በ16ኛው ክፍለ ዘመን ይኖር የነበረው ላ ፎንቴን የተባለው የፈረንሳይ ገጣሚና አፈ-ታሪክ ፀሀፊ ከፃፋቸው ተረቶች ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ቁራ፣ ከቁራ ቤተ-ዘመዶቹ ተለይቶ፣ ለአንድ ጌታ አድሮ ያገለግል ነበር፡፡ ከብዙ ዓመት በኋላ፣ ከጌታው ቤትም ወጣና ከአንዲት ጣውስ (Peacock) ጋር ወዳጅነት ጀመረ፡፡ ሆኖም ሁሌ በመንገድ ላይ ሳሉ ውበቷ የሷን ማማር የቁራውን መጥቆር በጣም እያጎላው ስለሚታይ፣ አብረው ሲሄዱ የተመለከተ ሁሉ “ይቺ ጣውስ እንዴት ውብ ናት?” “ቁራው እንዴት ጥቁር ነው?” እያለ አስተያየቱን ይሰጥ ጀመር፡፡ ይህን የተገነዘበው ቁራ እጅጉን የበታችነት ይሰማው ጀመር፡፡ በሄደበት ቦታ እያቀረቀረ በሀፍረቱም ምክንያት የገዛ መልኩ እያስጠላው መጣ፡፡ ስለዚህም አንድ ቀን ጧት ተነስቶ ለጣውሷ እንዲህ አላት፡-
“ከዛሬ ጀምሮ እኔ እንዳንቺ ማማር አለብኝ፤ ያንቺን ዓይነት በውብ ቀለማት የተጌጠ ላባና ጭራ ተክዬ መታየት አለብኝ፡፡”
ጣውሷም፤
“ቁራ ሆይ፤ ሁለታችን ተፈጥሯችን የተለያየ ነው፡፡ ያንተ መልክ በተፈጥሮው ጥቁር ነው፡፡ የእኔ ከተለያየ ቀለማት የተሰራ የዐይን ብሌን የመሰለ ጠቃጠቆ ኅብር ያለው ነው፡፡ የእኔ ክንፍ ለስላሳ፣ የጭንቅላቴም ጉትያ ልዩ የላባ ጉልላት ያለው ነው፡፡ ጭራዬም እንደምታይው መሬቱን እየጠረገ የሚሄድ ዘርፋፋ፣ ጥቅጥቅ ያለና ከግማሽ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ነው፡፡ እንዴት አድርገህ እኔን ለመምሰል ትችላለህ??” ስትል ጠየቀችው፡፡
ቁራውም፤
“በምንም ዓይነት አንቺ ከእኔ አትበልጪም” ሲል በግትርነት አረመረመ፡፡
ጣውሷም፤ “እኔኮ ከአንተ እበልጣለሁ አላልኩም፡፡ ግን ከአንተ እለያለሁ ነው የምለው”
ቁራው በእልህ እየበረረ፤ “እንዴት አንቺን ለመምሰል እንደማልችል አሳይሻለሁ” ብሎ የተለያየ ቀለም ያላቸው ላባዎች ወደሚያገኝበት ቦታ ሄደ፡፡ ከዚያ የራሱን ላባ አንስቶ በገላው ላይ ልዩ ልዩ ቀለም ያለው ላባና ረዥም ዘርፋፋ ጭራ አስተከለ፡፡ ከጣውሷ እኩልም የሆነ መሰለው፡፡ “ከእንግዲህ የተለየሁ ፍጡር መሆኔን ለማሳየት በየቦታው መዞር አለብኝ በሎ ከጣውሷ ተለይቶ ሄደ፡፡ ቀጥሎም ምን ዓይነት የተፈጥሮ ለውጥ እንዳመጣ ሊያሳየው ወደ ዱሮ ጌታው ተመልሶ ሄደ፡፡ መለወጡንም አስረዳው፡፡ ጌታውም፤ “በእርግጥ መለወጥህን ለማየት የገላህ ቆዳ ምን እንደሚመስል ማየት አለብኝ” ብሎ ተነስቶ ቁራውን ጨምድዶ ያዘው፡፡
ላባና ጭራውን ሁሉ ነጭቶ ነጭቶ ልሙጡ የውስጥ ቆዳው እስኪታይ ድረስ ላጭቶት ሲያበቃ “ቅንጣት ታህል እንኳ የተለወጥከው ነገር የለም - ሂድ ውጣ ከኔ ዘንድ አትቀመጥም!” ሲል አባረረው፡፡ ቁራም ተነስቶ “ወደ ጥንት ዘሮቼ ወደ ቁራዎቹ ዘንድ ሄጄ እቀላለቀላለሁ” ብሎ ወደ ቀየው ሄደ፡፡ እዚያ ሲደርስ ግን ያልጠበቀው ነገር ገጠመው፡፡ ዘመዶቼ በቁጣ “እንደዚህ ልሙጥ ገላ ያለውና አንድም ጥቁር ላባ በቆዳው ላይ የማይታይበት የቁራ ዝርያ አናውቅም፡፡ አንተ የእኛ ዘር አይደለህም፡፡ እንዲያውም እኛን መስለህ ልታጭበረብር ነው የመጣኸው” ብለው ተባብረው ደብድበው ገደሉት፡፡
