Saturday, 24 August 2024 19:32

አገጭህን ይዞ የሚለምንህ እምቢ ብትል በጥፊ ሊልህ!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አንድ የሞንጎላውያን ተረት እንዲህ ይለናል፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ጥንት፣ ግመል የዛሬው አጋዘን አይነት የሚያምሩ ቅርንጫፋማ ቀንዶች ነበሩት ይባል፡፡ ባለ አስራ ሁለት ቅርንጫፍ ቀንዶች ነበሩ፡፡ ቀንድ ብቻ አይደለም፤ እንዴት ያለ የሚያብለጨልጭ ሀር የመሰለ ጆፌ ረዥም ጭራም ነበረው፡፡
በዚያን ዘመን አጋዘን ደግሞ ቀንድ-አልባ ነበር፡፡ ሙልጭ ያለ ሌጣ ራስና አስቀያሚ መልክ ነበረው፡፡ ፈረስ ደግሞ ምንም ጭራ የሌለው ጉንድሽ ነበር፡፡
አንድ ቀን ግመሉ ውሃ ሊጠጣ ወደ ኃይቅ ወረደ አሉ፡፡ ውሃው ውስጥ ባየው የራሱ ውብ ምስል ተማረከ፡፡ “እንዴት  አምራለሁ!” አለ ለራሱ ራሱን በማድነቅ፡፡ “ምን አይነት ቆንጆ እንስሳ ነኝ እኔ!”
ይሄኔ አጋዘን ድንገት ከጫካ ብቅ ብሎ እያለከለከ መጣ፡፡
“ምን ሆነህ እንዲህ ትንፋሽ እስኪያጥርህ ታለከልካለህ ወዳጄ አጋዘን?” ሲል ጠየቀው ግመሉ፡፡
“አንተ ታድለሃል! እርጥብ ፀሐይ የመሰለ ቆንጆ መልክ ያለህ እንስሳ ነህ! እኔ ግን ምስኪን ነኝ፡፡ ዛሬ ማታ እንስሳት በሙሉ ወደሚሳተፉበት ፌስቲቫል የክብር እንግዳ ሆኜ ተጋብዤ ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል…”
“መቼም እንዲህ ያለ በነፃና በክብር የተጋበዝክበት ፀጋ በዋዛ አይገኝም” አለ ግመሉ፡፡
“እሱስ ነበር፡፡ ግን እንዲህ ያለ የተገጠበ ግንባር ይዤ ከነአስቀያሚ መልኬ እንዴት ብዬ እንስሳቱ ፊት እቀርባለሁ? እንደምታውቀው ነብር ዥጉርጉር ውብ ቆዳውን ይዞ የሚቀርብበት ድግስ ነው፡፡ ንሥርም ማራኪ ላባዋን የምታሳይበት መድረክ ነው፡፡ እኔ ምንም ቦታ አይኖረኝም፡፡ እባክህ ግመል ሆይ፤ ለአንድ ሁለት-ሦስት ሰዓት ቀንዶችህን አውሰኝ፡፡ መልሼ ልሰጥህ ቃል እገባልሃለሁ፡፡ ነገ በጠዋት የመጀመሪያ ሥራዬ፣ ያንተን ቀንድ መመለስ ነው ሲል” ተማፀነው፡፡
“ይሁን እሺ” አለ ግመል በለጋስ ኩራት፡፡ “እርግጥ አሁን ባለህበት ሁኔታ በጣም አስቀያሚ ነህ፡፡ ይህም ያሳዝነኛል፡፡ ስለዚህ ለዛሬ ማታ ተጊያጊያጥበትና አምረህ ቅረብ” አለና ባለቅርንጫፍ ቀንዶቹን አውልቆ ያውሰዋል፡፡ አጋዘኑ ጮቤ እየረገጠ ፈረጠጠ፡፡ ከዚያ ግመሉ አስጠነቀቀው፡፡ “ግን ልብ አድርግ፡፡ አንዲት ቅባት ወይም የፍሬ ጭማቂ ምናምን ይፈስስበትና ዋ!”
የፈረጠጠውን አጋዘን መንገድ ላይ ፈረስ አገኘውና፤
“እኔ አላምንም፤ እንዴት የሚያምር ቀንድ ነው ያለህ?” አለው፡፡
አጋዘን - “ቀንዴ በጣም ያምራል አይደል?! ግመል ነው የሰጠኝ” አለ፡፡
ፈረሱ - “እ….. እንዲህ ከሆነማ እኔም በጨዋ ወግ ከጠየቅሁኝ ግመል ለኔም የምፈልገውን ይሰጠኝ የሆናል!” አለ፡፡
ይሄ ሁሉ ሲሆን ግመሉ ኃይቁ ጋ ውሃ እየጠጣ፣ የበረሃዋን ጨረቃ ማድነቁን ቀጥሏል፡፡
በመጨረሻ ፈረስ ወደ ግመሉ ይመጣል፡፡
“ወዳጄ ግመል እንደምን አለህልኝ? ይገርምሃል ስፈልግህ ነው የተገናኘነው፡፡ እባክህ ለዛሬ ምሽት ውብ ጭራህን አበድረኝ ውለታህን እከፍላለሁ፡፡ ያቺን ያንተ አድናቂ የሆነችውን ፍቅረኛዬን በቅሎን ዛሬ ማታ አገኛለሁ፡፡ መቼም ያንተን ጭራ አድርጌ ፊቷ ብኩነሰነስ ልቧ ቅልጥ ነው የሚለው!”
