Thursday, 08 August 2024 00:00

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ የችግኝ ተከላ አከናወነ

Written by 
Rate this item
(3 votes)
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ለስድስተኛ ዙር “የምትተክል አገር፣ የሚያጸና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አንድ አካል የሆነ የችግኝ ተከላ ስነ ስርዓት ዛሬ በእንጦጦ ፓርክ አከናውኗል። በስነ ስርዓቱም የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ እናትዓለም መለሰ፣ በአዲስ አበባ ምክር ቤት የሴቶችና ሕጻናት የማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዘይነባ ሽኩር እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ታዋቂ ግለሰቦች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ከማዕከል እስከ ወረዳ የሚገኙ የኮሙኒኬሽን አመራሮችና ሰራተኞች መሳተፋቸው ተገልጿል።
ስነ ስርዓቱን በንግግር ያስጀመሩት ወይዘሮ እናትዓለም መለሰ፣ ታላላቅ ሃሳቦችን ስለሚያነሱ ግለሰቦች እና የእነርሱን ፈለግ ሲለሚከተሉ ወገኖች በማውሳት፣ የአረንጓዴ አሻራን ሃሳብ ማሰራጨት እንደሚገባ በአጽንዖት ገልጸዋል። ለስነ ስርዓቱ ተሳታፊዎች "አምና አብራችሁን ነበራችሁ። ምን ያህል ሃሳብ እንዳሰራጨን ሳይሆን እንደተከልን ታስታውሳላችሁ" ሲሉ ተናግረዋል።
ሃላፊዋ አክለውም፣ አገር በቀል ችግኞችን የመትከልን አስፈላጊነት ዘርዝረው፣ "ችግኞቹ የራሳቸው ታሪክ አላቸው። እናንተ ስትተክሏቸው ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠር ቶን ታሪክ ይኖራቸዋል።" ብለዋል።
በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ አገር በቀል ችግኞች በብዛት የተተከሉ ሲሆን፣ ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡ የስነ ስርዓቱ ተሳታፊዎች ችግኝ በመትከላቸው ዕርካታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል። ታዋቂው ተዋናይ እና የማስታወቂያ ባለሞያ ጥላሁን ጉግሳ እጅግ በጣም የጠለቀ ደስታ እንደተሰማው በመጠቆም፣ “ባለፈው ዓመት ‘ለነገ ዛሬ እንትከል’ ብለን ነበር። ያ ነገ ዛሬ ሆኖ ችግኝ ለመትከል በቅተናል። ይህንን ስራ አጥብቀን መያዝ ይኖርብናል።” በማለት ለአዲስ አድማስ ተናግሯል።
አያይዞም፣ እርሱ ለ12 ዓመታት ያህል በትወና እና በአዘጋጅነት የሚሳተፍበት “ቤቶች” የተሰኘው ሲትኮም ድራማ ላይ ስለአረንጓዴ ልማት መልዕክቶች ሲተላለፉ መቆየታቸውን አስታውሶ፣ የድራማው ተሳታፊ ባለሞያዎች ለ12 ዓመታት የችግኝ ተከላ እና እንክብካቤ ስራ ሲሰሩ መቆየታቸውን አስረድቷል።
ጋዜጠኛ ሽመልስ ለማ በበኩሉ፣ በዚህ ስነ ስርዓት ላይ በመሳተፉ ከልብ የመነጨ ደስታ እንደተሰማው ገልጿል። በተጨማሪም፣ ይህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን አረንጓዴ ልማት እያሳደገ እንደሚገኝ አመልክቷል። ሁሉም ወገን በዚህ መርሃ ግብር እንዲሳተፍ ጋዜጠኛ ሽመልስ ጥሪውን አቅርቧል።
 
 
 
 
 
 
 
 

 

 
Read 711 times