* * *
ካለ ራስ ተፈጥሮ ሌላውን መምሰል እንጂ መሆን አይቻልም፡፡ መምሰል ጊዜያዊ ቀለም ነው፡፡ መምሰል ጊዜያዊ ላባ ነው፡፡ መምሰል የሚነጭ መልክ ነው፡፡ ዕውነተኛ ማንነት በዚህም ቢሉት በዚያ መታየቱ የማይቀር ነው፡፡ ጅግራን ከጅግራ፣ ቆቅን ከቆቅ በአንድነት የሚያውላቸው የተፈጥሮ ባህሪ አላቸውና ከዝርያቸው ተነቅለው ጅግራም ቆቅ ልሁን ብትል አይሆንም፡፡ ቆቅም ጅግራ ልሁን ብትል ከንቱ ጥረት ነው፡፡
በሀገራችን ከጥንት ከጠዋት ጀምሮ ከቢሮ ወንበር እስከ ፖለቲካዊው የአደባባይ መድረክ መልካቸውን በመቀያየር፣ ሌላውን መስለውና አክለው ለመታየት የሞከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቡድኖች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች አያሌ ናቸው፡፡ ችግሩ ግን ወንበር ቢቀያይሩ፣ የፖለቲካ ዣንጥላ ቢዋዋሱ፣ ከአገር አገር ቢለውጡ፣ ከአህጉር አህጉር ቢዞሩ የሚመስሉት ሳይሆን፣ የሆኑት ብቅ ማለቱ አሌ አይባልም፡፡ በሎሚ እንደፃፉት ፊደል ቀስ እያለ እየደመቀ ዕውነተኛው ማንነት ይታያል፡፡
“ከመሰረትህ ጋር አትጣላ፣ ለሁልጊዜ ይሆንሃል፡፡ ከካብ ጋ አትጠጋ፣ እላይህ ላይ ይፈርሳል” ይሏልና ለመመሳሰል ብሎ የመሰረትን መልቀቅ ደግ አይደለም፡፡
ከኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ጊዜ ጀምሮ በፖለቲካ ትግል ተመክሮ ውስጥ የምናየው አንድ ቋሚ ክስተት የድርጅቶች መሰነጣጠቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያም፣ ከሀገር ውጪም በተፈጠረ በየትኛውም ድርጅት ውስጥ እስከ ዛሬ ይኸው የመሰነጣጠቅ ሂደት በተመሳሳይ በተደጋጋሚ መከሰቱ፣ ግለሰብም ቡድንም ጥሎ መውጣቱ ወደ ቋሚ ባህሪነት ማለፉን ያሳየናል፡፡ አንድም ደግሞ ወደ ጋራ ዕሳቤና መቻቻል ለመቃረብ የብዙ አንጃዎች መፈጠር እንቅፋት ሲሆን መክረሙን ያፀኸይልናል፡፡
ይሄ ክስተት የአገር ውስጥ መሆን ብቻ ሳይበቃው ከአገር ውጪም እየተዛመተ ፖለቲከኛው “በለጠች እንዲሉኝ አክሱም ጽዮን ቅበሩኝ” አለች እንደተባለው እኔ ብቻ ልደመጥ በሚል ግብዝነት እርስ በርሱ በተሻኮተ፣ ውስጥ ለውስጥ በተናቆረ ቁጥር መከፋፈል እንደ ዋና መርህ እየተያዘ ለባላንጣ ሲሳይ መሆን የእለት የሰርክ የታሪክ ምፀት ይሆናል፡፡ እየሆነም ነው፡፡ ከዚያ ለባላንጣ ማደር ይከተላል፡፡ ጠላት ተብሎ የነበረው መንግስትም “በቅሎ ወደ ፈለገችበት ትበል ብቻ ልጓም አጥብቅ” እያለ እንደየጉዳዩና እንደየጎራው እየቀየደ፣ በኪነ- ጥበቡ “እኔን ያለ የዘለዓለም ህይወት አለው” እያለ ያስጠጋል፣ ወይም ያቅፋል፡፡ ቀስ በቀስ የፖለቲካ ድርጅትነት ባህሪን ይተውና የግል የጥገኝነት ህይወት ይጀምራሉ፡፡ ዋና ባለጉዳይ የመሰሉም ያከሉም ይመስላቸዋል፡፡ “በቅሎ ፈረሶች መሀል ብትሆን ፈረስ የሆነች ይመስላታል” ነው ነገሩ፡፡
