1 ከርሞ (ዕድሜን ኖሮ) ማለፍ
የሰው ልጅ ዕድሜ ደረጃዎች አሉት ብሎ ማወጅ አዲስ ግኝት አይደለም፡፡ ዕድሜ በዓለም የኑሮ ቆይታ ውስጥ ሆነው የሚሸመግሉበት/የሚያረጁበት ወይንም የሚያልፉበት ዓመታት ቀመር ነው ብለን ብንወስደውስ? አያስኬድም? በዓለም ላይ የምናየው ሁሉ (ሰው፣ እንስሳት፣ ዛፍ፣ ደንጊያ፣ መሬት፣ ቤት፣ …) በቁጥር የሚተመን የዕድሜ/መክረሚያ ቀምር/ቁጥር አለው፡፡
በሰው ዕድሜ ላይ ለመጻፍ የሞከርኩት ካለ ምክንያት አይደለም፡፡ ወጣቶች በእያንዳንዱ የዕድሜ አጥራቸው ዙሪያ መሥራት ያሉባቸውን ተግባራት እየፈጸሙ እንዲቆዩ፤ ማስተካከል ያለባቸውንም ባሉበት ተጨባጭ ሁኔታ ዝግጁ ሆነው ቀድመው የሚያነጣጥሩበትን ዒላማ ለመጠቆም ነው፡፡ ባለ ዕድሜዎች (ጎልማሶች፣ አረጋውያንና ሽማግሌዎች) ደግሞ እያንዳንዷን የሕይወት ጉዟቸውን በሀሳብ መለስ ብለው እንዲቃኙበትና ለቀሪው መክረሚያቸው እንዲዘጋጁበት በማሰብ ነው፡፡
ማንም ሰው ፍጹም መሆን አይችልም፡፡ በረጅም ዕድሜና በጥሩ ስኬት ተሟልተው የተገኙ ካሉ በጣም ዕድለኛ የሆኑቱ ናቸው፡፡ ምናልባትም፤ ዘመን፣ ዕድሜና ምኞታቸው የተገጣጠሙላቸውና ረጅም የኑሮ ድልና ስኬት ያገኙቱ ደግሞ የተባረኩቱ ናቸው፡፡ በረከት ስጦታ እንጂ በዕድሜ ቆይታ/መክረም እና የሥራ ልፋት የሚያገኙት አይደለም፡፡ በረከት ለሁሉም ዕድሜ የሚቸር ስጦታ ነው፡፡ ዕድሜ በበረከት ምስጢር ውስጥ ተታትቶ (ተሸምኖ) ያለ መክረሚያ (ሕይወት) ነው፡፡
ኖሮ ማለፍ የቢሊዮኖች ዕጣ ፈንታ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ኖራችሁ ብቻ ለማለፍ አትኑሩ፡፡ ላኖረቻችሁ መሬት ምንም ነገር ሳትተዉላት ኑሮን ብቻ ኖራችሁም አትለፉ፡፡ ዛፍ እንኳን ቅርፊትና ቅጠሉን ለመሬት ትቶላት ያልፋል - ሊያዳብራት፡፡ ሲነድም አመዱ ይተርፋታል፡፡ ከመሬት በላይ ስታለፉት የኖራችሁት በስባሽ ሥጋ የሚቀበረው መሬት ውስጥ በመሆኑ፣ ለመሬት ያ ብቻ ይበቃታል ካላችሁ፣ ንፉግ ትሆናላችሁ፡፡ ከላይዋ ስትኖሩ የረገጣችኋት አንሶ፣ ለሁለተኛ ጊዜ መኖሪያ እንድትሆናችሁ ከውስጧ ስትከፈኑባት/ስትቀበሩባት መሬት እንኳን የምታዝንባችሁ ለመሆኑ አልጠራጠርም፡፡ ሁለቱንም ጊዜ ኖራችሁባት እንጂ ምንም ነገር ለመሬት አልተዋችሁላትምና እስቲ እዘኑላት? በላይዋ ላይ አንዲት ትንሽ ነገር እንኳን ተዉላት፡፡ ዕድሜን መቁጠር ይህን ካላከለ ምን ፋይዳ አለው?
