Sunday, 11 August 2024 20:42

ጦርነትን “ዕርም” ካላልን፣ የዶላር ዕጦት አይቀርልንም!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የውጭ ምንዛሬ በመንግሥት ተመን ሳይሆን በገበያ ዋጋ?
•     እንዲህ ዐይነት የምንዛሬ አሠራር ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ያልታየ “ሥር-ነቀል ለውጥ” ነው።
•     ጥቅሙና ጉዳቱ ላይ ሰዎች ብዙ መነጋገርና መከራከር፣ ከዚያም ባሻገር መጨቃጨቅ ይችላሉ።
አስጨፋሪዎችም አስለቃሾችም ሞልተዋል


ለክፉም ለደጉም፣ አዲሱ የምንዛሬ ሥርዓት በግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ ያልታየ “ታሪካዊ ለውጥ” መሆኑ ግን አያከራክርም። ብዙዎች በዚህ አባባል የሚስማሙ ይመስላል። “ለውጡን ቢቃወሙም ቢደግፉም”። ይህም ብቻ አይደለም።
እውነት ለመነጋገር ከፈለጉ፣ ቢያንስ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ የዋጋ ንረትንና የኑሮ ውድነትን እንደሚያባብስም መመስከር ይችላሉ - ለውጡን ቢደግፉም ቢቃወሙም፣ እውነታውን ላለማየት እስካልሸሹ ድረስ።
ሌሎች የመስማሚያ ነጥቦችም አሉ።
ነባሩ የምንዛሬ ተመን እንደስካሁኑ ወደፊት ሊቀጥል የማችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለመረዳት ከባድ አይደለም። በሆነ መንገድ ካልተስተካከለ በቀር፣ የመንግሥት የምንዛሬ ተመንና የጥቁር ገበያ ዋጋ በዕጥፍ ተለያይቶ እስከመቼ ይዘልቃል? በዚህ መንገድስ የኤክስፖርት ምርት እንዴት ሊያድግ ይችላል?
ከዐሥር ዓመት በፊት፣ አነስተኛ የወርቅ አምራቾች በዓመት ስምንት ኩንታል ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ የሸጡበት ጊዜ እንደነበር ይታወሳል።
የምንዛሬ ተመኑ አላዋጣ ሲላቸውስ? ለብሔራዊ ባንክ ከመሸጥ ይልቅ፣ በሰው በሰው፣ በነጋዴ በደላላ በየአካባቢያቸው በደህና ዋጋ ለመሸጥ ይሞክራሉ። ዞሮ ዞሮ በድንበር በኩል በኮንትሮባንድ በዶላር ወደ ውጭ አገር ይሄዳል። መንግሥት በቁጥጥር ብዛት ይህን ኮንትሮባንድ ማስተካከል አይችልም። ለነገሩ፣ አምራቾችም በቁፋሮ ያገኗትን ወርቅ በድብቅ ለመሸጥ እየተጨናነቁና በመንግሥት ቁጥጥር እየተሳቀቁ ምርታቸውን ማሳደግ አይችሉም። አገሪቱም ዶላር አታገኝም።
በዶላር ዕጥረት ሳቢያ ገደል አፋፍ ላይ የደረሰችው ለምን ሆነና! IMF ከሳምንት በፊት ባወጣው ሰነድ እንደገለጸው ከሆነ፣ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቆተ፣ ለአንድ ሳምንት የማዘልቅ ሆኗል። ይሰውረን አትሉም? የምንዛሬ ተመን፣ ከዚህ አደጋ አላዳነንም። ለአደጋ ዳረገን እንጂ። IMF እንደዚያ ይላል።
በእርግጥ የዶላር ዕጥረቱና አደጋው በፍጥነት እየተባባሰ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከክፉ ቀውስ የተጋለው፣ በጦርነት ሳቢያ ነው። ጦርነት መደበኛ ኑሮ ሊሆንብን ምን ቀረው? ከጦርነት ጋር አብረው የሚመጡ የሥነ ምግባር ብልሹነትና የሥርዓት አልበኝነት በሽታዎችን በየአካባቢያችሁ እየታዘባችሁ ነው? ሌላውን እርሱት። የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በመዘገብ የሚታወቀው ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ሰሞኑን ስለ ኢትዮጵያ ምን ብሎ እንደዘገበ አይታችኋል?
