ዛሬ
ፀጉሩ ላይ ሽበት ጣል ጣል አድርጎበታል፡፡ ሰውንቱ ኮስምኗል፡፡ እድሜ ተጫጭኖታል፡፡ በርግጥ 13 ዓመት ቀላል ጊዜ አይደለም፤ ያውም ከርቸሌ፡፡ የከርቸሌ እስረኞች በሙሉ ሸሪኮቹ ናቸው፡፡ የሰው መውደድ አለው፡፡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፤ ’ዘኔ‘ እያለ ያቆላምጡታል፡፡
ጨዋታ ያውቅበታል፡፡ ዘነበ ካለ እስረኛው ባይበላ ባይጠጣ ግዴለውም፡፡ የእርሱን ቀልድና ጨዋታ ሲኮመኩም መዋል ነው፡፡ አዳዲስ እስረኞችን የሚያለማምደውም ዘነበ ነው፡፡ የታሰሩበትን ምክንያት ይጠይቃቸዋል፤ ወንጀላቸውን ይናዘዙለታል፡፡ ሁልጊዜም የእርሱ እስር ከሌሎቹ እንደሚለይ ያስባል፤ በዚህም ይፅናናል፡፡ ሦስት አመት እንኳ ያልሞላውን ትዳሩን ጥሎ ዘብጥያ የወረደው፣ ሲያጭበረብር ወይም ሲሰርቅ ተይዞ እንዳልሆነ ሁሌም በኩራት ይደሰኩራ፡፡ እኔ የታሰርኩት ይላል ዘነበ፣ በጣቶቹ ወደ ራሱ እያመለከተ፤ “ለውሻዬ ፍቅር ስል ነው!” ከዚህ አልፎ ግን አንድ ቃል እንኳ አይተነፍስም፡፡ በዙሪያው የሚኮለከሉት እስረኞች፣ የዚህች አባባሉን ምስጢር ቢነግረን እያሉ፤ “እንዴት?” “ለውሻህ… ምን?” በሚሉ ጥያቄዎች ያዋክቡታል፡፡ ዘነበ ግን በጄ አይልም፡፡ ከተለመደው ንግግሩ ቅንጣት እንኳ አይጨምርም፡፡ ሁሌም ግን አዳዲስ እስረኞችን ያስለምዳል፡፡ ለነባሮቹ ወግ ያወጋል፤ እየኮመከ ያስቃቸዋል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ነው፣ አስራ ሦስት ዓመቷን ፉት ያደረጋት፡፡
***
የዛሬ 13 ዓመት
አቤል የረዥም አመት ጓደኛው ነው፤ ምስጢረኛው ማለት ይቀላል፡፡ ከዚያም በላይ የወንድሙ ያህል ነው፡፡ የትምህርት ቤት ባልንጀራው ብቻ አይደለም፤ ጭቃ አቡክተው አንድ ሰፈር ነው ያደጉት፡፡ ክፉ ደጉን አብረው አሳልፈዋል፡፡ ዘነበ ሲያገባ ጓደኝነታቸው ቀጥሏል፤ አንደኛ ሚዜው ነበር፡፡ የሰርጉ ሆሆታ ካበቃ በኋላ፣ ቤተኛ ሆኖ የዘለቀው አቤል ብቻ ነው፡፡ የዘነበ ሚስት ለአቤል ትልቅ አክብሮትና ፍቅር አላት፡፡ ሌላው ሁሉ በሆያ ሆዬው ማግስት ድምፁ ሲጠፋ አቤል በወዳጅነቱ ዘልቋል፡፡
ዘነበ ትዳር ከያዘ ሦስት አመት ሞላው፡፡ ባልና ሚስቱ ለልጅ አልታደሉም፡፡ የልጅ ምትክ የሆነችው ፒፒ ናት፤ ድንክየዋ የሳሎን ውሻ፡፡ ዘነበ ፒፒ ብሎ ለፈረንጅ የቀረበ ስም ሲያወጣላት፣ ሚስቱ ግን ምትኬ ትላታለች፡፡ ፒፒ ያደገችው ተሞላቅቃ ነው፡፡ ስንት ሺህ ብር በተገዛ ሶፋ ላይ እየሸናች፣ በፕረሽያ ምንጣፍ ላይ እየተንከባለለች፡፡ መኝታዋ ከባልና ሚስቱ መሃል ነው፡፡ የምትበላው በሰፊው የምግብ ጠረጴዛ ላይ ቂብብ ብላ፣ በሸክላ ሳህን ነው፡፡ የውሻ አመሏ ሁሉ ተቀይሮ የሰው አመል አውጥታለች፡፡ ከቸኮላትና ኬክ በቀር ንክች አታደርግም፡፡ በየሁለት ቀኑ ለሰስ ባለ ሙቅ ውሃና ልዩ መአዛ ባለው ሳሙና ገላዋን ትታጠብና ሽቶ ይርከፈከፍላታል፡፡
