Saturday, 31 August 2024 19:39

የዘመን መልክ!

Written by  ነቢል አዱኛ
Rate this item
(1 Vote)

፨ ‹አይዞህ› ‹አይዞህ› ተባብለው፤ ተደጋግፈው የቆሙ ቆርቆሮ ቤቶች ወዳሉበት መታጠፊያ ገባ። ለነገሮች ግድ የሚሰጠው አይመስልም። ፊቱ ላይ የበለዘ ምስል ብቻ ነው ያለው - ቆሳስሏል። ያበጠ ዓይን፣ ደም የደረቀበት ግንባር። የውስጥ ሃዘኑም ፊቱን አጎሳቁሎታል። አንጀትን ለማንሰፍሰፍ በቂ የኾነ ኹኔታ ላይ ነው ያለው። ከተዛዘሉት ቆርቆሮ ቤቶች በአንዱ ያለችዋ ጋ ሄደ። ሠማዩ የሱን ፊት መስሏል - ጠቁሯል። ቀና ብሎ አላያትም። ‹‹አዳር ነው ወይስ...?›› አለችው። መሬት መሬት እያየ ቆሟል። ‹‹አዎ››
‹‹አዳር?››
‹‹አዎ››
‘የፈለኩትን ብጠራ ይከፍላል’ ብላ አሰበች። ‹‹አንድ ሺህ ብር›› ከጓደኞቿ ጋር ተጠቃቀሰች። ‹‹እሺ›› ጓደኞቿ ሳቁ። ግድ አይሰጠውም እሱ።
ወዲያው ሲስማማ ‘ምነው በጨመርኩ!’ አለች። “ሁለት ሺህ ብለው ይከፍል ነበር?”... መልሶ ደግሞ አሳዘናት።
፨ ለቅልጥማም ሁለት የማያራምደው ቤት ቀድማው ገባች። ደብዛዛ ብርሃን ተቀበለው። የቤቱ ሶስት አራተኛ አልጋው ነው። ከቀረው አንድ እጅ ደሞ የምትቀባባው የተቀመጠባት ትንሽዬ ጠረጴዛ፤ ሌላው መቆሚያ። አልጋው ላይ ተቀመጠች። አንገቱን እንደደፋ ቆሟል። ባልተዘጋው በር ጓደኞቿ እያዩ ይስቃሉ። (ከሳቃቸው ጀርባ ቅናት ቢኖርም..) ‹‹በሩን ዝጋው›› አለችው። እጁን ከኪሱ ሳያወጣ በትክሻውና በእግሩ ገፍቶ ዘጋው። በሩን ተደግፎ ቆመ። እዝነቷ ወደ ፍርሃት ሳይለወጥ እንዲቀመጥ ጋበዘችው። በጃኬቱ ውስጥ ከሆዱ ጋር አጣብቆ ይዞት የነበረውን መጽሃፍ ጠረጴዛው ላይ ሲወረውረው፣ ቅባትና ሽቶዎቿ ወደቁ። ሁለቱም እኩል ደነገጡ። መጽሐፉ፤ የሽማግሌው ገጣሚ ፎቶ ያለበት ፊቱን እያሳየ፣ በጀርባው ወደቀ። ከቱታው ኪስ የታሸገ ብር አውጥቶ አሸከማት። ግራ ገባት። ተቀመጠ አልጋው ላይ። ‹‹ምንድነው?›› አለችው። አልመለሰላትም። እየፈራች እንደኾነ ተሰማት። ተነሳችና የወደቁትን እቃዎቿን መሰብሰብ ጀመረች። የጃኬቱን ዚፕ ሲከፍት ይሰማታል። ከፍርሃቷ እስክትላቀቅ አጎንብሳ ቆየች። ስትዞር መለመላውን ቆሟል። ደነገጠች። አሁን እሷን እያየ ነው፤ ፊቱ ላይ ግን ለውጥ የለም - ሃዘን እንዳዘለ ነው። የሷንም ቀሚስ አወለቀች። እጇን ይዞ ከፍ አረገው፦ ‹‹ሥንፈጠር እንዲህ ነበርን። እርቃን ኾነን ተወለድን። አባታችን አደም ሲፈጠር እርቃኑን ነበር፤ ሚስቱም እንደዛው።›› እጇን ለቀቃትና፤
‹‹ቁጭ በይ አኹን›› አላት። ተቀመጠችና ቀና ብላ እሱን ማየት ጀመረች። ‹‹ኹሉም ሰው ሲወለድ አባት እናት አለው አይደል?›› አላት። ‹‹አዎ››.. ፊቱ ላይ ምንም ለውጥ የለም። ‹‹እነዛ እናት እና አባትስ? ወላጅ አላቸው?››