ግመል በሚያምር ጭራው ኮራና የቀረበለት ጥያቄ አነሆስለው፡፡
“እውነትክን ነው? የእኔው አድናቂ ናት ማለት ነው? በል እሺ ለጊዜው ጭራ እንለዋወጥ፡፡ ግን ልባርግ ነገ በጠዋት አንዲት ፀጉር ሳትበላሽ እንድትመልስ፡፡ እንደምታውቀው በዓለም ላይ ያለው ምርጥና ቆንጆ ጭራ ይሄ ብቻ ነው!” አለና አስጠነቀቀው፡፡
ከዚህ ቀን በኋላ ብዙ ወራትና ብዙ አመታት አለፈ፡፡ ያም ሆኖ አጋዘኑ የግመሉን ቀንዶች አልመለሰለትም፡፡ ፈረስም ይሄው ዛሬ በየኮረብታው ላይ በግርማ ሞገስ ሶምሶማ የሚረግጠው፣ የግመሉን የተውሶ ጭራ እየነሰነሰ እንዳማረ እንደኮራ አለ፡፡ አንዳንድ ስዎች አንደሚሉት፤ ዛሬ ዛሬ ግመል ውሃ ሊጠጣ ወደ ኃይቅ በወረደ ቁጥር ሌጣና አስቀያሚ መልኩን ባየ ጊዜ ሁሉ ወደ ኋላው አፈግፍጎ እንደማስጎስበት ይላል፡፡ በዚያው የውሃ ጥሙን ይረሳዋል፡፡ በተጨማሪም ግመል አንገቱን ሰገግ አድርጎ ማዶ ማዶ እያየ የተከመረ አሸዋ ወይም ራቅ ያለ የተራራ ጫፍ ሲያይ በልቡ እንዲህ እያሰበ ነው ይላሉ፡-
“ለመሆኑ ያ ፈረስ ጭራዬን የሚመልስልኝ መቼ ነው?” ግመል ሆሌ ሀዘንተኛ የሚመስለን በዚሁ ምክንያት ነው ይባላል፡፡
*           *          *
በሀገራችን የአንዱ መሰረታዊ ንብረት የሌላው ማጌጫና መጠሪያ የሆነበት፣ ያንዱ ደግነትና ለጋስነት ሌላው በብልጥነት ግብር የሚጠራበት ካርድ የሆነበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ያንዱ ልባዊ መስዋዕትነት የሌላው መኳያና መዳሪያ፣ የሌላው ዓለም ማያ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ያንድ ጊዜ ግፍ ቁስሉ ሳይጠና ሌላ ግፍ በመጨማመር ያለፈውን ጥፋት ህጋዊ ለማድረግ መጣር በጣም የተዘወተረ ባህላዊ ተግባር ሆኗል፡፡ “የዝንጀሮ ልጅ ከተራራ አይወድቅም፡፡ አመለኛም አመሉን አይተውም” እንዲሉ ማለት ነው፡፡
ስንቱ መፈክሩን፣ ጥንስስ ሀሳቡን፣ እውቀቱን ተነጥቆ ሌላው በየአደባባዩ እንቁልልጬ ሲሉት እንደግመሉ “ለመሆኑ ያ ፈረስ ጭራዬን የሚመልስልኝ መቼ ነው?” ከሚል ልመናዊ ምኞት ባሻገር አማራጭ አጥቶ ቁጭ ብሏል፡፡
“የራስህ ዲሞክራሲ ነው፤ ሰጪም ነሺም የለብህም” ተብሎ ባዶ እጁን የተቀመጠ ስንቱ ነው? ትላንት ራሱ ባጠረው አጥር ከጨዋታው ውጪ ሆኖ እንቁልልጭ ሲባል የሚውል ስንቱ ነው? አባብሎ ለምኖ፣ ቅበረኝ ብሎ ጎጆ - ወጥቶ አላውቅህም ሲባል አፉን የዘጋ ስንቱ ነው? ውሃ ጠምቶት እንደ ግመሉ ጥሙን የረሳ ስንቱ ነው? ብዙ ጊዜ ተነስተው፣ ብዙ ጊዜ ተድበስብሰው፣ እንደገና ብዙ ጊዜ የሚያዳክሩን ስንት ጉዳዮች ይሆኑ?
ልመናዎች፣ ማቆሻበሎች፣ ያላንተ ማን አለኝ መባባሎች ለህዝብ ብዙ ፋይዳ እንዳልሰጠው ብዙ የቅርብና የሩቅ ትውስታዎች ይነግሩናል፡፡ ሁሌም ልብ የማይባለው ግን “አገጭህን ይዞ የሚለምንህ በጥፊ ሊልህ” የሚለው ተረት ነውና፣ ዛሬም በአፅንኦት ግንዛቤ ውስጥ ሊቀመጥ ይገባል!

Read 822 times