ራሺያ በጎጎል ካፖርት ውስጥ የተደበቀች ሀገር መሆኗን በስነ ፅሁፍ አለም መረዳት ከቻልን፣ የአፍሪካውያንን ብሎም የኢትዮጵያን ዘለሰኛ የኑረት ማህተም የምንፈትሸው ከተሰዳጅ የእግር አሻራው መሀል ቢሆንስ?
ከሚስጥራዊ የመቃብሮቻችን አፈር ላይ የበቀለ የአፀድ ቅርንጫፍ ላይ ያረፉ ወፎች እንዴት ለእኛ የሚሆን ዜማ አጡ? ታሪካችን ሁሉ ሲሄዱ ሲሄዱ መንገድ ላይ አለቁ እንጂ መንገድ አለቀ የሚል መደምደሚያ አለው?
መግቢያ
ሀገር የህልመኞች ውጥን ናት። የሩቅ አሳቢ ተጓዦች ምጥንም ጭምር..! የሚመጣው ትውልድ የሚመጣው፣ የሄደው ትውልድ በረገጠበት የእግር ዳናው ስፍር ነው። ታሪካችን በሰርዶ ሳር መሀል እግር እንዳበጀው ቀጭን የገጠር መንገድን ይመስላል። ሀገር፤ ሁሉ በዘፈቀደው የብርሃኑ ጭልታ የቸገረው ምንደኛ የሚጨልጣት ፅዋ ሳትሆን፣ ጥሙን እያስታመመ ለመጪው ትውልድ የሚቆጥባት የመቀነት ዳሩ እውነት ነች። ልቦና ካላዛለው የእምነት ሸክም የተገነባ ማህበረሰብ፣ ቤቱን እያቃጠለ ክረምቱን ልወጣ አይልም። አብሮ መቆም የሚሰጠውን ደጀን በመነጣጠል፣ ጦርና ጎራዴ አይበትነውምና..!
ሀሳብ፤ እነዚህን ተሻጋሪዎች ለማሻገር የምንጠቀምበት ስሁት ድልድያችን ነው። ከሀሳብም ሀሳብ.. ከድልድይም ኪነት!
”ሲጥል“ የአርአያችን፤ የዘመኑ ትሁት አባት፤ የትውልድን ሸክም ብቻውን በመወጣት የሚታትረው ሰው ረጅም ልቦለድ ነው። በስደተኛ የገፀባህሪያት ዶቃ ክሩን ውበት እያደረገ የሰፋልን ውብ ጌጥ..! መፅሐፉን በ280 ገፅና በ14 ምዕራፍ እንዲሁም በ98 ንዑስ ርዕስ ከፋፍሎ አቅርቦታል።
ከጀርባው ላይም እንደተገለፀው አደራደራቸው የጃዝ ሙዚቃን ቅርፅ የተላበሱ ናቸው። ንዑስ ርዕሶቹ ስር ያሉ ተረኮች ብቻቸውን ሲሆኑ ትርጉም የሚሰጡ፣ጠረን ያላቸው፣ ነጠላ ህይወት የተቸሩ መዳረሻዎችን ያቀፉ ሲሆን፤ በምዕራፍ ሲገመዱ ደግሞ ህብረ ዝማሬ ሆነው ቀጣዩ ጣዕምስ ምንድነው የሚያስብሉ ናቸው።
ስድሩ በአማርኛ ፊደላት ከሀ ማለዳ እስከ ቀትር (ምሽት)ነ የፊደል ድርድር ሽሩባ ይመስል የወረደ መልካ ነው። ( ከሀ እስከ ነ ያሉት ፊደላት እንደ ምዕራፍ ሲያገለግሉ ምንዝር ፊደላቶቹ ((ከሀ - ሆ)) ያሉት በንዑስ ርዕስነት ያገለግላሉ።)
