ኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት 60 ሚሊዮን ዶሮዎች ለምግብነት ይቀርባሉ።
አንድ የአሜሪካ ኩባንያ በየሳምንቱ 55 ሚሊዮን ዶሮዎችን ለምግብነት ያቀርባል።
የፋኦ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት ለምግብ የሚውሉ ዶሮዎች 60 ሚሊዮን ናቸው። አንድ ዶሮ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ በአማካይ 800 ግራም ሥጋ ማለት እንደሆነም መረጃው ይገልጻል። አንድ ኪሎ አይሞላም። የኤርትራ ዶሮ ግን ይበልጣል። የኤርትራ ዶሮ 730 ግራም እንደሆነ የፋኦ መረጃ ላይ ተጠቅሷል።
ሌሎች የአፍሪካ አገራት ግን በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ይሻላሉ። የአፍሪካ ዶሮ በአማካይ 1325 ግራም ክብደት አለው ተብሏል።
የሕንድ እና የቻይና ዶሮዎች ደግሞ 1550 ግራም።
በአውሮፓ አገራት ውስጥ የአንድ ዶሮ ክብደት በአማካይ 2000 ግራም ነው። በእርግጥ ከአገር አገር ይለያያል። በጀርመን አንድ ዶሮ 2300 ግራም ነው። በግሪክ ግን 1600 ግራም ብቻ።
የአሜሪካ ዶሮዎች ከሌሎች ይበልጣሉ - 2400 ግራም ናቸው።
በሌላ አነጋገር፣ አንድ የአሜሪካ ዶሮ 3 የኢትዮጵያ ዶሮ ነው።
ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በእንስሳት ብዛት ትታወቅ የለ? የኢትዮጵያ ዶሮዎች “የደለበ ሥጋ” ባይኖራቸውም፣ ቁጥራቸውን በማብዛት ልናካክሰው አንችልም?
አይደለም።
በዶሮዎች ክብደት ብቻ ሳይሆን በብዛትም፣ በሚዛን ብቻ ሳይሆን በቁጥርም… ኢትዮጵያ ወደ ኋላ ቀርታለች።
በመላው ዓለም በየዓመቱ፣ 75 ቢሊዮን ዶሮዎች ለምግብነት ይውላሉ። ለ8 ቢሊዮን ሕዝብ ማለት ነው። ለአንድ ሰው 9 ዶሮ መሆኑ ነው።
በኢትዮጵያ ግን፣ አንድ ዶሮ ለሁለት ሰው ነው። 60 ሚሊዮን ዶሮ ለ120 ሚሊዮን ሕዝብ።
ከአፍሪካ ጋር ብቻ ሲነጻጸርም በጣም ትንሽ ነው።
አፍሪካ ውስጥ ለ1.4 ቢሊዮን ሕዝብ 6 ቢሊዮን ዶሮ ለምግብነት ይውላሉ። ለአንድ ሰው አራት ዶሮ መሆኑ ነው።
ቻይና ለ1.4 ቢሊዮን ሕዝብ 11 ቢሊዮን ዶሮዎች። ለአንድ ሰው 8 ዶሮ።
በዓመት በአማካይ ለአንድ ሰው ስንት ዶሮ?
የአውሮፓ ሕብረት አገራት ውስጥ፣ ለ450 ሚሊዮን ሕዝብ ለምግብነት የሚውሉ ዶሮዎች ብዛት ከ6 ቢሊዮን በላይ ናቸው። ለአንድ ሰው 14 ዶሮዎች ይደርሱታል እንደማለት ነው - በአማካይ።
የአሜሪካ ግን ከዚህም ይበልጣል። 28 ዶሮ ለአንድ ሰው።
ግን የዶሮ ብዛት ብቻ አይደለም ጉዳዩ። መነሻችን ላይ እንዳየነው የዶሮዎቹ ክብደትም ጭምር ነው ልዩነቱ። በኪሎ እያነጻጸርን እንየው።
የአንድ ሰው አማካይ የዶሮ ሥጋ በዓመት
ለምግብነት የሚውለው የዓለማችን የዶሮ ሥጋ በአማካይ ለአንድ ሰው 16 ኪሎ ይደርሰዋል - በዓመት።
በኢትዮጵያና በኤርትራ ግን የአንድ ሰው አማካይ በዓመት ግማሽ ኪሎ ነው። እንዲያውም ከግማሽ ኪሎ በታች ነው።
የኢትዮጵያ የዶሮ ሥጋ ዕጥረት፣ ከአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር እንኳ በጣም የባሰ ነው። የአፍሪካ አማካይ የዶሮ ሥጋ ፍጆታ ከኢትዮጵያ በዐሥር ዕጥፍ ይበልጣል።
ከአውሮፓና ከአሜሪካ ጋር ሲነጻጸርማ የትና የት!
