Monday, 12 August 2024 00:00

ሀተታ ዘ Depression

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(0 votes)

“አላዛር ሰው የማይወድ፣ ሲቀርቡት ራሱን ወደ ጥርኝነት የሚቀይር፣ እንኳን ሲያወሩበት እንዲሁ ሲተነፍሱ ራሱ ሲመለከት የሚቀፈው፣ ብቻውን መሆን ቢፈልግም ያለበት የህይወት መከራ ከመንጋው ጋር የሚቀላቅለው፣ ስለሱ ማንም ሲያወራ ሲሰማ እንደ እብድ የሚያደርገው፣ ፊቱ የማይፈታ፣ በሰው መወደድ እርግማን የሚመስለው፣ ጅኑን ከጠጣ በኃላ ሙልጭ አድርጎ ለመሳደብ ቀደም ብሎ የውሸት ፈገግታ የሚያንጋጋ፣ ተስፋውና እምነቱ የቱ ጋር እንዳሉ ለማወቅ ምንም አይነት ፍላጎት የሌለው፣ ሲሳደብ ስድቡን ማንም የማያምንለት….” ብዬ ልፅፍ ብዬ ፅሁፉን አቆምኩት፡፡ እስካሁን ስፅፍ የነበረው ሰው ከነገረኝ አንፃን እንጂ አላዛርን ቀርቤ አናግሬው እና ፍልስፍናውን ተረድቼለት አልነበረም፡፡ እንዲሁ ሳየው ብቻ ሁሉም ነገር ድክም ያለው ሰው እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ዝምታውና ብቸኝነቱን መምረጡን ለብቻዬ ሆኜ ቀርቤው ማወቅ እፈልግ ነበር…ሁሌ ባየሁት ቁጥር፡፡
አንድ ቀን ግን እሱ የሚቅምበት ቤት ሄጄ አብሬው እየቃምኩ ምን እንደሚሆን ማወቅ ፈለኩኝ፡፡ አንድ ቀን ከሚያሙት ጉዋደኞቹ አንዱን ጠርቼ የት እንደሚቅም ጠይቄ ደረስኩበት፡፡ የተባልኩት ቦታ ሄድኩኝ፡፡ አንድ እንደ አባኮንዳ ተሰብስበው የፈዘዙ መርቃኞች ያሉበት ክፍል ውስጥ አላዛር ቁልጭ ቁልጭ እያለ ተመለከትኩት፡፡ ገና መቃም ሊጀምር ነው፡፡ ነገር ግን ፊቱ ላይ የሚታየው ድካም የትኛውንም የሰው ልጅ ካለበት የደስታ ከፍታ ላይ ፈጥፍጦ ወደ ጥልቅ መሰልቸት ውስጥ የሚሰደው አይነት ነው፡፡ ጫቱን ፈርቶታል፡፡ ቀና እያለ የከበቡትን የጫት አማኞች በንዴት እያያቸው ኩስትርትር ይላል፡፡ ማንም እንዲያዋራው እንደማይፈልግ በግፅ ያስታውቃል፡፡
ድንገት ብድግ ብሎ ከክፍሉ በመውጣት ውጭ ላይ ያለች በረንዳ ላይ ሄዶ ተቀመጠ፡፡ እስኪረጋጋ ድረስ ብዬ በዝምታ በክፍሉ ውስጥ ያሉትን አምሳለ አባኮንዳዎችን በጥንቃቄ ማጤን ጀመርኩ፡፡ አላዛርን የፈለኩት የትውልዱን መልክ ስላየሁበት ነው፡፡ ሆኖም አሁን ላይ ከፊቴ ተቀምጠው የሚፋዘዙትን ቃሚዎች ውስጥም ብዙ አይነት ስሜቶችን ለማንበብ ሞከርኩ፡፡