እርስ በርሱ የተሳሰረበት ገመድ፣ ለአንባቢው ረፍት ነሺና ወደፊትም አንደርዳሪ ነው። የአተራረክ ዘይቤውን በተመለከተ ወይም የቀለም ጥላውን ስያሜ ስለካ፣ በግሌ ይሄን መፅሐፍ በሁለት እከፍለዋለሁ። ይኸውም ዐሊይ መንደር እስኪገቡ ያለው ምዕራፍ ስነ ፅሁፋዊ ስልቱ ቦታን ፤ ሁኔታን ጊዜና ዕይታን በተባ ብዕሩ ለመግለፅ የሞከረ ብሎም የተሳካለት ሲሆን፤ ከዐሊይ መንደር ትውውቅ በኋላ ምናልባትም እስከመጨረሻው አዳዲስ ክስተታዊ ፣ ምልሰታዊና ሀሳባዊ የቅርርቦሽ ቁጭቶችን ያጣመረ ይመስለኛል። ልክ እንደወገብ መቀነት ቁጥር ፈታ ሸምቀቅ ደግሞም ቁጥር የሚለውን የፍሰቱን ማዕድ ከብቦ የተቀመጠ ልብ፣ ገና ቡራኬ ፀሎቱ ወገቡ ላይ ሳይደርስ በመስገብገብ እጁን ከመስደድ አይሰንፍም።
ደቂቅ የተፈጥሮ ሁነታዊ በረከቶችን አኳኳል ቅሽር ካለው የገለፃ መደብ ስር ስደረድረው በረሃ በዋለ ገላ ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሶ ከሙቀቱ ምጡ የመገላገል ያህል ነው።
(እንኳን ማሪያም ማረችን..!)
ሀ. የጅምር ፣ የርዕስና የሽፋን ስዕል ኪስ
ሲጥል ሲጀምር (ሊጥል ሲጀምር) የተለያየ የአኗኗር እይታና የህይወት ልምድ ያላቸው 10 የማይሞሉ ሰዎች፣ እንደተማከረ መንደርተኛ ካሉበት ሀገር ተነስተው፣ ንጋቱን ወደ አንዲት የገጠር ከተማ ለመሄድ ሌሊቱን ወጥነው አደሩ። መሄጃቸው ሲደርስ ግን ገሚሱ መኪና ያመልጠኛል ብሎ እንቅልፍ በዐይኑ ውልብ ሳይልበት ሲነጋ ሌላው በተቃራኒ የወደቀበት ሳይታወቀው ያነጋ ሆነ። ዘውትር ለእንጀራቸው ደርሰው ከሚመለሱት ከሾፌሩ፣ ከረዳቱና ከአንድ ሰው (ከሀዋ) በቀር ሁሉም ለሚሄዱበት ሀገር እንግዳ ናቸው።
ጉዞውን ሲጀምሩ እንዲህ ሆነ። መንገዱ አልፎ አልፎ ሰላም እንደሚርቀው ሰሙ። የግጭት ቀጠና በመሆን ባለመረጋጋት ጮጮ እንደሚናጥም ደረሱበት። ያሉት አልቀረምና አሰልቺውን የገጠር መንገድ አገባደው ልክ ወደ ከተማዋ ሲቃረቡ የምን መንገድ የምን ጉዞ ተባሉ። ምነው ቢሉ፤ «ጦርነት ተነስቶ» እህሳ ቢሉ «መንገድ ተዘጋ።!» (ወይ ጣጣ!) ታዲያስ ምን ይሻላል ቢሉ መካሪው ጎበዝ፤ «እፊት ለፊታችሁ አንዲት መንደር አለች፤ እዛ ግቡና ምትሹ ፀልዩ ማትሹ ደንሱ!» ተባለ። ሄዱና ገቡ። ዐሊይ የምትባለውን ወርቅ መንደር ስጋት ቅሞ ያመነዠከ፣ ዙሪያ ገባውን በግራ መጋባት በሚገላምጥ ልባቸው ተዋወቋት። እንግዲህ መፅሐፉ እኚህ ስደተኛ መፃጉዕ ተስፈኞች፣ ከዛሬ ነገ መንገዱ ተከፍቶ ወዳሰብንበት እንሄዳለን ባሉበት መንደር፣ ለድፍን 21 ቀናት የቆዩበትን የአብሮነት፣ የውጣውረድ የአስደንጋጭ ሚስጥራዊ ሁነትና ማንነታዊ የትግል አሳራቸውን ያዩባት ክታብ ነው።
ዐሊይ በብዙ ነገሯ የግርምት ደብር ነች። ሁሉ ተሟልቶ እንደተሰጣት ልጃገረድ ታሳሳለች። ተጋደሉብኝ ተጋደሉብኝ የምትል ትመስላለች። (ግን አትልም።) ለሁሉ ተብቃቅታ የተበጀች የልበ ብርሃኖች፤ የእግረ እርጥቦች ሰፈር....