የኃምሣ እና የመቶ ዕጥፍ ነው ልዩነቱ። የአውሮፓ የዶሮ ሥጋ አቅርቦት በዓመት ለአንድ ሰው 28 ኪሎ ገደማ ነው። በአሜሪካ ደግሞ 67 ኪሎ።
በእርግጥ የዶሮ ምርት እንዲህ ብዙ አልነበረም። ድሮ ድሮ የከብትና የበግ ሥጋ ነበር በብዛት የሚመረጠው።
የዛሬ ሰባ ዓመት፣ በአሜሪካ ለምግብነት ከሚዘጋጀው የሥጋ ምርት ውስጥ 12 በመቶ ያህሉ ብቻ ነበር የዶሮ ሥጋ። ዛሬ ከአሜሪካውያን የሥጋ ምግብ ውስጥ ግማሹ የዶሮ ሥጋ ነው። ምክንያት አለው
ዶሮ በሁለት ወር፣ በሬ በሁለት ዓመት
የዶሮ ሥጋ “ተመራጭ” የሆነው በዋጋው ነው። በእርባታ ፍጥነቱም።
አጥንት የሌለው “ለስቴክ” ተመራጭ የበሬ ሥጋ… በኪሎ 22 ዶላር ነው።
አጥንቱ የወጣ የዶሮ ፈረሰኛ፣ በኪሎ 10 ዶላር።
የተጣራ የአሳማ ሥጋ ደግሞ በኪሎ 9 ዶላር ገደማ።
የዶሮ ሥጋ ዋጋ ከበሬ ሥጋ በግማሽ የሚቀንስ መሆኑ ነው። አንዳንዴም በጣም ይወርዳል።
በሌላ በኩልም በሬ ከማርባትና ከማደለብ ይልቅ፣ ዶሮዎችን አርብቶ ለገበያ ማቅረብ ይቀልላል። ከብቶችን አርብቶና አደልቦ ለገበያ ለማድረስ ቢያንስ ቢያንስ 20 ወራትን ይፈጃል ይላል - የዎል ስትሪት ጆርናል ዘገባ።
ዶሮዎችን ግን በስድስት ሳምንት ለምሳ ማድረስ ይቻላል - ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ። ታዲያ የዶሮዎቹ ዐይነት ይለያያል። በአነስተኛ ቀለብ በፍጥነት የሚያድጉ ናቸው። ከኃምሣ ዓመታት በፊት በአሜሪካ የአንድ ዶሮ አማካይ ክብደት 1.4 ኪሎ ነበር። ዛሬ ከ2.4 ኪሎ ይበልጣል። የኢትዮጵያ የዶሮዎች ዝርያ ግን አልተሻሻለም። ክብደታቸውም ከድሮው አልተለወጠም - 0.8 ኪሎ ብቻ።
ለማንኛውም በዓለም ዙሪያ ከከብት ሥጋ ይልቅ የዶሮ ሥጋ በፍጥነት እየጨመረ የመጣው፣ በፍጥነት ማርባትና በአነስተኛ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ ስለተቻለ ነው።
በኢትዮጵያም ማሻሻል ይቻላል እያለ ነው - መንግሥት። በእርግጥም የኢትዮጵያ የዶሮ እርባታ በዓለም በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሣ፣ በትንሽ የማሻሻያ ለውጥ ከፍ ያለ ውጤት ማምጣት ይቻል ይሆናል - በቁጥርም በጥራትም።
የኢትዮጵያ ቁጥር፣ ከቁጥር አልገባም።
60 ሚሊዮን… 70 ሚሊዮን ዶሮ በዓመት? ከቁጥር የሚገባ ዐይነት አይደለም። በዓለም ዙሪያኮ 75 ቢሊዮን ዶሮዎች ናቸው ለምግብነት የሚውሉት። የኢትዮጵያ ድርሻ፣ ከ1000 ውስጥ 1 ብቻ ነው።
በሕዝብ ብዛት ከታየ ግን፣ ከዓለማችን 1000 ሰዎች መካከል 15ቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
የዚያኑ ያህል ድርሻ በዶሮ እርባታ ላይ የማይኖረን ለምንድነው? ያን ያህል የተራቀቀ ምሥጢር የለውም። አብዛኛው ሰው አብዛኛው ቤተሰብ ዶሮዎችን ማርባት ይችላል።
ነገር ግን፣ በመኖሪያ ቤት እርባታ ብቻ ብዙ ለውጥ ማምጣት አይቻልም። በሌሎች አገራት እጅግ ፈጣን ለውጥ የመጣው፣ በንግድ ድርጅቶች አማካኝነት ነው - የእርባታ ማዕከላትን፣ የቄራ ተቋማትንና የማሸጊያ ፋብሪካዎችን በማስፋፋት ነው የዶሮ ሥጋ የተትረፈረፈው። ከትንሽ መጀመርና ማደግ ከተቻለ ምን ችግር አለው?
