Saturday, 10 August 2024 22:04

የሾተላይ ችግር ይታከማል.....

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

“2 ልጆችን በሾተላይ ምክንያት ካጣን በኋላ አሁን ላይ በህክምና ልጅ አግኝተናል”
ነርስ ጃለኔ አርገታ እና አቶ ወንድሙ በየነ
ጥንዶች አንድ ልጅ ብቻ ወልደው በቀጣይ የተወለደው ልጅ ህይወት ሲያልፍ ወይም ሴቶች ለእርግዝና ሲቸገሩ በተለምዶ ሾተላይ አለባቸው ሲባል ይስተዋላል። በተለምዶ ሾተላይ ተብሎ የሚጠራው ችግር በህክምና አር ኤች ፋክተር(RH factor) ወይም አር ኤች ኢምኮፓተብሊቲ (RH incompatibility) የሚል ስያሜ አለው።
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም በማተርናል ፌታል ሜዲስን ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ “በተለምዶ ሾተላይ የሚባለው የአር ኤች ኔጌቲቭ ያላት እናት ጋር የተያያዘ ነው” ብለዋል። አር ኤች ኔጌቲቭ (RH negative) እናት ማለት የደም አይነቷ ማለትም ኤ፣ ቢ፣ ኤቢ እና ኦ(A, B, AB and O) አርኤች ፋክተር የሌለው ወይም ኔጌቲቭ (negative) የሆነ ማለት ነው። በደማቸው ውስጥ አር ኤች ፋክተር የሌላቸው ማለትም የደም አይነታቸው ኤ ኔጌቲቭ፣ ቢ ኔጌቲቭ፣ ኤቢ ኔጌቲቭ እና ኦ ኔጌቲቭ የሆኑ ሴቶች የደም አይነቱ ፓዝቲቭ(positive) ከሆነ ወንድ ሲፀንሱ እንዲሁም የፀነሱት ልጅ የደም አይነት ፓዝቲቭ (የአባቱን ሲይዝ) አር ኤች ፋክተር ወይም ኢንኬምፓቲቢሊቲ ተፈጠረ ይባላል።
“አባት ፓዝቲቭ፤ እናት ኔጌቲቭ ሆኖ ፅንሱ ኔጌቲቭ የሚሆንበት (የእናቱን የሚይዝበት) አጋጣሚ አለ። ይህ ምንም ችግር አይፈጥርም” ብለዋል ዶ/ር ሰኢድ አራጌ። የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት የጥንዶች የደም አይነት የሁለቱም ኔጌቲቭ፣ የተፀነሰው ልጅ ኔጌቲቭ እና የእናት የደም አይነት ፓዝቲቭ ሆኖ የአባት ኔጌቲቭ ከሆነ ሾተላይ የሚባለው ችግር አይፈጠርም። ስለሆነም ሾተላይ ተፈጠረ የሚባለው አባት ፓዘቲቭ፣ እናት ኔጌቲቭ እና ልጅ የአባቱን የደም አይነት ወስዶ ፓዘቲቭ በሚሆንበት ወቅት ብቻ ነው። እናት አር ኤች ፋክተር ሳይኖራት (ኔጌቲቭ ሆና) ፅንስ አርኤች ፋክተር ሲኖረው (ፓዝቲቭ ሲሆን) የእናት የበሽታ መከላከያ ስርአት የፅንሱን አርኤች እንደ ባዕድ ይቆጥረዋል። እናም መከላከያ በማመንጨት ፅንሱ ላይ ችግር ይፈጠራል። የተፀነሰው ልጅ ለዚህ ችግር ይበልጥ ተጋላጭ የሚሆነው ከ28 ሳምንት የእርግዝና ጊዜ በኋላ (ሊወለድ በተቃረበበት) ነው። ምክንያቱም የፅንስ ደም ወደ እናት የሚገባበት(የሚዘዋወርበት) እድል ይጨምራል።
የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት በመጀመሪያ እርግዝና ወቅት ሾተላይ የማጋጠም እድል አነስተኛ ነው። ይህ ችግር በይበልጥ የሚስተዋለው 2ኛ እና ከዛ በላይ በሆነ ፅንስ ላይ ነው። የመጀመሪያ ፅንስ ላይ የእናት የመከላከያ ስርአት እንደ በሽታ የቆጠረውን የጽንስ የደም አይነት የሚለይበት (recognition) የሚሰጥበት በመሆኑ ነው። እንዲሁም ችግሩ ቢያጋጥም እንኳን ልጁ ከተወለደ በኋላ ቢጫ ቢያደርግ ነው ብለዋል የህክምና ባለሙያው። ነገር ግን የመጀመሪያ እርግዝና ሲባል ከዚህ ቀደም ፅንስ ማቋረጥ እና መሰል ችግር ያላጋጠማት (እርግዝና ሙሉ በሙሉ ተፈጥሮ የማያውቅ) መሆን አለበት። ከዚህ ቀደም እናት ባላወቀችበት መንገድ እርግዝና ተፈጥሮ የነበረ ሊሆን ይችላል። ስለሆነም የመጀመሪያ እርግዝና በእርግጠኝነት ላይታወቅ ስለሚችል እንዲሁም በቀጣይ (2ኛ) እርግዝና ላይ የሚያስከትለውን ችግር ለመከላከል ህክምና መሰጠት የሚጀምረው በመጀመሪያ እርግዝና ወቅት ነው።
አርኤች ፋክተር (ሾተላይ) የሚያስከትለው ችግር
- ፅንሱ ሆድ ውስጥ እያለ የደም ማነስ ማጋጠም
  ፅንስ መቋረጥ
- ወቅቱ ሳይደርስ መወለድ
- ከተወለደ በኋላ የደም ማነስ ችግር
- የተወለደ ልጅ ቢጫ መሆን
- የተወለ ልጅ ላይ የአእምሮ ችግር
- ልጅ ከተወለደ በኋላ ህይወት ማጣት
