አንድ ተረት አለ። የኢንዶኔዢያ ሳይሆን አይቀርም።
አንዲት የመንደሩ ሰው ንብረት የሆነች በግ አልፋፋ ብላ ህዝቡ ሲጨነቅ፤ ሹሙ አዩና፤ ወደ አደባባዩ መጥተው፤ በውይይት መልክ፤ በኃይለ-ቃል ጠየቁ።
"ምንድን ነው ለዚች በግ ያስጨነቃችሁ"
የህዝቡ ተወካይም፤
"ማሳደግ አቃተን። ግጦሹ ተወደደ። የአራዳው ዘበኛ ያገኘችውን እንድትግጥ እድል አልሰጥ እያለ አለንጋ ያቀምሳታል። እንዳናርዳት አልሰባች፣ እንዲሁ እንዳንተዋት ጣጣዋ ተረፈን! እንዲያው ምን ይመክሩናል ሹም ሆይ?"
ሹሙም፤
"ለምን እኔ ግቢ መጥታ አትፋፋላችሁም?" ሲሉ፤ ጫን ብለው ጥያቄውን በጥያቄ መለሱ። መቼም ሹም ናቸውና የሹም ጥያቄ በአሉታ አይመለሰም። ከፊሉ ህዝብ ጭጭ አለ። ከፊሉ እሺም እምቢም ማለቱ በማይገባ ቋንቋ ራሱን ነቀነቀ። ጥቂቱ "ይሁን፤ እንደርሶ ግቢ የሚመች የት ይገኛል። ግቢዎስ ግቢያችን አይደለም ወይ?!" አላቸው።
በጊቱ ሹሙ ግቢ ገባች።
ጊዜ እየገፋ መጣ። በጊቱ ግን አልወፈረችም። ጭራሽ እየከሳች መጣች። ህዝቡ ወደ ሹሙ ግቢ አሻግሮ እያየ "ኧረ እቺን በግ አክስተው ሊገድሏት ነው፤ ጎበዝ?" እያለ በየመንደር መናኸሪያው ያጉተመትማል። ደፈር ያለም ሹሙን ወይም ባለሟሎቻቸውን ይጠይቃል። በተለያየ ጊዜ የተለያየ መልስ ያገኛል።
አንዴ፤ "የቤተ መንግሥት አጥር እየታከከች እየዋለች ስላስቸገረች ግጦሽ ተከልክላ ነው" ይባላል።
አንዴ ደግሞ፤ "የንጉሥ ማሳ ገብታ በአፈ-ላማ ተያዘች" ይባላል፤
"አሞሌ ሲሰጧት የቀላቢዋንም እጅ ልሼ ካልበላሁ እያለች አስቀየመችውና ተቀጣች" ይባላል። ደሞ ሌላ ቀን፤ እንዳጋጣሚ ደግሞ ባለሟል ይመጣና እውነቴን ያወጣል፤ "አፏን ሸብበው ሳር-ማሳ እየከተትዋት እንዴት ትወፍር። በዚያ ላይ ከወፈረች የጠገበች ትመስላለች፤ የህዝብ ሀብት ስለሆነች እንደከሳች ብትቆይ ምን አለበት? ትባላለች" ይላል።
ሌላ ውስጥ አዋቂ ይቀጥላል። "በተጨማሪም ደግሞ ከሌሎች በጎች ጋር ሲያዩዋት ታረግዝብናለች፣ "ወንድ" የወለደች እንደሁ ኋላ ምን ሊባል ነው፤ ሲሉ ነበረ" ብሎ ያጋልጣል። ጨመር አድርጎም፤ "ጎረቤትና የሩቅ አገር ሰው ሲመጣ ዐይን ትገባለች ብለው ገመድ ሆዷ ላይ ያስሩባታል" ብሎ ሚስጥር ያወጣል።
እንዲህ እንዲህ ስትባል፤ ቀን ገፋ። በሹሙ በኩል ያልፍልሻል፤ አይዞሽ ትጠግቢያለሽ፣ ስትባል፤ ህዝቡ በበኩሉ፣ ዘንድሮስ እንጃላት ሲላት፣ ገናን አለፈች። ፋሲካ ደረሰ።
ህዝቡ ከእንግዲህ መበያዋ ደረሰ ሲላት፣ ገናን አለፈች። ፋሲካ ደረሰ።
ህዝቡ እንግዲህ መበያዋ ደረሰ በቃ አለና አንገቱን ደፋ።
ይሄኔ አንድ ሽማግሌ የመጣው ይምጣ በሚል ድፍረት፤ ወደ ሹሙ ባለሟሎች ሄደው፤
"ኧረ እቺን በግ ሹሙ አክስተው ሲገድሏት ነው። መቼ ሊበሏት ነው?" ሲሉ ጠየቁ።
የባለሟሎቹ ተወካይም፤
"ገና ንጉሥ ፊት ቀርባ፤ አክሷት ባሉበት አፋቸው፣ ብሏት ያሉ እንደሆነ ነዋ!" አላቸው።
…
እንደ ከሲታዋ በግ ማደግ ያቃተው ዲሞክራሲያችን ያልታደለ ነው። እንደልብ ግጦሽ ሳር ማጣት የምስኪንነት ጥግ ነው። ደህና ግቢ ይግባ ሲባል በአፈ-ላማ ተይዞ፣ በቅጣት ታጥሮ፣ ግጦሽ ተከልክሎ፤ አፉ ተሸብሽቦ፣ ከተራበ አደጋ ነው ተብሎ፣ በJamming ታፍኖ፣ ከውጪ ሰውም ተከልክሎ… ከቶውንም ሊዘልቅ አይችልም። የፕሬስ ነፃነት "የተከለከለ የበሰለ ፍሬ" በሆነበት ቦታ የዲሞክራሲ ህልውና ቀርቶ ሽውታውም አይታሰብም።
