የአረንጓዴ አሻራ ቁጥሮች አስደናቂ ናቸው- በአገርም በአዲስ አበባም። ከዓመት ዓመት እየጨመረ የመጣው የችግኝ ብዛት ዘንድሮ ወደ 40 ቢሊዮን ይደርሳል። ምን ማለት እንደሆነ አስቡት።
የአገር አሻራ እየሰፋ
የችግኝ ቁጥር እየበዛ
2011 4.7 ቢሊዮን
2012 10.6 ቢሊዮን
2013 17.7 ቢሊዮን
2014 25 ቢሊዮን
2015 32.5 ቢሊዮን
2016 40 ቢሊዮን
ኢትዮጵያ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ቢተከል፣ ከአምስት ወይም ከስድስት ሜትር ባልበለጠ ርቀት ውስጥ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ የማግኘት ያህል ነው ብዛቱ። ታዲያ ይሄ ቀላል አሻራ ነው? የዚህ ታሪክ ተቋዳሽና ተከፋይ ኢትዮጵያውያንም ሚልዮኖች ናቸው። ደግነቱ፣ የታሪክ ተሳታፊ ብቻ ሳይሆን ባለቤት ለመሆን፣ የመግቢያ ፈቃድና ክፍያ አይጠየቅበትም። ሁሉም የዐቅሙን ያህል ችግኝ እየተከለ የታሪክ አሻራውን ለትውልዶች ይተክላል።
የአዲስ አበባን ደግሞ ተመልከቱ።
ዓምና የተተከሉ 17.5 ሚሊዮን ችግኞችን ጨምሮ ባለፉት አራት ዓመታት ከ58 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
ዘንድሮ 20 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ዘመቻ ሲታከልበት፣ ከ78 ሚሊዮን ያልፋል።
የችግኝ ብዛት በአዲስ አበባ
2011-14 41 ሚልዮን
2015 58.5 ሚልዮን
2016 78.5 ሚልዮን
አዲስ አበባን ከጥግ እስከ ጥግ በሦስት ሜትር ርቀት ችግኞችን የመትከል ያህል ነው ብዛቱ። ግን ገና ይቀረዋል።
ብዙ ስለሚቀረውም የከተማዋ ነዋሪዎች በየሳምንቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን ይተከላሉ።
እናንተም ወይ ተክላችኋል። ወይ ሲዘገብ ሰምታችኋል። ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ደግሞ በርካታ የሚዲያ ባለሙያዎችና የኪነጥበብ ሰዎች የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ባዘጋጀው ፕሮግራም፣ የድርሻቸውን ችግኝ ተክለዋል።
ዜና በመናገርና ሰዎችን በማበረታታት ብቻ ሳይሆን በተግባር አሻራቸውን በሥራ አሳይተዋል። መልካም ተግባርን ከሩቁ ማየትና መስማት… ጥሩ ነው። በጎ ነው። በተግባር ሲሠሩት ግን ልዩ ስሜት ይሰጣል ብሏል የሚዲያ ባለሙያው ሽመልስ ለማ።
ስሜቱንና ሐሳቡን ስንጠይቀው ሽመልስ እንዲህ ብሎናል።
በአካል መጥተህ ራስህ ስትሠራው የምታገኘው ስሜት ልዩ ነው። ራስህ እየተከልክ ነው ልዩነቱ የሚገባህ። እንደ ልጅህ ነው፣ ችግኝ ስትተክል የምትሳሳለት። የተከልኳቸው ችግኞች ላይ ጂፒኤስ ባስርላቸው ደስ ይለኛል። ካደጉ በኋላ “እነዚህ የእኔ ነበሩ” ስል ይታየኛል።
አስገራሚ የመንፈስ እርካታ እንደሚገኝበት ሽመልስ ሲገልፅ፣ “እንደ እኛ እናንተም መጥታችሁ አሻራችሁን አኑሩ። ትልቅ ታሪክ ነው” ብሏል ሽመልስ።
ታዋቂው የኪነጥበብ ሰውና “የቤቶች ድራማ” ፈጣሪ ጥላሁን ጉግሳ በበኩሉ፣ ችግኝ መትከል የሁላችንም ጉዳይ ነው፤ ለሌላ ብለን ሳይሆን ለልጆቻችን ነው የምንተክለው ብሎናል።
“ነገን ዛሬ መትከል” የሚለው መሪ ቃል ትልቅ ትርጉም የያዘ እንደሆነ ሲገልጽ፣ ለነገ የሚሆነውን ነገር ዛሬ ከወዲሁ መሥራት መቻል ማለት ነው ይላል። ታዲያ ይሄ እንዴት ያምልጠን?
የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባዘጋጀው በዚሁ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ የዛሬ ዓመት መጥተን ችግኞችን ተክለናል። ነገ ስንለው የነበረው ጊዜ… ይሄውና ዓመት ቆጥሮ መጣ።
ዘንድሮ ይሄውና ደረሰ። አሁንም እንደገና ለመጪው ጊዜ ለነገ እንተክላለን።
ጥቅሙ ለአገር ነው። ጥቅሙ ነገ ለሚመጡት ታዳጊዎች ነው። ጥቅሙ ለሕዝብ ነው። ለሌላ አይደለም።
የሁላችንም የጋራ ዓላማችን መሆን አለበት።
ለማንም ብዬ አይደለም የምተክለው። እኔ የምተክለው ለነገ ለልጆቼ ነው። ነገ ኢትዮጵያን ለሚረከቧት ትውልዶች ነው።
’ቤቶች’ ድራማ 12ኛ ዓመት የገባ ድራማ ነው ፤ አምስቱንም ዓመት በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈናል፤ ወደፊትም ይህንኑ እንቀጥላለን ብሏል- ጥላሁን ጉግሳ።
እውነት መቀጠል ማስቀጠል ነው የሚሻለው። በአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዘንድሮውን አረንጓዴ አሻራ ሲያስጀምሩም ይህን ነበር የተናገሩት። ከተማችንን እናበለጽጋለን፤ እያስዋብን እንቀጥላለን፤ የከተማችንን አረንጓዴ ሽፋን 30 በመቶ እናደርሳለን ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከ3 በመቶ በታች ወርዶ የነበረው አረንጓዴ ሽፋን ወደ 17 በመቶ ማደጉን የገለጹት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ልምላሜን ከማስፋፋትና ከተማን ከማስዋል ጎን ለጎን የአትክልትና የፍረፍሬ ችግኞችም እንደሚተከሉ ተናግረዋል። የኢኮኖሚና የኑሮ ጉዳይ፣ መንፈስን ከሚያድስ ውበትና የአካባቢ ልምላሜ ጋር የሚስማማ እንጂ የሚቃረን አይደለም።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው እንደተናገሩት ከሆነም ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴዓሻራ የተተከሉ የፍራፍሬ ችግኞች ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ ናቸው።
የአረንጓዴ አሻራ ትርጉሞች
አረንጓዴ አሻራ፣ አገርን አረንጓዴ ማልበስ ነው። ግን ከዚያም በላይ ነው።
በእርሻ ምርት ራሳችንን ችለን ለሌሎች ለመትረፍም ነው ችግኝ የምንተክለው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የፍራፍሬ ጭማቂ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች መስፋፋት አለባቸው። የሚሳካልን ግን ችግኞችን ከተከልን ነው።
በአፍሪካ በግዙፍነታቸው አንደኛና ሁለተኛ የሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን እየገነባን ነው። ግድቦቹ በቂ ውኃ የሚኖራቸውና ውጤታማ የሚሆኑት ግን ችግኞች ከተከልን ነው።
በእርሻም፣ በኢንዱስትሪም፣ በመሠረተ ልማትም… ሁሉም እንዲሳካ ነው ችግኝ የምንተክለው። ለነገ ለልጆቻችን የምንፈጥረው ሀብት ነው ብለዋል ጠ/ሚ ዐቢይ። ይህንም ሐሳብ ያፍታቱታል።
ኢትዮጵያ ካለ ምንም ጥርጥር ራሷን ትመግባለች። ለራሷ የሚበቃ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የሚተርፍ እህልና ፍራፍሬ ታመርታለች።
ካለ ምንም ጥርጥር ከተሞቿን ትለውጣለች።
ካለ ምንም ጥርጥር ከዕዳ ቀንበር ትገላገላለች።
ካለ ምንም ጥርጥር አርአያ የሆነ ሥራ በአፍሪካ ትሠራለች።
ብልጽግናዋን ታረጋግጣለች።
ይሄ ሁሉ እውነት እንደሆነ ከገለፁ በኋላ፣ ግን ምኞት ብቻ መሆን የለበትም ብለዋል።
ንግግር ብቻ መሆን የለበትም። በተግባር መሥራት አፈር መንካትና ችግኝ መትከል ይፈልጋል። ከተማ ማጽዳት ይፈልጋል።
አበርትተን ከሠራን በእርሻ ላይ ያመጣነው ውጤት በሌላም እናሳድገዋለን። በስንዴ ላይ ዓለም የሚመሰክርለት ውጤት አምጥተናል። ሩዝ በዕጥፍ ጨምሯል።
