በሁለቱም ጉንጮቻቸው እንባቸው ይወርዳል። ጣሪያው ላይ የተስፋ ችቦ ጨብጦ የሚያነድደው መልዐክ፤የተንጠለጠሉ የተስፋ አበባዎች፣የሉም። የሚታያቸው የገረረ በረሃ፣የነደደ ምድረበዳ ነው።ግን በጀርባቸው ተንጋልለው የሚያዩት ወደዚያ ነው።
በዚያ ላይ ግራና ቀኛቸው ተኝተው የሚያቃስቱ ሕመምተኞች ድምፅ ይበልጥ የነፍሳቸውን ዜማ እያመሳቀለው ነው።
ጉልበታቸው ከድቷቸዋል፤ ድሮ ጎረምሳ እያሉ አልጋውን ከነሰው መሸከም የሚችሉ ወጠምሻ ነበሩ። አሁን ግን አልጋቸው ሌትና ቀን ተሸክሟቸዋል።...ዘመን ንዶት ሁሉ ነገራቸው ተንጠፍጥፏል። የቀራቸው ጥቂት ተስፋ ነበር። እርሱም ሰሞኑን ዶክተሩ በተናገራቸው ቃል እንደ በጋ ደመና ሰማያቸውን አራቁቶታል። ድሮ ኀይል ነበራቸው፤
አሁን የቀራቸው እንባ ብቻ ነው። ዘመናቸውን ሁሉ ጠብ ያላለ እንባቸው አሁን ቀናቸው ሲንጠፈጠፍ ጉንጫቸው ማጠብ ጀምሯል።
“አንተ ኀይሌ” አሉ የተገረሙት ታናሽ እህታቸው።
መልስ አልሰጡም።
“ምን መሆንህ ነው?...በምድር ሕይወቴ ለእማዬ በስተቀር እንባዬ ፈስሶ አያውቅም አላልክም ነበር?”
እንባቸውን ጠራረጉ። የጉሉኮሷ ጠብታ ቀስ እያለች ወደ እርሳቸው ትንጠባጠባለች። የእርሳቸው እንባ ደግሞ ጉንጫቸው ላይ ብቻ ሳይሆን የልባቸውን ግድግዳ ታጥባለች። ደም በእንባ ይታጠብ ይመስል።
“አሁን ምን ይሁን ብለህ ነው የምታለቅሰው?”
ዝም።...ድሮም ብዙ አይናገሩም። ከተናደዱ ያናደዳቸውን ሰው በቴስታ ማፍረስ ነው። አሁን ግን እንባቸውን በአይበሉባቸው ያብሱና ሽቅብ ያንጋጥጣሉ።
“አታልቅስ፣ለራስህ አልቀሀል”
“እሺ”
“ምኑ ነው የሚያስለቅስህ?...ራስህን ጎዳህ እንጂ ለቤትህ ምን አጎደልክ?...በሽታ ላይ የጣለህ ልጆችህን ለማሳደግ ላይ ታች ያልክበት፣ለሀገርህ የሮጥክበት ነው።”
ሐኪሙ መጥቶ” አባቴ በሽታው መጨናነቅ አይወድድም፤ራስዎን ከጭንቀት ያውጡ”አላቸው። ራሳቸውን አንቀሳቅሰው መስማማታቸውን ገለፁ።
ግን ደስታቸው ጠፍቷል። እንዴት አድርገው ይችሉታል?...እኔ በልጅነቴ አባቴን በማጣቴ ያየሁትን አበሳ አልረሳውም አባት የሌለው ልጅ ቅጥር የሌለው እርሻ ነው፤ማንም ይፈነጭበታል፤ያለፈ ያገደመው ይረጋግጠዋል።” ሐሳባቸው ከአፋቸው አመለጣቸው።
“ልጆቼ ..እረኛ እንደሌለው መንጋ..”