ትልቁ የአሜሪካ የሥጋ አቅራቢ ኩባንያ፣ የዛሬ 90 ዓመት ከጓሮ የዶሮ እርባታ ነው የጀመረው። ከ30 ዓመታት ትግል በኋላ የእርባታ ብቻ ሳይሆን የቄራ ማዕከልና የማሸጊያ ፋብሪካ እየከፈተ ሥራውን ሲያስፋፋ፣ የአሜሪካ ትልቁ የሥጋ ኩባንያ ይሆናል ብሎ የጠበቀው አልነበረም። ቢሆንም ግን በሳምንት 120 ሺ ዶሮዎችን በቄራ ማዕከሉ ለገበያ ለማቅረብ መብቃቱ በጊዜው እንደ ተዓምር የሚወራለት ዕድገት ነበር። በዓመት ከ6 ሚሊዮን በላይ ዶሮዎች ማለት ነው።
ዛሬ ግን “ታይሰን ፉድስ”፣ በሳምንት 55 ሚሊዮን ዶሮዎችን በፋብሪካዎቹ አማካኝነት ለገበያ ያቀርባል። በዓመት 2.8 ቢሊዮን ዶሮዎች ማለት ነው። አሜሪካዊያን ከሚመገቡት የዶሮ ሥጋ ውስጥ ሩብ ያህሉ የሚቀርበው ከአንድ ኩባንያ ሲሆን አስቡት። ከጓሮ እርባታ ተነስቶ የመጣ ኩባንያ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው በቀላሉ አይደለም። ግን መድረስ ችሏል።
እንዲህ ዐይነት አስደናቂ ታሪክ ኢትዮጵያ ውስጥ በትንሹም ቢሆን ሊፈጠር ይችላል? ቅንጣት ታህል ዕድል ይኖረዋል? ቢችልስ እንፈቅድለታለን?
ይፈቀድለታል ወይ?
“መንግሥት ይፈቅድለታል ወይ?” ማለቴ አይደለም። እኛ “ሕዝብ” እንፈቅድለታለን ወይ ማለቴ ነው።
ለነገሩ፣ መጀመሪያውኑ ከመንግሥት ተቋማት በኩል የሚገጥመውን እንቅፋት ሳይሻገር እዚያው በእንጭጩ ተቀጭቶ ሊቀር ይችላል። ብዙ ዐይነት መንግሥት ነው ያለው። የፌደራል፣ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ… በእያንዳንዱ እርከን ውስጥም የጤና ተቆጣጣሪ፣ የግብር ተቆጣጣሪ፣ የኢንዱስትሪ ተቆጣጣሪ፣ የቢዝነስ ተቆጣጣሪ… የባለሥልጣን ዐይነትና ቁጥር ብዙ ነው።
አንዱ እርከንና አንዱ ባለሥልጣን የቢዝነስ ስኬት በይሁንታ ቢመለከት እንኳ፣ ሌሎቹ “ይሁንለት” ብለው ያልፉታል ወይ?
