Saturday, 10 August 2024 21:58

የጎፋ መሬት መንሸራተት አደጋና የአርባ ምንጭ ስጋት

Written by  ዳንኤል ካሳሁን
Rate this item
(3 votes)

በድንገት ሳይጠበቅ ተከስቶ፣ ውጤቱ ግን እጅግ ግዙፍ የሚሆንባቸው ክስተቶች አያሌ ናቸው። በተለያዩ አባባሎች ላይ እየታከለ አንድን ጉዳይ ለማግነን ጥቅም ላይ ይውላል። ማነው ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ የ“መሬት መንሸራተት” ነው። ያልተጠበቀና ሥር ነቀል የሆነ የምርጫ ውጤት፤ Landslide Victory፣  ያልተጠበቀ ቡድን ድል፤ Landslide Win፣ ያልተጠበቀ ድጋፍ፤ Landslide Support ወዘተ ይሰኛሉ። ወደ ገሃዱ ዓለም ስንመጣ ግን የመሬት መንሸራተት የሚያመለክተው አንድ የላይኛው የመሬት ክፍል በከፍተኛ ጉልበትና ፍጥነት የሚያካሂደው ቅጽበታዊ እንቅስቃሴ ነው።
የመሬት መንሸራተት ዕውቀት ሲጠነሰስ፡
ስለ መሬት መንሸራተት ሲነሳ ቀድሞ ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው ጉዳዩን በማይረሳ መልኩ ከበርካታ ዓመታት በፊት የጂኦሞርፎሎጂ (Geomorphology) ኮርስ ያስተማረንን ፕሮፌሰር ነው። ብራንካቾ የተባለ ድንቅ ጣሊያናዊ ምሁር። ለትምህርታዊ ጉዞ ወደ ወሎ፣ ጎንደርና ጎጃም ይዞን ተጉዟል። የተለያዩ ሥፍራዎችን በመቃኘት ሰፊ የግንዛቤ አድማስ እንዲኖረን አስችሎናል። ስለ መሬት መንሸራተት ከቃኘናቸው ስፍራዎች አንዱ የደሴ ከተማ ነው። በጦሳ ተራራ ላይ የሚታዩ የመሬት መንሸራተቶች ጥለው ያለፏቸው ጠባሳዎች (landslide scars) ይታያሉ። በከተማው የተገነቡ የተለያዩ የመከላከያ ስራዎች አሉ። ከደሴ በስተደቡብ ምሥራቅ የሚገኘው ከ“ዶሮ መዝለያ”  አካባቢ የመሬት መንሸራተትን በተመለከተ ጥሩ ትምህርት መቅሰሚያ ነው። ከመስክ ጉዞው በኋላ በጉዳዩ ያደረብኝ ፍላጎት አልተቋረጠም፣ የመሬት መንሸራተት ሲከሰት ትኩረቴ ይሳባል።
የመሬት መንሸራተት ለምን?
የመሬት መንሸራተት አደጋ የመለኮታዊ ፍርድና ቅጣት ምሳሌ ሆኖ በበርካታ ማህበረሰብ ይታመናል። በጃፓን አፈ ታሪክ ተራሮች የመናፍስት መኖሪያ ሥፍራ ናቸው። የመሬት መንሸራተት የሚከሰተው ደግሞ የተራራው መናፍስት በማህበረሰቡ ሲናደዱ ነው ተብሎ ይታመናል። የመሬት መንሸራተት ሲከሰት “ተራራው ጭንቅላቱን እየነቀነቀ ነው” ብለው የሚያስቡ አካባቢዎችም አሉ።
ኢትዮጵያ የተራራማና ኮረብታማ ሥፍራዎች  ከሚበረክቱባቸው አገራት አንዷ ናት። በእሳተ ገሞራ አማካይነት በተፈጠሩ ተራሮች ሳቢያ፣ በስምጥ ሸለቆ በሚፈጠር የመሬት ገጽ መዛነፍ ሳቢያ፣ እንዲሁም ወንዞቻችን በሚፈጥሩት ሸለቆዎች ሳቢያ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ተዳፋትነት ባላቸው መሬቶች ላይ ይኖራሉ። በተዳፋት መሬት ላይ የሚገኝ አፈሩና ደንጋዩ አንድ ቦታ ረግቶ ለመቀመጥ ያዳግተዋል። ውሎ አድሮ መንሸራተቱ አይቀሬ ነው። የስበት (ግራቪቲ) ኃይል ልክ እንደ ማግኔት ወደ ቁልቁል ይስበዋል። የተዳፋት መጠኑ ከፍ ባለበት ስፍራ የስበት ጉልበቱም ከፍ ይላል።
ለምን በዝናብ ወቅት ይበረክታል?