ሰውን እንደ ሰው መቀበል በሚችል በፅኑ ፍልስፍና ላይ ቆማ ሳገኛት ጦርነቱ ቀጥሎ የልቦለዱ ዓብይ ሁነት እዚሁ እንዲከወን ወደድኩ። አላሳፈረችኝም። እዝነ ልቦናዬም ሌላ መንደር ሳያይ ተደመደመ። ዐሊይ የብዙ መልካም ልማዶችና ደንቦች ውጤት ናት። ማህበረሰቡ ይህቺን መንደር ለማቆም የተራመደበት እያንዳንዱ የእግር ዳና ፡ ይዞ የመጣው ለውጥና በረከት የተጓዦችን ልብ በማኖህለል እዛው ለማስቀረት የቋመጠ ነው። ሰው የተስፋ በካሩን የህልም ደብሩን ሲያገኝ በእፎይታ ታዛ አርፎ የመጣበትን ብርቱ የመንገድ ቀበኛ፤ ከእረፍቱ ሸንጎ ስር ረታሁ ሲል ይሟገታል። በረታሁ ሲል ይተዝታል።
እውን እነኚያ ገፀ ባህሪያትስ ሆነ አንባቢ ለዚያች መንደር እንግዳ መሆን ይቻለዋል?
እኔ ግን አይመስለኝም።
ርዕስ
ተግ ብዬ ሳስብ ርዕሱ አሟልቶ መጽሐፉን ለመጠቅለል ከሚሰጠኝ ትርጉም በላይ በግምት ያስተሳሰርኳቸው ገመዶች ይህን አይነት ጅራፍ ሊሰሩልኝ የሚችሉ ይመስለኛል።
ገመድ አንድ፦ ሀዋ ሲጥልባት መርጌታ ሐብቱን ትጠራጠራለች (ትቃወማለች)
ገመድ ሁለት፦ ምንተስኖት ሲጥልበት ስብሰባቸውን አይወደውም፤ ሁሌ ንጡል ነው።
ገመድ ሶስት፦ መርጌታ ሀብቱ ሲጥልባቸው፣ አንተነህን ይጠራጠሩታል
ለመጠቅለል ያህል፣ በዚህ ልቦለድ ተረክ ውስጥ እንደታሪክ የተሰባሰቡበት መንገድ ተማክረው ወጥነው በወጡበት ጉዞ ሳይሆን፣ እግር ጥሏቸው የተገኙ መንገደኞች ናቸው። እግር ሲጥል እንዲህ ያለ ቤተሰብን ያስመሰርታል። ያጣነው ልብ ለልብ መገናኘቱን አይደል?
