Friday, 23 August 2024 20:39

በማገዶ ጭስና ተቀጣጣይ ነገሮች የሚመጣ የሳንባ ካንሰር መስፋፋቱ ተጠቆመ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በማገዶ እንጨትና ተቀጣጣይ ነገሮች አማካይነት የሚመጣ የሳንባ ካንሰር መጨመሩን የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ባወጣው ጥናት  አመልክቷል፡፡ “የሳንባ ካንሰር የተጋላጭነት መጠን  በሴቶችና በወንዶች መካከል ተመጣጣኝ ነው" ብሏል - ጥናቱ፡፡

ብዙዎቹ የሳንባ ካንሰር ታማሚዎች ወደ ሕክምና ተቋማት የሚመጡት ዘግይተው መሆኑ ያመለከተው ጥናቱ፤ የሳንባ ካንሰር አራት ደረጃዎች እንዳሉትም ይጠቁማል፡፡ በመጀመሪያው  የሳንባ ካንሰር ደረጃ  ላይ የሚገኝ ታማሚ ወደ  ሕክምና ተቋም ከመጣ፣ የመዳን ዕድሉ ሰፊ መሆኑን የሚጠቅሰው ጥናቱ፤ በሦስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ከመጣ ግን የመፈወስ ዕድሉ ጠባብ ነው ይላል።

በአገራችን ከ90 በመቶ በላይ የሳንባ ካንሰር ታማሚዎች ወደ ሕክምና ቦታ የሚመጡት የመጨረሻዎቹ ሁለት ደረጃዎች ላይ ከደረሱ በኋላ መሆኑን የገለጸ ጥናቱ፤ በኢትዮጵያ የሳንባ ካንሰር ሕሙማን አማካይ ዕድሜ፣ ከሌሎች አገራት አማካይ የሳንባ ካንሰር ታማሚዎች አንጻር ወጣት መሆናቸው ተጠቁሟል። በዚህም 55 ወይም 56 ዓመት ዕድሜያቸው ላይ ታማሚ እንደሚሆኑ ነው ጥናቱ ያረጋገጠው፡፡

ጥናቱ በማገዶ እንጨቶች፣ በከሰል፣ በኩበት ጭስና ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮች የሚመጣው የሳንባ ካንሰር አይነት እየጨመረ መምጣቱን አመልክቷል፡፡ ይሁንና የትኛው የማገዶ ዓይነት የሚለው ተጨማሪ ጥናት ይፈልጋል ተብሏል።

“የሳንባ ካንሰር በሲጋራ ጭስ አማካኝነት የሚመጣ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ሲጋራ የሚያጨሱ ሴቶች ቁጥር ከ1 በመቶ በታች ሆኖ እያለ ለሳንባ ካንሰር ያላቸው ተጋላጭነት ግን ከወንዶች እኩል ነው" ሲል የኢትዮጵያ ቶራሲክ ማሕበር በጥናቱ አመልክቷል።

Read 129 times