የሰው ልጅ የኑሮ ዓይነቱና ሂደቱ ብዙ ነው፡፡ በኑሮ ዘመኑ ምኞቱ በስኬት የተሟላለት፣ ግን ደግሞ ዕድሜን ያልተቸረ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ያን ዓይነቱን ሰው “በአጭር ባይቀጭ ኖሮ የት በደረሰ” ተብሎ ይወራለታል፡፡ ይቆጩለታል፡፡ “ቢኖር ኖሮ…” ብለው መኖሩን ይመኙለታል፡፡ በአጭር መቀጨት በራሱ አወያይ ሃሳብ ነውና ልዝለለው፡፡
ዕድሜ የተቸረውና ምኞቱ በስኬት የተሟላለት ሰው ደግሞ አለ፡፡ ያንን ዓይነቱን ሰው “በዕድሜው ሙሉ ምኞቱን አሳክቶ የኖረ ሰው ነበር” በመባል ይታወሳል፡፡ እንደሱ በሆንኩኝ የሚል ምኞትን የሚጭርባቸው ሰዎችም ቀላል አይሆኑም፡፡ በዙሪያው ተኮልኩለው ሞቱን/ማለፉን ሳይሆን ኑሮውን ይመኙታል፡፡ ለራሳቸው ዕድሜንና ስኬትን መመኘታቸው መሆኑንም ልብ በሉላቸው፡፡ ሌላው ደግሞ፣ ዕድሜ ተችሮት፣ ምኞቱን ሳያሳካና ማንም እዚህ ግባ ሳይለው ኖሮ ሊያልፍ ይችላል፡፡ ያን ዓይነቱን ሰው ደግሞ “የዕድሜ ጠናዛ” (ዕድሜውን ብቻ በመቁጠር በዓለም ላይ የኖረ) በማለት እንዳልተሳካለትና ቢሠራም የማይሆንለት እንደነበረ በማንሳት ይታወሳል፡፡ እንዲታወስ ካላቸው ቁጭት ሳይሆን፣ አንስቶ ለመጣል (ለወሬ) ሲሉ ያነሱታል (አንስቶ መጣልም ባህል ነው)፡፡ “አይጣል ነው!” ሲባል አልሰማችሁም?
ከጠቀስኳቸው ከሦስቱ ዓይነት ሰዎች የትኛው ይሻላል ብዬ በመጠየቅ ምርጫን አላቀርብላችሁም፡፡ ይህን ዓይነት ጥያቄ “ስድብ” ነው፡፡ ሁሉም ሰው በኑሮ ዘመኑ መታወሻ ነገር ያለው መሆኑን ግን ያዙልኝ፡፡ ወይ በስንፍናው፣ ወይ በክፋቱ፣ ወይ በታታሪነቱ፣ ወይ በመልካም ሥራው፣ በሃብቱ ወይንም በድሕነቱ እንዲታወስ ይሆናል፡፡ ይበልጥ የሚታወሰው ግን የሚታወስ ሥራ የሠራው ነው በማለት፣ ኖሮ ብቻ ያለፈውን ሰው እንዴት ማስታወስ እንደሚቻል እያሰላሰላችሁ አብረን እንዝለቅ፡፡
2. ዕድሜና ስኬት
የሰው ልጅ ዕድሜ ከብዙ ክንዋኔዎች ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገዶች ይገናኛል፡፡ በዓለም ላይ የሚገኝ አብዛኛው ስኬት (የሃብት፣ የሥራ፣ …) እና ድል (የድርጊት/ውድድር ለምሳሌ፣ ስፖርት) የሚገኘው በወጣትነት ዕድሜ ነው፡፡ ስኬትና ድል ሲጨምር፣ እውቅና እያደገና የግል ዝና እየገነነ ይሄዳል፡፡ የግል ዝና ለአገርም/ለዜጎችም ይተርፋል፡፡ በአንፃሩ፣ ድል ከእድሜና ከተለያዩ አካላዊና ስነ-ልቡናዊ ሁኔታዎች ጋር በቅርብ የተዛመደ በመሆኑ እየቀነሰ መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ በስፖርት (ለምሳሌ፣ ሩጫ፣ እግር ኳስና ቅርጫት ኳስ በመሳሰሉ መስኮች) በግልና በቡድን የተገኙ ድሎችንና ዝናን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዕድሜ ሲጨምር የውድድር ስፖርትን የመከወን ኃይል/ጉልበት በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ በእግር ኳሱም ይሁን በሩጫው