በሲጥል ውስጥ
- ፍቅር ሲጥል አብሮነትን ፣ መሰብሰብን ፣ መዋደድን ከየተጓዡ ጉያ አይተናል።
- ህይወት ሲጥል መዳንን ፣ ማበብን ፣ መተሳሰርን አግኝተናል።
በምትኩም
- ሞት ሲጥል ምንተስኖትን አጥተናል።
የልቦለዱም ዓብይ ጥላ በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ በተጣለ የብርሃንና የትኩስ የጉዞ ተስፋ የሚደመደም ነው።
የሽፋን ስዕል
የበዛ የእግር ዳና መንገዱ ላይ ይታያል። ከወዲያ የአንድ ሰው ጥላ ተርታ ሰርቶ ቆሟል። ከወዲህ ባለቤት የሌለው የወጣት ልጅ ጫማ ተቀምጧል። ጫማው አላረጀም። አላደፈም፡፡ ገና ያልተኼደበት ድባብ አለው። ሊኖር ሲያስብ የሞተን ትውልድ ህይወት የሚወክል መስሎ ታይቶኛል። በውስጡ ካሉ ገፀ ባህሪያት በዘመንም በፋሽንም ይኼ ጫማ የሚወክለው ምንተስኖትን ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ምንተስኖት ወጣትነትን ማጣጣም ቸግሮት የሚጠብቀውን እልፍ ድንግል መንገድ ሳይገረስስ የወደቀ ገፀ ባህሪ ነው። የህፅናዊነት (Absurdism) አመለካከት ተራማጅ የሆኑ ባህሪዎች በብዛት የሚስተዋሉበት ሲሆን፤ በህይወት ትርጉም አልባነት የዳከረ ኋላም ራሱን በማጥፋት መፍትሔው መገላገል እንደሆነ እምኖ ሞትን በራሱ ላይ ያወጀ ነው።
ለ. ውክልና በአሊጎሪካል የአተራረክ ኪስ ውስጥ
¹ ሀሳብ በሀገር ድር
ተጓዦቹ ይዘው የተነሱት ሀሳብ ወይም ህልም በሀገር ይመሰላል። እያንዳንዱ ሰው የሚጓዘው ድኅነትን ፤ ማግኘትን ፤ ማረፍን ፤ ሰላምንና ፀጥታን ፈልጎ ነው። ከተስፋ ታሪካችን ዳርቻ ላይም ኢትዮጵያ የምትጠብቀው አካል እንዳለ በተለያየ መንገድ ቢገለፅም፤ እሷ ግን ከመጠበቅ ይልቅ ሄዶ ማግኘትን ምርጫዋ ያደረገች አይመስለኝም። በዚህ ውስጥ እያንዳንዱ ተጓዥ የያዘው ሀሳብና ትልም በሀገር እንደተመሰለ አስባለሁ። ሆኖም ግን በመፅሐፉ ውስጥ እንደምንመለከተው፤ ትርክት በወለደው የዘመን አረም እየተጠለፈች ማደር ከሚገባት ይልቅ በማይገባት ላይ በማደር ትማስናለች። ሩቅ አስባ ቅርብ ማደሯ ከመፈክርም አልፎ ሩቅ እያሰበች ቅርብ እያደረች፣ መድረሻዋን የዘነጋች በሚመስል ውጥንቅጥ ውስጥ የተዘፈቀች ይመስለኛል።
² መኪና በእሴት ድባብ ስም
መኪናዋ በዘመኑ የደረስንበትን ኢትዮጵያዊ የባህል እሴቱን ትወክላለች። መኪናዋ በመፈብረኪያዋ አልያ በመሰሪያ ዘመኗ እንደ አዲስነቷ የጤና እክሎች ያልገጠሟት ... ሰላሟ ያልተናጋ አካሏ ሽባ ያልሆነ ነው። ይህ የየትኛውም አዲስ መኪና ጠባይ ነው። ሁሉም ነገር ገር የሚሆንበት ሰሞን አለ። እየቆየ ግን ሁሉም ይከዳል። በሩም አልታዘዝ ይላል፤ ለመነሳት ትለግማለች። ሌላም ሌላም ...
በዚህ የልቦለድ ድርሰት ውስጥም እሴትና ባህልን በአሊጎሪካል የአተረጓጎም ዘዴ የገባችው መኪና ጠባይም ይኸው ነው።
ልክ ታሪኳ ሲጀምር ነዳጅ ለመቅዳት በሚል ሰበብ ተሳፋሪዋን ስታጉላላ ትስተዋላለች። እንደመጣችም መምጣቷን ያዩ ተጓዦቹም ቀጣይ የስንብታቸው ምዕራፍ ከእሷ ጋ መሆኑን አምነው ለመቀበል ሲተናነቃቸው ይስተዋላሉ። (የጠበቁት ሌላ የመጣው ሌላ..) ከመስተዋልም ብሶ ጉዳዩ በቤርሳቤህ ትችትን ሁሉ ሲያስተናግድ እንመለከታለን፦
«በቃ፤ በዚህ ነው የምንሄደው?» አለች።
«ምነው?»