ነርስ ጃለኔ አርገታ በአርኤች ፋክተር ምክንያት 2 ልጆችን ያጣች እና አሁን ላይ ባገኘችው ህክምና አማካኝነት ልጅ የወለደች እናት ናት። ነርስ ጃለኔ አርገታ እና አቶ ወንድሙ በየነን ያገኘናቸው በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ከተወለደውን ልጃቸው ጋር ነው። ኑሯቸውን ያደረጉት በቢሾፍቱ ከተማ ሲሆን ወደ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል የሄዱት የአር ኤች ኢንኮፓተብሊቲ ችግር ስላለባቸው ነው።
ጥንዶቹ ትዳር ከመመስረታቸው አስቀድሞ በእጮኝነት ጊዜ ስለ ደም አይነት(አር ኤች ፋክተር) ተነጋግረዋል። እናም ትዳር ከመሰረቱ በኋላ የመጀመሪያ ልጃቸው ከመወለዱ አስቀድሞ ህክምና አድርገው ነብር። ነገር ግን 2 እና 3ኛ እርግዝና ላይ ተገቢውን ህክምና ሳያደርጉ ቀሩ። “የነበረውን ችግር እናውቃለን። ግን ወደ ተሻለ የህክምና ተቋም ቶሎ አልሄድንም” በማለት ተናግሯል አቶ ወንድሙ በየነ። ሁለተኛ ልጃቸው እንደተወለደ ህይወቱ አለፈ። ሶስተኛዋም በተመሳሳይ በህይወት መቆየት አልቻለችም። ነገር ግን በአራተኛ እርግዝና ወቅት ተገቢውን ህክምና አደረጉ። ጤናማ ልጅ አገኙ።
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም በማተርናል ፌታል ሜዲስን ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ እንደተናገሩት ነርስ ጃለኔ አር ኤች ኔጌቲቭ ስትሆን 4ኛ የፀነሰችው ልጅ ደግሞ ፓዝቲቭ ነው። ልጁ ሆድ ውስጥ እያለ የደም ማነስ ችግር አጋጠመው። የፅንስ እና የእናት ደም ተመሳሳይ እንዲሆን ለማድረግ ፅንስ ሆድ ውስጥ እያለ ኔጌቲቭ ደም ተሰጠው። ይህም በፅንሱ ላይ ችግር እንዳይፈጠር እና በጤንነት እንዲወለድ አድርጎታል።
“ህክምና ይለያያል። ተገቢው ህክምና የሚሰጥበት የህክምና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል” ብላለች ነርስ ጃለኔ አርገታ። እንዲሁም በነፍሰ ጡር ሴት ዙሪያ ያሉ ሰዎች ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግራለች። ለዚህም ባለቤቷን እንደ ምሳሌ ጠቅሳለች። “የተፈጥሮ ነገር ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም። ለሌሎች ሰዎች ተመርምራችሁ የደም አይነታችሁን እወቁ እና ታክማችሁ መውለድ ትችላላችሁ እያልኩ እመክራለው” ብሏል ወንድሙ በየነ። ወንድሙ እንደተናገረው ችግሩን ከአምልኮ ጋር የማያይዝ ሁኔታዎች(እሳቤዎች) አሉ።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለምአቀፍ ደረጃ እንደየ ሀገሩ የተለያየ ቢሆንም የደም አይነታቸው ፖዝምታቲቭ(positive) ማለትም አር ኤች ፋክተር ያላቸው ሰዎች ብዛት ኔጌቲቭ(negative) የደም አይነት ካላቸው (አር ኤች ፋክተር ከሌላቸው) ሰዎች አንፃር ከፍተኛ ነው። እንደ ዶ/ር ሰኢድ አራጌ ንግግር የአር ኤች ፋክተር ችግር በፐርሰንት ሲቀመጥ ከ100 ሰዎች መካከል በ16 ላይ ያጋጥማል። በኢትዮጵያ ይህ ችግር 6ከመቶ የመከሰት እድል አለው።
ለፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም በማተርናል ሜድስን ሰብ ስፔሻሊስት ለሆኑት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ “የተፀነሰው ልጅ የደም አይነት (አር ኤች ፋክተር) የሚታወቅበት እንዲሁም ህክምና እንዲያገኝ የሚደረግበት ወቅት መቼ ነው?” የሚል ጥያቄ አቅርበንላቸዋል። “የልጁን አር ኤች አይነት ናሙና በመውሰድ መለየት ይቻላል። ነገር ግን ናሙና ለመውሰድ በምንጠቀመው መርፌ አማካኝነት ከእናት ወደ ልጅ የሚኖረውን የድም መፍሰስ ማባባስ አንፈልግም” በማለት ምላሽ ሰተዋል። ስለሆነም ኔጌቲቭ የሆነች (አርኤች ፋክተር የሌላት) እና ፓዘቲቭ አርኤች ካለው የፀነሰች ነፍሰ ጡር ሴት 28ኛ ሳምንት ላይ ህክምና ይሰጣታል። ይህም ጽንሱ ፖዘቲቭ ከሆነ ችግር አንዳይፈጠር ያደርጋል። ኔጌቲቭ ከሆነ ደግሞ ጥቅም ባይኖረውም ጉዳት አያስከትልም። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም በማተርናል ፌታል ሜዲስን ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ እንደተናገሩት ይህ ህክምና ምንም አይነት ተጓዳኝ ችግር ስለማያስከትል ተጋላጭ ለሆኑ እናቶች በሙሉ እንዲሰጥ ይደረጋል።
በቀጣይ እትም እንመለስበታለን

Read 364 times