ከዚህ ቀደም በነበረው እትም ስለአር ኤች ፋክተር (RH factor) ወይም በተለምዶ ሾተላይ ተብሎ ስለሚጠራው ችግር ምንነት እና ስለሚያስከትለው ችግር ማቅረባችን ይታወሳል። የዚህን ቀጣይ ክፍል ለንባብ እንሆ ብለናል።
አቶ ከፍያለው ያሬድ ይባላሉ። ኑሯቸውን ያደረጉት በገጠር ከተማ ውስጥ ነው። አቶ ከፍያለው ከመጀመሪያ ሚስታቸው 1 ከሁለተኛ ሚስታቸው 5 ልጆችን ወልደዋል። ገና በለጋ እድሜያቸው ያገቧትን የመጀመሪያ ሚስታቸውን ለመለየት የተገደዱት ሚስታቸው ሁለተኛ ልጅ መውለድ ባለመቻላቸው ነበር። ልጅ አለመወለዱ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ የተፀነሰው ልጅ መውረድ(መቋረጥ) በእሳቸው እና የአከባቢው ሰው “እርግማን ቢኖርባት ነው” የሚል እሳቤ አመጣ። ይህ እርግማን ደግሞ ከሚስታቸው አልፎ በአቶ ከፍያለውም ላይ ችግር የሚያስከትል ነውና የመጀመሪያ ሚስታቸውን ለመተው መረጡ። በዛ ላይ 1 ልጅ ብቻ ወልደው መቅረት የማይታሰብ ነበር። እናም ሌላ ሚስት አግብተው 5 ልጆችን ወለዱ። አቶ ከፍያለው ከመጀመሪያ ሚስታቸው የወለዷትን ልጅ ከእናቷ ጋር በመተው የእናቷ እርግማን ሰለባ እንድትሆን አልፈለጉም። እናትም ልጃቸውን ለማሳደግ አቅም ስላነሳቸው ለአባት ለመስጠት ተገደዱ።
የአቶ ከፍያለው የቀድሞ ሚስት ድህነት፣ በሽታ እና ብቸኝነት ስለተደራረበባቸው ብዙም ሳይቆዩ ከእዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። አቶ ከፍያለው እና የአከባቢው ሰው ግን በዘራቸው የተዋረሰ ባዕድ አምልኮ ህይወታቸውን እንዳሳጣቸው አሰበ።
ይህ ታሪክ ከተፈጠረ 20 ዓመታት አልፈዋል። አቶ ከፍያለው ግን የትላንት ያህል ያስታውሱታል። የህይወታቸው መጥፎ ክፍል ነው። ያሳደረባቸው ጠባሳም ቀላል አይደለም። ምንም እንኳን የመጀመሪያ ሚስታቸውን የተለዩት እሳቸው ቢሆኑም የመጀመሪያ ፍቅራቸው ናትና ሁልጊዜም ያስታውሷታል። አንዳንዴም “የሚስቴ መሞት ምክንያት ነኝ” የሚል ሀሳብ ውል ስለሚልባቸው በእርጅና ምክንያት የታደከመው ልባቸውን ፀፀት ይበልጥ ሲያዳክመው ይሰማቸዋል። እናም ከገቡበት የትዝታ ባህር፤ የፀፀት ማዕበል በልጃቸው ፅጌሬዳ ቀዝፈው ይወጣሉ። የቀድሞ ሚስታቸው ማስታወሻ ናትና።
ከአቶ ከፍያለው የመጀመሪያ ሚስት የተወለደችው ፅጌሬዳ ለአቅመ ሄዋን ደርሳ ትዳር መስርታለች። ፅጌሬዳ ከእናቷ ጋር በተመሳሳይ መልኩ አንድ ልጅ ከወለደች በኋላ ሁለተኛ መድገም አልቻለችም። ይህም የአከባቢውን ሰው ግምት የሚያረጋግጥ ሆነ። ልክ እንደ እናቷ በአከባቢው ሰው ለሚነገረው ንግርት ሰለባ ሆነች። ግን ከእናቷ የሚለያት አንድ እውነታ አለ። 2ኛ ልጅ ባለመውለዷ ምክንያት ባለቤቷ አልተዋትም። ህክምና እንድታገኝ አደረገ። እናም ሁለተኛ እና ሶስተኛ ልጅ መውለድ ቻለች። የፅጌሬዳ መውለድ ለእሷ እና ለትዳር አጋሯ ብቻ ሳይሆን ለመንደሩ ሰው አዲስ መንገድ የከፈተ ሆነ።