«አለንዴ ይኼን ዓይነት መኪና? ከገቢያ አልጠፋም? ቅርስ ነገር... ሙዝየም ውስጥ ብቻ መስሎኝ መገኛው።»
«ቢኖር ነው እንግዲህ...» አለ፤ እንጀራ መብያው ስለተናቀበት፣ በተራው ሊያጣጥላት ቃላት አማረጠ።
«በእውነቱ በእዚህ ባረጀና ባፈጀ መኪና መጓዝ ወደ ድሮ ከመሳፈር እኩል ነው።» አለች፣ ምንተስኖትን በዐይኗ እየማተረች። ያየው ነገር ምን እንደፈጠረበት ለማወቅ ፈልጋለች።
ሾፌሩም በመኪናው ይዞታ ላይ የሚደረገውን ትችትና አስታየት ቸል ብሎ መሪውን እንደጨበጠ፣ ከጀርባው የሚከናወነውን በሚመለከትበት መስታወት ላይ እያፈጠጠ ነው። በበቀደመ አቋሙ የጸና መሆኑን ለማሳየትም፣ «ኣ? ምን ወሰናችሁ? እናንተን ብቻ ጭኖ ወደ ደብረሠምራ መኼድ ምንም አይነፋም። በዚያ ላይ መንገዱ ፒስታ ነው፣ ጠመዝማዛ ነው፤ መኪናዬ አቻዮ ስለሆነች እንጂ መንገዱ በማንም አለሁ ባይ ውሽልሽል መኪና የሚሞከር አይደለም ....» አለ
(ገፅ 34)
እዚህ ጋ ነው እንግዲህ ባህር ከሆነው የጉዘት አፅናፍ ዳር፤ ገና ከመነሻው እየተመናመነ እጃችን ላይ በመፈረካከስ ላይ የሚገኘውን ሀገራዊ መልካም እሴት የሚሞግተው። በነበር የተረት መጫኛ ተቀብቅቦና በትውስታችን ጓዳ ታስሮ ተጥሎ በአዲስ መቀየር ሲኖርበት፣ ዛሬም እንዲህ ይባላል እንዴ? ይሄ አልቀረም ወይ? እየተባለ አዲሱ ባህልና ማንነት የማይደፍረውን እሾሃማ የፒስታ መንገድ እንደ አክርማ ሰንጥቆ ወደ ፊት የሚተመው የእሴታችን ግልባጭ የጎፈሩ ምስል ነው።
ሀገር እንደ ሀገር በወርቃማ የታሪክ ዘመኗ የምታጣው የለምና ዘንበል ሲልም የምታገኘው ብርቅ ይሆንባታል። እሴታችን ሙሉ ለሙሉ ጠፍቷል እንዳንል መኪናዋ በናወዘ አንጎሏ በቆሳሰለ አካሏ ውስጥም ትጓዛለች። ለእኔ ስነ ምግባር መስሎ ከተሰማኝ አንዱ፤ የነበረ ግን አሁን ላይ የማይሰራው የመኪናዋ ሙዚቃ ወይም ሬዲዮ ነው። እንደሚታወቀው መከባበር የቻለ ማህበረሰብ መግባባት አይቸግረውም። የተግባባ ባላንጣ ደግሞ ወግ አያጣውም። ወግ የተወጋ መንገድ ፤ ረጅሙን የድካም አክናድ ያሳጥራልና..!
በዚህም ልቦለድ ውስጥ የሱራፌልን ጥያቄ ዋቢ አድርገን እንቀጥል ..
«ፓይለታችን!»
