Saturday, 17 August 2024 19:52

ጦርነት ለኦሊምፒክ ውጤትም ጥሩ አይደለም

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(1 Vote)

የዘንድሮ ኦሊምፒክ “አልሆነልንም” ብለዋል ብዙ ኢትዮጵያውያን። “ያስቆጫል፤ ያናድዳል” ብለው የተበሳጩም ሞልተዋል። እጅግ ያዘኑ ደግሞ ብዙ ናቸው። ተብሰልስለው ማልቀስ ጭምር።
ይህን የምለው በሰዎች ሐዘን ላይ ለመቀለድ ወይም ለማላገጥ አይደለም። መልካም ነገር ተመኝተው ከልብ ስለተቆረቆሩ ለምን ይቀለድባቸዋል? ደግሞም፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ወርቅ ሜዳሊያዎችን ሲቀዳጁ፣ እርስ በርስ እየተከታተሉ በአሸናፊነት ሲነግሡ የማየት ዕድል ይናፍቃል። ድንቅ ብቃትን የማየትና የማድነቅ ምኞት፣ ብርቱ የመንፈስ ፍላጎት ነው። እጅግ በጣም የተቀደሰ መንፈስ። የተመኘውን ስናገኝ የመደሰታችን ያህል የተመኘነውን ስናጣ ደግሞ ማዘናችን አይገርምም።
መቆጨትስ? መናደድስ? እንዲህ ዐይነት ስሜቶች ቢፈጠሩብንም አይገርምም። “ይቻል ነበር” ከሚል ግምት ጋር ነው፣ የመቆጨት ስሜት የሚመጣው። “የተበላሸ ነገር አለ” ብለን ካሰብን ደግሞ መናደዳችን አይቀርም። እሺ ይሁን።
አንዳንዴ ግን የምናበዛው ይመስላል።
የአትሌቶች አመራረጥ ላይ እንዲሁ በደፈናው አንዳች ሸፍጥ ወይም ሤራ ቢኖር ነው ብለን ከመገመት አልፈን ወደ ውንጀላ ለመሮጥ አይናችንን አናሽም። ከዚያም እንሻገራለን እንጂ። አሠልጣኝ መሆን ያምረናል - ያለሞያችን። እንዲያውም፣ የንዴትና የብስጭት ንግግራችንን የሚሰማ ሰው፣ እንደ ተበዳይ ሊቆጥረን ይችላል።
የውድድር ሜዳው ውስጥ ገብተን መሮጥና ማሸነፍ የምንችል ነው የሚመስለው - አነጋገራችን። የምር እናበዛዋለን።
ለነገሩማ፣ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤት በጣም ዝቅተኛ ነው ወይ ብለንም መጠየቅ አለብን።
የኢትዮጵያ አትሌቶች በዘንድሮ ውጤታቸው ከአፍሪካ 4ኛ ደረጃ አግኝተዋል። አዎ፣ ከኬንያ ጋር ሲነጻጸር፣ ውጤታቸው እጅግ ወደ ኋላ ቀርቷል። ቢሆንም ግን በጣም መጥፎ ነው የሚባል አይደለም።
የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፉ የአፍሪካ አትሌቶች ብዙ አይደሉም። ዘጠኝ የአፍሪካ አገራት ብቻ ናቸው በወርቅ የነገሡ አትሌቶችን ለማየት የታደሉት። ኢትዮጵያ ከነዚህ ውስጥ አንዷ ናት። ምንም ቢሆን የአትሌቶችን ውጤት ማናናቅ የለብንም ለማለት ፈልጌ ነው።