‹‹አዎ››
‹‹ቀጥሎ ያሉትስ?››
ዝም አለች።
‹‹መልሺልኝ!›› ተቆጣ።
‹‹አዎ አላቸው››
‹‹እንደዛ እያለ መጨረሻ ማን ጋ ይደርሳል፤ አደም ጋ። የኹሉም አባት። ሥለዚህ የሰው ልጅ የአንድ ቤተሰብ አባል ኾነ።›› ዝም ብላ እያየችው ነው። ፈርታለች። ‹‹እንዳይበርድሽ ልበሺ ልብስሽን›› አለ። ቶሎ ተነስታ ለበሰችና ተቀመጠች። ‹‹አደም እና ሃዋ ሲወልዱ ሲዋለዱ የሰው ዘር በዛ፤ ተባዛ። ወደ ተለያየ አቅጣጫ ተበታተነ። የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል ኖረው። ግን አየሽ እዚህ ላይ ነው ጥበቡ። የተለያየን ባንኾን አንዳይነት ብንኾን እርስ በርስ እንጨራረስ ነበር። ልዩነታችን ነው የጠቀመን - ለመተዋወቅ እንድንፈልግ አደረገ። እኔ እንደውም እንደሚመስለኝ ወንድማማቾቹ ሃቢል እና ቃቢል የተገዳደሉት አንድ አይነት መኾን ሲሰለቻቸው ነው። ብዙ ቢኾኑ መገዳደልን ጭራሽ አያስቡም ነበር።›› ቤቱን በአይኑ መቃኘት ጀመረ። እሷንም ልብ ብሎ አያት። በልቡ “ኦ ቆንጅዬ!” አለ። እሷ በፍርሃት ተሸብባ ቁጭ ብላለች። እንደምንም ራሷን አደፋፍራ ‹‹አንተስ አይበርድህም? አትለብስም?›› አለችው።
‹‹ኦ! እሺ።›› አለና ለበሰ። ተመልሶ ቆሞ ማውራት ጀመረ። ‹‹ግን በጣም የሚገርመው ለመተዋወቅ መለያየታችን፤ ለመጠላላት ሰበባችን ኾነ። ከነዚህ የአደም ልጆች የበላይ አለ?›› አላት።
‹‹እኔንጃ›› አለች የምትመልሰው ግራ ገብቷት። ‹‹የለም! የበታችሽ አለ? የለም! ሁሉም የአንድ ቤተሰብ ልጅ ነው። እንደነዚህ ቆርቆሮ ቤቶች ተደጋግፈን ምድርን ማልማት ሲገባን ተገዳደልን፤ ተራራቅን።›› ድንገት እግሯ ላይ ወድቆ ማልቀስ ጀመረ። ደነገጠች። የምትናገረው ቢጠፋት ጸጉሩን እያሻሸች አባበለችው። አሳዘናት። ኹለቱም ያለ ድምጽ ማልቀስ ጀመሩ። መጽሐፉ ገጽ ላይ ያለው ሰው እየታዘባቸው ይመስላል። ቀና አለና ትናንት የደረሰበትን እንደ-ተንበረከከ መናገር ጀመረ።››
፨ ጌራ የሚያፈቅራት ፍቅረኛው ነበረች። እሷም የምትወደው። ነፍሱን ሙሉ ይወዳት ነበር። እሷ የምትወደውንም ይወድ ነበር። ግጥም እና ቴአትር ትወዳለች። ከትምህርት መጽሐፍ ውጪ የማያውቀው ለሷ ሲል መጽሃፍ ቀበኛ ኾነ። የጸጋዬ ገብረመድህን አድናቂ ናት። እሱን በጣም ከመውደዷ የተነሳ በሱ መቅናት ጀምሮ ነበር። እሷ የሰጠችው ስጦታ የጸጋዬ ታሪክ ያለበትን መጽሐፍ ነው። እንደሚጋቡ ተነጋግረው፤ ብዙ እቅድ ይዘው ተለያዩ። በምን? እናቷ ጠርተውት ‹‹ልጄ አንተ ጥሩ ልጅ ነበርክ። ባሏ ብትኾን ደስ ይለኝ ነበር። ግን የኛ ብሄር እና ያንተ.. አንድ አይደለም። እናም አባቷ ለሃገሯ ልጅ ሊድራት አስቧል።›› አሉት። በቃ በዚህ ምክንያት ተለያዩ። በጣም አዘነ።