ቁልቁለታማ በሆነ ስፍራ ላይ በሚዘንብ ወቅት በአፈርና ኮረት ቅንጣቶች መሃል በሚኖረው ክፍተት ውሃ ይቋጠራል። ባጋደለው መሬት ላይም ክብደትን ያስከትላል። በተጨማሪም የዝናብ ውሃው ወደ ከርሰ ምድር በሚሰግርበት ወቅት ልክ እንደ ሸክላ የተጠቀጠቀ ንጣፍ ሲያጋጥመው መስረጉ ይስተጓጉላል። በውጤቱም እንደ ሳሙና የሟሟለጭ (lubrication) ባህሪ አስከትሎ፣ የላይኛው የመሬት ክፍል ቁልቁል እንዲንሸራተት ያመቻቻል።
ጭቃ ሰውን ይውጣል?
ሰዎች ሃፍረት ሲሰማቸውና የሰውን ዐይን ፍጹም መሸሽ ሲሹ በተለምዶ “መሬት ተሰንጥቃ ብትውጠኝ” ብለው ይመኛሉ። ከመሬት መንሸራተት አደጋዎች አንዱ ባህሪ ሰዉን፣ እንስሳቱንና አገር ምድሩን በጭቃ ለውሶ መዋጥ ነው። ከጎፋ የመሬት መንሸራተት ተጠቂዎቹ አንዷ ወይዘሮ ፀጋነሽ ኦቦሌ፣ ስድስት ልጆቿን ጨምሮ ከብዙ ሰዎች ጋር በጭቃ ተውጣ እንደነበር አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። መትረፏ ተአምር ነው።
አደጋን አስከፊ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች አንዱ ፍጥነቱ ነው።  ያላንዳች ማስጠንቀቂያ ከች ይላል። ለሽሽት ጊዜ አይሰጥም። በሰዓት ከ56 ኪሎ ሜትር በላይ ሊፈጥን ይችላል። መሬቱ መንሸራተት ሲጀምር ኃይለኛና ጆሮ የሚያደነቁር ድምጽ ሊሰማ ይችላል። ለምሳሌ ከጎፋው አደጋ በተአምር የተረፈው ረዳት ኢንስፔክተር፤ መሬቱ “የፍንዳታ አይነት ድምጽ” አሰምቶና ተወርውሮ ወደ ህዝቡ እንደመጣ ተናግሯል። በከፍተኛ ፍጥነትና በድንገተኝነት ዛፎች፣ ድንጋዮችና አፈሮች ቁልቁል ይዘረገፋሉ። ምድሪቱ  ስለምትናወጥ ሰዎች ሚዛናቸውን ያጣሉ። በየትኛው አቅጣጫ እንደሚሸሹ ስለማያውቁ፣ በፍጥነት በሚንቀሳቀሱ ፍርስራሾች ሊደናቀፉና በጭቃ  ሊቀበሩ ይችላል።
የመሬት መንሸራተት ሲከሰት አፈር፣ ድንጋይ፣ ቤት፣ ቁሳቁስ፣ ሰውና እንስሳን ደበላልቆ ሲያጓጉዝ ለየት ያለ ጉዳይም ያጋጥማል። ለምሳሌ ከ40 ዓመታት በፊት በጣልያን አንድ የመኖሪያ ቤት 60 ሜትሮች ቁልቁል ተንሸራቷል። አንዳችም ጉዳት ሳይደርስበት በአዲስ ስፍራ ላይ በመቆሙ “ተጓዡ ቤት” የሚል ስም ወጥቶለት የጎብኚዎች መናኸሪያ ሆኗል። ሌላም አለ። በአሜሪካ የዋሺንግተን ግዛት የሚገኝ ደን በመሬት ናዳ ተንሸራቶ ቁመናው ሳይዛነፍ በሀይቅ መሃል ደርሶ ታይቷል። “ተንሳፋፊው ደን” ተሰኝቶ የጎብኚዎች መዳረሻ ሆኗል።
በተራራማና ሸለቆዎች አካባቢ ዝናብ ባይኖር እንኳ ርዕደ መሬት ሲከሰት የመሬት መንሸራተት ሊቀሰቅስ ይችላል።  ይህ አልበቃ ብሎ በአሉታዊ የመሬት አጠቃቀም ዘይቤ ሳቢያም የመሬት መንሸራተት ሊቀሰቀስና ሊፋጠን ይችላል።
የአየር ንብረት ለውጥና የመሬት መንሸራተት፡
ብዙ ሰዎችና ሚዲያው የአየር ንብረት ለውጥ በምድር ሙቀት መጠን መጨመር ሳቢያ ብቻ እንደሚከሰት አድርገው ይረዳሉ። ስለተጽዕኖው ሲያስቡም የበረሃማነት፣ የዝናብ እጥረት፣ የድርቅ፣ የደን ቃጠሎ፣ የቬክተር ወለድና የወባ በሽታ፣ ወዘተ መስፋፋትን ይጠቅሳሉ። ነገር ግን የአየር ንብረት ከመጠን በላይ የሆነ ዝናብ አስከትሎ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋዎችን ሊያስከትል ይችላል። ዝናቡ ሲኮሳተርብንም ሆነ ሲስቅልን ትልቅ አደጋ ይገጥመናል ማለት ነው። ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፤ የአየር ንብረት ለውጥ እየተባባሰ በመሄድ መጪው ጊዜ እጅግ ፈታኝ ይሆናል። የመሬት መንሽራተትም እየተባባሱ ከሚሄዱ አደጋዎች አንዱ ነው።
አንድ ያጣላል?
“አንድ ያጣላል” የሚለው አባባል ደስ የሚያሰኘው ለበጎ ተግባር ሲሆን ነው። ጉርሻ ባንድ ብቻ አይቆምም... የቡና ስርዓትም በአቦል አይጠናቀቅም... ቶና እና በረካና ደጋግሙ ይባላል እንጂ። አንዳንዴ የሰው ሰራሽም ይሁን የተፈጥሮ አደጋ በአንድ ጊዜ ጥቃት ሳይቋጭ ተደጋግሞ ከተከሰተ መከራው ወደ አሰቃቂነት ደረጃ ይሸጋገራል። ለምሳሌ የአሜሪካው የ1994 ዓ.ም የሽብር ጥቃትን እንውሰድ። በአልቃይዳ የተጠለፈው የመጀመሪያው ቦይንግ አውሮፕላን፣ የኒውዮርክ ዓለም ንግድ ማዕከል የሰሜን ታወርን የመታው ከጧቱ 2፡45 ላይ ነበር። በርካቶች ሞቱ። የመጀመሪያው አደጋ አልበቃ ብሎ ሁለተኛው የአጥፍቶ ጠፊ ቦይንግ አውሮፕላን ከጧቱ 9፡03 ላይ ከደቡብ ታወር ፎቆ ጋር ተላተመ። በሰሜን ታወር ላይ የደረሰውን አደጋ ለመታደግ በርብርብ ላይ የነበሩትን የእሳት አደጋ ተከላካዮችና ፖሊሶችን ጨምሮ በደቡቡ ታወር ላይ የነበሩ በርካታ ሰዎችን ገደለ። በድምሩ 2,973 ሰዎች፣ በተደጋጋሚው ጥቃት ሰለባ ሆኑ።
በ2003 ዓ.ም በጃፓን የተከሰተውን በሬክተር ሚዛን፣ 9.1 የሆነ ርዕደ መሬትን መጥቀስ ይቻላል። በግዝፈቱ በጃፓን 1ኛ፣ በዓለማችን 4ኛ ሆኗል። የ18,000 ጃፓናውያንን ሕይወት ቀጥፎ የፕላኔታቸንን አክሲስ በ24 ሴ.ሜ. አንፏቋል።  የመጀመሪያው ዙር ርዕደ መሬት የሱናሚ አደጋ አስከትሎ በርካቶችን ጎዳ። ቀጥሎ የመጣው ርዕደ መሬት እጅግ ከፍተኛ ሱናሚ አስነስቶ፣ ከፍተኛ የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመትን አስከትሏል። “ከድጡ ወደ ማጡ” እንደማለት።
