Sunday, 11 August 2024 21:17

“ውቧ - የሙት መንፈስ”

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(3 votes)

[ህይወት በሞት መቃብር ውስጥ]

(አጭር ልብወለድ)

በመጀመሪያ ይኼን እወቁ፡-
“እኔ ከእራሴ ጋር ስጋጭ ፣ እኔ ከእራሴ ጋር ስጣላ ብታዩ እንኳን አትፍረዱብኝ። ሰላም ያለ ጦርነት፣ እርቅም ያለ ግጭት አይመጣምና።”
ሞት ውጦት አንድ አገር ላይ እንደ ተፋዉ ፥ ሰው ጠልቶት ክእልፍኝ ቤቱ እንደገፋው - ለአገሩ እንግዳ፣ ለሰዉም ባዳ ሆኛለሁ። ብቸኝነቴ እንዳይታይ ሰው ያለመፈለግ ጭንብሌን አጠልቃለሁ። አገር አልባነቴን “መላው ዓለም አገሬ ነው” በሚል ፍልስፍና እጋርዳለሁ። ህመሜን ቆንጆ ምክንያታዊ ቀለም እቀባውና አሳምረዋለሁ። ስቃዬን በፈገግታዬ አይነ- እርግብ እሸፍነዋለሁ። ዓለምን የምዋጋት ሽምቅ ነው። ህይወትን የምታገላት ዋሻዬ  ውስጥ ተደብቄ ነው።
ጭንብሌን ተዋግቶ ያሸነፈ ጎበዝ የለም። ዓይነ እርግቤን ገልጦ እኔን ለማየት የደፈረ ብርቱ እስካሁን አልታየም። ጥሩ ጭንቅላት አለህ ይሉኛል። በእርግጥ አሪፍ አዕምሮ ነው ያለኝ። ለጨለማዬ የውሸት ብርሐናዊ ሸማ ሸምኖ ማልበስ ፥ ስቃዬን ሃሳዊ የደስታን ፍካት ጠልፎ ማድመቅ ላይ ጎበዝ ነኝ።
ለፍርሐቴ የጀግንነት ሎጂክ አለኝ። ልቤ ለተስፋ መቁረጤ ተስፈኛ ዝማሬ አልነጠፈበትም። ነፍሴ ለእንባዬ የደስታ  ማህሌት ለሊቱን ሙሉ ለመቆም አይደክምም። ኒቼ እንዲህ አይደል ያለው፤“በፈገግታዬ አትሸወዱ። ፈገግ የምለው ስቃዬን ለመደበቅ ነው። ስቃዬ አሳፋሪ ነውና ለማንም ማሳየት አልፈልግም።
መንገድ ላይ ስሄድ ድንገት አንዷ መጥታ አቅፋ ብትስመኝ ደስ ይለኛል። ነገር ግን ድንገት ሴቶች ሲያዩኝ ኮስታራ ገፄ ያሸሻቸዋል። ጠጋ ብለው ቢያወሩኝ ደስተኛ ነኝ፣ ግን ጠጋ ብለው ሲያወሩኝ ንግግሬ አጥንት ይሰብራል። ቀለል ያለ ህይወትን መኖር ይከብደኛል። ተራ ነገር እያሰቡ መዋል ላይ ሰነፍ ነኝ። በትንሽ በትልቁ ለምን አልስቅም? በሳር በቅጠሉ ለምን ፈገግ አልልም? ግራ ተጋብቻለሁ። ሰማይ እንደተደፋበት ሰው ቀና ማለት እንኳን ከብዶኛል።
በዚህ ጨለማ ውስጥ ለዓመታት ተመላልሻለሁ። እውነተኛ ብርሐን ይናፍቀኛል፤ ግን ብርሐንን አወግዛለሁ። ሳቅና ጨዋታን ብመኝም … ጨዋታን እሸሻለሁ። ተርቦ ሳለ ጠገብኩ እንደሚል ኩራተኛ ሀሚና ነኝ።
በቁሙ ሞቶ ሳለ መኖሩን ደጋግሞ እንደሚናገር ምዉት ሆኛለሁ። ሰው ጤነኛነቱን አብዝቶ ከተናገረ በጠና ታሟል ማለት ነው። ሁሌ ስለ ፍቅር የሚፅፍ ገጣሚ፣ ልቡ ለፍቅር ባዶ ቢሆን ነው። ሰው ፍቅርን ፈልጎ ባጣ ጊዜ ደጋግሞ ስለ ፍቅር ይፅፋል አሊያም ይቀኛል። ጥሩ ባለቅኔ በጥሩ ማጣት፣ በመልካም መነፈግ፣ በአሪፍ ህመም ውስጥ የተመላለሰ ነው። አንዳንዴ ህመምህ ሲነጥፍ ብዕርህም አብሮ ይነጥፋል።
በብቸኝነት ዘገር ተወግቶ የሚደማውን ልቤን ጌጥ ይመስል ስኩራራበት አረፍዳለሁ። ቁስሉን እንደ ንቃት እመለከታለሁ። ልቤ ውስጥ ውስጡን መሾዉን ያንጎራጉራል።  ሞቶ ሳለ አለሁ ለሚል እሱነቱ እርሙን ያወጣል።
ብርሐንን እየናፈቀ ግን ከጨለማ ውጪ ዓለም የለኝም እንደሚለው እንደዛ …
እድሜውን አቀርቅሮ ገፍቶ ግን ቀና ብሎ  እንደሚራመደው እንደዛ …
የእግር መንገድ ሳደርግ ብዙ ጊዜ እራሴን ስለማጥፋት አስባለሁ። እራሴን የማጥፋት ወኔ ግን የለኝም።
ምናልባት ይሄን ትርጉም አልባ ህይወት ለመኖር ተረግሚያለሁ።