አቤል ከጋቢና ወርዶ የኮረኮንቹን መንገድ ሲይዝ፣ ሰዎች ውሻቸውን ይዘው ሲሄዱ ይመለከታል፡፡ ከዘነበ ጋር የተወያዩት ነገር ትዝ አለው፤ የፒፒ ክትባት፡፡ ሰዎቹን ተከትሎ መጨረሻቸውን ተመለከተ፡፡ ከዚያም ወደ ዘነበ ቤት አመራ፡፡ ከእርምጃው ነጠቅ ነጠቅ እያለ ቤት ደረሰ፡፡ ከዘነበ ጋር ተማከረ፡፡ ጊዜ አላጠፋም፡፡ ዘነበ አቤልና ፒፒ መኪና ውስጥ ገብተው ተፈተለኩ፡፡
እድለኞች ነበሩ፡፡ አንድም ሰው ሁሉ አስከትቦ ጨርሷል፤ አሊያም ገና በመንገድ ላይ ነው፡፡ አቤል ፒፒን ታቅፎ ፊት ፊት፣ ዘነበ ኋላ ኋላ ተከተለ፡፡ ነጭ ቀለሙ ወደ አመድማ የተቀየረ ካፖርትና ላስቲክ ቦት ጫማ ያደረጉ ሽማግሌ፣ አንድ ዛፍ ስር ቆመዋል፤ የክትባት ባለሙያ መሆናቸው ነው፡፡ ኑሮ ያጎሳቆላቸው የሚመስሉት ሽማግሌ፣ በመጠጥ ብዛት ጉንጭና ጉንጫቸው በልዟል፡፡ ፊታቸው ላይ ቅንጣት የተስፋ ዘለላ አይታይም፡፡ ጓንት ባጠለቀ እጃቸው ሲሪንጁን ያፍተለትሉታል፡፡ መርፌውን ለመውጋት የቸኮሉ ይመስላል፡፡
“ውይ ምን ትመስላለች!” አሉ፤ ትንሿን ውሻ በርበሬ በመሰለ ትላልቅ አይናቸው እያስተዋሉ፡፡
“ወዲህ አምጣት!” አሉ አፍጥጠው፣ ትግስት በጎደለው አነጋገር፡፡
ዘነበ ትንሽ ወደፊት ተጠጋና፤ “ያማት ይሆን?” አለ ለአቤል፤ በሹክሹክታ፡፡
“ያማት ይሆን?” ሽማግሌው በረዥሙ እየሳቁ - የለበጣ ነበር፡፡
“ወዲህ በል ባክህ፣ ወረፋው እየበዛ ነው!”
አቤል ፒፒን እንዳቀፈ ወደ ሽማግሌው ተጠጋ፡፡ ፒፒ ፈርታለች፡፡ ሰውነቷ ሲንቀጠቀጥ አቤልን ነዘረው፡፡ ነጫጭ ብይ አይኖቿ ወዲህ ወዲያ ተንከራተቱ፡፡ አቤል እንደ ማባበል በአንድ እጁ ፀጉሯን እያሻሸ፣ በሌላ እጁ ወደ መርፌው አመቻቻት፡፡ ሽማግሌው የፒፒን የተደራረበ ፀጉር ጓንት ባጠለቀ እጃቸው ገለጥ ገለጥ አድርገው፣ መርፌውን ወደ ፒፒ ሰደዱት፤ ፒፒ እንደ አራስ ልጅ እሪ ብላ አለቀሰች፡፡
“የኛ መድሀኒት የዋዛ መሰልዎት!” አሉ ሽማግሌው፡፡
“እንዴት?” ጠየቀ ዘነበ፡፡
“ክንችር ነዋ!”
“ማለት….?”
አካባቢው ግራ በመጋባት ስሜት ተሞላ፡፡
“ድብን ነዋ! አያዩትም ልውሽ የለም እኮ!”
እውነትም ፒፒ ተዝለፈለፈች - ብዙም ሳትቆይ አሸለበች፡፡
ሽማግሌው በኩራት ሰፋ ሰፋ የማለት ስሜት ይታይባቸዋል፡፡ አቤል የሚወዳትን ውሻ በድን በእቅፉ እንደያዘ ራሱ በድን ሆኖ ቀረ፡፡ ዘነበ ወደ አለማወቅ ስሜት ተሸጋገረ፡፡ በደመ ነብስ ሽጉጡን መዝዞ አወጣ፡፡
***
(ከአዲስ አድማስ የግንቦት 14 ቀን 1996 ዓ.ም ዕትም የተወሰደ)
Saturday, 24 August 2024 00:00
ስለ ፍቅር….
Written by ነቢይ መኮንን ኢዮብ ካሣ
Published in
ጥበብ