ዐለም የምትሽከረከረው በዛቢያዋ ብቻ አይደለም፤ሥነ ልቡናዊ ስካር በሚያንገዳግዳቸው ግራ የተጋቡ ሰዎችም ጭምር ነው። ዐለም ላይ ጥፋት መጣ፤ጦርነት ተቀሰቀሰ በተባለ ቁጥር፣ደም የነካው ሰይፍ፣ባሩድ ያጠለሸው ምድር ባየን ጊዜ፣ ሰይጣን ላይ የምንፈርደው ፍርድ ሁሌ ትክክል አይደለም፤ ሌላ ያሸመቀ ሰው ሠራሽ ሰይጣንም አለ። የወደቀ ሰይጣንና ቅዱሳን መላዕክት እንዳለ ሁሉ፣ ሰባሪና መልካም መልክ ሠሪ ሥነ ልቡናዊ አናፂ አለ።
የሰው ልጅ የትናንት ማንነቱ ውጤት መሆኑን በተለያዩ መንገዶች በድርበቡ ብንረዳም፤ የዘርፉ ባለሞያዎ ጎልጉለው ሲያወጡት ግን የምንደነቅበት የሕይወት ፈርጅ የትየለሌ ነው። የትኛውም ትራሳችንን ካራጠበ እንባ ጀርባ፣ ሳቃችንን ከነጠቀ ሠቀቀን በስቲያ ጠዝጣዥ ቁስል አለ።
ከጋዜጣ ያነበብናቸው፣ከመጻሕፍት የቃረምናቸው፣ምናልባትም ለቅምሻ ያህል አንድና ሁለት ኮርስ ላይ ያገኘናቸው የሳይኮሎጂ ዕውቀት ጥሪቶች ቢኖሩም፤አሁን ግን በድንግዝግዝ ያየናቸውን ምስሎች ጥርት አድርገው፣ በተወለወለ መስታወት ፊት የሚያቆሙን የዘርፉ ጠቢባን ብቅ ብለዋል። Human Behaviour ላይ ስለ ናፖሊዮን ጀግንነት፣የቁመቱ አጭርነት ዕዳ እየተከፈለ እንደሆን፣የሚሎሶቪች የደም ፍቅር፣ የባሩድ ዜማ ናፍቆት፣ቤቱ ውስጥ የእናቱና የአባቱ መራራ ሕይወትና ራስን ማጥፋት ውጤት እንደሆነ ሰምተን ወይ አንብበን ይሆናል።
የዚህ ዐይነቱ ጭላንጭል “ጎረቤት ሲንኳኳ ይሰማል ያንተ ቤት” ዐይነት ዜማ ሊሆን ይችላል። አሁን ግን “ምን ሆኛለሁ?” በሚል ርዕስ ብዕረኛው ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ የጻፈው፣ታዋቂዋ የሥነልቦና ባለሞያዋ ትዕግሥት ዋልተንጉሥ፣ ዕውቀቷን በተግባራዊ ልምምድ ፈትፍታ ያቀረበችበት መጽሐፍ የእያንዳንዳችንን ቤት ማንኳኳት ጀምሯል።
ይህ የተጠረዘ እንግዳ ጉዳችንን ዘርዝሮ፣ታሪካችንን በርብሮ፣ትዝታችንን ከእነ ቀለሙ፣ሥራችንን ከእነ ምስሉ ያመጣና ያስደነግጠናል። ለካስ ..ያቀማጠልናቸው ብሶቶቻችን፣ዙፋን ሰጥተን ያነገሥናቸው ጠባያት እንደ ሽንኩርት ሲላጡ መልካቸው ሌላ፣ ቋንቋቸው የግሪንቢጥ ነው?...እስከ ዛሬ የኖርነው ኑሮ፣ የሳቅነው ሳቅ፣ የሮጥንበት መም፣ የሸሸነው እውነት፣ መጽሐፉን ገልጠን ስናነብብ ፣ እንግዳና ባለ ሌላ መልክ ነው።