በወጣትነት ዕድሜ ተጀምሮ ወደ ጉልምስናው ሲቃረቡ የማቆም ሂደት የሚዘወተረው ተሳትፎው ስኬትን በነበረው ሁኔታ ሊያስቀጥል ስለማይችል ነው፡፡ ሆኖም፣ ዝና በአንድ ወቅት በተከናወነ ሁኔታ ላይ መመስረት በመቻሉ የሚቀጥል ሲሆን፣ ስኬት ግን የዕለት ጥረት ውጤት ነውና ዕድሜ ሲገፋ ይለግማል፡፡ ስኬትን ለማስቀጠል በድል የጨበጡትን ዝናና ወረት (ገንዘብ) በስስት/በዘዴ ሊጠብቁት የሚገባው ለዚያ ነው፡፡
ድልን ዕድሜ የሚጫነው በመሆኑ፣ በዕድሜው መግፋት ምክንያት ድል ያልቀናው ሰው የቀድሞ ዝናውን አያጣውም፡፡ እሱ ያገኘው ድል የራሱ ቢሆንም ከእሱ በኋላ የሚመጣ ወጣት ድሉን ሊጋራውና እንደ አርአያው ሊመለከተውም ይችላል፡፡ ሁሉም በዘመኑ ባለዝናና ባለድል ሆኖ ሊወደስና ሊከበር ይችላል፡፡ ልዩነቱ እያንዳንዱ ባለድል ድሉንና ዝናውን የሚጠብቅበት መንገድ ነው፡፡
ዝና የሰው ልጅ ስስ ብልት ነው - እስከ መጨረሻው በስስት ተንከባክባችሁ ጠብቁኝ ይላል፡፡ አንዱ ከአንዱ በአንጻራዊ ሁኔታ የተሻለ ድል ሊያስመዘግብ ይችል እንደሆነ እንጂ፣ ድል አንዴ ከተመዘገበ ለባለድሉ ቋሚ ዝና ይፈጥረለታል፡፡ አጭርም ሆነ ረዥም ዕድሜ፣ ተከናውኖ የተመዘገበን ዝና አይሽርም፡፡
ድል ለዝና፣ ዝናም ለበለጠ ድል የሚያነሳሱ/የሚያበቁ ናቸውና፤ ድል ሲቀዘቅዝ ዝና በነበረበት ግለት ላይቀጥል ይችላል፡፡ እውቅናው የጨመረለት ሰው ባገኘው እውቅና መኩራራቱም የተለመደ የሰው ባሕርይ ነው፡፡ ባለድል የሆኑ ጥቂት ሰዎች፣ ድልን እያጠነከሩ ካልሄዱ ዝና ሊቀንስ እንደሚችልና እውቅናም እንደሚጋሽብ የማያሰላስሉ ይኖራሉ፡፡ የዕድሜ ባለጸጋ የሆነ ባለዝና የሚኖረው አማራጭ፣ የነበረውን ዝና በሌሎች መልካም ተግባራት ማስጠበቅ ነው፡፡ እንደቀድሞው ያለ ሌላ ተመሳሳይ ድል ማስመዝገብ ላይሆንለት ይችላል፡፡ የዕድሜ ባለጸጎች ላገኛችሁት ዝና መጠንቀቅ ያለባችሁ፣ ዝናችሁ በዕድሜአችሁ አማካኝነት እንዳይበላሽ ነው፡፡ ቅርሳችሁ ስለሆነ ልትጠብቁት ይገባል ለማለት ነው፡፡
አንድ ጊዜ/ወቅት ድልን ከተጎናጸፉ በኋላ፣ ምንጊዜም በዚያ ዝና ብቻ እንዲሞገሱ “ሌላውን መተላለፌን ተውት” በማለት ለሰውም ሆነ ለራሳቸው ክብር የማይጠነቀቁ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ድሉ ያስገኘላቸው ዝና ቶሎ የሚያሰክራቸውና በፍጥነት ታይተው እንደጤዛ የሚረግፉም በርካታ ናቸው፡፡ አንዴ ባስመዘገቡት ድል እስከ ዕለተ-ሞታቸው ተከብረውና ተወድደው የሚኖሩ ዕድለኞችም አሉ፡፡ እኒህኞቹን በዘላቂነት ሊያስከብራቸው የቻለው ከድል በኋላ ያስመዘገቧቸው መልካም ባህሪያት ጭምር ናቸው፡፡ ድል ከመልካም ተግባርና ባህሪይ ጋር ሲጣመር የዝናን ዘላለማዊ የመሆን ዕድሉን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ዕድሜም ክብር ተችሮት ከዝና ጋር አብሮ ይዘልቃል፡፡