ያማረች፣ ንጹሕ የሆነች፣ ለኑሮ የተመቸችና የምትስማማ፣ ቱሪስቶችንም የምትስብ ኢትዮጵያን ለማየት እናም ለመገንባት የሚፈልግ ማንም ትውልድ ቢኖር፣ ቀላሉ ሥራ ችግኝ በመትከል መጀመር ነው።
አስፋልት፣ ግድብ፣ ሕንጻ የውጭ ምንዛሪ ይፈልጋል።
ችግኝ መትከል ግን በራሳችን ዐቅም ልንሠራው እንችላለን። 130 ሺ የችግኝ ጣቢያዎች አሉ።
ለልጆቻችን ውብ አገር ማዘጋጀት እንችላለን።
አገሩን የሚወድ ማንም ሰው፣ ማንም ዜጋ፣… ሁሉም ሰው፣ ችግኝ እየተከለ አብረን ለአገር ለትውልድ እንስራ። የመንግሥት፣ የአንድ ፓርቲ፣ የአንድ ዘመን ሥራ አይደለም ብለዋል።
የመትከል፣ የማስቀጠል፣ የማጽናት፣ የመጠበቅ ሥራ ነው።፣
አብረን ተባብረን ብንቆም አገራችን ያማረች ትሆናለች።
እየመጣ ያለውን ፍሬ፣ እየመጣ ያለውን ውጤት፣ ለሥራ በመትጋት ብቻ የሚጨበጥ ስለሆነ፣ ሁላችንም እንድንተጋ አደራ እላለሁ።
ለመነሣት ማኮብኮብ የጀመረ ሀገር ከየአቅጣጫው ዱላ ይሰነዘርበታል። ጨክነን ከሠራን ግን እናሳካዋለን። ወደ ከፍታ እንነሣለን። ደቡብ ኮሪያ አሳክታለች። ቻይና አሳክታለች። ሲንጋፖር አሳክታለች። አሜሪካ አሳክታለች። ጀርመን አሳክታለች። ኢትዮጵያ ከማንም አታንስም። እናሳካዋለን። የምናሳካው ግን፣ ጨክነን በመስራት ብቻ ነው።
ተባብረን ከሠራን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ማስረከብ እንደምንችል ምንም ጥርጥር የለውም። በዛው እምነት ነው የምንሠራው። በዛው መንፈስ ነው የምንተጋው። ውጤቱም ያማረ ነው።
ከሕዝባችን ጋር ሆነን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን እናሸጋግራለን ብለዋል- ጠ/ሚ ዐቢይ።
የኢትዮጵያ መንገድ ይለያል፤ ያዋጣለል።
አንዳንድ ተላላ አገራት፣… የእርሻ መሬትን መቀነስ፣ መስኖን ማስቀረት፣ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎችን ዐቅም ማዳከም፣ መብራት የማጥፋት ክብረ በዓል” በሚል ፈሊጥ ኢኮኖሚያቸውን ያዳክማሉ። ራሳቸውን ይቀጣሉ።
ኢትዮጵያ ግን፣ በአረንጓዴ አሻራ በቢሊዮን በቢሊዮን ችግኞችን እየተከለች በእርሻና በመስኖ ላይ ትተጋለች። ከልመና ለመገላገል ብቻ ሳይሆን ለመበልጸግ በበጋ እርሻ ስንዴ ታመርታለች።
የተራቆቱ አካባቢዎችን በአረንጓዴ አሻራ አለምልማ እያሳመረች፣ በኮሪደር ልማት መዲናዋን እንደ ስሟ እንድታብብ 24 ሰዓት ትሰራለች።
አዲስ አበባ በብርሃናት ፈክታ ለሌሎችም አርአያ ትሆናለች። ሁሉንም ከተሞች ከጨለማ አውጥታ ለማድመቅ ትሠራለች።
ያማረ ነገር ማን ይጠላል? በአዲስ አበባ በጥቂት ወራት የኮሪደር ልማት አማካኝነት የመጣውን ለውጥ መታዘብ ትችላላችሁ።
የቤተሰብ የአመሻሽ ሽርሽር ዘንድሮ እንዴት እየተለመደ እንደመጣ አይታችኋል?
አረንጓዴ አሻራ ከዚህ ሁሉ ጋር የተዋደደ ታሪክ ነው።
በቲክቶክ የሚታወቀው ምንቴ ቢሊየነር ደግሞ፣ አረንጓዴ አሻራን ከአስተሳሰብ ለውጥ ጋር ያዛምደዋል።
አስተሳሰባችንን እየተከልን ነው። ችግኝን ስንተክል፣ መልካም አስተሳሰብንም በውስጣችን እንዲተከል እፈልጋለሁ።
በአንድ ፍሬ ዛፍ ውስጥ ብዙ ጫካ እንደሚኖር ማመን አለብን። በአንድ ሰው ውስጥም እንደዛው ብዙ ሕዝብ አለ። ስለዚህ ይህንን አምነን በምንገኝበት ሁሉ አሻራችንን መጣል አለብን ይላል- ምንቴ።
ምድርን የሚያለማው የሰው ልጅ ነው።
በሰውም ላይ ጥሩ አንደበት መናገር አለብን።
አብረን ተባብረን እናልማ፤ ባላችሁበት ችግኝ ትከሉ! የሚል መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ከገለፀ በኋላ እንዲህ ይላል።
እዚህ አገር ላይ ማንኛውም ሰው ሃብታም መሆን “አለበት” ብዬ ነው የማምነው።
ሰርተን፣ ተግተን ...ተባብረን እንደዚህ ከሰራን፣ ድህነት እኛ ጋር የሚቀመጥበት ምክንያት የለውም። አሽቀንጥረን እንጥላለን።
ስለዚህ ችግኝን ትከሉ፤ ጥሩ ሃሳቦችን እርስ በርስ እንተካከል! አገራችንን እንቀይር! እናልማ! ይላል ምንቴ።