“ፍቅርን ፈራን መቀራረብ ፈራን
እንዳልተዛመድን እንዳልተዋደድን
ፈርተን መዋደድን ጉርብትናን ናድን
እኛነትን ትተን እኔነት ለመድን።”
የሚለውን ግጥም ‹አንብብልኝ› ስትለው የነበረችው እሷ ነበረች። እሷ የሰጠችው መጽሐፍ ትታው ለሄደችበት ሃዘኑ መተከዣ ኾነው።
፨ <<እሳት ወይ አበባ>> ቴአትር ይታያል በተባለ ሰዓት ኹሉ ያቺን መጽሐፍ አንግቶ ይጓዛል። አስር.. አስራአምስት... ሃያ ጊዜ አይቶታል። ዕድሜው እና ጉልበቱ በፈቀደ ኹሉ መቶ... ሺህ ... ሚሊዮን ጊዜ’ም የማየት ተስፋ ነበረው።
፨ ትናንት፤ ቴአትሩን አይቶ ወደ ቤቱ እየተመለሰ ነው። አምሽቶ ነው ሰፈር የደረሰው። የሰፈሩ ፈታሾች ያዙት።
‹‹ሥምህ ማነው?›› አለው፤ ከከበቡት መሃል አንዱ። ነገራቸው።
‹‹የአባትህስ?›› መታወቂያውን እየተቀበሉት።
‹‹መሃመድ ሁሴን በላይ››
‹‹ዋው! የበላይ ልጅ ነሃ?››
ዝም አለ። ‹‹እስኪ የያዝከው ምንድነው›› ጠየቀ ሌላኛው። አሳያቸው።
‹‹እሳት እና ውሃ ነው የሚለው?››
‹‹አዎ›› የመጽሐፉ የገጽ ሽፋን ላይ ያለው ሰው እንዲታየው ባትሪ አበራበት።
‹‹ኦ! ጸጋዬ ገብረመድህን!›› አለ። ሌሎቹ ፈታሾች ተቀብለውት፤
‹‹አዎ! የአንቦው ጸጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ ሮባ!››
‹‹አንተ ከየት ነህ፤ የበላይ ልጅ ከአንቦ ነህ?››
‹‹አይደለኹም››
‹‹ከየት ነህ? አትመልስም!›› ቆጣ አለ አንደኛው
‹‹ከኢትዮጵያ››
‹‹ሃሃ..ከኢትዮጵያ። ኢትዮጵያ የት ክልል?››
‹‹በቃ ኢትዮጵያ። ክልል የለኝም። የተሰመረ የታጠረ ቦታ አልተወለድኩም። ከኢትዮጵያ ነኝ!››
( “ፍቅርን ፈራን ጥላቻን ሰራን ብቸኝነትን ጠራን
በጋራ ቤታችን ድንበር አጥር ሰራን።”)
ትዕዛዝ ባለመሰማቱ ማጉረምረም ጀመሩ። ‹‹የእናትህ ሥም ማነው?››
‹‹ሃዋ››
‹‹ሃዋ ማን?››
‹‹ሃዋ ፈጣሪ››
‹‹ፈጣሪ? ምንድነው የምታወራው?››
‹‹የአደም እና ሃዋ ልጆች ነን! ኹላችንም ወንድማማቾች ነን!›› ለሚጠይቁት ጥያቄ የሚመልስላቸው መልስ አልገጥም አላቸው።
‹‹ማንም ከማንም አይለያይም። ኹላችንም የአንድ አባት እና እናት ልጆች ነን››
‹‹አይደለንም!›› አለ አንዱ
‹‹ብሔር፣ ዘር የሚባል መከፋፈያ የለም!››
‹‹አለ!››
‹‹የለም!››--ተጣሉ በዚህ።
( “ መወያየት ጠላን መነጋገር ጠላን
መደማመጥ ጠፍቶ መነቋቆር በዝቶ
መናናቅ በርክቶ
መመካከርን ስንረሳ መከባበርን ስንረሳ
እጃችን በወንድማችን ላይ ዱላ አነሳ” )
፨ እግሯን አቅፎ ሲያለቅስ አነሳችው።

 

Read 124 times