የምንዛሬ አሠራር ለውጥ፣ የአይኤምኤፍና የዓለም ባንክ ብድር… ምናምን አልዘገበም። ለእግረ መንገድ ያህል ጠቀስ ጠቀስ አድርጎ ጽፏል። የዘገባው ዋና ትኩረት ግን ሌላ ነው። የሰዎች እገታ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ እንደመጣ በሰፊው ይተነትናል።
የምንዛሬ የማሻሻያ ለውጥ፣ ኢንቨስትመንትንና ኤክስፖርትን ለማሳደግ ሊጠቅም ይችላል። ሰላም ከሌለ፣ ጦርነት ካልቆመ፣ ሥርዓት አልበኝነት ከተስፋፋ፣ ሽፍትነትና እገታ “ሃይ ባይ” ካጣ… ለኢንቨስትመንት የሚጓጓ አይኖርም። ከኢንቨስትመንት የሚሸሽ እንጂ። ዘኢኮኖሚስት እንደዚያ ብሏል። እኛስ የጦርነትን ክፋት ጠፍቶን ነው?
ጦርነት የማዘውተው አባዜያችንን ካላራገፍን፣ ከዶላር ዕጦት አንገላገልም። ጦርነትን ዕርም ብለን ካልተውን፣ የትኛውም ዐይነት የምንዛሬ አሠራር የትም አያደርሰንም። ጦርነትን መግታትና ማስቀረትም ግን በቂ አይደለም።
በእስከዛሬው የምንዛሬ አሠራር የዶላር ዕጥረትን ማቃለል አይቻልም። በሌላ አነጋገር፣ የውጭ ኢንቨስትመንትንና ኤክስፖርትን የሚያዳክም እንጂ የሚያሳድግ አይደለም - ነባሩ የምንዛሬ አሠራር።
እንደታሰበው ቢሆን፣ ዘንድሮ ከኤክስፖርት ምርት 10 ቢሊዮን ዶላር ገደማ መገኘት ነበረበት። ግን ብዙም ፎቀቅ አላለም።


*

ሥር-ነቀል የምንዛሬ ለውጥ - ብዙ ጣጣ አለው!
በሌላ በኩልም ግን፣ ነባሩ የምንዛሬ አሠራር በአንዴ ከሥር ተነቃቅሎ ሲለወጥ ብዙ ነገሮችን ያናጋሉ። ለኢኮኖሚ አደጋዎችም ያጋልጣል። “ነባር የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች” በሙሉ እንደገና ካልተከለሱና ካልተለወጡ፣ ከአዲሱ የምንዛሬ አሠራር ጋር አብረው ሊሄዱ አይችሉም። የፋብሪካዎች ሥራ በመለዋወጫ ዕቃ ዕጦት እንዳይደናቀፍ “ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ በመንግሥት ተወስኗል” የሚል ዜና ካሁን በኋላ አይሠራም።
“የውጭ ምንዛሬ ለፍጆታ ሸቀጦች አናባክንም። የውጭ ምንዛሬ፣ ነዳጅና ማዳበሪያ ለመሳሰሉ መሠረታዊ ምርቶች፣ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ዕድገት የሚያስፈልጉ የፋብሪካ ማሽኖች መዋል አለበት”… እንዲህ ዐይነት አባባል ካሁን በኋላ ብዙ አያስኬድም። ለጊዜው ለሁለት ለሦስት ዓመት ያህል፣ ለነዳጅና ለማዳበሪያ የዶላር ኮታና ድጎማ መመደብ ይቻላል። ግን ለጊዜው ብቻ ነው ተብሏል። ወደ ፊት አይኖርም።
“ስንዴና ስኳር ከእንግዲህ ከውጭ አንገዛም። ብስኩትና ማስቲካ ከውጭ አናስገባም! የሸቀጥ ማራገፊያ አንሆንም”… የሚሉ አባባሎችም ከእንግዲህ ብዙ አያራምዱም። ይህም ብቻ አይደለም።
እንደምታውቁት፣ የኤሌክትሪክ ግድብ፣ የመንገድ ግንባታ፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የማዳበሪያና የስኳር ፋብሪካ… የመንግሥት የፕሮጀክቶች ዐይነትና ቁጥር ብዙ ነው። ካሁን በኋላ ግን፣ እንደ ልብ መሆን አይቻልም። የምንዛሬ ገበያ ለመንግሥት አስቸጋሪ ነው። መንግሥት ከውጭ እየተበደረ የፕሮጀክቶችን የመጀመር ብዙ ዐቅም አይኖረውም። ዕዳ ከተከማቸበት በኋላ ብድሩን እንዴት መመለስ ይችላል?