ወደ ጎፋው አደጋ ስንመጣ፡
በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ  ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ የተከሰተው ተፈጥሯዊ የመሬት ናዳ አደጋ፣ ከኒውዮርኩም ሆነ ከጃፓኑ አደጋዎች ጋር የሚመሳሰልበት መልክ አለው።  ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው ናዳ ሲከሰት እሁድ ለሊት ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ የቀበሌውን ሊቀ መንበር ጨምሮ አራት ሰዎችን በመቅበር ነበር። በማግስቱ ፖሊስና በርካታ ሰዎች በስፍራው ተገኝተው ተጎጂዎቹን በርብርብ ሊታደጓቸው እየሞከሩ ሳለ፣ ሌላ መጠነ ሰፊ ናዳ በድጋሚ ተከሰተ። ዕድሜና ፆታ ሳይለይ፣ የበርካቶች ሕይወት በቅጽበት ተቀጠፈ። የሟቾችና ቁስለኞች ትክክለኛ ቁጥር ገና በትክክል ባይታወቅም፣ አደጋው በኢትዮጵያ ከፍተኛው አሰቃቂ የመሬት ናዳ ሆኗል። ሕይወትና ንብረታቸውን ላጡ ዜጎቻችን ነፍስ ይማር።
ከጎፋ በተጨማሪ በርካታ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች እየተከሰቱ ነው። ሲዳማን፣ ደሴን፣ ወላይታን፣ ጎንደርን፣ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል። በተለይም የጎፋውን የመሬት መንሸራተት አደጋን ተከትሎ የሚደረገው ርብርብ የሚደነቅ ነው። አንዳንድ ባለሥልጣናትና ባለሙያዎች በሚዲያ የመፍትሔ ሃሳቦች እየሰጡ ነው። የመፍትሔ ሐሳቦቹ እንደወረዱ ቢተገበሩ ሊያስከትሉ የሚችሉትን የጎንዮሽ ጉዳትን በማሰብ ስጋት አደረብኝ። እስኪ ጥቂቶቹን የመፍትሔ ሃሳቦች  ቀለል ባለ መልኩ እንፈትሻቸው።
ጥናቱ መች ጠፋ፡
የጎፋውን አደጋ ተከትሎ የመሬት መንሸራተት ተጋላጭ ቦታዎች ላይ ሰፊ ጥናት እንዲካሄድ እየተመከረ ነው። እንደ ጂኦሞርፎሎጂስቶች አባባል፤ በአንድ ቁልቁለታማ ስፍራ የቀድሞ የመሬት መንሸራተት ጠባሳ ከታየ በአካባቢው ወደፊት ሌላ የመሬት መንሸራተት ሊከሰት ይችላል። በቅርብ ጊዜ ያልተከሰተ ቢሆንም እንኳ የመሬት መንሸራተት ሊከሰት እንደሚችል ማወቅ ይቻላል። ጉዳዩ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ተጠንቷል። ለምሳሌ በደሴ፣ በወልዲያ፣ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በአባይ ወንዝ ሸለቆ፣ በጣርማ በር፣ በወንዶ ገነት፣ በጎፋ፣ በግልገል ጊቤ፣ ወዘተ። በወፍ በረር ተጨምቆ ሲታይ ጥናቶቹ የሚጋሩት ተቀራራቢ ዘዴ፣ ግኝትና በስተመጨረሻ የሚያቀርቧቸው የመሬት መንሸራተት ተጋላጭነት ካርታዎች (landslide susceptibility map) አሏቸው። ስለዚህ የግድ በሁሉም ተራራና ሸንተረር ጥናት እስኪደረግ መጠበቅ አይገባም።  