከውስጤ ማጉተምተም አፈትልካ የወጣች መስሎኝ፤ተሳፋሪውን ዘወር ዘወር ብዬ ጎበኘሁት፡፡ ምንም የተፈጠረ ነገር የለም፤ በቀጭኑ የተለቀቀው ሙዚቃ፣ ተሳፋሪውን አርምሞ ውስጥ ከትቶታል፡፡ ከያኒው ኮርኳሪ ስንኞችን በዜማ ጅረት ላይ እንደ ታንኳ ቀዝፎ ከጆሮ ያደርሳል፡
ቀጭን ጌታ ሄዶ ቀጭን ጌታ መጣ
ደንዳናው ጫንቃዬ አመል አላወጣ
ልቤም አለገመም
ሆዴም አልጎደለም
እኔ ምንተዳዬ
የምል ወለም ዘለም፤
“ይሄ ደፋር ከያኒ እየቦጠለቀ እኮ ነው፤ እኔ ቦተሊካ አይገባኝም፤ቅርብ አዳሪ ነኝ፤ቅርብህን ተመልከት የተባልኩ ባለራዕይ ትውልድ፤” በሩቁ ቦተሊካ፣ የቅርቤን ጠይም በመዘንጋቴ እየተቆጨኹ፣ በዐይኔ ልዘይራት ፊቴን ወደ እርሷ መለስኩ፡፡
ውበቷ ከቅድሙ በባሰ ተጋነነብኝ፤ ስልኳን ጆሮዋ ላይ ለጥፋ ታንሾካሹካለች፡፡ የፍቅር ጨዋታ እንደሆነ አካላዊ ቋንቋዋ ያሳብቃል፡፡ በየመሀሉ እያዋዛች ትስለመለማለች፡፡ ቅናት ቢጤ በውስጤ ሲያቆጠቁጥ ተሰማኝ፡፡ በማላውቃት ሴት በተፈጠረብኝ የስሜት መቅበዝበዝ ራሴን ታዘብኩት፡፡
ባለሦስት እግር መንኮራኮር ከሚኒባሷ ፊት ጥልቅ ስትል፣ መብከንከኔ ተናጠበ፡፡ የዘዋሪው ፍሬን አያያዝ፣ እኔን እና ውቧን ጉብል አካል ለአካል “ቺርስ” አባባለን፡፡
“ውይ ተረፍን” አለች የተበታተነውን የስልኳን ቀፎ እየገጣጠመች፡፡
“ደግማ ብትገባበት ምን አለ?” ወርቃማው ዕድል እንዳያመልጠኝ ምላሴን አሾልኩ፡፡
“ምን ማለት ነው?”
“ደግሜ እንድገጭሽ”
ቀልዴ እንዳልከሸፈ የገባኝ፤ ጠይም ገጽታዋ እንደ ጸሐይ ሲበራ ነው፡፡ “የመጀመሪያው ቀልድ ከተሳካልህ፤ክሌቱ፣ሰልስቱ ብለህ አከታትል፤ያን ጊዜ የዘራኽውን ሳቅ ታጭዳለህ፤” ብሎ የመከረኝ ሴት አውል ባልንጀራዬ፣ ትዝ አለኝ እና ወዝ ያለው ጫወታ ላክል አፌን ሳሞጠሙጥ፤
“ወራጅ” አለች
ሙዳ ሥጋ ከላዬ ላይ ተገንጥሎ ሲወድቅ ተሰማኝ፡፡ በአቅመቢስነት ስሜት በዐይኔ ተከተልኳት፡፡ ቄንጠኛነቷ ከሰረገላ ላይ የምትወርድ ንግሥት አስመስሏታል፡፡ ጠይም አስማት፡፡ ልዘይራት ስሰናዳ፣ በሦስት ፊደል በታነጸ መቀስ ቃል ተሰናካከልኩኝ፡፡ ወ ራ ጅ! ከከካርሳዋ ሚኒባስ ያተረፍኩት የቃል ውርስ፣ ሰቀቀን ሆኖብኛል፡፡ ሚኒባስ ላይ በተሰቀልኩ ቁጥር፣ ጦሰኛውን ቃል ላለመስማት፣ ጆሮዬን እደፍናለሁ፡፡ ወራጅ! ለካስ ተሰቅሎ መውረድ እንዲህ ያማል፡፡ ወራጅ!
Thursday, 08 August 2024 06:51
ሚኒባሷ
Written by ደረጀ ይመር
Published in
ልብ-ወለድ