Sunday, 18 August 2024 19:06

“በሰራሁባቸው የአፍሪካ አገራት “ጥቁር ገበያ” የሚባል ሰምቼ አላውቅም”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ለመክፈት የሚፈልጉ የስራ ፈቃድ ማመልከቻ እንዲያቀርቡጥሪ ያደረገው ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም.ነበር። በዚህም ጥሪው በአገር ውስጥም ሆነ ውጭ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደኢትዮጵያውያን ማመልከቻውን ማቅረብ እንደሚችሉ መግለጹ አይዘነጋም። የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች መከፈታቸው ፋይዳው ምንድን ነው? ምንስ ተግዳሮት
ይኖራቸዋል? በዚህ ረገድ የአፍሪካ አገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ከምጣኔ ሃብት ባለሞያው የፖሊሲ አማካሪው ቆስጠንጢኖስ በርሀ ተስፋ (ዶ/ር) ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።


          የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች መከፈት ለአገራችን ምን ጥቅም ያስገኛል?
ይሄ ሁሉም አገር ውስጥ ያለ ነው። በተለይ በየአየር ማረፊያው የውጭ ምንዛሪየሚመነዝሩት እነሱ ናቸው። በአብዛኛው እነዚህ “የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች” የሚባሉት  በየኤርፖርቱ፣ ቱሪስቶች በሚበዙበት አካባቢ...ከተማ ውስጥ ደግሞ፣ በትልልቅ የገበያ አዳራሾች ይገኛሉ። በርግጥ አሁን እየጠፉ ነው ያሉት። ምክንያቱም በኤሌክትሮኒክ መገበያየት ተችሏል። ኬንያ ኤርፖርት የነበሩት በሙሉ የሉም። ምክንያቱም ሰዎች አሁን በስልካቸው የሳፋሪኮም ሲም ካርድ ይገዙና ኤምፔሳ ውስጥ ይገባሉ። ከክሬዲት ወይም ዴቢት ካርዳቸው ወደ ስልካቸው ገንዘብ ያስተላልፋሉ። ከዚያ በኋላ በሽልንግ ይመጣላቸዋል።
አገራችን ውስጥ በርከት ያለ የውጭ ምንዛሪ ሠዎች እጅ ይኖራል የሚል ግምት አለ፤ ሰዎች እንዲሁ “መጠባበቂያ” ብለው የሚይዙት። እኒህ ሰዎች ባንክ ሄደው፣ ተሰልፈው  ለመመንዘር ጊዜ የላቸውም። በቀላሉ የግል ምንዛሪ ቢሮዎች ሄደው ግን መመንዘር ይችላሉ።
የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ኤርፖርት ውስጥ ባንኮችን ተክተው ሊሰሩ የሚችሉ ናቸው። በርግጥ የግል ባንኮች ከሚሰጡት ምንዛሪ በታች ነው የሚመነዝሩት። አንደኛ ኮሚሽን አላቸው። ሁለተኛ ከነእርሱ በታች በመስጠት ብዙ ትርፍ ያገኛሉ። እንግዲህ የግሎቹ አንዱ ተግዳሮት ሊሆን የሚችለው ይህ ነው። ምክንያቱም አንድ ሰው ሊመነዝር ሲሄድ፣ ዛሬ “የምንለውጥበት ገንዘብ ይህ ነው” ብለው  ይለጥፋሉ። ብዙ ትርፍ የሚገኝበት ስራ ነው። ነገር  ግን አገራችን ውስጥ ብሔራዊ ባንክ በቅርብ ስለሚቆጣጠራቸው፣ እንደዚህ ዓይነት ነገር ውስጥ የመግባት ዕቅድ አይኖራቸወም። በቀላሉ የግል ምንዛሪ ቢሮዎች ሄደው ግን መመንዘር ይችላሉ።  የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ለቱሪዝም ትልቅ አስተዋጽዖ “ይኖረዋል” ብዬ ነው የማስበው።
የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችና ባንኮች ምንና ምን ናቸው?