አጎነበሱ እህታቸው።
“ይልቅ እባክህ ለራስህ አስብ”
“ተዪ በልጆቼ አትምጪብኝ፤ገና ብዙ ይቀራቸዋል።”
እህትዬው እንደመናደድ ቃጣቸውና ነገር ላለማክረር ዝም አሉ።
ውሎ ሲያድር፣ችግሩ እየባሰ፣ሕመሙ እየጠናባቸው መጣ። እንደ አባት ሳይሆን እንደ እናት፣ጡት የሚያጠቡትን ልጅ ጥለው የሚሄዱ ያህል አዘኑ። ስለዚህም እንደ መጸሐፍ ቅዱሱ ሕዝቅያስ ዕድሜ ጨምርልኝ ብለው አለቀሱ። ከእግዚአብሔርም ዘንድ ምህረትን ለመኑ።
“ልጆቼን ለወግ ማዕረግ ሳላበቃ፣ሳልድር ሳልኩል፣ሳላስመርቅ አትግደለኝ፤እንደ ንጉሥ ሕዝቅያስ በቸርነትህ ዕድሜ ቀጥልልኝ።” አሁን
አለቀሱ እህትየው። ወንድማቸው እንዲህ ለሞት የሚንቀጠቀጡ ፍርክርክ አልነበሩም። ጀግና ነበሩ። በስንት የጦር ግንባር፣ስንት ሺህ ጦር ሲመሩ አንድ ቀን ለሞት በርግገው አያውቁም። ዕድሜ ልካቸውን ጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸውም በዚህ እንደተደነቁ ነበር።
አሁን ግን ዘግይተው የወለዷቸው ልጆቻቸው ሞትን በጦር ሜዳ ደፍረው፣በመኝታ ላይ እንዲፈሩት ድፍረታቸውን ነጠቁት።
“የወለደ፣አልጠደቀ”አሉና በነጠላቸው ጫፍ እንባቸውን አበሱ።
“ለዛሬ ልጆች ይህን ያህል መጨነቅ!” አሉና ዝም አሉ።
አሁንም የወንድማቸው ምጥ ጨምሯል። ሐኪም
ሰውዬው እንዳይጨነቁ እያስጠነቀቁ ነው።
በዚህ መሐል አንድ ጓደኛቸው መጥተው ትክዝ ብለው አዩዋቸውና እንደ አዲስ ፣ “አይ ጀነራል፣ምድር የማይትችልህ ጀግና፣ወንዞችን የምታስደነግጥ ሰው፣አልጋ ችሎ ያዘህ?”
ከንፈራቸውን ነከሱ።
ምሥራቅ ቢሆን ምዕራብ፣ሰሜን ቢሆን ደቡብ ያልረገጠው ምድር፣ያላንቀጠቀጠው አልነበረም። ዛሬ አልጋ ላይ ወደቀ። ከበደ ሚካኤል ‘ጎበዝ ይሸነፋል፤ሐኪምም ይሞታል’ያሉት እውነት ነው።
እንደቆሙ ጠይቀዋቸው ሊወጡ ሲሉ፣ “ኮሎኔል”አሉ በደከመ ድምፅ “ልጆቼን አደራ!”
እህታቸው ጣልቃ ገብተው፣”አንተ ደሞ ለሁሉ አደራ አትበል!..”
“ጌታዬ ተጨንቆ እያስጨነቀን ነው። ልጆቹ ጨው አይደሉ፣አይሟሙ...ለሄደ ለመጣው ሁሉ ‘አደራ’ይላል። ያንተ ልጆች ከማን ልጆች ይለያሉ?”
ኮሎኔሉ መልስ አልሰጡም፤ትንሽ ቆም አሉና”እኔ ማንም አይደለሁም፤በጦር ሜዳ በእሳት መሀል ሞትን አንድ ላይ የተጋፈጥን፣ግማሽ ዳቦ ለሁለት የበላን፣በቀንና ሌት በአውሬ መካከል አብረን የተንከራተትን ነን። ኀይለ ልዑል ለእኔ ወንድሜ ነው። መወለድ ቋንቋ ነው። ስንት ደስታና መከራ አሳልፈናል። ስንት ክፉና ደግ አይተናል?”