ይህ ባህሪ በተለይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትራጆ-ኮሜዲ ተውኔት ውስጥ የተለመደ የመሆኑን ያህል የአሳዛኝ ቀልዱ መሪ - ተዋንያን ሁሌም ምሁራን መሆናቸው ደግሞ ዘግናኝ ሀቅ ያደርገዋል፡፡ ብለብስም ያምርብኛል፣ ራቁቴንም ያምርብኛል ብለው የተፈጠሙ ሊቀ-ሊቃውንት ክራራቸውን አዲስ ዘፈን የቃኙት በመሰላቸው ቁጥር የሚታዘባቸው ህዝብ “ብትናገር ያምናውን፣ ብትፈትል አንድ ልቃቂት” እያለ እንደሚተርት ልብ አይሉም፡፡ ይልቁንም “ረጅም የማይዘለው አጭር የማይሾልከው አጥር እናጥራለን” እያሉ ሊኮሩና ሊገበዙ ከአንገታቸው የጠለቀውና ሀብል ወይ ሜዳልያ የመሰላቸው ሸምቀቆ ክር፣ ጠብቆ መተንፈሻ ያሳጣቸዋል፡፡ ያነጎቱትን ቲዎሪ እንኳ አላባውን ሳይበሉ ልሳናቸው ይዘጋል፡፡
በሀገራችን ይህ አሳዛኝ የታሪክ ስላቅ ያዳበርነው ከዓለም ታሪክ ክፉ ክፉውን ወስደን ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከሮማ ነገስታት ንጉሳዊ ሴራን ተውሰን፣ከፈረንሳይ የደም ዘመን (Reign of Terror) የአንገት መቅያውን መጥረቢያ (Guillotine) ተረክበን፣ ከሩሲያ አብዮት አብዮታዊ አምባገነንነትን፣ ምሁራዊ መከዳዳትንና አንጃ ፈጠራን ወስደን ከአገር በቀሉ የአበሻ ምቀኝነትና ክፋት ጋር ቀምመን የትግል -ስልት፣ ስር ነቀል ስትራቴጂ፣ ሂሳዊ ድጋፍ፣ ቅን ተቃዋሚነት፣ ብክነት (Decadence)፣ ሪፎርሚዝም፣ ሊበራሊዝም ወዘተ ብለን፣ የማታ ማታ በየቲዎሪው ማሳ ስንማስን ውለን ወይ በሙስና ወይ በማናለብኝነት ወይ በግል ጥቅም ወይ በወገን- ማርባት፣ ወይ በሹመት -ዘውድ መጫን፣ ወይ በእልፍኝ አስከልካይነት አሊያም ውጪ በስደት ላይ-ታች በማለት…. እንገኛለን፡፡
ዋናው ጉዳይ ግን ለህዝቡስ ለአገሩስ ምን በጀነው? የተማሩ የተመራመሩ፣ በረዥሙ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ የታገሉና የሚታገሉ የሚመስሉ፣ የሰሩና የሚሰሩም የሚመስሉ ሁሉ ከቡድናዊ ድርጅታዊና ፖለቲካዊ ጥቅም ባሻገርና ከትልቁ የአገር ዕድገት ስእል አንፃር ምን ጠብ አረጉለት? ምን ግብዓት፣ ምን ፋይዳ፣ ምን ንጥረ-ነገር አፈሩለት? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡
“ተሸክመዋል እንዳይባሉ በብታቸው፣ ፈጭተዋል እንዳይባሉ ግማሽ ቁና” የሚለውን ተረትም ልብ እንዲሉ መምከር የሚያሻው አሁን ነው፡፡
Published in
ርዕሰ አንቀፅ