ሰሞኑን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ለመንግስት መ/ቤቶች የፃፉት ደብዳቤ፤ ህገ-መንግስታዊ መብቶችን የሚጥስ ነው ሲሉ በትግራይ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነቅፈዋል። ደብዳቤው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፈቀደው ውጭ ሰልፍና ስብሰባ ማካሄድ እንደማይፈቅድ ይገልፃል።
ከአዲስ አድማስ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባል አቶ ኪሩቤል ገብረእግዚአብሔር በሰጡት አስተያየት፤ አቶ ጌታቸው ረዳ “ለክልሉ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የጻፉት ደብዳቤ፤ የመንግስት ሰራተኛን የሚመለከትና ስምንት ሰዓት የመስራት ግዴታ እንዳለበት የሚያስረዳ እንዲሁም የሕግ ጉዳዮችን የጠቃቀሰ ነው”፤ ሲሉ አስረድተዋል። አንድ ፓርቲ የመንግስት አዳራሽን በልዩ ሁኔታ መጠቀም እንደማይኖርበትም ይኸው ደብዳቤ እንደሚያብራራ ነው የተናገሩት።
የአቶ ጌታቸው ደብዳቤው የመንቀሳቀስ፣ የመሰብሰብና ሃሳብን የመግለጽ መብቶች ላይ ጉዳት ማድረሱ እንደማይቀርና በሕግ ሰበብ የሚፈጠር ችግር ሊኖር እንደሚችል አቶ ኪሩቤል ገልጸዋል። “በደፈናው ስብሰባ እና ሰልፍ ‘አይቻልም’ ማለት አግባብነት የለውም። ፈቃድ የሚጠየቀው ሰላማዊ ሰልፉ ላይ የጸጥታ እንከን እንዳይፈጠር ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ነው” ብለዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት ላይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሕዝቡ እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተውጣጥቶ እንደሚቋቋም ቢገለጽም፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ምስረታ ላይ ፓርቲያቸው አለመሳተፉን አቶ ኪሩቤል አስታውሰዋል። የጊዜያዊ አስተዳደሩን ምስረታ “የአንድ ፈረስ ግልቢያ ይመስላል” ሲሉ የነቀፉት አመራሩ፣ “ባንክ እና ታንክ የሌላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጸጥታ አካሉ ገለልተኛ እስከሆነ ድረስ መንግስት ለማቋቋም አቅም አያንሳቸውም፤ በዚህ ስጋት ምክንያት ነው ፓርቲዎቹን የሚደፈጥጧቸው።” ብለዋል።
“አሁን በፈጠሩት ሽኩቻ እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እና ህወሓት አንድ ናቸው። ህወሓት ብቻውን መንግስት ሊሆን አይገባውም። ሕዝቡን ከሚወክሉ ተቋማት ተውጣጥቶ ነው መንግስት መቋቋም ያለበት።” ብለዋል-አቶ ኪሩቤል።
በትግራይ ክልል የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በህወሓት ውስጥ ከተፈጠረው ክፍፍል ጋር በተያያዘ ሁሉንም የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ ክልላዊ መንግሥት እንዲመሰረት ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን ፓርቲዎቹ ጥሪውን ያቀረቡት፣ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ዋነኛ አደጋ “ሥርዓት የወለደው ስንፍና ነው” በማለት ነው። “አንድ የፖለቲካ ድርጅት ሲታመም የማይታመም መንግሥት ያስፈልገናል። ይህም የሚሆነው ሁሉንም ድርጅቶች ያካተተ እና ሕዝብን ማሰለፍ የሚችል መንግሥት ሲቋቋም ነው” ብለዋል፤ ተቃዋሚዎቹ።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፈቀደው ውጪ ሌላ ስብሰባ ማካሄድ እንደማይቻል የሚያትተው የፕሬዚዳንቱ ደብዳቤ፣ “የኮሌራ በሽታ መከላከል፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለስና የክልሉን ግዛታዊ አንድነት ማስከበር፤ እንዲሁም በጀት መዝጋትና በጀት ማዘጋጀት የመሳሰሉ ሌሎች ሕዝባዊና መንግስታዊ ዕቅዶች” የጊዜያዊ አስተዳደሩ መሆናቸውን ይገልጻል። “ከዚህ ውጭ የሚደረጉ ሰብሰባዎች የተያዘውን ዕቅድ ስለሚጎዱ አይፈቀዱም” ይላል-ደብዳቤው።
Saturday, 24 August 2024 19:10
በአቶ ጌታቸው ረዳ የተጻፈው ደብዳቤ ሕገ መንግስታዊ መብቶችን ይጥሳል ተባለ
Written by Administrator
Published in
ዜና