እህትዬው ምን ለማለት እንደፈለጉ ለኮሎኔል ሲያስረዷቸው ጉንጫቸው ላይ ያለውን ጠባሳ አዩ። ወታደር ቤት ሆኖ ጠባሳ ፊት ላይ መኖሩ ብርቅ አይደለም። ብዙ ጊዜ እንደማኅተምና ማስታወሻ ምልክት ማኖሩ ግድ ይመስላል። ለሀገሩ አንዳንዱ እግሩን፣አንዳንዱ እጁን፤ሌላው ጆሮውንና ዐይኑን ይሰጣል።
ሆዳቸው እንደ መራራት ብሎ ኮሎኔሉን በዐይን ሸኙዋቸው። ሠሞኑን ደጋግመው መጥተው ጠይቀዋቸዋል። እየባሰባቸው ሄዶ እኒያ ጀግና አልጋ ላይ ታጠጥፈው መውደቃቸው እውን አልመስል ያላቸው ይመስል፣በመጡ ቁጥር ይገረማሉ። ሕይወትና ሞት በሰው ልጅ ውስጥ ተቃቅፈው ቢኖሩም፤ጀግና ግን ከአልጋ ይልቅ ጦርሜዳ ከነሙሉ ጉልበት መውደቅን ይመርጣል። ለዚያ ነው ተመትቶ፣ቆስሎ ሲገኝ”ጨርሰኝ”ብሎ የሚለምነው። ጀግና አልጋን ከሞት በላይ ይፈራዋል፤ይጠላዋል። ጀኔራል ግን ለልጆቻቸው ብለው ሞትን ታገሱ።
ቢሆንም ሰው እንደተመኘውና እንደተመቸው ብቻ አይኖርምና ሕመሙ ቀጥሎ፣ጸሎታቸው ተንጠልጥሎ ቆየ።
እርሳቸው “ትንሽ ዕድሜ”እያሉ ሲለምኑ፣እህትዬው ሲያስታምሙ ነጋ-መሸ።
አንድ ቀን በተመሳሳይ ስሜት፣በተመሳሳይ ሁኔታ ሳሉ፣ለጆሮም ለምናብም የራቀ ነገር ተሰማና ለታማሚው ጀነራል መናገር ምጥ ሆነ። እህታቸው ምድር ጠበባቸው።
እንባቸው ዱብ-ዱብ አለ።
ምን ብለው ይናገራሉ?
“ምንድነው?”
“ምንም”
“የሆነ ነገርማ አለ...የምታንሾካሹኩት ምንድነው?”
“ምንም የለም፤አርፈህ ተኛ አትጨነቅ”
ሳይታሰብ የሠፈራቸው ወፈፌ ጥልቅ አለች።
“ንገሪያቸው”
“እረፊ”
“ምን አርፋለሁ?...እርሳቸው ከዛሬ ነገ ‘ለልጆቼ በዳንኩ’ሲሉ ወንድም ወንድሙን መግደሉ አይገርምም?
“ማን ማንን ገደለ?”አሉ በድንገት ጥየቃ የመጡት ኮሎኔል።
የጀኔራሉ ልጅ የራሱን ወንድም”
“ምን ነው አለ?”
“በውርስ ተጣልተው ነዋ!”
“የምን ውርስ?”
“አባታቸው ሲሞቱ የሚካፈሉትን”
“በስመ አብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ!”
ምልልሷ ጆሯቸው ላይ ጥልቅ አለች።
“ኸ?” አሉና ጭጭ አሉ።
እህት ደረት መምታት ጀመሩ።”እናቸው እንኳን ይህን ጉድ አላየች!”
የሕይወት ቀለማት ቡራቡሬ!...አባት ለልጆች፤ልጆች ለሀብት!
Published in
ጥበብ