መጽሐፉ በመጀመሪያው “የታመመ ቤተሰብ” የሚለው ክፍል፣ አስታማሚ ያለበት ሳይሆን አስተላላፊ ሕመም የሚያጋባበት ስለሆነ፣በሽታው በትንፋሽ ሳይሆን፣ በኑሮ ውስጥ በማየትና በመስማት የሚጋባ፣በሕክምና መሳሪያ የማይታይ ረቂቅ ነው። ታዲያ መድኀኒቱ ስለ ትናንት ከባለሞያዎች ጋር በማውራት ብቻ ቁልጭ ብሎ የሚወጣ ነው። መጽሐፉ ለሚያነሳቸው ጉዳዮች፣ለሚመዝዛቸው የቁስለት ክሮች ተጨባጭ ማሳያዎች ስላሉት ረቂቅ ሳይሆን የሚታይና የሚዳሰስ ነው።
ምዕራፍ አንድ ላይ የምናያት ለባሏ መልካም ሆና፣በምላሹ እርሱ የከፋባት ሴት፣ጨጓራዋን ታምማ የግል ሆስፒታል ለሕክምና ስትሄድ፣ዶክተሩ ስለ ጉዳቷና ኑሮዋ ሲጠይቃት፣የቤቷን ችግር ትነግረዋለች። ዶክተሩ በዚያው ቀዝቃዛ ልቧ ሳለች ድንገት እቅፍ አድርጎ ይስማታል። ያ ደስታ ለጊዜው ከባሏ የተሻለ ድንቅ ዐለም ያሳያት ቢመስላትም፤ብዙ አልዘለቀም። እርሱም ትንሽ ቆይቶ እንደ ባሏ ግድየለሽና ብዙም ትኩረት የማይሰጥ ሆነባት። ስለዚህ አዘነች። እናም “ለምንድነው ጥሩ እያደረግሁ እንኳ ወንዶች የማይወድዱኝ?...“ ወደሚል የቀድሞ እንጉርጉሮዋ ተመለሰች።
መጽሐፉ ግን ነገሩን ከምንጩ ይቆፍረዋል። ዐይኖቻችንን ገልጦ የረሳነውን አስታውሶ ያስደምመናል፤ከዚያም የምክክር አገልግሎት በመሥጠት ደጁ የፊጢኝ ወደታሠረው ወደ ትናንት በመውሰድ አስገራሚውን ቋጠሮ መፍቻ ውሉን ያስገኛል፡፡ መቼም መጽሐፉን ላነበበ ሰው፣ የኛ የሰዎች ነገር ጉድ ነው፤ጭራው ረዥም፣ጥልቀቱ ሩቅ ነው። አንዳንዴ ቤታችን ጉልላት ላይ ፊጥ ብሎ የአደባባይ መታወቂያችን ለሚሆነው ጠባይ, ኪነጥበባትም የራሳቸው ሚና አላቸው ይለናል - “ምን ሆኛለሁ?”።
ለቁስላችን ፈውስ ከመሆን ይልቅ ሚጥሚጣ እየነሰነሱ ፣”ልክ ነህ” እያሉ የእንባችንን ምንጭ ይበልጥ ይቆፍሩታል። እስቲ መጽሐፉ ስለዚህ መስክ የሚለውን እንይ፤
“ፊልም፣ሙዚቃ፣ልብወለድ ኅብረተሰብ የሚፈጥሩ እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ፍቅር ላይ ሲመጣ ግን እነርሱ የሚነግሩን እውነቱን እንዳንጋፈጠው የሚያደርጉን ይሆናል። እንደ ጌዴዎን አባባል (ጌዴዎን የሳይኮሎጂስቷ የምክር አገልግሎት ደንበኛ ሲሆን፤ ስሙ ተቀይሮ የቀረበ ነው) ብዙ ሀያላን እኮ ስለ ፍቅር ራሳቸውን አጥፍተዋል” ብለን እንድንመሰክር የሚያደርጉን ኪነ ጥበባት ናቸው።”
ቤታችን ያጋጠመን እጃችን ላይ ያለው ፍቅር ደግሞ ሌላ ነው። በፍቅር ስም ብዙ እንባ እንደሚፈስስ፣ብዙ ሥቃይ የሚቀበሉ ነፍሳት እንደሚቃትቱ፣መጽሐፉ ይነግረናል።