አንደኛው ቁንድድ ያለው ፀጉሩን እየቆነደደ ባፈጠጠበት ወለል ላይ አይኖቹን በይዶ ተቀምጧል፡፡ አይኖቹ ላይ ሀሳብ አይታይም፡፡ እንዲሁ መፍዘዝ ልማድ ሆኖበት ከወለሉ ጋር በፍቅር የወደቀ ነው የሚመስለው፡፡ ሌላኛው ጠቃጠቆ ስልክ ይዞ ዝም ብሎ በጣቱ ይድጣታል፡፡ አዲስ ገዝቶ እንደሆነ ጠረጠርኩ፡፡ በህይወቴ እንዲህ ያለ ስልክ ይዞ ስልኩ እስኪደማ ድረስ የሚጠቀጥቅ ሰው አይቼ አላውቅም፡፡ ምናልባት ጌም እየተጫወተ ነው ብዬ ገመትኩ፡፡ ልጁ ግን ሌላ ማንም ያልተረዳው አይነት ጥበብ ከስልኩ ውስጥ ደብድቦ እያወጣው ነው የሚመስለው፡፡ አንደኛው ደግሞ ትኩረት የማይስብ አይነት መስሎ ተደብቆ ሌሎቹ የሚሆኑት እየሰረቀ የሚያየው አይነቱ ነው፡፡ ቀላዋጭ ቃሚ ነው፡፡ ሲጀመር የቃሚም ለዛ የለውም፡፡ የሚያዋራውን ሰው እያሰሰ ነው የሚመስለው፡፡ ብቸኝነቱ በግድ ቃሚ ያደረገው ነው የሚመስለው፡፡ ጉልበታም ቃሚ፡፡ መርቅኖም ጠዋት ላይ ለስራ እንደሚሰናዳ ሰው ነው የሚመስለው፡፡ የተሸከመው የጫት ነዶ ቀስ ተብሎ እንዲለመን አድርጎ የገዛው ነው የሚመስለው፡፡ ሸሚዙን ተኩሶ ጫት የሚቅም ሰው እሱን ብቻ ነው የማውቀው፡፡ ባንክ ቤት ሄዶ ቢቅም ይሻለው ነበር፡፡ አሰልቺ ቃሚ፡፡
አላዛር ለምን እነዚህ ሰዎች ሊቀርባቸው እና ሊርቃቸው እንደሚፈልግ የገባኝ መሰለኝ፡፡ የቃሚ ነፍስ ወሬ ያደክማታል፣ የቃሚ ምላስ አንዴ ከተከፈተ መዝጊያው ሊሆን የሚችለው ሰው ያጣ ሰዓት ላይ ነው፡፡ ሁሉም እንደደከማቸው ገብቶት ነው ወደ እነሱ የተጠጋው፡፡ ቅመው እንደ ኳስ የሚነጥረው ሀሳብና ልባቸውን ለማረጋጋት የሚታገሉ እና እንደ ፊኛ የተነፋፋው ባዶነታቸው ውስጥ ትርጉም ለመፈለግ በጫት እንጨት የሀሳባቸውን ባህር ሲቀዝፉት ይታያሉ፡፡ ይቅር በሉኝ …ያስጠላሉ፡፡ ያኔ ነው የአላዛር ትርጉም አልባ የሚመስለው ንዴቱ ፍንትው ብሎ የታየኝ፡፡
አብሬያቸው እየፈዘዝኩ እና እየተፋጠጥኩ የተወሰነ ጊዜ ያህል ጫቱን አነከትኩት፡፡ ጫቱን በጎሰጎስኩት ቁጥር ጭንቅላቴ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ እንግዳ ድምፅ ይሰማኝ ጀመር፡፡ የምርቃናን መምጣት የሚያበስር የመለከት ድምፅ መሆኑ ነው፡፡ ብው አልኩኝ …ብብብውው፡፡