                   *  *  *
እናቴን አላውቃትም። ግን በህልሜ ሁሌ አያታለሁ። እድገቴና ንቃቴ ውስጥ ባትገኝም … ህልሜ መሐል ድንገት መጥታ በማስባቸው ነገሮች ስትደነቅ ቢያንስ ነፍሷ ተቀብሎኛል ብዬ እፅናናለሁ። ሳላውቃት የፃፍኩላትን ደብዳቤ ደጋግሜ አነበዋለሁ። አንዳንዴ ዘግይቶ፣ አንዳንዴ ፈጥኖ የሚገባን እውነት አለ።
እናት ወይ እህት አሊያም አንዲት ሴት ጓደኛ ቢኖረኝ፣ ምናልባት እንደ ባለቅኔው ካህሊል የኔም የነፍሴ መስኮት በሴቶች ይከፈት ይሆናል። የእኔ የነፍሴ መስኮት ግን ለዘላለም የተከረቸመ ይመስላል።
የወንድ ነፍስ ያለ ሴት ይነቃ ዘንድ አልተፈቀደም። ምናልባት ወንድ ያለ ሴት፣ ወንድ እንዳይሆን ተረግሟል።
ለምንድነው ይሄን ሁሉ የማይረባ ነገር የምዘበዝበው? ቆይ ቆይ … ለምንድነው ነው ሴት  ወይ ሰው ያስፈለገኝ? በፍፁም! ሁለቱም አያስፈልጉኝም። የአዕምሮ ልህቀት ያላቸው ሰዎች ከሰው ከፍ ብለው የሚበሩ እንጂ ከሰው ሥር ሆነው ፍቅርን የሚለምኑ ለማኞች አይደሉም። ለመሆኑ ትልቅ ንቃት ወይም ታላቅ አዕምሮ እንዳለኝ የሚክድ ሰው አለ?
ሰው ሰው ያስፈለገው ደካማ ስለሆነ ነው። ወንድ በሴት ጭን የሚታሰረው ተፈጥሮው ውሽልሽል፣ ማንነቱ ልፍስፍስ ስለሆነ ነው። ለወንድ ሴት ያስፈለገችው፣ ወንድ ከሴት ደጃፍ የሚሮጠው፣ ደደብና ደካማ ስለሆነ ነው።
ሰው እግዜር እንኳን ያስፈለገው ደካማና ልፍስፍስ ስለሆነ ነው።
እኔ የእራሴ ፍቅረኛም፣ የእራሴ ጓደኛም ነኝ።
እኔ የእራሴ እናትና አባት፣ የእራሴ ቤተሰብም ነኝ።
እኔ የእራሴ ህዝብ፣ የእራሴ አገር ነኝ።
እኔ የእራሴ እግዜር፣ የእራሴ ሰይጣን ነኝ።
ቅድም የብቸኝነት ዘገር አደማኝ ስል ምን ማለቴ ነው?
በኩሸት የእናንተን ሃዘኔታ ልሰርቅ አደባሁ እንዴ? ብቸኝነት ሲያልፍም ነክቶኝ አያውቅም። ብቻነት ውስጥ ደስተኛ ነኝ። እኔ ማለት በብርሃን የተጥለቀለቅሁ የብሩህ አዕምሮ ባለቤት ነኝ። ከዚህ ደንቆሮ ህዝብ ጋር ተቀምጬ ተረት ልተርት፣ ገመና አነፍንፌ እንደ ባልቴት ቡና ላይ ሀሜት እንደ ቅኔ ልደረድር አልችልም።