«አቤት!» አለ ሾፌሩ፣ ዐይኑን ከመንገዱ ሳይመልስ፣ ጆሮውን ግን ከጀርባው ለሚመጣው መመሪያ አመቻችቶ።
«አቦ ሙዚቃ ክፈትልን፣ ወይም ሬዲዮ ነገር። ዝምታችን ሲጨንቅ። ዝምታው ብቻውን ሊሰለቅጠን እኮ ነው።
«ቴፑ ተበላሽቷል።»
«አስክሬን ጭነን ቀብር የምንሄድ አስመሰልከውኮ።»
«ምን ይደረግ በሞባይሌ እንዳልከፍትላችሁ <ኒቶርኩ> አይሰራም። በቃ ረዳቴ ያንጎራጉርላችኋ፤..... ገፅ 37
³ መንገድ እንደዘመን
መንገዱን በጊዜ ወይም በዘመን ብንመስለው በመፅሐፉ ውስጥ በውክል የገባውን የእኛኑ ታሪክ ይመስላል። የቱ ጋ እና መች ‘ለት እንደሆነ ባይገባኝም የዘመናችን መንገድ ላይ ያቺ ጥቁር ድመት አቋርጣለች። ልክ እንደ መሪጌታው ሁሉ ከወጣት ነብስ እየተበደረ ሄደ ሲባል እየመጣ ያመሰን ቁጥሩ ጥቂት አይደለም። ጠወለገ ብለን ያፈካነው አበባ አብቦ ፤ በማበብ ላይ የሚገኘው ጠውልጎ፣ ሴራው ባይገባንም ለሰይጣን ስራውን ሰጥተናል። እንደ ላስብ አርዝሜ ስንሄድ ሰው ስንመለስ ጋን እየሆኑ በእንቆቅልሽ ወንጭፎቻቸው አይከኖቻችንን ከጎናችን የነጠቁን ቁጥራቸው ይታወቅ ይሆን?
የዘመኑ መንፈስ እንዳሻው ምህዋሩን በርብሮ ፍለጋውን እንዳያሳካ ጉድለት ያዘለው እሴትና ለሀበሻዊ ማንነቱ ጀርባውን ሰጥቶ ለመንገጫገጭና ለብልሽት የዳረገው ይህ ጎዳና ለተጓዡም ፈተና መሆኑን ቀጥሏል። ከሁሉ ከሁሉ ልክ በበዓሉ ግርማ ከአድማስ ባሻገር ልቦለድ ውስጥ ጢንዚዛው በረጋውና ዝምታ እንደአዘቅት በዋጠው ቤት ውስጥ ድንገት በመግባት የቤቱን የፀጥታ ድባብ በመናድ፣ መጪው የትረካ ሁናቴ ውስጥ ትንቢታዊ የትረካ ዳናን ጥሎ እንደሄደና ቀድሞ ያልታየንን እንዳሳየን ሁሉ በዚህም ልቦለድ ውስጥ መንገድ ሰብራ የምታቋርጠው ጅራተ ቆራጣ፤ የዓይነ ስውሯ ጥቁር ድመት ገጠመኝም፣ ተጓዦቹ ካሰቡበት በሰላም እንደማይደርሱና እክል እንደሚገጥማቸው ጠቋሚ ምልክት ነበር።
በሌላም አቅጣጫ የድመቷ በዚያ መንገድ ላይ ማቋረጥ ነባር ለሆነው ለእኛ አይነት ማህበረሰብ፣ በሀገረሰባዊ የእምነት ልኬት መተርጎሚያው ይለይ እንጂ አተረጓጎሙ ተመሳሳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ሐ. የምስስሎሽና የባህላዊ እምነት ኪስ