ተጨማሪው ጥናት ለየት ያለ አዲስ መረጃንና ብልሃትን የማይወልድ ከሆነ ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ ማባከኑ ብዙም ፋይዳ አይኖረውም።
ቅድመ ዝግጁነት፡
በተለይም ጃፓን የመሬት መንሸራተትን ለመቆጣጠር የላቀ ቴክኖሎጂን በመመርኮዝ ከፍተኛ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ላሉ ነዋሪዎች፣ የመሬት መንሸራተት ማስጠንቀቂያዎችንና ማንቂያዎችን ትሰጣለች። የየአካባቢው አስተዳደር የማንቂያ ስርዓት ዘርግቶ የድምጽ ማጉያዎችን፣ ሳይረንንና የሞባይል ማንቂያዎችን በመጠቀም ለማህበረሰቡ አደጋው መቃረቡን በፍጥነትና በጥራት ያሳውቃሉ።
የመሬት መንሸራተትን አደጋ ለመቋቋም የኅብረተሰብ አቀፍ ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ የተለመደ ነው። በተለይም በመስሪያ ቤቶችና በትምህርት ተቋማት ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ልምምድ ያደርጋሉ። በማናቸውም ሰዓት አደጋው ቢከሰት ዜጎች ያላንዳች መደነጋገር ማድረግ ያለባቸውን የተጠና ድርጊት በማከናወን ህይወታቸውን ይታገዳሉ። ለምሳሌ በታይዋን፣ በትምህርት ቤቶች በሙዚቃ የታጀቡ  የዳንስ ልምምዶችን ከአደጋ መከላከል እንቅስቃሴ ጋር አጣምረው ስለሚያካሂዱ ልምምዱ አስደሳችና አሳታፊ ይሆናል። አደጋ ድንገት ቢከሰት ምን ማድረግ እንዳለባቸው በቀላሉ እንዲያስታውሱ ያግዛል። ይህን አካሄድ ለርዕደ መሬት፣ ለቶርኔዶ፣ ለሔሪኬን፣ ለጎርፍ፤ ለሱናሚ፣ ወዘተ ይተገብሩታል።
በአገራችን የሶሻል ሚዲያ በሰፊው እየተዘወተረ መጥቷል። በየአካባቢው ካሉ ታዋቂ ዩቱበሮችና ቲክታከሮች ጋር በመቀናጀት ከአደጋ ዝግጁነት እንቅስቃሴ ጋር የተጣጣመ የዳንስ ውዝዋዜ ተዘጋጅተው ለወጣቶች ቢቀርቡ፣ ልምምዱን በሚሊዮኖች ወጣቶች አዕምሮ ለማስረጽ ያስችላል። በተመሳሳይ መልኩ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመዝሙር ትምህርት፣ እንደየአካባቢው የአደጋ አይነት፣ ለዝግጁነት የሚረዳ የዳንስ እንቅስቃሴ ካሪኩለም ቀርጾ መተርጎም አንዱ መንገድ ነው።
ዛፍ፣ ዛፍ፣ ዛፍ!