በአንዳች ተአምር እንቅፋቶችን እያሸነፈ በዕድገት የሚገሠግሥ የቢዝነስ ሰው ቢኖርስ? የመንግሥት ተቋማት ባያሰናክሉትስ? ያኔ… ሁሉም ነገር አማን ይሆናል ብላችሁ እንዳታስቡ!
ማንም ከጓሮ የተነሣ ዶሮ አርቢ በዓመታት ጥረትና ትጋት ስኬታማ ሲሆን… እኛ ዝም እንለዋለን? ሕዝብ ዝም ብሎ ያየዋል?
“አናደንቀውም ወይ?” ማለቴ አይደለም። ወይ ማድነቅ! ከነጭራሹ ገና ከመነሻው አሰናክለን አናስቀረውም ወይ ማለቴ ነው። ስኬታማ ከሆነኮ በደለኛ ሆኖ ነው የሚታየን። “ምን ተጠቀምን? ምን አተረፍን?” ብለን ከማሰብ ይልቅ፣ “አተረፈብን! ተጠቀመብን!” የሚል ክፉ ስሜት የሚፈጠርብን አይመስላችሁም?
እዚህ ላይም ነው ችግሩ።
ገና ከመነሻው በብዙ ዓመታት ጥረት እያደገና እየተስፋፋ የሚዘልቅ የቢዝነስ ሰው ወይም የቢዝነስ ድርጅት በኛ አገር ብዙም አልተለመደም። ኢትዮጵያ ውስጥ ድንቅ ሰዎች የሉም ማለቴ አይደለም። አሉ። ግን ምን ዋጋ አለው? ፈተናቸው ብዙ ነው።
በአንድ በኩል በአርአያነት የሚጠቀስ “የቢዝነስ ልምድና ባሕል” ብዙም የለም። በትንሽ ማሳ የሚካሄድ አነስተኛ የእርሻ ሥራና አነስተኛ የንግድ ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም የተለመደ ሙያ ነው። ብዙ ምዕተ ዓመታትን ያስቆጠረ ባሕል ነው ማለት ይቻላል። ጥሩ መነሻ ነው። በሰፊው እያመረተ በሰፊው ለገበያ የሚያቀርብ ቢዝነስ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም ታሪክ የለውም።
ይህም ብቻ አይደለም። በቢዝነስ ተቋም አማካኝነት የሚካሄድ የፋብሪካ ሥራም ሆነ የእንስሳት እርባታ፣ ከሌሎች የንግድ ሥራዎች ይለያል። ይከብዳል። ዕለት በዕለት ፋታ አይሰጥም። በትጋትና በጥንቃቄ የማምረት የቢዝነስ ሙያ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሣ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እስከዛሬ ብዙም የማደግ ዕድል አላገኘም።
ወይ በጥቂት ዓመታት ውስጥ መክኖ ይጠፋል። ወይም ደግሞ ዕድገቱ እየተገታ በዐጭር ይቀራል።
ይህን አስቸጋሪ ታሪክ ለመሻገር በጥንቃቄ የሚተጉ የሙያ ሰዎች ቢኖሩ እንኳ፣ ብዙ እንቅፋት ይገጥማቸዋል። የፋብሪካ ሥራና የእንስሳት እርባታ የመንግሥት ቁጥጥር የሚበዛበት ሥራ ነው። ለነገሩ የቢዝነስ ፈቃድ ማስመዝገብ እንኳ እጅግ ከባድ ዐቀበት ስናደርገው አልነበር?