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም በማተርናል ፌታል ሜዲስን ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው የሚያገለግሉት። እንዲሁም በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ህክምና የሚሰጡ ሲሆን የበረካህ ስፔሻሊቲ ክሊኒክ ባለቤትም ናቸው። አርኤች ፋክተር (ኢንኮምፓትቢሊቲ) ላለባቸው ጥንዶች[ፅንስ] ህክምና ይሰጣሉ። እንደ ዶ/ር ሰኢድ አራጌ ንግግር አንዲት ሴት ይህ ችግር አጋጥሟታል የሚባለው የአባት የደም አይነት ፓዝቲቭ(አር ኤች ፋክተር ያለው)፣ የእናት ኔጌቲቭ(አር ኤች ፋክተር ፋክተር የሌለው) እና የተፀነሰው ልጅ ፓዝቲቭ(አር ኤች ፋክተር ያለው) ሲሆን ነው ብለዋል።
“40 በመቶ የሚሆን ፅንስ የእናትን የደም አይነት ይይዛል” በማለት እናቶች (ሴቶች) የደም አይነታቸው ኔጌቲቭ (አር ኤች የሌለው) ስለሆነ ብቻ በፅንስ ላይ የሚያጋጥም ችግር (ሾተላይ) አለባቸው ማለት አለመሆኑን ዶ/ር ሰኢድ አራጌ ተናግረዋል። ስለሆነም የአባት የደም አይነት ፓዘቲቭ ቢሆንም 40በመቶ የሚሆነው ፅንስ የእናትን የደም አይነት ኔጌቲቭ ስለሚይዝ ችግር አያጋጥመውም። በተመሳሳይ የጥንዶቹ(የሁለቱም) የደም አይነት ኔጌቲቭ ከሆነ የሚፅነሰው ልጅም ኔጌቲቭ ስለሚሆን የሾተላይ ችግር አይፈጠርም። እንዲሁም ከዚህ ቀደም የሾተላይ ችግር ያጋጠማቸው ጥንዶች በቀጣይ እርግዝና ላይ ፅንሱ የእናትን የደም አይነት(ኔጋቲቭ) የመያዝ እድል ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን ፅንሱ በድጋሚ የአባቱን የደም አይነት ከያዘ ህክምና እንዲያገኝ ይደረጋል።
ለአርኤች ኢንኮፓቲቢሊቲ (RH incompatibility) ወይም ሾተላይ የሚሰጥ ህክምና
ከዚህ ቀደም የሾተላይ ችግር ያጋጠማቸው እናቶች በቀጣይ እርግዝና ለችግሩ ተጋላጭ መሆን ወይም አለመሆናቸውን ለማወቅ የሚደረግ የላብራቶሪ ምርመራ
28ኛ የእርግዝና ሳምንት ላይ የሚሰጥ መድሃኒት
ከወሊድ በኋላ የሚሰጥ መድሃኒት
ፅንስ ሆድ ውስጥ እያለ ደም እንዲሰጠው ማድረግ
ልጅ ከተወለደ በኋላ የሚሰጥ ህክምና
የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት ፅንስ ሆድ ውስጥ እያለ የደም ማነስ ሲያጋጥመው ደም እንዲሰጠው ይደረጋል። ይህም የደም አይነታቸው ኔጊቲቭ (አር ኤች ፋክተር ከሌላቸው) ሰዎች የተወሰደ ነው። በይበልጥ ኦ ኔጌቲቭ (O Negative) የደም አይነት ለፅንሱ እንዲሰጥ ይደረጋል። ስለሆነም የፅንሱ እና የእናት የደም አይነት ኔጌቲቭ (ተመሳሳይ) እንዲሆን በማድረግ ችግሩን ያስተካክላል። እንደ ዶ/ር ሰኢድ አራጌ ንግግር እናት ኔጌቲቭ [Negative] እና አባት ፓዝቲቭ[Positive] የደም አይነት ላለው ፅንስ በሙሉ 28ኛ የእርግዝና ሳምንት ላይ ህክምና ይሰጣል። ነገር ግን በዚህ ወቅት የሚሰጥ ህክምና በድጋሚ ከወሊድ በኋላ እንዲሰጥ የሚደረገው ፅንሱ ከተወለደ በኋላ ፓዝቲቭ የደም አይነት እንዳለው ሲረጋገጥ ነው። ከእናቱ ጋር በተመሳሳይ መልኩ ኔጌቲቭ ከሆነ ህክምና (መድሃኒት) አያስፈልገውም። ፅንስ ሆድ ውስጥ እያለ የደም አይነቱን ማወቅ ይቻላል። ነገር ግን የደም አይነቱን ለማወቅ በሚደረግ ምርመራ ችግሩን ላለማባባስ ሲባል በ28ኛ የእርግዝና ሳምንት ላይ ተጋላጭ ለሆኑ እናቶች በሙሉ ህክምናውን መስጠት ተመራጭ ተደርጓል። “ለመድሃኒት መግዣ 28ኛ ሳምንት ላይ ያወጡትን ገንዘብ ያጣሉ እንጂ ሌላ የሚከስሩት ነገር የለም። ተጓዳኝ ጉዳት የለውም” ብለዋል ዶ/ር ሰኢድ አራጌ። አክለውም የመድሃኒቱን ውድ መሆን ጠቅሰው ነገር ግን ከሚወጣው ገንዘብ ጋር ሲነጻጻር የመድሃኒቱ ጥቅም ይበልጣል ብለዋል።