“በፍቅር ስም ዐለም ላይ፣ሀገራችን ውስጥ፣ቤታችን የሆነው ብዙ ነው።በፍቅር ስም ሰዎች ይገደላሉ። በፍቅር ስም ሰዎች ይወጋሉ።በፍቅር ስም ሰዎች በራሳቸው ላይ እርምጃ ይወስዳሉ።ይታመማሉ፤ይጎሳቆላ፤ሀብትና ንብረታቸውን ሳይቀር አሳልፈው ይሰጣሉ።ይህ ሁሉ በፍቅር ስም የሚሆን ነው።”
ለምሳሌ ሰዎች ሲጠቁ፣ “ስለሚወድደኝ ነው፤ቀንቶ ነው” እያሉ የሚያሽሞነሙኑት ነገር ስህተት ነው ይላል መጽሐፉ። “የሚደበድበኝኮ ስለሚቀና ነው።ደግ እኮ ነው ብታዪው። አቤት ሰጥቶ እንደማይጠግብ” እየተባለ የሚሸፈነው ነገር ጭምብሉ ሲገለጥ ሌላ ነው።
ደብዳቢው ግን የራሱ ቁስል አለበት። እዚሁ መጽሐፍ ላይ የተገለጠ ስሙ የተጠቀሰ ባለትዳር፣ የሚስቱን ረዥም ጸጉር ጨምድዶ ይደበድባታል። ግን ሚስቱን አይጠላም። ከሚስቱ ጋር ግጭታቸው ስለበዛ የልጅነት ሕይወቱን ሲያስታውስ፣ለካ እናቱም ጸጉራቸው ረዥም ነበር። ጸብ በተነሳ ጊዜ አባቱ ጸጉራቸውን ጨምድዶ ከደበደባቸው በኋላ ጸብ ይቆማል። ያ የልጅነት እምነት ውስጡ ተደብቆ ብቅ ሲል፣ እርሱም ያንኑ የታመመ ቤተሰብ ሕይወት ይደግማል።
ሌላው ገራሚው ነገር የሰው ልጅ አእምሮ የሕመማችንን ጠባሳ፣በአካልና በአእምሮ እስክንጠነክር መደበቁ ነው። ይሁን እንጂ ያንን የምንሸከምበት ጫንቃ ስናወጣ የሰወረውን ሁሉ ጎልጉሎ ተወጣው ማለቱ ነው። የጥላሁን ገሠሠን የህይወት ታሪክ ሸጋ አድርጎ የጻፈው ዘከርያ መሐመድ፣ ጥላሁን ገሠሠ በወላጆቹ የተተወበትን ልጅነት፣ እንዴት ሲሸሽ እንደኖረና ግድ ሆኖበትም ከተናገረ፣ ያኛውን ክዶ ሌላ ተረክ ከመፍጠሩ ጋር ስናስተያየው፣ ብዙ የቁስለት እውነቶች አጠገባችን ይታዩናል።
ለምሳሌ በኩርፊያ ያደጉ ልጆች፣ የእናቶቻቸውን ፈገግታ ለማግኘት የማያደርጉት ነገር፣ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። የሚኖሩት ያንን ኩርፊያ ለማትነን፣ከፊታቸው ላይ የምትወጣውን ፀሐይ ለመሞቅ ብቻ ይሆናል። ለራሳቸው የማያደርጉትን ለእናታቸው ያደርጋሉ። በዚህኛው ልምምድ ከአባት ይልቅ ለማኅበራዊነት ቅርቧ እርሷ በመሆኗ ብዙ ግንኙነት፣ ኩርፊያ፣ ፈገግታ የሚመጣው ከእርሷ ነው። ገጽ 47 ላይ ለዚህ ማሳያ የሚሆን አንድ ታሪክ አለ።
አንዲት ደንበኛዬ አለች። ከዩኒቨርስቲ ሁሉንም ትምህርት “A” አምጥታ በከፍተኛ ማዕረግ ነው የተመረቀችው። እንደተመረቀችም ሥራ ተቀጥራ ጥሩ ደሞዝ ታገኛለች። ነገር ግን በሕይወቷ ደስተኛ አይደለችም። የምረቃዋ ዕለት እናት፣አባት፣ወንድም፣እህት ሁሉ በደስታ ሲሠክሩ እርሷ ግን ደስተኛ አይደለችም።...የምታወራው ከእናቷ ጋር ብቻ ነው። ከሥራ ገብታ እናቷን በሥራ ማገዝ ነው ደስታዋ!