በእርግጥ፣ ከዐሥር ዓመታት በፊት ከነበረው ውጤት ጋር ስናስተያየው፣ የዘንድሮው የፓሪስ ውጤት በጣም አንሶ ሊታየን እንደሚችል አያከራክርም።
ግን ደግሞ፣ ከአራት ዓመት በፊት የቶክዮ ኦሊምፒክን መርሳት የለብንም። ያኔም ከዘንድሮ የተሻለ ውጤት አልተገኘም።
እንዲያውም የቶክዮው ውጤት በ30 ዓመታት ውስጥ በጣም ዝቅተኛው ውጤት ነው።
1 ወርቅ፣ 1 ብር፣ 2 ነሐስ ነው - የቶክዮ ውጤት።
1 ወርቅ፣ 3 ብር ነው - የፓሪስ ውጤት። ይሄ ይሻላል። በጣም የተሻለ ባይሆንም።
ምን ዋጋ አለው? አሁንማ የብር ሜዳሊያ… በርከት ማለቱ፣ የተፎካካሪነት ደረጃን የሚጠቁም ስለሆነ፣ የወርቅ ሜዳሊያ ብቻ በማየት አላግባብ የዘንድሮውን አቅልለን ልናየው አይገባም።
እንዲያም ሆኖ ግን፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እስከዛሬ በኦሊምፒክ ያስመዘገቡትን የውጤት ታሪክ አንድ በአንድ ብንመለከት… ለካ ብዙ ውድና ድንቅ ሰናይ ነበር ያስብላል። አሁንማምንስ ማለት ይቻላል? ያሳዝናል። ያስቆጫል።
የቶክዮና የፓሪስ ዝቅተኛ ውጤት… የአትሌቶችን የስኬት ታሪክ ወደ ታች የሚያወርድ ነው ማለት ይቻላል። 20 ዓመታትን የኋሊት የሚመልስ ነውና ያሳዝናል። መናደድ ግን ትንሽ ከልክ ማለፍ ይሆናል። “መብታችን ተጣሰ፤ ንብረታችን ተወሰደ” ካላልን በቀር፣ አለቦታችን ገብተን ብንበሳጭ ጤናማ ትርጉም አይኖረውም።
እንዲህ ሲባል ግን የኦሎምፒክ ውጤት ከከፍታ ወደ ዝቅታ ሲወርድ በቸልታ እንየው፤ ባይሞቀን ባይበርደን ይሻላል ማለት አይደለም። ያናድዳል ባይባል እንኳ ያስቆጨናል። “ሰበቡስ ምንድነው?” ብለን እንድንጠይቅም ያስገድደናል።
የተቋማትና የመሪዎች ግርግር፣ ሽኩቻና ውዝግብ ብዙ ነገሮችን ያበላሻል። አንዳንዴማ፣ በእልህ ተጠማመው “ሞቼ ነው ተቀብሬ? ተያይዘን አብረን እንወርዳታለን እንጂ ምን የባሰ ይመጣል?” እያሉ በአትሌቶች ሕይወት ላይ የሚጫወቱ ይመስላሉ። ይሄ ትልቅ መሰናክል ብቻ ሳይሆን ማምለጫ የሌለው የውድቀት ቁልቁለት ሊሆን እንደሚችል ምን ጥያቄ አለው?
እንዲህ ሲባል ግን፣ ያለ ሐሳብ በችኮላ ሰዎችን ለመወንጀል እንደመሮጥ አትቁጠሩት።
ሌሎች እንቅፋቶች እንደሚኖሩ ለመካድም አይደለም።
የዕድል ጉዳይ?
በየጊዜው የሚፈጠሩ የአመራረጥ ስህተቶች ይኖራሉ።
“እንዳለመታደል” የሚቆጠሩ አሳዛኝ አጋጣሚዎችም ይከሰታሉ። ሰምታችሁ ይሆናል።
“ኢትዮጵያ በወርቅ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ የገባችው፣ በድንቅ የአትሌቲክስ ብቃት ነው” ከማለት ጎን ለጎን፣ “ባልተጠበቀ አጋጣሚ የመጣ የወርቅ ሜዳሊያ ነው” የሚሉ ሰዎችን አልሰማችሁም?