ቢመዘገብም ግን፣ የሥራ ቦታ ማግኘት መከራ ነው።
እንደምንም ሥራውን ከትንሽ ጀምሮ ቀስ በቀስ እየተሳካለት ትርፋማ ቢሆንም እንኳ፣ የታክስ ክፍያው ቀላል አይደለም። በአውሮፓና በአሜሪካ በጣም ስኬታማ የቢዝነስ ድርጅቶች የተመሠረቱትና ጠንካራ የቢዝነስ ልምድ የገነቡት፣ “የገቢ ግብር፣ የሽያጭ ታክስ”… ምናምን ሳይኖር በፊት ነው።
የዘመናችን ትልቁ የሥጋ ኩባንያ በተፈጠረበት ጊዜ፣ የታክስ ክፍያዎች ከ5 ወይም ከ10 በመቶ አይበልጡም ነበር። ብዙም አይከብድም። ስለማይከብድም፣ ታክስ ላለመክፈል ሕገወጥ መንገዶችን የሚሞክር ወይም ወደ ኮንትሮባንድ የሚያዘነብል ሰው ብዙ አይኖርም። ከሞከረና ካዘነበለም አይቀናውም። በጥቃቅን የመኖሪያ ቤት እርባታ ላይ ተወስኖ ይቀራል።
የታክስ ክፍያዎች የማይከብዱና የማይጎዱ ከሆነ፣ ድብብቆሽ ምን ያደርጋል? በግልጽ መሥራት እንጂ። በዚህም መንገድ ነው ጠንካራ የቢዝነስ ልምድና ባህል የሚፈጠረው።
ዛሬ ግን፣ በየአገሩ የታክስ ሸክሞች በላይ በላዩ እየተደራረቡ ከብደዋል። በአውሮፓ አገራት የታክስ ክፍያዎች ከ20 በመቶ አልፈው፣ 30 በመቶም ተሻግረው፣ ከ40 በመቶ በላይ ሆነዋል።
ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ድሀ አገራትም፣ ከዚህ መጥፎ የታክስ ወረርሽን አላመለጡም። መጥፎነቱ ደግሞ፣ ድሀ አገራት ገና የቢዝነስ ባህልና ልምድ ሳያዳብሩ በፊት በታክስ ወረርሽኝ መለከፋቸው፣ በታክስ ሸክም ራሳቸውን መድፈቃቸው ነው። የፋብሪካና የእንስሳት እርባታ ሥራዎች የዚህ ሸክም ሰለባዎች ናቸው። የቢዝነስ ተቋማት 15 በመቶ የሽያጭ ታክስ አለባቸው። እስከ 35 በመቶ የሚደርስ የገቢ ግብር ታክስም ይጠብቃቸዋል። ቀላል ፈተና አይደለም።
በዚያ ላይ የፋብሪካ ምርት እና የእንስሳት እርባታ ሥራዎች በተፈጥሯቸው በጣም ከባድ ሥራዎች ናቸው። ሀብት ቢኖራችሁ አስቡት። ጥሪታችሁን የዶሮ እርባታ ላይ ከምታውሉ፣ የአስመጪና ላኪ የንግድ ሥራ ላይ ብትገቡበት አይሻላችሁም?
ኤሌክትሪክ እየተቋረጠ አደጋ የሚደርስበት ወይም ሥራ የሚፈታ ፋብሪካ… ኪሳራው ቀላል አይደለም። የእንስሳት እርባታ ማዕከላትና የሥጋ ማቀናበሪያ ተቋማትም በጣም አስተማማኝ አይደሉም። ለበሽታ ወይም ለጥቃት ይጋለጣሉ።
ታዲያ የጅምላ ንግድ አይሻላችሁም? ሸቀጦች “ቋሚ ንብረት” ስላልሆኑ፣ ለአደጋ የመጋለጥ ዕድላቸው ትንሽ ነው።
በዚያ ላይ፣ መንግሥት የሆነ አዲስ ሕግ፣ አዲስ ክልከላና ቁጥጥር ካመጣ፣ የንግድ ሥራችሁን በፍጥነት መቀየር ትችላላችሁ።
የዘይት ንግድና የዘይት ፋብሪካ ልዩነታቸው የትና የት! መንግሥት በዘይት ገበያ ላይ የዋጋ ተመን ቢያወጣ፣ ዘይት አስመጪዎች እሱን ትተው ወደ ሌላ መዞር ይችላሉ። የዘይት ፋብሪካ ግን ወደ ምን ይዞራል? ቀልጦ ይቀራል እንጂ። ወይም ዝገት ይበላዋል።
የአስመጪና የላኪ ንግድ በጣም ቀላል ሥራ ባይሆንም፣ ከፋብሪካና ከዶሮ እርባታ ጋር ሲነጻጸር ግን ቀላል ሥራ ነው። ሕንጻ ገንብተው ለማከራየት ቢሞክሩስ? አዎ፣ ሕንጻው ጥሩ አስተዳዳሪ ይፈልጋል፤ ክትትልና ዕድሳትም ይኖራል። ነገር ግን፣ እንደ ፋብሪካ አይከብድም።
የኪራይ ሕንጻ አንዴ ከተገነባ በኋላ ብዙ ሠራተኛ አይጠይቅም። ፋብሪካ ግን ብዙ ሠራተኞችና ሙያተኞች ያስፈልጉታል። እንዲሁም የዕለት ተዕለት ጥንቃቄና ትጋት፣ ጥሬ ዕቃዎችና የፋብሪካ መለዋወጫ ቁሳቁስ፣ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስመር… ምኑ ይቆጠራል?