ይህ አሳዛኝ ሕይወት ነው። ይህ የሆነው እናቷ በልጅነቷ በኩርፊያ አሸማቅቀው የእርሳቸው ፈገግታ ረሀብተኛ እንድትሆን ስላደረጓት ነው። የፊታቸው ባሪያ ናት። ዘመኗን በሙሉ ለራሷ ደስታ ሳይሆን ለእናቷ ደስታ ትኖራለች። የእርሷ ደስታ ተነጥቋል፤ዘመኗ ተሠርቋል። ይህንን ግን እናቷም እርሷም አያውቁም። ይህ ልቃቂት የሚተረተረው ከሥነ ልቡና ባለሞያ ጋር በሚደረግ ውይይት ወቅት ነው። ለመታከምም መጀመሪያ ሕመምን ማወቅ ይቀድማል።
እኛ ጠባዬ የምንላቸው ብዙ ነገሮች ቁስሎቻችን ናቸው። የተገለጡ ችግሮቻችን እንደሳል ሲሆኑ፣ የተደበቁት ኒሞኒያ ናቸው፣ በሚል መጽሐፉ በተደጋጋሚ ያነጻጽርልናል።
“ከባዱ የልጅነት ጊዜ” በሚል ርዕስ ስለ ልጅነት በተጻፈው ክፍል፣ በዋናነት የተለያየ ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። እነዚህም፣
የሜዲሊያ ልጅ
ተሸካሚው ልጅ
የጠፋው ልጅ
የተቀባው ልጅ
አስታራቂው ልጅ
ሞግዚቱ ልጅ
ብርቅዬው ልጅ
የሜዳሊያው ልጅ፣ቤተሰቡን በአንድ ዘርፍ ስም የሚያስጠራና የሚያስከብር፣ እንደልቡ መሆን የሚጠበቅበት፣ በስማቸው የቤተሰባቸውን ስም ማስጠራት ነው፤ ካልተሳካ ግን የሚጠብቀው ኩርፊያና ትኩረት ማጣት ነው። ተሸካሚው ልጅ፣እንደ ጦስ ዶሮ የቤተሰቡን ችግር መሸከም፣ቁጣቸውን መቀበል፣መከራቸውን መካፈል ነው። ሁሉም የተዘረዘሩት የየራሳቸው ኀላፊነት፣ዕድል መከራ የተመደበላቸው ናቸው። ይህ ክፍል ጠቅለል አድርጎ ሲያስቀምጥ፤ ሕፃኑ ከሦስት ወራት በኋላ ስሜታዊው የአንጎል ክፍል ማደግ ይጀምራል ይላል። እንግዲህ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የስሜታዊና ማኅበራዊ ዕድገታችን መሠረት ይጣላል። በመጀመሪያዎቹ አምስት ዐመታት የሚኖረው የሕይወት ገጠመኝ፣ በልጁ የወደፊት ሕይወት ላይ ወሳኝነት አለው።
በዚህ ዕድሜው “አባቴ አይወድደኝም፤ምክንያቱም እኔ ተወዳጅ ስላልሆንኩኝ” የሚል ዐይነት ስሜት ስለሚሰማቸው፣ ጥንቃቄ የሚጠይቅ የዕድሜ አንጓ ነው የሚል መልዕክት አለው። መጽሐፉ የልጅነት ሕይወት ከምንም በላይ ለማንነታችን ወሳኝ መሠረት መሆኑን የተለያዩ ጥናቶችን በማሳያነት ተጠቅሞ ይነግረናል። ገጽ 82 ላይ “አብዛኛው ሰብዕናችን የሚቀረጸውና ማንነታችን የሚገነባው በቤተሰብ ውስጥ ነው። እነ አካባቢ፣ትምህርት ቤት፣ማኅበረሰብ የሚመጡት ከቤተሰብ ቀጥሎ ነው” ይልና የቤተሰብን ሚና ያሳየናል። በታመመ ቤተሰብ ውስጥ ያለውን ግንኙነት ሲያሳየን፤ “ታዛይ”፣ “አዛይ”፣ “ፈላጭ ቆራጭ” ብሎ ያስቀምጣል።