የምንዛሬ ተመንና የምንዛሬ ገበያ - የሒሳብ ልዩነት።
የውጭ ብድር ከነወለዱ በየዓመቱ 2 ቢሊዮን ዶላር ሲከፍል እንደነበር ታስታውሳላችሁ። ያው መንግሥት ዶላር አይወልድም። ራሱ መንግሥት በሚመራው ተመን፣ በ60 ብር የምንዛሬ ሒሳብ ከባንኮች ዶላር ይወስዳል።
2 ቢሊዮን ዶላር ለመውሰድ 120 ቢሊዮን ብር ይከፍል ነበር ማለት ነው።
አሁንስ?
የምንዛሬ ዋጋው 100 ብር እያለፈ አይደል? በመቶ ብር ብናሰላው እንኳ፣ መንግሥት ከባንኮች 2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት 200 ቢሊዮን ብር መክፈል ይኖርበታል።
ልዩነቱ ቀላል አይደለም። የመንግሥት በጀት ላይ ተጨማሪ የ80 ቢሊዮን ብር ወጪ ያስከትልበታል - የምንዛሬ አሠራር ስለተለወጠ ብቻ።
በሌላ አነጋገር፣ ዶላር ለመንግሥትም እጅግ ውድ ይሆንበታል። መንግሥት ቅድሚያ በሚሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ “አዳዲስ ግንባታዎችን እጀምራለሁ፤ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን እሠራለሁ” እያለ የውጭ ብድር የማምጣት ዐቅሙ ይዳከማል።
እንዲህ ሲባል ግን፣ ሙሉ ለሙሉ ከፕሮጀክቶችና ከውጭ ብድር ጋር ይቆራረጣል ማለት አይደለም።
የዓለም ባንክና የአፍሪካ ልማት ባንክ ከመሳሰሉ ተቋማት ጥቂት የፕሮጀክት ብድሮችን ማግኘቱ አይቀርም። ነገር ግን፣ አሁን አሁን የፕሮጀክቶቹ ባህርይም እየተቀየረ አይደል?
ድሮ ድሮ አብዛኛው ብድርና እርዳታ… የመንገድ ግንባታና የኤሌክትሪክ ግድብ ለመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ነበር የሚውለው። ዛሬ ዛሬ ግን፣ ለምግብ ዋስትና… ማለትም ችግረኛ የገጠርና የከተማ ነዋሪዎችን ለመርዳት ነው ብድር የሚመጣው። አስቸጋሪ ነው። በብድር በልቶ ማደር! ወዴት እንደሚያደርሰን እንጃ።
የሆነ ሆኖ፣ የዶላር ጨዋታው “ከነባር የምንዛሬ ተመን” ወደ “አዲስ የምንዛሬ ገበያ” ሲለወጥ፣ “ነባር የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም” ጊዜ ያልፍባቸዋል።
“ጥራት ያለው የቡና ምርት በአገር ውስጥ ገበያ ለመሸጥ የሞከሩ ነጋዴዎች በፖሊስ ክትትል ተያዙ፣ ንብረታቸው ተወረሰ” የሚሉ ዜናዎችን ታስታውሱ ይሆናል።
የራሳቸውን ምርት ወደ ገበያ አውጥተው ለመሸጥ ስለሞከሩ እንደ ሌባ ይቆጠራሉ። ውንጀላውማ ከዚህም ይብሳል። በአገር ኢኮኖሚ ላይ አሻጥር የሠሩ፣ የአገር ክህደት የፈጸሙ ያህል ነው የክስ መዓት የሚወራባቸው። ለምን እንደሆነ ይገባችኋል መቼም።
ያው፣ መንግሥት ዶላር ይፈልጋል። ማን የማይፈልግ አለ? ዶላር ተገኝቶ ነው! ሁሉም ይፈልጋል። መንግሥትም ዶላር ይፈልጋል። የመንግሥት ፍላጎት ግን ትንሽ ለየት ይላል። ጉልበት ይጨምርበታል። በምንዛሬ አሠራር ላይ አዲስ ሕግ ማወጅ፣ ደንብና መመሪያ አውጥቶ በጉልበት ማስፈጸም ይችላል። ራሱ ባወጣው የምንዛሬ ተመን የሰዎችን ዶላር ይወስዳል። ማን ከልካይ አለበት?
