(የኢዜማ የቀድሞ ዋና ጸሐፊ)
ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣
የቀድሞ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉ
ከሃላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው ይታወሳል።
የለቀቁበትን ምክንያት ለፓርቲው ባስገቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ ላይ ሲገልጹ፣
ከፓርቲው አቋምና አካሄድ ጋር “ባለመስማማታቸው” መሆኑን ጠቅሰዋል።
አቶ አበበ ከአዲስ
አድማስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከኢዜማ የለቀቁበትን ምክንያትና
ስለፓርቲያቸው በዝርዝር ያብራራሉ፤
ቀጣይ የፖለቲካ መዳረሻቸውንም
ያመላክታሉ እነሆ፡-
ከኢዜማ ለመልቀቅ ያስገደድዎ ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
እንግዲህ ላለፉት አምስት ዓመት ከሶስት ወራት አካባቢ የኢዜማ ዋና ጸሃፊ በመሆን፣ ፓርቲውን ሳገለግል ነበር። መጀመሪያ የነበረውን የፓርቲውን ቁመና ስናይ፣ በጣም ጠንካራ የሆነ መዋቅር በመላ አገሪቱ ያለው፤ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከፍተኛ የሆነ መገዳደርን ያሳየ፣ ብዙ ዕጩዎችን በማቅረብ ከገዢው ፓርቲ ሁለተኛ ሆኖ ቀጥሎ የነበረ ፓርቲ ነው። በዚያ ውስጥ መዋቅራችንን ዘርግተን በደንብ በጥንካሬ ነው የተንቀሳቀስነው። ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ግን ፓርቲው ቀስ እያለ ለሕዝብ ያለውን ወገንተኝነት ወይም የሕዝብ ድምጽ የመሆን አቅሙ እየቀነሰ መጣ። መዋቅሩም ከምርጫ ማግስት ጀምሮ ፓርቲው በሚይዛቸው የተለያዩ አቋሞች ምክንያት ከፓርቲው እየተነጠለ ሲመጣ፣ እጃችን ላይ ቀስ እያለ እየሟሟ መምጣት ጀመረ። አንድ የሚገዳደር ፓርቲ መሆን አልቻለም። የመለሳለስ ባሕርይው ተከታዮችንም፣ አባላትንም እያሳጣው መጣ። ይህን ጉዳይ በብዙ መልኩ ብንሞክርም፣ ማስታረቅ አልተቻለም። ከመንግስት ጋርም አብሮ በመስራት ሂደት ውስጥ “ምንድን ነው ፓርቲው ያገኘው? አገር ምን ተጠቀመች? ፓርቲውስ ምን ተጠቀመ?” የሚለው መገምገም ነበረበት። መጀመሪያ እኛ ማድረግ የነበረብን ፓርቲውን ማቆም ነው። ፓርቲው ቆሞ፣ እንደ አገር ተገዳዳሪ፣ ተፎካካሪ ሆኖ በደንብ መውጣት የሚችል ፓርቲ መሆን አለበት። በአንድ በኩል ገዢው ፓርቲ ብቻ በየአምስት ዓመቱ እየተመረጠ አይደለም የሚገዛው። ሕዝቡ ሲከፋው፣ ‘’ይኼኛውን ፓርቲ ስልጣን ላይ አውጥተን እንሞክረው” የሚል መሆን አለበት። ይህን መሆን አልቻለም። ከዚህ ይልቅ እያደር እንደበረዶ እጃችን ላይ መሟሟት ሲጀምር፣ ጉዳዩን ቆም ብለን ማጥናት አልቻልንም። ከዚህ መታደግ ስላልተቻለ፣ በዚህ ዓይነት መቀጠሉ የትም እንደማያደርስ ሳይ፣ በቃ -- እዚያ ውስጥ ጊዜዬን ማባከን አስቸጋሪ ስለሚሆን፣ ፓርቲውን ትቼ ወጥቼያለሁ።
ቅድም የጠቃቀሷቸው ነገሮች አሉ። ፓርቲው በጊዜ ሂደት የሕዝብ ድምጽ የመሆን አቅሙ እየቀነሰ “መጥቷል” ብለዋል። ይህን አቅሙን በትክክል መቼ ላይ ነው እያጣ የመጣው?