ሦስተኛውን እንደምሳሌ ብናይ፣ አንድ አባት ልጁን “ፕሮፌሰር መሆን አለብህ” ወይም “ሜዳሊያ ካላገኘህ”ብሎ ካስጨነቀው. ይህ ጤናማ ነገር አይደለም። አባትዬው ልጁ እንዲጎብዝ ሳይሆን፣የራሱን የልጅነት ክፍተት ለመሙላት፣ቁጭቱን ለመወጣት የሚያመጣው ጫና ነው። ዞሮ ዞሮ የቆየና ተደብቆ የኖረ ሕመም ነው። ይህ ሕመም ደግሞ ካልታከመ የቤተሰብ ይሆናል። ለምክክር ከመጡት ደንበኞች የአንዷን እንመልከት።
ይህቺ ደንበኛ ተምራ፣ሥራ ይዛ፣ትዳር መሥርታ የምትኖር ናት። ነገር ግን አንድ ችግር ነበረባት። ለምን እንደሆነ ባታውቀውም፣ቤቷ ሰዎች ሰብሰብ ሲሉ አትወድድም። የባሏ ዘመዶች ሲመጡ ይጨንቃታል። በአጠቃላይ ሰው አትፈልግም።
ታዲያ በሳይኮሎጂ ባለሞያዋ የምክክር አገልግሎት ወቅት ወደ ልጅነቷ መለስ ብለው ሲቃኙ ትዝታዋ ተዘረገፈ። እናቷ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በፍቅር የሚኖሩ ይመስል ነበር። እናቷ አጠገባቸው ሳሉ የሚወድዷቸው የሚመስሉት ጎረቤቶች፣እናቷ ዞር ሲሉ ሲያላግጡባቸውና ሲያሽሟጥጧቸው ትሰማ ነበር። ታዲያ አሁን አድጋ ትልቅ ሰው ሆና ቤቷ ሰዎች ሰብሰብ ሲሉ እንደ እናቷ የሚያላግጡባትና የሚያሽሟጥጡባት እየመሰላት ይጨንቃታል። ይህ የልጅነት ሕመም ነው።
መጽሐፉ ውስጥ እንደሚታየው፤ ለምክክር ከሚመጡት ሰዎች ውስጥ 90% ትልልቅ ሰዎች ሲሆኑ፣ የነዚህ ሰዎች 90% ችግር መነሻው ልጅነታቸው ነው። ልጅነት በብዙ ታላላቅ ሰዎች ሕይወት ስላለው ተጽዕኖ ካሰብን ታላቁ ጄነራል ናፖሊዮ ቦናፖርት፣ ሥዕል ሲስል የሚስለው ወታደሮችን መሆኑ፣በልጅነት ነውጠኛ ነቱ፣የዊንስተር ቸርችል አሻንጉሊቶች ወታደራዊ መሆናቸው ሁሉ ሊከሰትልን ይችላል።
ከዚህ በላይ ግን “ምን ሆኛለሁ?” የሚለው ትዕግስት ዋልተንጉሥና ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ በጥሩ ቅንጅት ያዘጋጁት መጽሐፍ፣ አጠገባችን ብቻ ሳይሆን፣በውስጣችን ያለውንና የማናውቀውን መልካችንን ያሳየናል። ለልጆቻችን ሕይወት ከመንጋደድ ቀድሞ የተሻለውን መንገድ ያሳየናል።
Tuesday, 20 August 2024 20:26
“ምን ሆኛለሁ?” የማናየው ሥውሩ ጠባሳ!
Written by ደረጀ በላይነህ
Published in
ጥበብ