የወርቅ ባለ ሜዳሊያ ታምራት ቶላ፣ በማራቶን ውድድሩ ውስጥ የተካተተው “በአጋጣሚ” ነው ማለት አይቻልም? ሌላ አትሌት የጤና እክል ስለገጠመው ነው ታምራት ቶላ የፓሪስን ማራቶን ለመሮጥና የወርቅ ሜዳሊያ ለማሸነፍ ዕድል ያገኘው ተብሏል።
በእርግጥ፣ ታምራት ቶላ ካሁን በፊትም የኦሊምፒክ ባለ ሜዳሊያ ነው። ዘንድሮም ድንቅ ብቃት ባይኖረው ኖሮ፣ ውድድር ወስጥ የመካተት ዕድል አይኖረውም ነበር። በጣት ከሚቆጠሩ ቀዳሚ የማራቶን ሯጮች መሀል የሚጠቀስ ምርጥ አትሌት ባይሆን ኖሮ፣ በተጠባባቂነት አይመረጥም ነበር። ዞሮ ዞሮ አጋጣሚ ቢፈጠር ባይፈጠር፣ የመወዳደር ዕድል ስለተገኘ ብቻ፣ በአሸናፊነት የወርቅ ባለቤት መሆን አይቻልም - በብቃትና በብርቱ ጥረት እንጂ።
ቢሆንም ግን፣ “በማራቶን ላይ የመወዳደር ዕድል ላያገኝ ይችል ነበር” ብለን ስናስብ፣ እንዲህ ዐይነት አጋጣሚዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉና የሜዳሊያ ውጤትና ሰንጠረዥ ላይ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ መገመት አያስቸግርም።
እንዲያም ሆኖ፣ የኦሎምፒክ ውጤት የወረደው በድንገተኛ ክስተት እንዳልሆነ ማን ያጣዋል? የቶክዮ ዝቅተኛ ውጤት ላይ የዘንድሮውም ሲታከልበት፣ “የአጋጣሚዎችና የዕድሎች ጉዳይ ነው” ለማለት አይቻልም።
የተበላሸ ነገር አለ።
ደም ብለው ከተጠቀሱት ምክንያቶችና ሰበቦች በተጨማሪ፣ ዋናውና ትልቁ ችግር፣…. “በአገር ላይ የመጣ ችግር” ነው። እርጋታና ሰላም ርቆናል። ወይም ርቀናል።
የፖለቲካ አተካራ አብዝተናል። ወይም በዝቶብናል።
ከዚያም አልፈን፣ ጦርነቶችን ፈጥረናል፤ ወይም ለጦርነቶች መንገድ ከፍተናል።
የአትሌቲክስ ላይ ብቻ የመጣ ችግር አይደለም። በአገር ላይ የመጣ ችግር ነው። ከፖለቲካ አተካራና ከጦርነት መታቀብ፣ ወደ ኑሮና ወደ ቁምነገር፣ ብንመለስ ወደ ሰላም ብናተኩር ለኦሎሚፒክም ይበጃል።
ብስጭትና ንዴት…. ምን ያደርጋል? እንዲያውም፣ የኦሊምፒክን ትርጉም ያጠፋብናል።
ድንቅ ብቃቶችን በየዐይነቱ ዐይተን ለመደነቅ፣ ለማድነቅና መንፈሳችንን ለማደስ የምንችልበት ልዩ ዕድል ልዩ በረከት መሆኑ ነው- የኦሊምፒክ ክብር።
ብዙዎቻችን እንደ አትሌቶች መሆን አንችልም። ከአለም አንደኛ የመሆን ብቃት የለውም አብዛኛው ሰው። ነገር ግን የዓለም አንደኛ የሆኑ የብቃት ሰዎችን በማየት ነው መንፈሱን ማደስ የሚችለው።
እንዴት መግለጽ እንደሚቻል አንጃ። ከሃይማኖት ጋር ይመስላል።