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም በማተርናል ፌታል ሜዲስን ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ እንደተናገሩት ፅንስ ሲቋረጥ ወይም ልጅ ህይወቱን ሲያጣ ከአር ኤች ችግር ጋር የማማያዝ ሁኔታዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። “አርኤች ኔጌቲቭ ወይም ፓዘቲቭ የሆኑ እናቶች በእርግዝና ወቅት በተለያየ በሽታ (ችግር) ምክንያት ልጅ ሊያጡ ይችላሉ። ነገር ግን ከአርኤች ፋክተር (የሾተላይ ችግር) ጋር ሊያያዝ አይገባውም” ብለዋል። በሾተላይ ላይ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ ለሁለት ችግሮች ያጋልጣል። የመጀመሪያው የእናቶችን ትክክለኛ ችግር እንዳይታወቅ ማድረጉ ሲሆን በዚህም አስፈላጊውን ህክምና እናዳያገኙ ያደርጋል። ሁለተኛው ደግሞ የስናልቦና ችግር በማስከተል በቀጣይ እርግዝና ላይ ጫና ማስከተሉ ነው።
“የተሳሳተ ግንዛቤ አለ። አር ኤች ኔጌቲቭ ስለሆኑ ብቻ በሽታ እንዳለባቸው የሚያስቡ አሉ። አር ኤች ኔጌቲቭ የሆኑ ሰዎች ጤናማ ናቸው። መውለድ ይችላሉ” ብለዋል ዶ/ር ሰኢድ አራጌ። ስለሆነም ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች ችግሩን አስቀድሞ በመከላከል እና ህክምና በማድረግ መውለድ ይቻላሉ።
የአር ኤች ፋክተር ችግር (ሾተላይ) መከላከያ መንገድ
ትዳር ሲመሰረት የአር ኤች ፋክተር ምርመራ ማድረግ
ኔጌቲቭ የደም አይነት ያላቸው ሰዎች ደም ቢለግሱ
ተጋላጭ የሆኑ እናቶች በማንኛውም ችግር ፅንስ መቋረጥ ሲያጋጥማቸው ህክምና ማድረግ (መድሃኒት መውሰድ)
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም በማተርናል ፌታል ሜዲስን ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ በኢትዮጵያ በየትኛውም አከባቢ የሚገኙ ተጋላጭ የሆኑ እናቶች ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመሄድ ህክምናውን ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል። ስለሆነም ችግሩ የተባባሰ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ህክምናውን ለማድረግ የህክምና ባለሙያዎች ወደ ሆስፒታሉ ታካሚዎችን እንዲልኩ መልእክት አስተላልፈዋል።
Saturday, 17 August 2024 19:56
“ለሾተላይ ችግር ተጋላጭ የሆኑ እናቶች መውለድ ይችላሉ”
Written by የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም በማተርናል ፌታል ሜዲስን ሰብ ስፔሻሊስት ዶ/ር ሰኢድ አራጌ
Published in
ላንተና ላንቺ