ጥራት ያለው የቡና ምርት እዚሁ መርካቶ ውስጥ ከተሸጠ መንግሥት ምንም ጥቅም አያገኝም። ቡናው ወደ ውጭ ከተላከ ግን ዶላር ይመጣል። ወደ ባንክ ይገባል። መንግሥት በገበያ ዋጋ ሳይሆን በራሱ የምንዛሬ ተመን ዶላሩን ይወስዳል - ለምሳሴ በ60 ብር ሒሳብ። ይህን እንዳያስቀሩበት ነው በኤክስፖርት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያካሂደው።
አሁን ግን፣ መንግሥት የሰዎችን ዶላር መውሰድ ከፈለገ… ያው በገበያ ዋጋ መግዛት ይኖርበታል ተብሏል። በመቶ ምናምን ብር ሒሳብ መሆኑ ነው። ቡና ነጋዴዎች ምን ቸገራቸው? በገበያ ዋጋ የዶላራቸውን ምንዛሬ የሚያገኙ ከሆነ፣ የራሳቸውን ንብረት በድብቅ በአገር ውስጥ ለመሸጥ የሚሞክሩበት ምክንያት ብዙም አይኖርም። ከሸጡም… ያው በገዛ ንብረታቸው ማን ይከለክላቸዋል? ወርቅ አምራቾችም እንዲሁ!
መንግሥትስ፣ እንደ ድሮው የኤክስፖርት ዶላሮችን በአነስተኛ የምንዛሬ ተመን መውሰድ ካልቻለ፣ ለቁጥጥር መስገበገብ ምን ያደርግለታል?
ምናለፋችሁ! የምንዛሬ አሠራር ላይ የተደረገው ለውጥ ሁሉንም ነገር ይነካካል። እንዲህ ሲባል ግን፣ “በምንዛሬ ተመን” ምትክ የመጣው “የምንዛሬ ገበያ” ምን ዐይነት መልክ እንደሚኖረው ሙሉ ለሙሉ ይታወቃል ማለት አይደለም።
የምንዛሬ ገበያው ምን ያህል ለገበያ እንደሚለቀቅ ከወዲሁ እርግጡን መናገር ያስቸግራል።
“ማስተካከያ ሕጎችን”፣ “ማሻሻያ ደንቦችን”፣ “ማሟያ መመሪያዎችን”… በየጊዜው በቁጥ ቁጥ እያዘጋጁ ማምጣት የተለመደ ነው። በሳምንታት ውስጥ፣ ወይም በጥቂት ወራት፣ አለያም ከመንፈቅና ከዓመት በኋላ፣ የምንዛሬ ገበያው መልክና አሠራር ቀስ በቀስ እየተቀየረ ሊሄድ ይችላል። ፊቱ ወደ ግራ ይሁን ወደ ቀኝ፣ ወዴት አቅጣጫ እንደሚዞር መገመት ቢያስቸግርም፣… ሲውል ሲያድር፣ ብዙም ሳይቆይ፣ አንድ ሁለት እያሉ፣ የማሻሻያ አንቀጾችና ልዩ መመሪያዎች እንደሚመጡ ግን አትጠራጠሩ።
እንደ ሁኔታው ነው። በአንድ በኩል መንግሥት አሁኑኑ ከIMFና ከዓለም ባንክ ጋር መጣላት አይፈልግም። የለየት ጥል ይቅርና ኩርፊያም ጉዳት ይኖረዋል። በዶላር ዕጥረት ሳቢያ ከገደል አፋፍ ላይ የደረሰች አገር ምን ዐቅም ይኖራታል? ግንባራቸውን ከቋጠሩባት ምን ይውጣታል?
