- "በጽናት እንታገላለን"
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በትናንትናው ዕለት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተደረገውን ሹምሽር ነቅፏል። ድርጅቱ ነቀፌታውን ያሰማው ዛሬ ማለዳ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር በጻፉት ደብዳቤ ላይ ነው።
በደብዳቤው ላይ ህወሓትን ለማፍረስ ጥረት "ያደርጋሉ" ያላቸው ግለሰቦች በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁሞ፣ "ይሁንና በውጭም ሆነ በውስጥ ድርጅቱን ለማፍረስ ያደረጉት ጥረት ባለመሳካቱ፣ ድርጅቱ በጊዜያዊው አስተዳደር ውስጥ የተሰጡትን ስልጣኖች ከሕግ እና የተቋም አሰራር ውጪ የመንጠቅ ስራ አጠናክረው ቀጥለዋል" ብሏል። "የሕዝባችንን፣ የድርጅታችንን እና የፖለቲካችንን አንድነት ለመጠበቅ በትዕግስት እና በተቋማዊ አሰራር ስንታገል ቆይተናል" ያለው ህወሓት፤ "ዕለታዊ አዋኪ አጀንዳ በመፍጠር ሃላፊነት ላይ መቆየት የፈለጉ" ሲል የጠራቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች በዞን አመራርነት ደረጃ የሚገኙ የህወሓት አባላትን ከስልጣን ማውረዳቸው ገልጿል።
አያይዞም፣ "ይህ ድርጊት ህወሓትን ከስር መሰረቱ ነቅሎ የመጣል የተቀናጀ ዘመቻ ነው። በአንድ ወገን ብቻ የሚደረግ ሹምሽር ተቀባይነት የለውም" በማለት ነቀፋውን ያቀረበው ድርጅቱ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ መዳቢነት የተሾሙ አመራሮች በስራ ቦታቸው ላይ ሆነው ስራቸውን መስራት እንደማይችሉ በአጽንዖት አመልክቷል። "በአንድ ወገን እየተደረገ ነው" ያለውን ድርጅቱን የማፍረስ እንቅስቃሴ "በጽናት እንታገላለን" ብሏል።
ህወሓት 14ኛ ጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባዔውን ማካሄዱ ተከትሎ፣ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የድርጅቱ ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል "የራሳችንን አመራር በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ መመደብ እንችላለን" ሲሉ "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተው ነበር። ይሁንና በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና ህወሓት መካከል የሚስተዋለው ፍትጊያ እያየለ ቢመጣ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እንደማያመሩ መግለጻቸው ይታወሳል።
ትናንት ከሃላፊነታቸው የተነሱት በጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባዔው በፖሊት ቢሮ አባልነት የተመረጡት ወይዘሮ ሊያ ካሳ ሲሆኑ፣ የደቡብ ምስራቅ አስተዳዳሪ ነበሩ። በእርሳቸው ምትክ የእንደርታ ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ፀጋይ ገብረተኽለ መሾማቸውን ፕሬዝዳንት ጌታቸው ትናንት በጻፉት ደብዳቤ ጠቅሰዋል።