በሀገራችን እንደ ምስኪኗ በግ የሆኑ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ከዛሬ ነገ ይመለሳሉ ሲባል ጭራሽ "እነዚህ ጥያቄዎች የእኛ አልነበሩም እንዴ?" እስከሚባል ድረስ ከኦርጅናሌ ባለቤታቸው እጅ ይወጣሉ። የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄዎች፣ በተለይም ደግሞ የፕሬስ ነጸነት ጥያቄ፣ ከከሲታዋ በግ በበለጠ እሰው ግቢ ገብቶ ቀልጦ የቀረ ይመስላል። ሰሚ ጆሮ፣ አዛኝ አንጀት ያገኘ አይመስልም። ይልቁንም "ጎራዴን እጀታውን የያዘ ያሸንፋል" የተባለው አነጋገር ዛሬ ከምንም ጊዜ የበለጠ ሚዛን ያነሳው በሱው ሰበብ ነው። "ስለቱን የያዙ ቢንጠለጠሉበት እጃቸውን ማጣት ይሆናል ዕጣ-ፈንታቸው። "ከእጃችን በቀር የምናጣው ነገር የለም" ካላሉ በቀር። ( We have nothing to lose except our chains እንዲሉ)
የተሄደበት መንገድ ሁሉ ወደዚያው ወደተነሳበት የሚመልሰን ከሆነ "ነገር ቢኖራችሁ ነው እንጂ፣ የማለዳው መንገድ ጠፍቶባችሁ ነው ወይ?" ያሰኛል።
አንድ ዘመን የአዲስ አበባ ሰው የኮክቴል ድግስ ሲጠራ ጠብ የሚልለት ነገር ሳይኖር በባዶ ሆዱ ዘፈን ብቻ እየሰማ፣ ሠርግ አጅቦ መመለሱ ልማድ ሲሆንበት "የድጋፍ ሠልፍ" የሚል ስም አውጥቶለት ነበር አሉ።
ለአሳታፊ ዲሞክራሲ ቁልፉ ግትርነት የሌለበትና "ስሜት ያልተጫጫነው" ውይይት ለማካሄድ መቻል ነበር ቢያድለን፤ ሆኖም ነገራችን ሁሉ "ቤቴን ሠርቼ ጣራ ስመታ ሆነ እንጂ ምክራችሁስ የሚወድቅም ነገር አልነበረው" ያለው ጮሌ ቤተ-ሰሪ ዓይነት ሆነ።
"ለዲሞክራሲያዊ ውይይቱ" ሁሉ የጦር ስትራቴጂ አውጥተን፣ አንዘልቀውም ብሎ ማሰብ የአባት ነው። ረዥምና ዘላቂ በሚመስለን ዕድሜያችን ውስጥ ምን እንደሚያጋጥመን ሳናውቅ የተከለከለ መንገድ፣ የተዘጋ በር፣ የታጠረ አዕምሮ፣ የተሸበሸበ አፍ፣ በጓጉንቸር ሽቦ የተለጠፈ ብዕር ይዞ ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ፣ ለነፃነትና ለፍትህ የቆመ ፕሬስ ማለም፣ የማለም "ነፃነት" እንጂ የፕሬስ ነፃነት አይሆንም። ማለምም ተበርትቶ- መተኛት ከተቻለ ነው። ከቶውንም በስርጥ መንገድም መጣ በቀለበት መንገድ፣ በአውራ ጎዳናም መጣ በመጋቢ መንገድ፣ እንደብራ መብረቅም መጣ እንደ ነጎድጓዳማ ዶፍ፤ "ዝናብና አዋቂ ሲመጡ ያስተውላሉ" ነውና ዓይኑን ለከፈተ ዜጋ የቀጭን ትዕዛዛት አመጣጥ ይታየዋል። "ገና ንጉሥ ፊት ቀርባ አክሷት ባሉበት አፋቸው፣ ብሏት ያሉ እንደሁ ነዋ" እንደተባለችው በግ የመሆን ሥጋት ለተጋረጠበት የሀሳብ ነፃነት፤
"አቤት በሰማይ ያለ ምፅአት
አቤት በምድር ያለ መዓት" ቢለው፤ "የት አየኸው?"፣ "አመጣጡን መች አጣሁ" የሚለው ተረት ወቅታዊ ሆኗል። ከሁሉም ይሰውረን።
Saturday, 10 August 2024 21:57
"አቤት በሰማይ ያለ ምፅዓት!" አቤት በምድር ያለ መዓት" "የት አየኸው?"፤ "አመጣጡን መች አጣሁት!"
Written by Administrator
Published in
ርዕሰ አንቀፅ