አብዛኛው ሰው በስነ- ምግባር ታንፆ ወደ ፍፅምና ወደ ቅድስና ለመድረስ እሮጣለሁ ብሎ አይደለም የእግዚአብሔርን ፍፅምና በአክብሮት በአድናቆት የሚመለከተው። አንድ ስንዝር መጓዝና መሻሻል … ትርጉም የሚኖረው ግን የፍጹምና ከፍታዎችን በማክበር ነው። የዓለም አንደኛ በማየት።
የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የኦሊምፒክ ውጤት - በ32 ዓመታት ልዩነት። የባርሲሎና ኦሊምፒክ ባለ ብዙ ታሪክ ነው። ያኔ በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ አትሌቶች በሞስኮ ከተካሄደው ኦሊምፒክ በቀር በሦስት የኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ አልተፈቀደላቸውም።
አሳዛኝም አስቂኝም ታሪክ ነው።
በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላይ ማዕቀብ ያደረገባቸው፣ ራሱ የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑን አስቡት።
በካናዳ ሞንትሪያል፣ በአሜሪካ ሎሳንጀለስ፣ ከዚያም በደቡብ ኮሪያ ሴኡል ከተሞች ውስጥ በተካሄዱ ኦሊምፒኮች ላይ ኢትዮጵያውያን አልተገኙም። ለምን? በአንድ በኩል አገሬው ያኔ ሰላም አልነበረውም። በዚያ ላይ የያኔው መንግሥት “የሶሻሊዝም ጠበቃ ነኝ፤ የካፒታሊዝም ደመኛ ነኝ” በሚል ቀሽም የፖለቲካ ፈሊጥ ነው አሉ “የኦሊምፒክ ውድድሮች” ላይ ያመጸው። በኢትዮጵያን አትሌቶች ላይ የፈረደባቸው ቢባል ይሻላል።
ደርግ በወደቀ በዓመቱ በባርሲሎና ኦሊምፒክ ላይ ነው የኢትዮጵያ አትሌቶች ታሪክ እንደገና እንደ አዲስ የሚጀምረው።
ታሪከኛነቱ ይህ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ አትሌቶች፣ በወድድር የውጤት ዘንጠረዥ ላይ ከዓለም የ33ኛ ደረጃ ለማግኘት ችለዋል። ይህም ብቻ አይደለም።
ከዚያ በፊት በኦሊምፒክ መንደር የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች 3 ብቻ ነበሩ። አበበ በቂላ ሁለት ወርቅ፣ ማሞ ወልዴ አንድ ወርቅ፣ እንዲሁም ምሩጽ ይፍጠር ሁለት ወርቅ።
በባርሲሎና ኦሊምፒክ ላይ የመጀመሪያዋ ሴት ኢትዮጵያዊ አትሌት የሜዳሊያ ባለቤት በመሆን አዲስ ታሪክ አስመዘገበች። ለዚያውም የወርቅ ሜዳሊያ። ጀግናዋ ደራርቱ ቱሉ።
ከዚያ በኋላ የአትላንታ ኦሊምፒክ መጣ። ያኔም ነው ኃይሌ ገብረሥላሴ የሚነግሠው። በዐሥር ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያውን አጠለቀ። ለዚያውም የኦሊምፒክ ሪከርድ በማስመዝገብ። ፋጡማ ሮባ ደግሞ በማራቶን ሌላ የወርቅ ሜዳሊያ!