ሰው በዕድሜው ምክንያት የበለጠ ድል የመሥራት/የማስመዝገብ አቅሙ እየደከመ ቢመጣም፣ ቀደም ተጎናጽፎት የነበረው ድል ዝናውን ጠብቆ የሚያቆይለት እየመሰለው መኩራራቱን ይቀጥላል፡፡ ድሉ ፈጥሮለት የነበረውን የዝና ሞቅታ ባለበት እንዲቆይ የሚችለውን ከማድረግም አይቆጠብም፡፡ በርካቶች ማበረታቻ እጽ እስከመጠቀም የሚደርሱት ለዚያ ነው፡፡ ያን ጊዜ የውድቀትን ቁልቁለት ይያያዙታል፡፡ ዕድሜ፣ ድልና ዝናም ከንቱ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ረገድ ታሪክ ያሳየን ነገር አለ፡፡
የዓለም ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች የነበረውን ማራዶናን የማስታውሰው በቁጭት ነው፡፡ ማራዶና በድንገት ተከስቶ ብርሀኑን ለዓለም ያበራና በቶሎ የጠፋ ኮከብ ይመስለኛል፡፡ ዝናውና (የስፖርት ቤተሰቦች ፍቅርና ሀዘን) በእጽ ሱስ ተለክፎ በኑሮው የተንገዳገደባቸው ዓመታት ከሕሊና የሚጠፉ አይደሉም፡፡ ሮናልዲኒዮን የትኛው ላይ ልመድበው ይሆን? ድንቁ የኳስ ከያኒ ሮናልዲኒዮ (ስሙን በትክክል ጽፌው ይሆን?) ዕድሜ ብቻውን አልተሟገተውም፡፡ ያገኘው ዝና ከቁጥጥር ውጪ አውጥቶት የሚሠራውን አሳጣው ልበል? አሱንም ሳስብ ሀዘን ይሰማኛል፡፡
ከፍተኛ ዝና ላይ የነበረውና፣ “የኳስ ንጉሥ” ተብሎ ተወዳጅነቱን እንደያዘ ተከብሮ በመኖር ለህልፈተ ሥጋ የበቃው፣ የዕድሜ ባለጸጋው የብራዚሉ ፔሌን ማየት ደግሞ በሌላው ጠርዝ የሚገኝ ትልቅ ትምህርት/አርአያነት ነው፡፡
እግር ኳስን እንደ ምሳሌ ወሰድኩኝ እንጂ፣ በሁሉም ድልና ዝና በሚያስገኙ ስፖርቶች (ለምሳሌ፣ አትሌቲክስ፣ የቅርጫት ኳስ) ውስጥ የሚገኙ አያሌ ባለ ድልና ዝናዎች አሁንም አሉ፡፡ ለአብነት ያህል ግን የኳሱ ይበቃል፡፡ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ከገባሁኝ፣ በአገራችን ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ብዙዎች አሉ፡፡ ዝናን ከዕድሜ ጋር ይዘው በጉዞ ላይ የሚገኙ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አረጋውያን አትሌቶች አሉን፡፡ የኋለኞች/የአሁኖቹ ከፊተኞች መልካም ቢማሩ፣ መልካምን ይሠራሉ፡፡
በጥቅሉ፣ ባለ ድልና ባለዝናው ሁሉ በዕድሜው ምክንያት የለመደውን ሲያጣ የቀድሞውን ድልና ዝና በሃሳብ መመኘቱ የሰው ባሕሪ ነውና ቀድሞ ማሰብ ዋጋ አለው፡፡ አንድ ሥፍራ ላይ ሲደርስ ይበቃኛል ማለት እንደሚገባው ቀድሞ ካላሰበ፣ ወይም በእጁ ላለው ድልና ዝና ካልተጠነቀቀ፣ እንደ ቁማርተኛ ሰው መሆኑም እሙን ነው፡፡ ዕድሜ፣ አንድ ሥፍራ ላይ ሲደርሱ ያገኘሁት በቃኝ ማለትን የግድ ይላል፡፡ ጉልበትን፣ ወቅትን፣ ዕድሜንና ተጽዕኖውን ቀድሞ ማጤን ብልህነት ይመስለኛል፡፡
3. የቁማርተኛ ሰው ባህሪ
የቁማርተኛ ሰው ባህሪ ይገርመኛል፡፡ ድልን/ስኬትን ከቁማርተኛ ሰው ባህሪ ጋር ሳነጻጽር፣ ዕድሜም በውስጡ እንዳለበት እያሰባችሁ ተከተሉኝ፡፡
ቁማርተኛ ሰው ሲቀናው ብዙ ለማግኘት፣ ሳይቀናው ደግሞ እያደር ሊቀናው እንደሚችል እልህ ተያይዞ ቁማር “መጫወቱን” ይቀጥላል፡፡ ሊቀናውም ላይቀናውም ይችላል፡፡ የት ላይ ማቆም እንዳለበት መወሰን ይከብደዋልና ይቀጥላል፡፡ የሚታየው ያጣው (“የተበላው”) ገንዘቡ ነው፡፡