በሰሞኑ አንዳንድ ባለሥልጣናትና ባለሙያዎች በመሬት መንሸራተት ተጋላጭ ቦታዎች ላይ የዛፍ ችግኝ በብዛት እንዲተከል እየመከሩ ነው። የዛፍ ጠቀሜታው በርካታ ስለመሆኑ አያከራክርም። ነገር ግን ዛፎች የመሬት መንሸራተትን ለመቀነስ እንደሚረዱ ሁሉ ለማባባስም አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላል። ስለዚህ አተገባበሩ ጠለቅ ያለ ምርመራ ያሻዋል። አንደኛ ዛፎች የራሳቸው ክብደት ስላላቸው ሸክሙ የሚያርፈው ባልተረጋገው መሬት ላይ ነው። አንድ ትልቅ ዛፎ በአማካይ እስከ 6 ሺህ ኪሎ ግራም ይመዝናል። ተዳፋትነታቸው ከፍ ባለ አካባቢ በርካታ ችግኞችን ብንተክል የመሬት መንሸራተትን ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህ የዛፎቹን የጥግግት መጠንን ያላገናዘበ ምክር ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል። ሁለተኛ የዛፎችን ሥር ባህሪ (root architecture) መገንዘብ ያስፈልጋል።
አንዳንዱ የዛፍ ሥር ውሃ ለማግኘት በአጭር ጥልቀት ተወስኖ ወደ ጎን በሰፊው በመሰራጨት ነው (shallow rooted)። በተቃራኒው ደግሞ ሥሮቻቸው ወደ ከርሰምድር ጠልቀው (deep rooted) ውሃን የሚስቡ አሉ። አጫጭሮቹ ሥሮች ሊንሸራተት ያቆበቆበውን ሊያባብሱት፣ ረዣዥም ሥር ያላቸው ዛፎች የላይኛውን የመሬት ክፍል ጥልቅ ከሆነው ከርሰ ምድር ጠፍረው ሊይዙት ይችላሉ። ምንም እንኳ አገር በቀል ዛፎች በርካታ ጠቀሜታ ቢኖራቸውም፣ የመሬት መንሸራተትን ለመታገድ ሲባል የባሕር ዛፍን ተከል ማስቀደም ሳይበጅ ይቀራል? ባሕር ዛፍ በተፈጥሮው ውሃ ወዳድ ነው። ጠጥቶ አይጠግብም። ስለዚህም ሲኦል ድረስ ወርዶ ውሃ ከማሰስ አይመለስም። በዚህም ሳቢያ የሥሩ ርዝመት ከመሬት በላይ ካለው ከዛፉ ቁመት ይስተካከላል ይባላል። ሆኖም ሌላውን ተክል ስለሚመርዝ (በአንዳንድ ገበሬዎች አባባል “በመሬቱ ላይ ሽንት ስለሚሸና”) አመጣጥኖ መትከል ይገባል። ጠቀሜታውም ከአፈር ሥር ያሉና መሬትን ሊያንሸራትቱ የሚችሉ የተጠራቀሙ ውሃዎችን ለማጠንፈፍ ብቻ ሳይሆን፣ በፍጥነት ስለሚያድግ ለማገዶ፣ ለግንባታ፣ እንዲሁም ለገቢ ማስገኛነት ስለሚውል ባሕር ዛፍን አመጣጥኖ መትከሉ ከግንዛቤ ቢገባ መልካም ነው።  
የምድር ኮንዶም፡
የመሬት መንሸራተት በሚበረክትባቸው አካባቢዎች አደጋውን ለመከላከል ዛፍ መትከል ራሱ አደጋውን ሊያባብስ የሚችል ከሆነ መፍትሔው ምን ይሆን ብለን በመግቢያው ላይ ለተጠቀሰው ፕሮፌሰር በመስክ ጉዞ ወቅት ጠይቀነው ነበር። እርሱም ይህ ጥያቄ ጣልያን ውስጥም ፈታኝ ጉዳይ እንደሆነባቸው ጠቅሶ፣ አንድ የቀድሞ የሙያ ባልደረባው የነገረውን መፍትሔ አጋራን። በተጨማሪ በዝናብ ሳቢያ በተወሰነ አካባቢ የመሬት መንሸራተት እንዳይባባስ ስፍራውን በሰፊ የፕላስቲክ ንጣፍ መሸፈን መሆኑን ነገረን። የዚህ አሰራር የቀልድ መጠሪያም “የመሬት ኮንዶም” መሆኑን አጫወተን።
ችግሩን መጋፈጥ ወይንስ መሸሽ?