የተሻለ ንቃት ያለው ሰው ሁሌም ይነጠላል። ከዚህ ህዝብ ጋር ሆኜ ስለ ሚስቲሲዝም ባወራ፣ እንደ ጆርዳን ብሩኖ በጥዋፍ ያቃጥለኛል። ስለ ፍልስፍናዊ አብርሆት ብናገር፣ እንደ ሶቅራጠስ በመርዝ ይገለኛል። አዲስ ሃሳብ ባመጣ፣ እንደ ክርስቶስ “የዓለም ንጉስ ነኝ” ብሏል ብሎ ይሰቅለኛል።
ቆይ …በእርግጥ ትረካዬ ግራ ሊጋችባችሁ ይችላል። አተራረኬ ጨርቁን እንደቀደደ እብድ ነው። ቢሆንም ግን ታላቅ ፍሬ አለው። አይ መናገር አለብህ ትንሽም ቢሆን …ምንም በብሩህ አዕምሮዬ ብኩራራ፣ በታላላቅ ፍልስፍናዊ ሃሳቦቼ ደረቴን ብነፋ፣ በሥነ ፅሁፍ እውቀቴ ብታበይም …አንዳንዴ ሃዘን በጥፍራም እጆቹ ይዳስሰኛል።  ሰው ማቀፍ ያምረኛል። ሴቶች ቢያወሩኝ ስል እመኛለሁ። ግን አንዳንዴ ነው።
ቀባጠርኩኝ አይደል ቅድም … ቢሆንም ያን  ያህል አሳሳቢ ብቸኝነት የለብኝም።
ውስጤ ስቃይ እንዳለ ግን ልደብቃችሁ አልሻም።  ያ ስቃይ ግን ለእኔ ጥበብን የምቀዳጅበት ወሳኝ ሁነት ነው። የአዕምሮ ህመም አለብኝ።  ግን ታክሜ አላውቅም። ምክንያቱም ክሀኪሙ በላይ ስለ አዕምሮ ህመም እውቀት ስላለኝ ነው። እውቀቶቼን የማገኛቸው እንደ ተራ ህዝብ ከመጽሐፍ ላይ አይደለም። የልቤን ገፅ እየገለጥኩ፣ ነፍሴን እያነበብኩ ነው እውቀቶቼን የማገኛቸው።
ግልፁን ልንገራችሁ? ከእኔ በላይ የሚያውቅ ሰው ያለ አይመስለኝም። በፊት አነብ ነበር። መጽሐፍ ግን በጣም አሰልቺ ነገር ሆነብኝ። መጽሐፎቼን ሁሉ ሽጫቸዋለሁ። ዓለም ላይ ያሉ የታላላቅ ፈላስፎችን ሃሳብ እንኳን ማንበብ ከተውኩ ቆየሁ። በመጀመሪያ ፍልስፍናን በጣም እንደምንቅ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ። ሥነ ፅሁፍን ምን ብዙ ባነብም ያን ያህል አያረካኝም። ታሪክማ ጭራሽ ያንገሸግሸኛል። ባጠቃላይ መጽሐፎች ለእኔ የሚረቡ አይደሉም።
እና መሸ። ለእግር መንገድ ወጣሁ። እራመዳለሁ። ድንገት ግን የጨረቃ ብርሀን የፈሰሰባት ሴት ልጅ አየሁ። መላው ህዋሳቴ ተነቃቃ። ስታልፈኝ ሽቶዋ አፍንጫዬን ሞልቶ ሰላም አረበብኝ። ተከተልኳት። በጣም ታምራለች። ሴት አተኩሬ እንኳን ካየሁ አመታት አልፎኝ ነበር። ተጠግቼ  ነካውዃት። ዞረች። ጨረቃ ወደ እኔ ሙሉ ፊቷን ያዞረች መሰለኝ።