የፋብሪካ ሥራ ወይም የዶሮ እርባታ ቢዝነሶች በብዙ ፈተና የተከበቡ ናቸው።
ይሄን ሁሉ ፈተና አሸንፈው ለስኬት የሚበቁ ጥቂት ሰዎች ቢኖሩ እንኳ፣ ሥራቸውን በየአካባቢው ለማስፋፋት ሲሞክሩ ብዙ ችግር እንደ አዲስ ይገጥማቸዋል።
“ገበያውን እየተቆጣጠረው ነው። እየነገደብን ነው። እያተረፈብን ነው” የሚሉ ቅሬታዎችና ውንጀላዎች መበርከት ይጀምራሉ። ያኔ ማን ያድነዋል? ስንቱን ውንጀላ አስተባብሎ፣ ከስንቱ ጋር ተከራክሮና ታግሎ ይችለዋል?
ከሥራው ይልቅ በየቦታውና በየጊዜው የሚፈለፈሉ እንቅፋቶች እጅግ አሰልቺና አድካሚ ይሆኑበታል።
ምርታማና ስኬታማ መሆን… ፈተና ውስጥ መግባት ነው። ምርቱ ትንሽ እየበዛ ጎላ ብሎ መታየት ሲጀምር… የውንጀላና የቁጥጥር ኢላማ ይሆናል።
ትንሽ ገበሬ ወይም ትንሽ የሸክላ ሥራ ብዙም ቁጥጥር የለበትም። የዋጋ ተመን አይታወጅበትም። “ከዋጋ በላይ ትሸጣለህ” ተብሎ ቤቱ አይታሸግበትም። አይታሰርም። ቢዝነሱ ትልቅ ከሆነ ግን፣ ባይታሰር እንኳ ከቁጥጥር አያመልጥም። የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ስንት ዐይነት የዋጋ ቁጥጥር፣ ስንት ዐይነት የሽያጭ ገደብና የኮታ መመሪያዎችን እንዳስተናገዱ ማስታወስ ትችላላችሁ።
በእርግጥ፣ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ከምንዛሬ ለውጥ ጋር ተያይዞ የመንግሥት የዋጋ ቁጥጥርና ወከባ ቢበራከትም፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥት ከአላስፈላጊ ቁጥጥሮች ቆጠብ ለማለት ያሳየውን ጥሩ ጅምር ለመዘንጋት አይደለም።
ወደፊትም ቢሆን ከአላስፈላጊ የዋጋ ተመኖችና ቁጥጥሮች እየተቆጠበ ከቀጠለ፣ በአንድ በኩል የአገሪቱን ገበያ ከመረበሽ ይድናል፤ በሌላ በኩልም ለአምራቾች በተለይም ለፋብሪካዎች እንዲሁም የዶሮ እርባታ ለመሳሰሉ ኢንቨስትመንቶች የሚያመች የተረጋጋና አስተማማኝ አገር ለመፍጠር ይረዳል።
በዐጭሩ፣ እንደ ኢንዱስትሪ ሥራ፣ የእንስሳት እርባታም ለአገር ኢኮኖሚና ለዜጎች ኑሮ እጅግ ወሳኝ መሆናቸውንና የዚያኑ ያህልም እጅግ ከባድ ሥራዎች መሆናቸውን ከተገነዘብን፣ በተቻለ መጠን ሁሉንም እንቅፋቶች ለማስወገድ በትጋት እንድንጥር ሊያነሣሣን ይችላል። አለዚያ ብዙ ስኬቶች በጅምር ተቀጭተው ይቀሩብናል።
Saturday, 24 August 2024 19:39
ዶሮ ወጥ ይኑር፤ የዶሮ ፋብሪካ ይጨመርበት
Written by ዮሐንስ ሰ.
Published in
ነፃ አስተያየት