የጎፋውን አደጋ ተከትሎ አንዳንድ ባለሥልጣናትና ባለሙያዎች የመሬት መንሸራተት ተጋላጭ ዜጎች ወደ ሌላ ስፍራ ይስፈሩ ብለው እንደ ቀላል ሲመክሩ ይደመጣል። ካለው ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር እድገትና የእርሻ መሬት ጥበት እውነታ ስንነሳ፣ እውን ነጻ የሆነ አመቺ የመስፈሪያና የእርሻ መሬት አለ? ቢኖር እንኳ ከቀድሞ የሰፈራ መርሃ ግብር ስህተቶቻችን መማር አይኖርብንም? የደርግ መንግስት በሰባዎቹ ዓመታት በድርቅ ችግር ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከመኖሪያ ቀያቸው ወደ ሌላ “አመቺ ስፍራዎች” በግድም ሆነ በውድ እንዲሰፍሩ አድርጓል። ውጤቱ ምን ነበር? ግማሾቹ  የደርግ መንግስት በወደቀ ማግስት ወደ ቀያቸው ተመለሱ። የቀሩት ደግሞ በጊዜ ሂደት የደረሰባቸው የሞትና የስደት እንግልት የሚረሳ አይደለም። ችግሩ ዛሬም አለና!
አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች አልፎ አልፎ የሚከሰት አደጋን በመሸሽ መኖሪያቸውን በቀላሉ አይቀይሩም። እርግጥ ነው ይህ ውሳኔ በሌሎች ሰዎች ሲታይ “አደጋን መጋበዝ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፣ Living on the edge እንዲሉ። ሰዎች ከተወለዱበት ስፍራ ጋር ስር የሰደደ ባህላዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ታሪካዊ ትስስር ስላላቸው ጥሎ መጓዙ ቀላል አይሆንም። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በከፍተኛ ደረጃ ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ በሆኑ በርካታ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚኖሩባቸውን የአለማችን ከተሞችን በማየት ነው። ሳን ፍራንሲስኮ እና ሎስ አንጀለስ (አሜሪካ)፣ ሙምባይ (ህንድ)፣ ሳንትያጎ (ቺሊ)፣ ማኒላ (ፊሊፒንስ)፣ ካትማንዱ (ኔፓል) ጥቂቶቹ ናቸው።
የመሬት አጠቃቀምና የግንባታን ሕግን ማዘመን፡
ከቅድመ ትንበያ ባልተናነሰ የመሬት አጠቃቀምን በማዘመን የአደጋ ተጋላጭነትን ሊቀንሱ የሚችሉ ተግባራትን መተግበር  ያሻል። የመሬት መንሸራተት ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች ላይ ግዙፍ ግንባታ መፍቀድ በቶኖች የሚቆጠሩ የድንጋይ፣ የኮረት፣ የአሸዋ፣ የሲሚንቶ፣ የብረት ወዘተ የግንባታ ቁሳቁሶች በመሬቱ ላይ ተጨማሪ ክብደትን እንዲያሳርፉ መጋበዝ ነው። ይህ ደግሞ የአካባቢውን አለመረጋጋት ያፋጥነዋል። የህንጻ ዲዛይን ፈቃድ ሲሰጥ ቤቶች ቀላል ክብደት ካላቸው ጥሬ ዕቃዎች እንዲገነቡ ቢደረግ መልካም ነው። ጃፓንና ሆንግ ኮንግ ተግብረውታል። ግንባታ የሚፈቀድባቸው ስፍራዎች የመሬት ተዳፋት መጠን ተለይቶ መተግበር ይኖርበታል። ውሃ አንድ ስፍራ ላይ እንዳይታቆር የተለያዩ ዘዴዎች በስራ ላይ መዋል ይኖርባቸዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ስጋት፡