ለብድር የዘረጉትን እጅ እንደገና መልሰው ካጠፉ፣ ነገሩ ሁሉ “ፉርሽ” ይሆናል። ብድር ቢያቋርጡባት አይደለም ቢያዘገዩባትም እንኳ ትቸገራለች።
የተመደበውን ብድር እየወሰደች ካጋመሰች በኋላ፣… ለጊዜው ከዶላር ዕጥረት ትንሽ ፋታ ካገኘች፣… ከዓመት ከሁለት ዓመት በኋላ መንግሥት ምን ለማድረግ እንደሚወስን ማን ያውቃል? አሁን በጀመረው መንገድ “የምንዛሬ ገበያን” አጥብቆ መያዝና መቀጠል ይችላል። ከባድ ነው። ግን ይቻላል።
በሌላ በኩል ግን…. አዳዲስ ፕሮጀክቶችን መገንባት ሲያምረው፣ ዶላር ሲቸግረው፣ በጀት ሲያጥረው፣ በአነስተኛ የምንዛሬ ተመን ከባንኮች ዶላር መውሰድ ሊያሠኘው ይችላል።
ለይቶለት ወደ ምንዛሬ ተመን ባይመለስ እንኳ፣ “የገበያ ማሻሻያ ደንቦችን” ወይም “ጊዜያዊ አስቸኳይ መመሪያዎችን” ማወጅ አያቅተውም። ምክንያትና ሰበብ አይጠፋም። “አገራዊ ፕሮጀክቶች”፣ “ወሳኝ የኢኮኖሚ ዘርፎች”፣ “ድሀ ተኮር ምርቶች”፣ “ሕዝባዊ ጥያቄዎች”… በልዩ አሠራርና በልዩ ተመን የዶላር ኮታ የሚያገኙበት መመሪያ ቁጥር 1 ቁጥር 2 እያለ ማውጣት ይችላል።
መቼም IMFና የዓለም ባንክ… “የምንዛሬ ገበያ ተነካ፣ ተጣሰ” ብለው ወዲያውኑ እንደማይጣሉት ቢያስብ ቢገምት ብዙም አይገርምም። ትችትና ቅሬታ ይሰነዝሩ ይሆናል። ለማኩረፍ ግን ጊዜ ሊፈጅባቸው ይችላል።
መንግሥት በዚህ ግምት ተማምኖ፣ የምንዛሬ ገበያውን ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞው የምንዛሬ ተመን እያንሸራተተ ለማስጠጋት ቢሞክር ማን ይመልሰዋል? እንዲያውም “ሚዛኑን የጠበቀ የምንዛሬ ሥርዓት” የሚል የሙገሳ አስተያየት ሊቀርብለት ይችላል።
ችግሩ ምንድነው? የተቀየጠ የተቃወሰ የምንዛሬ ሥርዓት ሆኖ ሊያርፈው ይችላል።
ከሆነ አይቀር፣ “የገበያ ምንዛሬ” ብለው ከጀመሩት አይቀር፣ ያንኑን እያጣሩና ቅጥ አያስያዙ ለመጓዝ መጣር ይሻላል። በእርግጥ ዋናው ትኩረት ለሥራ የተመቸ አገርና ሥርዓት የመፍጠር ጉዳይ ነው። ኢንቨስትመንት እየተስፋፋ ኤክስፖርት የሚያድግበት ጸዳ ሥርዓት ነው ዋናው ቁም ነገር። እንደ አያያዛችን ሆነ ግን፣ ሁለመናችንን በጦርነት የተጠመደ ነው የሚመስለው። ጸዳ ያለ ሥርዓት ይቅርና አገርን ማረጋጋትና ሰላምን በወጉ መፍጠር አቅቶናል።

Read 561 times