የግሎቹ የሚመነዝሩትን ብር ከባንክ ነው የሚወስዱት። የውጭ ምንዛሪውንም ባንክ ወስደው ነው የሚያስቀምጡት። ስለዚህ ከባንክ ጋር ነው የሚሰሩት። ብዙ አገራት የባንክ ቅርንጫፎቻቸው እየዘጉ ነው ያሉት። አሁን ስዊድን፣ ደቡብ ኮሪያ በሶስት ዓመት ውስጥ የባንክ ቅርንጫፍ የሚባል አገራቸው ውስጥ አይኖራቸውም። ምክንያቱም ሰዎች  በስልካቸው  መገበያየት ጀምረዋል። በአገራችን የኢንተርኔት ነገር የማያወላዳ ስለሆነ ነው እንጂ አሁን ኤምፔሳ የዛሬ አምስት ዓመት በስልክ የተገበያዩ ኬንያውያን፣ ወደ 45 ትሪልዮን ሽልንግ ነው ያስተላለፉት። ስለዚህ ወደፊት ባንክ ቅርንጫፎች መኖራቸው ምንም ጥቅም አይኖራቸውም። ቅርንጫፍ ሲኖር ቤት ይከራያሉ። ሰራተኛ ይቀጥራሉ። ዕቃ መግዛት አለባቸው። ይህ  ባንኮችን ከውጪ የሚያድናቸውና አትራፊ የሚያደርጋቸው  እየሆነ መጥቷል። አገራችንም ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ዝውውር ስትገባ፣ ኢንተርኔት ደህና ሲሆን፣ ከእርሱ ጋር የተያያዙ ብዙ ስራዎች ይመጣሉ። በፋይናንሻል ቴክኖሎጂ (ፊንቴክ) ብዙ ወጣቶች በናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ኬንያ፣ ግብጽ፣ ድቡብ አፍሪካ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላርና፣ ከዚያም በላይ ኢንቨስትመንት የአገራቸው ያመጡ አሉ። እነዚህ ልጆች በሃያዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ናቸው። ቴሌ እንግዲህ አሁን በካፒታል ገበያ ውስጥ ሲገባ፣ ለወጣቶችም ትንሽ ክፍተት ይኖራል የሚል ግምት አለኝ። እነዚህ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ከባንክ ጋር ነው የሚሰሩት። እነርሱ በሚመርጡት ባንክ ሄደው ነው የውጭ ምንዛሪ የሚያስቀምጡት። አንዳንዴ የውጭ ምንዛሪም ሊፈልጉ ይችላሉ። አብዛኛው እነርሱም የሚፈልጉት የአገር ውስጥ ብር ነው። እናም፣ ከባንክ ጋር የሚወዳደሩበት ነገር የለም። የባንክን ስራ የሚያቀልሉ ናቸው።
 እንግዲህ የግል ምንዛሪ  ቢሮዎች የሚከፈቱት አንድም ስራ ለማሳለጥ ነው። ቅድም እንዳልኩት ሌሎች አገሮች የዲጂታል ግብይት ከተጀመረ በኋላ፣ እነርሱም አላስፈላጊ እየሆኑ መጥተዋል። ግን አገራችን ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ፣ ቱሪስቶች በሚመጡበት ጊዜ፣ በየቦታው  የባንክ ቅርንጫፍ ላያገኙ ይችላሉ። በአብዛኛው የባንክ ተደራሽነት (ፋይናንሻል ኢንተርሚዴሽን የሚባለው) አገራችን ውስጥ በጣም ትንሽ ነው። በተለይም የቱሪስት መዳረሻዎች  የምንላቸው አካባቢዎች፣  የባንክ ተደራሽነት ላይኖራቸው ይችላል። ስለዚህ እነርሱ ይመነዝሩላቸዋል። ሁለተኛ ባንኮች አንዳንዴ ገንዘብ ለማውጣት ሲኬድ።  “ሲስተም” የለም ይባላል። እነዚህ ግን  ሥራቸው ብር መመንዘር ስለሆነ፣ በቀላሉ ፈጣን አገልግሎት ይሰጣሉ። በተለይ ለቱሪዝም ዘርፉ አስፈላጊ ናቸው።   የዲጂታል ግብይታችን በጣም ሰፍቶ እስኪሻሻል ድረስ፣ ጥሩ ስራ ሊሰሩ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ።
በአፍሪካ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ተሞክሮዎች ምን ይመስላል?