ይቅርታ ሰፈሩ ግር ብሎኝ ነው። እዚህ ሰፈር ነሽ?
አዎ! ምን ጠፍቶህ ነው?
እኔንጃ!
ማለት?
ማለት የጠፋብኝ ሰውና አካባቢ እራሱ ሳይጠፋኝ አይቀርም!
ከየት ነው የመጣኸው?
ከገነት ወይ ከገሃነብ ነው፤ ሌላ ከየት ሊሆን ይችላል?
ሳቀች።
እየቀለድክ ነው?
እኔ ቀልድ አላውቅም። ዝም ብዬ አየሁሽና ተከተልኩሽ። ግርታዬን ብታጠፊው ብዬ ነው።
አሃ!
ማለቴ ቆንጆ ነሽ።
ገባኝ …  ና ቡና ልጋብዝህ
አይ እኔ እንደ ባልቴት ቡና አላንቃርርም ። ሲጀመር ብናወራ እንኳን አትረጂኝም። በቃ እንደውም ልሂድ።
እሺ
መንገዷን ቀጠለች። እኔም ድጋሜ እጇን ያዝኳትና ስትዞር፤
ብቻዬን ለእረጅም ጊዜ ስለኖርኩ ሰው አስፈልጎኝ ነው ይቅርታ። ሳይሽ ደግሞ በጣም ውብ ነሽ።
ተጠምጥማ አቀፈችኝ።
ያኔ ቀለጥኩ። ማውራት ቀርቶ መተንፈስ ከበደኝ። እጄን ይዛኝ መጓዝ ጀመርን። ይዛኝ ልትጠፋ ይሆን?
ብዙም ባይሆን በትንሹ የተባረኩ ሴቶች አሉ መሰለኝ …እንደኔ አይነት ሰዎች ግን ምናልባት በዘመን አንዴ ቢኖሩ ነው። ግን ስታቅፈኝ እብደቴ ሞቶ ዳግም እንደ ሰው የተወለድኩ መሰለኝ። አዕምሮዬ ስለ እነዚህ ነገሮች ሲያስብ እራሴን መቃብር ውስጥ አገኘሁት። ለሁለት ሰው ትንሽ የሚሰፋ መቃብር ተቆፍሯል።
እዚህ ውስጥ እንድንኖር ጋበዘችኝ። ከእሷ ጋር እንኳን መቃብር ሲኦልም ገነት ነው። ለወንድ ሴት ያለችበት ሲኦል ገነት፣ ሴት የሌለችበት ገነት ሲኦል ነው ለካ።
መቃብር ውስጥ ተወዳጀውዃት። ይህቺ ሴት ግን የሙት መንፈስ እንደሆነች ዘግይቼ ተረዳሁ። ዋናው ግን ሴት መሆኗ ነበር። የሙት መንፈስ ፆታ አለው ትሉኝ ይሆናል። መልሴ ግን  “እኔ ምን አውቄ” ይሉት ግርታ ነው።
የሙታን ዓለም ከህያዋን ዓለም ይበልጣል። ከህያዋን ዓለም በላይ ደማቅና ውብ ነው። ሞትም ከህይወት ይበልጣል። የአብርሐምና የሳራ ያድርግላችሁ ብላችሁ እንዳትመርቁን። አብርሐምና ሳራ ሙታን ዓለም ውስጥ ጥንዶች አይደሉም። እኛ እንደነሱ የህያው ዓለም ተረት አይደለንም።  እኛ በሞት ውስጥ ህይወት ዘርተን የምንኖር የመቃብር ጥንዶች ነን።

Read 303 times
More in this category: « ሚኒባሷ