ከእልሁ የሚነቃው ደግሞ በእጁ የነበረው ገንዘብ በሙሉ ሲያልቅና ምንም ማድረግ እንደማይችል ሲረዳ ብቻ ነው፡፡ በጥቅሉ፣ ቀሪ ገንዘብ በእጁ ቢኖር ኖሮ የቀድሞ ገንዘቡን ሁሉ መልሶ ሊያገኝ እንደሚችል ይመኛል እንጂ፣ አልቻልኩም ብሎ ምኞቱንና እልሁን አይገታም፡፡ ምኞት፣ እልህን በውስጡ ቀላቅሎ የያዘ የሰዎች ሁሉ ጉልበት ነው፡፡ እልህ ደግሞ ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ነገር የማድረግ ኃይልን የሚቸር የሰው ድክመት ወይንም ብርታት ነው፡፡ እልህ ብርታት ሲሆን ሰውን ይገነባል፡፡ ድክመት ሲሆን ደግሞ ሰውን ያሳንሳል፡፡ ብርታትና ድክመት በሰው ልጆች የዕድሜ ሂደት ውስጥ የሚከሰቱ ጠባያት ናቸው፡፡
ብልህ ቁማርተኛ ሲበላና (በ ይላላ) ሲበላ (በ ይጥበቅ) ጠባዩና በዚያም ሳቢያ የሚወስናቸው ኤኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ይለያያሉ፡፡ ብልህ ቁማርተኛ የሚበላው (በ ይጥበቅ) ቀድሞ የበላውን የተቀናቃኙን ገንዘብ ነው፡፡ ከራሱ የሚሰጠው ጥቂት ነው፡፡ ሊያጣ የሚችለውን ሊያገኝ ከሚችለው አንጻር አስቀድሞ ያሰላል፡፡
ብዙው ቁማርተኛ ከእልሁ የሚነቃው ሁሉንም ገንዘቡን ካጣ በኋላ ሊሆን ይችላል፡፡ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውን በመያዣነት አሲዘው የሚጫወቱ ቁማርተኞች አሉ ይባላል፡፡ ያጡትን ለመመለስ ካላቸው እልህና ምኞት በስተቀር፣ ያሲያዙትን ንብረት በተጨማሪ ሊያጡት እንደሚችሉ በዚያን የጫዎታ ወቅት የደረሱበት የባህሪ ለውጥ አይፈቅድላቸውም፡፡ የሚታያቸው በፊት ያጡት ገንዘብ ሊሆን ይችላል፡፡ ያጡትን መልሰው ማግኘት ሲመኙ፣ የያዙትን ማጣት ሊከተል መቻሉ ግን ሊያልፉት የማይችሉት እውነት ነው፡፡
በርካቶች ከዝና ማማ ላይ ወርደው ተንኮታኩተዋል፡፡ ተጎናጽፎት በነበረው ድል ሳቢያ የተቸረው ዝና እንደነበረ እንዲቆይ የሚመኝ እንዳለ ሁሉ፣ የተበላውን ቁማር ለመመለስ ንብረቱን ሁሉ አስይዞ በእልህ ወደ ኪሳራ የሚንደረደርም አለ፡፡ በእጅ ላይ ባለ ነገር መርካት ትልቅ ችሎታ ነው፡፡ እያንዳንዱ ዕድሜ፣ ድልና ዝና በእጅ ውስጥ የሚገኝ እንቁ ነው፡፡ የዕድሜን፣ የድልንና የዝናን ውኃ ልክ በማወቅ መኖር መልካም ነው፡፡
ይበቃኛል ማለት ከተቻለ፣ በእጅ ያለው ካጡት ይልቅ ይበልጣል፡፡ በቃኝ ማለት መቻል ትልቅ ዕውቀት፣ ሙሉ ሃብት ነው፡፡ ሁሉም ግን አይታደለውም፡፡ ቁማርተኛ ሰው በቃኝ ብሎ ቢያስብ እንኳን የመወሰን ችሎታውና የቁማሩ ባህሪ አይፈቅዱለትም፡፡ ዕድሜም የራሱ ባህሪያት አሉት፡፡ የዕድሜን ቁጥሩን እንጂ ሂደቱንና መጨረሻውን መገመትና መቆጣጠር ከባድ ነው - ጥሩው መጥፎ፣ መጥፎው ደግሞ መልካም ሆኖ ሊደመደም ይችላል፡፡ ዕድሜ አንዳንዴ ምስጢር ነው፡፡
ሰላም ለሁላችን፡፡
Published in
ህብረተሰብ