የዛኔ ሰዓት ላይ አላዛርም እንደሚመረቅን ጠረጠርኩ፡፡ ቀስ ብዬ ወደ ውጭ ወጣሁ፡፡ አላዛር ባዶ አየር ላይ ፈዞ አየሁት፡፡ አላማ ያለው ይመስላል፡፡ የሆነ ነገር ለማድረግ፡፡ የሆነ የቃሚ ነገር ሊያደርግ ፈለጎ መላ የጠፋው ምስኪን መርቃኝ ነው የሚመስለው፡፡ ከሌሎቹ የሚለየው ብቻውን መሆኑ ብቻ ነው፡፡
“መቀመጫ ስንት ነው …ሳልጠይቅ ገብቼ እኮ”  አልኩት በጫት ምክንያት ምራቅ ርቆት በደራረቀው አንደበቴ፡፡
አላዛር ዞር ብሎ አየኝ፡፡ እንዳየኝ ድክም አልኩት፡፡ ሆኖም እየታገለ በስቃይ መልስ ሰጠኝ፡፡
“20 ብር ይመስለኛል፡፡”  
ቶሎ ተናግሮ ጀርባ ለመስጠት እስኪመስልበት ድረስ ፊቱን ከኔ በተቃራኒ አዙሮ መፍዘዙን ተያያዘው፡፡ ምን እያሰበ እንደሆነ ካወኩኝ በቂዬ ነው፡፡ በቀጣይ ለምሰራው ድርሰቴ ግብዓት ይሆነኛል፡፡ የምፈልገው ይህንኑ ብቻ ነው፡፡ ሰበብ ልሰጠው አሰብኩ….
“ጫቱም ይደክመን ጀመር እኮ ባክህ፡፡ የበፊት ምርቃና ራሱ ጠፋ፡፡ አሁን ግን መረቀንን ነው የሚባለው….?”
ሲጋራውን አውጥቶ ለኮሰው፡፡ ሰውነቱ ከሰትሰት ያለች ስለሆነች ሲጋራው ከጣቶቹ ይወፍሩ ነበር፡፡ እንዴትም አድርጎ አንዴ ማግ ካደረጋት በኃላ ስልችት እያለው ማውራት ጀመረ…
“ምን አውቃለሁ የኔ ወንድም፡፡ ምን አይነት ጥያቄ ነው የጠየከኝ፡፡ አንተ መመርቀን አቃተህና ድፍን ሀገር ሲያበሰኳ ብቻ የሚውል መሰለህ….ወይስ ብዙ አመት ስትፈሸፍሸው ነው የከረምከው…?”
“እኔ እንኳን መቃም ከጀመርኩ ሁለት ሶስት አመት ቢሆነኝ ነው፡፡”
“ምን ነክቶህ ነው በዚህ እድሜህ የጀመርከው? ወይስ ሌላውን አመት ረስተህው ነው?”
“እንደዛማ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡ ጫት እጅግ ወሰብሰብ ያለ ቅጠል ነው፡፡ የምትጠቀምበት ከሆነ ይጠቅማል፡፡ አለበለዚያ ራሱ ሌላ በሽታ ሆኖ ይመጣብሀል፡፡ እኔ ግን ይቅርታ አድርግልኝና በጣም ነው መቃሜን የምወደው፡፡ “ አልኩት፡፡
“ታዲያ አላዛር ምን ያድርግ ወንድሜ? ምን አይነት ሰው ነህ ደግሞ አንተ፡፡ ካስመረቀነህ ለምን ያገኘህውን ፅጌሬዳ ስታሻምድ አትውልም…ምንም ህይወት የሌለው ጨዋታ ነው እየተጫወትክ ያለህው፡፡ ወይስ ሳላወራ አልወጣም ብለህ ነው የመጣህው…ውስጥ የሚጫወቱ ሰዎች የሉም…?”