ከምርጫው ማግስት በኋላ፣ ከመንግስት ጋር አብሮ የመስራት ስምምነት ከተደረገ በኋላ፣ ቀስ እያለ ይህን አቅሙን እያጣ መጣ። ከመንግስት ጋር መስራት ሌላ፣ የሕዝብ ድምጽ መሆን ሌላ። ይህን ብለን ነው አብሮ መስራት የሚለውን ያኔ የተቀበልነው። “አብሮ መስራት” የሚለው ቋንቋ በደንብ መገምገም አለበት። ቅድም እንዳልኩህ ምንድን ነው ለፓርቲው የጠቀመው? አንደኛ ፓርቲው ማደግ መቻል አለበት። አስራ አራት ሚሊዮን አባል “አለኝ” ከሚል ፓርቲ ጋር ነው የምንገዳደረው። አስራ አራት ሚሊዮን ማለት አንድ ሶስተኛ ወይም አንድ አራተኛ መራጭ ሕዝብ ማለት ነው። ስለዚህ ከዚህ ጋር የሚገዳደር ፓርቲ የራሱን መዋቅር እየዘረጋ፣ 547 መቀመጫዎችን ጭምር ሸፍኖ፣ ስራ መስራት ሲገባው፣ በዚህ ደረጃ እጁ ላይ ያለውን መዋቅር ጭምር እስከ ማጣት ድረስ ቁልቁል መውረድ “ምንድን ነው ተስፋው?” የሚለው ነገር በጣም ነው ጥያቄ የሚፈጥርብኝ። ታግለህ ለውጥ የማታመጣ ከሆነ፣ ታግለህ ልዩነት ፈጥረህ ለሕዝብ ድምጽ መሆን የማትችል ከሆነ፣ ነገ ወደ ስልጣን የመምጫው መንገድ በየቀኑ እየጠበበ የሚመጣ ከሆነ፣ ምንድን ነው ትርጉሙ …ተቃዋሚ ብቻ መሆኑ? ይሄ ደግሞ ሞልቷል በጣም! በዚህ መልኩ የሚቃወሙ ፓርቲዎች ናቸው ያሉት። አማራጭ ይዘን የምንቀርብ አለመሆናችን በጣም ነው የሚያሳዝነው።
ወደ እርስዎ ስንመጣ፣ ኢዜማ በሚከተለው የፖለቲካ አካሄድ መቼ ነው አመኔታዎን የቀነሱት? በምን ምክንያት?
ይህን ነገር ማሰብ ከጀመርኩ ወደ አንድ ዓመት ገደማ ይሆነኛል። ከአምና ጀምሮ ጥሩ አመለካከት አልነበረኝም። ይሄ ነገር በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ፣ የእኔ ከዚህ ፓርቲ ጋር መቀጠሌ “እስከ ምን ድረስ ነው?” የሚል ጥያቄ በውስጤ አነሳለሁ፤ ብዙ ጊዜ። ብዙ የምቀርባቸው ሰዎች ትንሽ እንድቆይ ይገፋፉኝ ነበር። ነገር ግን በየጊዜው የማያቸው ነገሮች -- አንደኛ ፓርቲው ቀድሞ ከነበረው ወደ 4 መቶ የምርጫ ክልሎች አካባቢ መዋቅር ዘርግተን እንንቀሳቀስ ነበር። ዛሬ ግን ያ የለም። ጭራሽ ቁልቁል ነው የሄደው። የቀሩትን አይደለም ለመድረስ፣ ያሉትንም ከእጃችን እያጣን ነው። የሸፈንናቸው አካባቢዎችን ጭምር … በጣም ነው የሚያሳዝነው … በየጊዜው አባላት እየቀነሱ እና እየጫጩ ነው የመጡት። መዋቅሩ ችግር ውስጥ ሲገባ እየተመለከትኩ ነው። ይህንን ቆም ብለን ገምግመን፣ “ምንድን ነው ችግሩ?” ብለን፣ ችግሩን ለይተን መስራት ነበረብን። ይህን ማሰራት የሚችል ነገር የለም። “ከመንግስት ጋር አብሮ መስራት” የሚለውን ነገር መገምገም አለብን። “በመስራት የተገኘው ጥቅም ምንድን ነው?” ማየት መቻል አለብን። የጎዳን ነገር ካለ፣ ቆም ብለን ማሰብ ያስፈልገናል። “እንዴት ነው ከመንግስት ጋር እየሰራን ያለነው? በምን ያህል ፍጥነት እየሄደ ነው? ስንት ቦታ ነው የምንሰራንው? ምን ያህል ሰው ነው ሃላፊነት ላይ ያለው? ስንት ክልሎች ላይ ነው የምንሰራው?” -- ይህን በደንብ ተገምግሞ ቆም ብለን በዚህ ሶስት ዓመት ውስጥ ማሰብ ነበረብን። ይሄን ማድረግ አልቻልንም። እንዴት አንድ ፓርቲ በየዓመቱ ያለውን ውድቀት እና ከፍታ አይፈትሽም? መቼም ኢዜማ በሰነድ አይታማም። የያዘው አቋም፣ ያለው ፕሮግራም በጣም አመርቂ ነው። ማኒፌስቶዎቹ በጣም አጓጊ ናቸው። የዜግነት ፖለቲካን በመስበክ እንደኢዜማ ዓይነት ፓርቲ የለም። በጣም ጥሩ ነገር ነው ያለው። ነገር ግን ተግባራዊ የማይደረግ ከሆነ፣ ማኒፌስቶውን እና ፕሮግራሙን ብቻ እያደነቅን መኖር አያስኬድም። መተግበር አለበት። ሁለተኛ በአንድ ወቅት የነበረህን ድጋፍ እያጣህ ትመጣለህ። የአንድ ፓርቲ ትልቁ ሃላፊነት ለምርጫ ከመወዳደር ባሻገር፣ ገዢው ፓርቲ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ዕለት በዕለት፣ እግር በእግር ተከትለህ እየነቀስክ ማጋለጥ ነው፤ ትልቁ ነገር። ኢትዮጵያ በብዙ ችግሮች የተወሳሰበች አገር ነች። ችግሮቿ ፖለቲካዊ ናቸው። የመንግስትን አካሄድ እየነቀስክ አውጥተህ መንቀፍና እንዲያስተካክል መታገል አስፈላጊ ነው የሚሆነው። ዝም. . .ዝም የምትል ከሆነ፣ ምንድን ነው ትርጉሙ? ሕዝቡ. . .በየጊዜው እየጠላን. . .እየራቀን. . .ድጋፉን የሚሰጠን እያጣን ሲመጣ፣ የራሱ አባላት እና አመራሮች ለቅቀው ሲሄዱ፣ ምንድን ነው ትርጉሙ? ይሄን ማስተካከል አልተቻለም።
እንግዲህ እርስዎ በፓርቲ አመራር ላይ እያሉ፣ ሌሎች ቀድመው ፓርቲውን ለቀዋል። የእርስዎና የእነሱ የመልቀቅ ሰበብ ይለያያል?
የሁለታችን አለቃቀቅ ይለያያል እኮ! እነርሱ የለቀቁት ፓርቲው የመጀመሪያውን ጉባዔ አድርጎ፣ ሁለተኛ ዙር ምርጫ ሲያደርግ ነው። ምርጫው ላይ ተወዳድረዋል። መሪም፣ ሊቀ መንበርም ለመሆን። በዚያ ሂደት ውስጥ አልፈውበት ሄደዋል። ከዚያም በኋላ፣ ለወራት ያህል ከፓርቲው ጋር ቆይተዋል። እኔ ግን በዚያ ሰዓት ላይ በምርጫው ተሳትፌ፣ የያዝኩትን ቦታ እንደያዝኩ በከፍተኛ ድምጽ ተመርጬ አልፌ ነው የመጣሁት። የእነርሱ አለቃቀቅ እና የእኔ አለቃቀቅ አይገናኝም። “ለምን አንድ ላይ አልሆነም?” ለሚለው፣ ምንም የሚያገናኘን ነገር የለም። ስለዚህ ያንን ማነጻጸር አይቻልም። በመሰረቱ፣ እኔ ሰውን ተከትዬ አልወጣም። በራሴ ጊዜ ነው። “ዘግይተሃል” የሚለውን አልቀበልም። “ከአሁን አሁን ይሻሻላል” የሚል ዕምነት ነበረኝ። በተለይ፣ ሁለተኛው ዙር ምርጫ ከተደረገ በኋላ፣ የነበረው መገፋፋት ይቆምና ፓርቲው በደንብ ተጠናክሮ ይወጣል የሚል የጸና አቋም ነበረኝ። ይህንን ደግሞ መጠበቅ ግድ ነው የሚለው። እርሱን ጠብቄያለሁ። እኔ ያሰብኩት ሃሳብ ባለመሳካቱ፣ “ዘግይቼያለሁ” ብዬም አልቆጭም። የወጣሁበት ተገቢ ሰዓት ነው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ የእኔ አወጣጥ ከእነርሱ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። አሁንም ማንም “ውጣ” ብሎ ያስገደደኝ የለም። በዚህ ዓይነት መቀጠል እንደማልችል ሳውቅ፣ በፈቃዴ ነው ሃላፊነቴን የለቀቅኩት።
አንዳንድ ወገኖች “ኢዜማ የገዢው ፓርቲ ተላላኪ እንጂ ራሱን የቻለ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ፓርቲ አይደለም” የሚል ፍረጃ ያቀርባሉ። እንደ አንድ የቀድሞ አመራር ይሄን ፍረጃ እንዴት ይመለከቱታል?