የሲድኒ ኦሊምፒክ - ኢትዮጵያውያን የገነኑበት
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አዲስ የድል ከፍታ ለማሳየት የቻሉበት ልዩ ታሪክ ነው - የሲድኒ ኦሊምፒክ። አራት አትሌቶች የወርቅ ሜዳሊያ ለማሸነፍ የቻሉበት ሌላ ኦሊምፒክ እስከ ዛሬ አልታየም።
ኃይሌ ገብረሥላሴ እንደገና የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ የአበበ በቂላና የምሩጽ ይፍጠርን ታሪክ ደገመው። ደራርቱ ቱሉም ጨመረችበት። ለሁለተኛ ጊዜ በወርቅ ሜዳሊያ ለማጌጥ በቃች። ገዛኸኝ አበራ በማራቶን፣ ሚሊዮን ወልዴ በአምስት ሺህ ሜትር በየፊናቸው የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆነዋል።
የጌጤ ዋሚ ታሪክም አለ። የቀድሞ የኦሊምፒክ የነሐስ ሜዳሊያ ታሪኳ ላይ፣ በሲድኒ ኦሊምፒክ አንድ የብር አንድ የነሐስ ሜዳሊያዎችን ለመጨመር ችላለች - በአምስትና በዐሥር ሺህ ሜትር።
የአቴንስ ኦሊምፒክ - የቀነኒሣና የመሠረት ወርቆች
ቀነኒሣ በቀለ በዐሥር ሺህ ሜትር የኦሊምፒክ ሪከርድ በመስበት የወርቅ ሜዳሊያ ከማግኘቱ በተጨማሪ፣ በአምስት ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸንፏል።
መሠረት ደፋር፣ በአምስት ሺህ ሜትር ወርቅ አሸንፋለች።
የቤጂንግ ኦሊምፒክ - ቀነኒሣና ጥሩነሽ የነገሡበት
ጥሩነሽ ዲባባና ቀነኒሣ በቀለ በየፊናቸው በአምስትና በዐሥር ሺህ ሜትር ድርብ የወርቅ ሜዳሊያዎችን በአስደናቂ ድል ተቀዳጅተዋል። ቀነኒሣ በሁለቱም ሩጫዎች የኦሊምፒክ ሪከርዶችን ሰብሯል። ጥሩነሽ ደግሞ የ10000 ሜትር ሪከርድ ሰብራለች።
የለንደን ኦሊምፒክ - ጥሩነሽ፣ መሠረት፣ ቲኪ
ጥሩነሽ በዐሥር ሺህ ሜትር፣ መሠረት ደፋር በአምስት ሺህ ሜትር፣ ቲኪ ገላና ደግሞ የኦሎምፒክ ሪከርድ በማሻሻል ጭምር በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፈዋል።
በሪዮ፣ በቶክዮ፣ በፓሪስ ኦሊምፒኮች አንድ አንድ ወርቅ
አልማዝ አያና፣ ሰለሞን ባረጋ፣ እና ታምራት ቶላ ናቸው ወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፉት። የአልማዝ አያና ለየት የሚለው፣ የኦሊምፒክ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሪከርድ በመስበር ማሸነፏ ነው።
በኦሊምፒክ የሜዳሊያ ብዛት - ጥሩነሽና ቀነኒሳ
እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ካገኟቸው 24 ወርቅ ሜዳሊያዎች መካከል 16ቱ በ7 አትሌቶች የተገኙ ናቸው።
ጥሩነሽ ዲባባ በኦሊምፒክ ውድድሮች 3 ወርቅና 3 ነሐስ ሜዳሊያዎችን አሸንፋለች።
ቀነኒሳ በቀለ 3 ወርቅና 1 ብር ሜዳሊያዎችን ተቀዳጅቷል።
በወርቅ ሜዳሊያ የደመቁት ድንቅ አትሌቶች፣ ራሳቸውን እንደ ልዩ ሰው እንደ ብርቅ ሰው ላይቆጥሩ ይችላሉ። ብዙዎቻችንም እንደዚያ ለማሰብ እንቸገራለን። ግን ሌላ ትርጉም እስካልሰጠነው ድረስ፣ “እንዲሁ በደርዘን በደርዘን በየዓመቱ የሚመጡ ዐይነት ሰዎች አይደሉም” ብለን ለመናገር ምንም የሚከብድ ነገር የለውም።
ለነገሩማ፣ የኦሊምፒክ ውድድሮች ትልቁ መንፈሳዊ ፋይዳና በረከት፣ አስደናቂ የብቃት ሰዎችን በማየት የመደነቅና የማድነቅ መንፈሳዊ ድግስ መሆኑ ላይ ነው።

Read 302 times