የግዴን ፈገግ ብዬለት መልስ ሰጠሁት…
“ውስጥ በሙሉ መርቅነዋል…ድንገት ግን አንዱ ልጅ ስለኳስ ሊያወራ ፈልጎ ወሬውን ጀምሮት ደክሞት ከመሀል አቆመው፡፡”  
“እና እኔ እንድጨርስልህ ነው የመጣህው….?” አለ አላዛር የምሩን መናደድ ውስጥ እየገባ፡፡
አላማዬን አሳክቼ መውጣት ስላለብኝ ትዕግስት በላይ ላይ ደርቤ አላዛርን መታገል ውስጥ ገባሁ፡፡ አላዛርም እየተነጫነጨም ቢሆን መልስ ይሰጠኛል፡፡ ማውራት ባይፈልግም እሱም ያልገባውን ንዴቱን ሊወጣብኝ ይመስል በጠየኩት ቁጥር በስድብ መሳይ መልሶች አብሮኝ የምርቃናውን እብደት ያቀዘቅዛል፡፡
ሆኖም ከብዙ ትግል በኃላ እንደምንም ተላመድን፡፡ ብዙም እውቀት ያለው ሰው አይደለም፡፡ የሰማውን ግን እንደራሱ አድርጎ እንደሚያወራ ደርሼበታለሁ፡፡ እያንዳንዱ የሚጠቀማቸው ቃላት በግድ እያወጣቸው እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ቃላቶቹም አንዳንዴ ትርጉም አልባ ይሆናሉ፡፡ ምንም አላማ የሌላቸው የድምፅ እቃዎች ነው የሚመስሉት፡፡  እኔ ግን ልሰለቸው አልቻልኩም፡፡ እንዲህ ያለ በንዴት እና በድካም የሚያወራ ሰው አይቼ አላውቅም፡፡
የምርም የንግግር ዘዬው ከሌሎች ሰዎች ቢለይም ነፍሱ ላይ ቆንጥር ሆና የምትመገምገው የመሰላቸት ቁስል ግን አሁን ያለውን የሀገሬ ህዝብን መልክ ይመስል ነበር፡፡ ድካም የተጫነው ፣ ጭንቀት የጭንቅላቱ ደንበኛ የሆነበት፣ የኑሮ ካርታው ውስብስቡ የወጣበት፣ ሰው በመሆኑና በመኖሩ ውስጥ ምክንያትም አላማም የጠፋበት፣ ሳይተኛ ገና ፀሀይ የወጣችበት፣ በስራ ማጣቱ ሁሌ ፍርሀት ውስጥ እየተዘፈቀ የሚወጣ፣ እድሜውን ዝም ብሎ መቁጠር የሰለቸው፣ ወደ የት እያደገ እንደሆነ ግራ የገባው፣ መተንፈስ የሰለቸው፣ ፊቱንና ፀጉሩን ታጥቦ ያለችውን ልብስ ለብሶ ስለወጣ ብቻ ስራ የሰራ የሚመስለው፣ የሰፈሩ ሰው ሀሜት ድክምክም ያደረገው፣ የሰው ውድቀት እያሳደደ በመስማት ራሱን የሚያፅናና….ብዙ ባዶነት ውስጥ የተለየ ባዶነት የሚያስስ ትውልድ በሙሉ አላዛር ነፍስ ውስጥ ተጠግጥጎ እንደ ጋኔል የሰፈረ ይመስላል፡፡ ይሄ እኔ ነኝ ያልኩት፡፡ አላዛር ምንም ማለትም ማድረግም እንደማይፈልግ ግን እንደሚያውቀው ያስታውቅበታል፡፡
እንደምንም ታግዬ ያጎለበትኩት ግንኙነት አድጎ አብረን መጠጥ እንድንጠጣ ጋብዤው ተያይዘን ወደ አንድ ግሮሰሪ ገባን፡፡