በዚህ ደረጃ ፓርቲውን ማውረድ ጥሩ አይደለም። ብዙዎች ‘ተለጣፊ’ የሚል ስያሜ ይሰጣሉ። ከዚህ አንጻር ይህን ያስባለን አብሮ መስራት የሚለውን በግልጽ ለይተን መጠቀም ስላልቻልን ነው። የቱ ጋ ነው አብረን የምንሰራው? አገርን ከማልማት እና ሰላምን ከመጠበቅ አንጻር? የቱ ጋ ነው የምንቃወመው? የሚለውን ለይተን ባለመንቀሳቀሳችን የተፈጠረ ነው፤ ይህ ስያሜ። አንዳንዴ ሕዝቡ እንደዚህ ቢለን አትፈርድበትም። ስለዚህ ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው የሚሆነው።
ያኔ ከመንግስት ጋር አብሮ የመስራት ጉዳይ እንደአጀንዳ ሲቀርብ፣ እርስዎ እንደደገፉት ይነገራል። በዚህ ጉዳይ ላይ የድጋፍ ድምጽ በመስጠትዎ የመጸጸት ስሜት ይሰማዎታል?
ምንም አልጸጸትም። እኔ ብቻ አይደለሁም። ለቅቀው የወጡት፣ እነ አንዱዓለምም -- እነ የሺዋስም -- በስራ አስፈጻሚም፣ በጉባዔው ላይም ደግፈነዋል እኮ፤ “አብሮ መስራት” የሚለውን ሃሳብ። ይህ ምንም ሊዋሽ አይገባውም። አብሮ መስራት ማለት እኮ ለዘላለም መጣበቅ አይደለም። ቆም ብሎ አስቦ የማያሰራ ጉዳይ ካለ፣ ገምግሞ ለቅቆ መውጣት ይቻላል። በወቅቱ ያንን ውሳኔ መወሰናችን ስሕተት አልነበረም። ስሕተቱ እኛ ጋ ነው። እኛ ያንን ገምግመን “ምን ላይ ደርሷል?” ብለን፣ የምንወጣ ከሆነ ገምግመንና ጉዳቱ ካመዘነ በጉባዔ አስወስነን ለቅቆ መውጣት ይቻላል፤ “አብሮ መስራት አያስኬደንም” ብለን። የእኔ ጥያቄ “ለምን መገምገም ተሳነን?” የሚል እንጂ የተወሰነውን ውሳኔ ሁላችንም ተስማምተን የወሰንነው ነው። በዚህ ቅር አይሰኝም። ያኔም ትክክል ነበርኩ፤ አሁንም ትክክል ነኝ። የተቃውሞ ሃሳባችን ለመግለጽ አያግደንም። ምክንያቱም በርካታ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር አብረው እየሰሩ፣ የሕዝብ ድምጽ ሲሆኑ እንሰማቸዋለን።
መጀመሪያ አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትሕ (አንድነት)፣ በኋላም ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ነበሩ። አንድነት ሲፈርስ፣ እርስዎና ጓዶችዎ ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ገብታችሁ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያለው የእርስዎን የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ “ንግግራቸውና ተግባራቸው አይገጥምም የሚሉ ወገኖች አሉ። የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው? ራስዎን እንደ አንድ ፖለቲከኛ እንዴት ይገልጡታል?