ከላይ በጠቀሱት የመሬት መንሸራተት አደጋ መንስኤዎችና አባባሽ ድርጊቶች ተመርኩዘን ወደፊት ሊገጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን ከወዲሁ ማንሳት ተገቢ በመሆኑ የአርባ ምንጭ ከተማ ስጋቴን ባጋራ ደስ ይለኛል። በተፈጥሮ ውበት የታደለችው አርባ ምንጭ፣ በጋንታ ተራራ ግርጌ ተመስርታለች። ልብ ብሎ ላስተዋለ በተራራው መካከለኛ ክፍል፣ ማለትም ከቤሬ ትንሽ ከፍ ብሎ ቀድሞ ተከስቶ እንደነበረ የሚያመላክት የመሬት መንሸራተት ጠባሳ ይታያል። አንድ ትልቅ የተጎመደ የመሬት ክፍል ከተራራው አናት ተነስቶ ቁልቁል በመጓዝ ላይ ሳለ ቤሬ አካባቢ ሲደርስ ተደነቃቅፎ እንደቆመ መገመት ይቻላል። ለጊዜው ያረፈበት ስፍራ ዘቅዛቃ መሬት በመሆኑ መቼ እንደሚሆን አይታውቅ እንጂ፣ ይህ ጉማጅ የመሬት ክፍል ቁልቁል ወደ ሼቻ ክፍለ ከተማ እንዲንሸራተት የሚገፋፉት ቢያንስ ሦስት አበይት ምክንያቶች አሉ።
አንደኛ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ሲከሰት ነው። ተራራውን በሸፈነው አፈር ላይ አሉታዊ ክብደት ይጨምራል። በሌላ በኩል ደግም የአፈር ርጥበቱ ረግቶ የቆመውን ጉማጅ የመሬት ክፍል አዳልጦ እንዲንሸራተት ያስገድደዋል። ሁለተኛ፣ የአርባ ምንጭ ከተማ የመሬት ርዕደት የሚበረክትበት የታላቁ የምስራቅ አፍሪካ የስምጥ ሸለቆ አካል በመሆኗ ክስተቱ የመሬት መንሸራተቱን ሊቀሰቅሰው ይችላል። ሦስተኛ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በጋንታ ተራራ ላይ የሰዎች እንቅስቃሴ ጨምሯል። የመኪና መንገድ ተገንብቶበታል፣ የትራፊክ ፍሰቱ ጨምሯል፣ የህንጻ ግንባታ መስፋፋት አለ፤ የድንጋይ ማምረቻ ካባም በተራራው ግርጌ ይካሄዳል።
የኔ ስጋት ይህ ሁሉ ሳይበቃ በተራራው ላይ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ግንባታ ከተካሄደ ነው። ጋንታ ተራራ ላይ ሆኖ መላው የአርባ ምንጭ ከተማን፣ የአካባቢውን ደን፣ የእግዜር ድልድይን እና የአባያ እና ጫሞ ሀይቆችን ጠቅላይ ዕይታን (panoramic view) ስለሚያጎናፅፍ፣ መንግስትም ሆነ የንግዱ ማህበረሰብ በተራራው ላይ ሆቴሎች ወይም ሎጆች እንዲገነቡ የሚፈቅዱ ከሆነ የመሬት መናድ በቀላሉ ሊቀሰቀስ ይችላል። ይልቅስ የአርባ ምንጭ ከተማ የመሬት አስተዳደር በርካታ የመሬት መንሸራተት ጥናትና የኤንጂነሪንግ ክንውን በሰፊው ከተካሄደበት ከደሴ ከተማ ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግ አመቺ ተሞክሮዎችን መተግበር ብልህነት ነው።
ማጠቃለያ፡
ይህ ጽሁፍ የመሬት መንሸራተት ድግግሞሹና ኃያልነቱ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንደማይመጣ፣ መደረግ ያለበት የመሬት መንሸራተቱን አባባሽ ድርጊቶች መቀነስና የማህበረሰቡን የአደጋ መቋቋም አቅምና ዝግጁነት ማዳበር እንጂ ክስተቱን ማስቆምም ሆነ ሸሽቶ መኖር እንደማይቻል ያስገነዝባል። በተለይም የጎፋን የመሬት መንሸራተት አደጋን በተመለከተ ባለሥልጣናትና ባለሙያዎች በሚዲያ አቅርበውት የነበሩትን 1ኛ “የመሬት መንሸራተት ተጋላጭነት ባለባቸው የሚኖሩ ሰዎች ወደ ሌላ ቦታ ይስፈሩ”፣ 2ኛ “የመሬት መንሸራተትን ለማስቀረት ዛፎችን በሰፊው ይትከሉ”፣ 3ኛ “ተጨማሪ ጥናቶች ይካሄዱ” የሚሉትን የመፍትሔ ሃሳቦቻቸውን መከለስና ማሻሻል እንደሚገባ ይሞግታል።


Read 318 times