- ሁሉም አገር አለው። አሁን ለምሳሌ:- ኬንያ አለ። ታንዛኒያ አለ። ዩጋንዳ አለ። ናይጄሪያ አለ። የሌለበት አገር የለም። እኛ እኮ የፋይናንስ ሴክተሩን ዘግተን ስለቆየን ነው ይህ ሁሉ ጭቅጭቅ የመጣው። በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የውጭ ባንኮችም ነበሩን- እነ ባንኮ ዲ ሮማ። ካፒታል ገበያም ነበረን። አብዛኞቹ ደርግ የወረሳቸው ኩባንያዎች በካፒታል ገበያ የተቋቋሙ ነበሩ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስካሁን ድረስ አክሲዮን ኩባንያ ነው። ...በዚያን ጊዜ ትልቁ አክሲዮን ገዢ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነበር። ያው የግል ሴክተሩ በጣም ጠንካራ ስላልሆነ፣ ትንንሽ ኩባንያዎች ኢምፖርት ኤክስፖርት፣ እርሻ ላይ የተሰማሩ… ካፒታል ገበያ እየገቡ ነበር ገንዘብ ፈሰስ የሚያደርጉት። እርግጥ እንደ አሁኑ በጣም ውስብስብ የሆነ ካፒታል ገበያ አይደለም። አሁን በኢንተርኔት ዘመን ካፒታል ገበያዎች በጣም ውስብስብ ሆነዋል። ካፒታል ገበያዎች በጣም ተስፋፍተው ብዙ ስራ እየሰሩ ነው። አሁን ኩባንያዎች አክስዮን መሸጥ ብቻ ሳይሆን የፋይናንስ ገበያዎችም ያካሂዳሉ- ገንዘብ ይገበያያሉ። ሰዎች አንዱን ገንዘብ ይገዙና ያስቀምጣሉ። ያ ገንዘብ ይጨምራል ወይም ይከስራል ሲባል ደግሞ እንደገና እርሱን እየሸጡ ይቀይራሉ። እነ ማሌዢያ፣ ኢንዶኔዢያ እንደዚህ ዓይነት ብዙ ጨዋታዎች ተጫውተዋል። በተለይ በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ አገሮች የቅኝ ግዛቱን የፋይናንስ ስርዓት እንዳለ ነው የቀጠሉት። ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች አፍሪካ ውስጥ በደንብ ይሰራሉ። በደንብ ገንዘብ ይመነዝራሉ።
የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ለነዚህ አገራት የኢኮኖሚ ዕንቅስቃሴ ምን ፋይዳ አላቸው?