እኔ የኢዜማ መዋቅሮችን ድምጽ የምሰማ፣ አባላቱ እና አመራሮቹ በሚገባ የሚወዱኝ፣ ድምጽ መሆን የሚገባኝ ቦታ ላይ ለእነርሱ ድምጽ የምሆን፣ በግሌ ማድረግ የሚገባኝን ነገር ሃላፊነትን ሳላይ የማገለግል፣ አንዳንዴም አስቸጋሪ ነገር ሲመጣ፣ በዚህ ዕድሜዬ ቢሮ አድሬ የማገለግል ነበርኩ። ለነፍሴ ሳልሳሳ በስድስተኛው ዙር አገራዊ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከአዲስ አበባ እስከ አርሲ -- ሲሬ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ይርጋጨፌ ድረስ፣ ትልቅ ስራ ስሰራ የቆየሁ ሰው ነኝ። ከዚህ ባሻገር የፖለቲካ ነገር ሆኖ፣ ምናልባት ቃል ገብተንላቸው ያልተሳካ ነገር ካለ፣ እኔ ብቻ ሳልሆን በጋራ ነው የምንጠየቀው። በግሌ የማደርገው ነገር ስለሌለ ማለት ነው። የጋራ አመራር ነው ያለው። አንድነት ፓርቲ ውስጥ በቆየሁበት አጭር ጊዜ በጣም በርካታ ስራዎችን ሰርቼ፣ ፓርቲው ሲፈርስ ዕንባ አውጥቼ አልቅሼ፤ በወቅቱ የታሰሩ የትግል ጓዶች ስለነበሩ፣ እነርሱን ጥለን ቤት አንቀመጥም ብለን ነው ሰማያዊን የተቀላቀልነው። የነበረው አማራጭ ሰማያዊ ፓርቲ ብቻ ነው። እዚያም የራሴን የትግል አስተዋጽዖ አድርጌያለሁ። መክፈል የሚገባኝን … ትብዛም፣ ትነስም …መስዋዕትነት ከፍያለሁ። ከዚህ አንጻር እኔ ቃል ገብቼ ያልተሰሩ ስራዎች ካሉ፣ እንዲህ ነው ተብሎ ቢነገረኝ፣ ደስ ይለኛል፤ በደፈናው ከሚሆን።
አሁን ላይ -- ከኢዜማ ለቅቆ እንደወጣ አንድ ፖለቲከኛ … ፓርቲውን በሩቁ ሲመለከቱት፣ ምንድን ነው የሚሰማዎ? ለራስዎ ስለፓርቲው ምን ይነግሩታል?
ገና አስረኛ ቀኔ ነው ትቼ ከወጣሁ። እየሰራኋቸው ያሉ ስራዎች አሉ። በደንብ አድርጌ የማነብባቸው ነገሮች አሉ። የምፈትሻቸው ነገሮች አሉ። በቅርብ ጊዜ ውስጥ አንድ የራሴን አስተያየት ስለኢዜማ እሰጣለሁ። ፓርቲው ተጠናክሮ ቢወጣ ደስ ይለኛል። ምንም ጥርጥር የለውም። የሚቀጥለው ትውልድ ተክቶት ቢሰራ፣ ጥሩ ፕሮግራም አለው፤ ጥሩ ማኒፌስቶ አለው። ራስን አጠንክሮ፣ ድክመትን ፈትሾ መውጣት ነው።
ቅድም ያነሷቸው የፓርቲው ሳንካዎች አሉ። እነዚያን ፓርቲው አርማለሁ ቢል፣ እርስዎ ወደ ኢዜማ ይመለሳሉ?
እኔ ከዚህ በኋላ፣ ወደ ኢዜማ አልመለስም። ጓዜን ጠቅልዬ ነው የወጣሁት። ከአባልነትም፣ ከአመራርነትም ነው ራሴን ያገለልኩት። ነገር ግን እኔ ካልበላሁ፣ ጭሬ ላጥፋው አልልም። የሚቀጥለው ትውልድ እኔ የምነግርህን ድክመቶች. . .አሁን አልተናገርኋቸውም፣ ወደፊት የምናገራቸውን አርሞ የሚወጣ ከሆነ፣ በጥንካሬው በጣም ደስ ይለኛል። ቅር አይለኝም። ትልቅ አማራጭ ፓርቲ አድርጎ ማውጣት ተገቢ ነው። “ለምን እኔ አልኖርኩበትም?” ብዬ አልቆጭም።
ከዚህ በፊት የጠቀሱልኝን ድክመቶች በሚመለከት፣ እርስዎ ያደረጓቸው የውስጠ ፓርቲ ትግሎች ነበሩ?