ማንም እንዳይጠጋን አድርጎ ጨለም ያለ በረንዳ ላይ ተቀምጦ መጠጡን እየለጋ በፀጥታ ሲጋራውን ያንቦለቡለው ጀመር፡፡ እኔም በመጀመሪያ መርቅኜ ስለነበር ማውራቱን አልፈለኩትም ነበር፡፡ ከቆይታ በኃላ ግን ጅኑን አዘዘ፡፡ ሁለት ደብል አድርጎ፡፡ አላዛር ደሞ ጅን ሲጠጣ ምድር ላይ ያሉት ጅኒዎች በሙላ እንደሚሰፍሩበት ተነግሮኛል፡፡ እናም እዚህ ሰዓት ላይ ያለበትን ጭንቀት በሙሉ እንዲነግረኝ ጥያቄ ከጭንቅላቴ እልብ ጀመር፡፡
“አላዛር ግን ህይወት ላንተ ምንድን ናት…?” ድንገት ጠየኩት፡፡
የስካር ወጋገን አይኖቹ ላይ የሚያንፀባርቁበት አላዛር ዞሮ ተመለከተኝ፡፡
“ምን አባህ ስለሆንክ ነው ድንገት መጥተህ በጥያቄ የምታንገላታኝ” ምን መስዬ ታየሁህ …?” መልሱ ክው አደረገኝ…
“አይ ያው ለጨዋታ ብዬ ነው…” አልኩት ነገሮችን ለማረጋትት እየሞከርኩ፡፡
“ህይወት ብሎ ጨዋታ አለ እንዴ? ይመስለኛል ጭንቅላቱን ሰልል ተብለህ ነው የተላከው፡፡ ማን እንደላከህ ደግሞ የማላውቅ እንዳይመስልህ፡፡ ሁለታችሁንም ደግሞ ጉድ ነው የምሰራችሁ፡፡ እባብ ሁላ…ዝም ብለህ ስታስመስል እኮ ጤና የተነሳህ ሰው እንደሆንክ ጠርጥሬያለሁ፡፡”
“አረ አላዛር ማንም አላከኝም፡፡ ድንገት ስለተግባባን ነው አብረን እያወራን ያለነው እንጂ ሌላ ምን አላማ የለኝም፡፡”  አልኩት የምሩን እየተናደደ እንደሆነ ገብቶኝ፡፡
“አሁን ተነስተህ ከፊቴ ጥፋ፡፡ የጋበዝከውን ጅን ከፍለህልኝ ብቻ ወደ ምትስብበት ቦታ ሳብ…እዚ ካንተ ጋር ህይወት ሞት እያልኩ ስለፋደድ አላመሽም፡፡ ፈጠን ብለህ ሂድልኝ…”
ደንግጬ ከተቀመጥኩበት በመነሳት ሂሳብ መክፈል ጀመርኩ፡፡ ሂሳብ ከፍዬም ለመሰናበት ሞከርኩ..
“እሺ በቃ አላዛር…መልካም አዳር”
አላዛር በንዴት እያየኝ ይህን አለኝ…
“እዛው የምታድርበት እደር…እኔ አላዛር ጉዳዬ ይመስልሀል፡፡ ከቻልክ ከዚህ በኃላ በደረስኩበት እንዳትደርስ፡፡ የላከህንም ሰው ምን አድርጌ እንዳባረርኩህ በደንብ አድርገህ ንገረው፡፡ ሂድ አሁን….”
እኔም ወደ ቤቴ እየሄድኩኝ ይህ አሰብኩ….
ህዝቤ አብዷል፡፡ የህይወት ቀለሙ ከላዩ ላይ ተገፏል፡፡ ምክንያት ኖሮት ከእንቅልፉ የሚነቃ ሰው እስኪፈጠር ድረስ አሁን ገብቼ ከተኛሁ በኃላ ባልነቃ ታላቅ ፍቃዴ ነው፡፡ አላዛር ሁላችንም ነን…ሁላችንም አላዛር ነን፡፡ ደክሞናል… ማንም ሳይደርስብን ኖረን መሞት ነው የምንፈልገው …በቃ፡፡

Read 156 times