ብዙ ጊዜ  ከእነርሱ ጋር የተያያዘ ችግር በሚመጣበት ጊዜ ቶሎ በይታወቃል-መንግስት አብሮ ካልተጨመረበት በስተቀር። አሁን በናይጄሪያ ለምሳሌ፣ በአንድ ወቅት 20 ቢሊዮን ዶላር ጠፋ፤ ከነዳጅ ያገኙት ክፍያ። ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ይህን የጠፋ ገንዘብ አስገኛለሁ። ብለው ነው ሁለቴ የተመረጡት። ነገር ግን እርሱንም ሳያገኙ፣ ኢኮኖሚውን አውድመውት ነው ለአዲስ ፕሬዝዳንት ያስረከቡት። እነዚህ ቢሮዎች ብዙ ወንጀል ሊሰሩ የሚችሉበት ሁኔታ አለ። ዋናው ነገር ምንድን ነው፤ በተለይ  አዳዲስ ባንኮች በሚገቡበት ጊዜ፣ ጠንካራ የገንዘብ አስተዳደር (ሞኒተሪ ፖሊሲ አድሚኒስትሬሽን) ስርዓት ያስፈልገናል። እነርሱን የሚቆጣጠር የአስተዳደር ድርጅት (ሬጉላቶሪ ኢንስቲትዩሽን) የግድ ነው። ስለዚህ ብሔራዊ ባንክና ሌሎች በቁጥጥርና አስተዳደር ስራ የሚሰማሩ የመንግስት ተቋማት፣ ከፍተኛ ክሕሎት ያላቸውና ይህን መቆጣጠር የሚችሉ መሆን አለባቸው። አሁን አንዳንድ ባንኮቻችን የብር መንሳፈፍ የሚባለው ታሪክ የገባቸው አይመስለኝም። አልለመዱትም።  ስንቶቹ የፋይናንስ ክሕሎት እንዳላቸው አላውቅም። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ አካውንቲንግ፣ ኢኮኖሚክስ የተማሩ ናቸው። ግን ከዚያ ሌላ በእንደዚህ ዓይነት ባንክ ውስጥ መስራት ያስፈልጋል፤ ይህንን ልምድ ለማግኘት። ምናልባት በውጭ ባንኮች የሰሩ ሰዎች እኝደዚህ ዓይነት ነገር ቶሎ ሊገባቸው ይችላል። አብዛኛዎቹ የብር ዋጋ እንዲህ ወደ ሰማይ የሚቆልሉት… በዌስተርን ዩኒየን የዲያስፖራ ገንዘብ ሲመጣ፣ ኮድ ነው የሚላከው። ስለዚህ አንዱ ባንክ 57 ብር ነው የምሰጠው፤ ሌላው ባንክ 105 እሰጣለሁ ካለ፣ 107 የሚሰጠው ጋ ነው የሚሄዱት። ለዚህ ነው የሚቆልሉት። እስከ አሁን ድረስ ዶላር ያገኙ አይመስለኝም፤ ዶላርም የሸጡ አይመስለኝም። እነዚህ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በየቀኑ የሚሰሩትን ነገር ለማወቅ፣ ገንዘብ ወደ ማጠብ እንዳይገቡና፣ በጥቁር ገበያ ውስጥ እንዳይሰማሩ… ጥብቅ የሆነ አሰራር ያስፈልጋል።
እነዚህን የግል ምንዛሪ ቢሮዎች ለማስተዳደር የሚያስችል የሕግና የአስተዳደር አቅም አለን ብለው ያስባሉ?
ብሔራዊ ባንክ እንደዚህ ዓይነት መመሪያ ያወጣው ይህ አቅም ‘አለን‘ ብሎ ነው። አሁን ይህን ፈቃድ ሲሰጥ የራሱን አቅም ግንባታ ማካሄድ ይኖርበታል። ደግሞ ያንን “አድርጓል” ብዬ ነው የማስበው። ከዚህ የባሰ አሁን የውጭ ባንኮች ይመጣሉ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ። እነርሱን ማስተዳደር መቻል ይኖርብናል። በዚያ ላይ ሰፋ ያለ ክህሎት ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ይህንን በማስተዳደር። ብሔራዊ ባንክ አካባቢ ከፍተኛ የአቅም ግንባታ ‘ያስፈልጋል’ ብዬ አምናለሁ።
እኔ 26 የአፍሪካ አገሮች ሰርቼአለሁ። “የጥቁር ገበያ” የሚባል ሰምቼ አላውቅም። የላቸውም። እኛ አገር ብቻ ነው ያለው። እሱንም መንግስት ነው ያመጣብን ዓለም የደረሰበት አልደርስም ብሎ  የሙጥኝ በማለቱ ነው  ለዚህ የዳረገን።  የመንግስት ሃላፊዎች ቁጥጥራቸውን አጥብቀው የሚሰሩ ከሆነ፣ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ምንም ነገር ሊያደርጉ አይችሉም። ካልሆነ ግን እነርሱም ወደ ጥቁር ገበያ ሊቀየሩ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ።

Read 631 times