የጎንዮሽ ፍትጊያውን ሳልፋተግ፣ ዝም ብዬ አልወጣም። ስላልቻልኩ ወጥቼአለሁ። ሃይሌን መጨረስ የለብኝም ብዬ ነው የወጣሁት። ወደፊት እርሱን እገልጸዋለሁ።
በእርስዎ የቀድሞ የትግል አጋሮች “የንጋት ኮከብ” የተሰኘ አዲስ ፓርቲ እየተቋቋመ ነው። ስለዚህ ፓርቲ መረጃ ነበረዎ? ወይስ እንደማንኛውም ሰው ነው የሰሙት?
እኔ እንደማንም ሰው ነው የሰማሁት። የእኔ ጉዳይ ከእነርሱ ጋር የሚነካካ አይደለም። አማራጭ ፓርቲ መመስረት ካስፈለገ፣ መመስረት ነው። እኔ ግን በግል ዕይታዬ ተፈልፍሎ ያለ ፓርቲ ብዙ ነው። አዲስ ፓርቲ አቋቁሞ እንደገና ከዜሮ መጀመር ከባድ ነው። ያሉትም በዝተዋል። እንመሰርታለን ካሉ ደግሞ መብታቸው ነው። እኔ ምንም መረጃው የለኝም። በቀለ ይኑርበት ከበደ፣ አንዱዓለም ይኑርበት የሺዋስ ምንም የማውቀው ነገር የለም።
ለመቀላቀል ሃሳብ የለዎትም?
አዲስ ፓርቲ በተመሰረተ ቁጥር እያንኳኳሁ አልሄድም። እንዲህ ዓይነት ሱሰኛም አይደለሁም።
ስለዚህ አቶ አበበን በምን እንጠብቃቸው? ከዚህ በፊት መምሕር እንደነበሩ ሰምቼአለሁ። በእንጨት ስራ ላይ ሞያ እንዳለዎ ይታወቃል። በፖለቲካ ውስጥም እንቅስቃሴ አድርገዋል። እና፣ እርስዎን በምን እንጠብቅዎ?
እኔ በፖለቲካ ዕንቅስቃሴ ውስጥ እቀጥላለሁ፤ በሚቀጥለው የሕይወት ዘመኔ። በኢትዮጵያ እኔ የማስበው ዓይነት ዴሞክራሲ እስኪሰፍን ትግሉን አላቆምም። ሰላማዊ ትግል ነው የሚያዋጣው። በአንድ የፖለቲካ ዕንቅስቃሴ ላይ መገለጥ እችላለሁ ብዬ አስባለሁ። እርሱም ሩቅ ላይሆን ይችላል። ከዚያ ውጭ ግን ደራሲ ነኝ። ራሴን ማሞገስ ስለማልፈልግ ነው። ሁለት ለሕትመት በቅተው እስከ ሶስተኛ ዕትም የደረሱ መጽሐፎች ነበሩኝ። “የሲዖል ፍርደኞች 1 እና 2” መጽሐፍት አሉኝ። እግዚአብሔር ቢረዳኝ፣ በሚቀጥለው ዓመት በተከታታይ ሶስት መጽሐፍትን አወጣለሁ፡ አንድ ያልታተመ፣ የአርትዖት ስራ የማከናውንበት ቀድሞ የተሰራ መጽሐፍ አለ። የስዕል እና የቅርጻ ቅርጽ ሞያዬ ከፍተኛ ነው። አሁን ወደዚያ አልመለስም። ሰው በስተርጅናው የሚሰራው አንድም ጽሁፍ ነው። ወደ ጽሁፍ ስራዎቼ እመለሳለሁ። አሁንም እየሰራሁ ነው ያለሁት። ከሰላማዊ ትግሉ አልሸሽም። ሚዲያ ላይ ሄጄ አንዳንድ አስተያየቶችን እየሰጠሁ ነው። የአገሬን የፖለቲካ ሁኔታ መተንተን፣ በእኔ የዕውቀት ደረጃ ያለውን ሁኔታ መግለጽ፣ መንግስት ሊያስተካክላቸው የሚገባቸውን ነገሮች መተቸት፣ ሰላማዊ ትግል እንዴት እንደሚያስፈልግ፤ በተለይ አሁን አገሪቱ ካለችበት ውጥንቅጥ ለመውጣት፣ አሁን የተያዘው የዕርቅ ጉዳይ ጠንክሮ እንዲወጣ ምክረ ሃሳብ አቀርባለሁ፤ እንደአቅሜ።
Published in
ነፃ አስተያየት