ምስስሎሽን በተመለከተ አንዳንድ ቦታ ላይ በዚህ ልቦለድ ውስጥ የሚገኙ ደቂቅ አጋጣሚ ለበስ ተረኮች እንዳሻቸው የሚመነዘሩ፤ የሚሰነዘሩ ድፍን በረከቶች እንጂ እንዲሁ እንደወፍ ዘራሽ ተክል ያቆጠቆጡ አይደሉም። ተክለ ቁመናቸውን በአሊጎሪካል የአተራረክ ዘይቤ ጥግ ጥጉን የሚያሶመሱሙ ተረኮች፣ ልክ እንደወንዝ እግራቸውን ከቀያቸው ሳይነቅሉ፣ ሰው ሀገር የሚገኙ ብልጦች ናቸው። ( ልክ እንደተዋነይ በደመና የመሳፈርን እድል ተችረው ይሆን? እንጃ! መሪጌታ ከኼዱበት ሲመለሱ በእዩኤል በኩል የምንጠይቃቸው ይሆናል )
ከዚህም ለመመንዘር እኛን ለመምሰል በጥብቅ ቃላት የታሰሩ አጋጣሚ ለበስ ተረኮች ውስጥ የሚከተሉትን እንመልከት።
¹ በረጋሚው ከንፈር የወደቀ ትውልድ
«ለመሆኑ ደብረሠምራ አድጋለች?» የሚል ጥያቄ አስከተለ።
«ደብረሠምራ ልታድግ? አልሰሜን ግባ በለው! ፈፅሞ አላደገችም፤ አታድግምም።»
«ለምን?»
«ተረግማለቻ፤ ሰምተህ ይሆናል፣ የሆነ ጊዜ ፅላቷ ተሰርቆ ነበር። ሁለት ሦስት ወጣቶች ናቸው አሉ፣ ጽላቷን ሰርቀው መልሰው ማህበረሰቡ ተራበ ምናምን ብለው ጆሮውን ያሉት። ጽላቱን መልሰው አልሸጡትም? ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ደብረሠምራ ይህን ዐይታ ዝም በማለቷ የሀይማኖት አባቶች ከተማይቱን አምርረው ዕድሜ ልክሽን እንደዳከርሽ ኑሪ፣ ከእንፉቅቅሽ አትነሺ! ብለው ረግመዋታል።» አለ ረዳቱ። ገፅ 35
...እውን ጽላት እምነት አይደለም? እኛስ ሆድ ጎደለ ብለን እምነታችንን በሸጥን በማግስቱ ጉበናችን ስር ራብ አስተክዞን፣ ታሪካችን ስማችን በረሀብ መዝገብ ተፅፎ ለዘመን ዘመናት አልታወስንም? የስንዴን እርጥባን እየጣሉብን በገዛ የስንዴ ማሳችን ላይ ባሩድ ተክለን፣ ህይወት እያረምን ሞት አላጎነቆልንም?
እኔም ዛሬ ላይ በገጣሚ እዩኤል ደርብን ግጥም እየጮህኩ የምጠይቅ ይመስለኛል።
«ዓመቱ ስንት ነው የፀሎት መሰሚያው?
ስንት ነው ዘመኑ የእምባ መታበሻው?
ይሄን ያህል ዘመን አንጋጣን ስንጮህ
ምህረት የራቀን
ምን ያህል ቢያንስ ነው የደም እምባ ፀሎት
ከእሱ ያላስታረቀን?
እርግማንስ ከሆንን
ስንት ዘመን ቀረን ርግማን ልንሽር?
መቼስ አያዋጣም በጎበጠ ወገብ መታጠቅ ምንሽር!.. »
(እዩኤል ደርብ / ልብ ያለህ ልብ በል/)
² ደስታ ያስካዳት ቀዬ
አንዱ ልጅ፣ ”ጋሽ ሾፌር የዚህ ልጅ ሰፈር ደርሰናል፤ አውርደው! ወራጅ! ወራጅ! ወራጅ! » አለ ጮክ ብሎ።
ሾፌሩ ፍሬኑን ቀዝቀዝ አድርጎ ማቆም ሲጀምር ውሸቱን ነው፤ ውሸቱን ነው፤ የ’ዚህ ሰፈር ሰው አይደለሁም።» አለ ልጁ፤ እነሱ ከሚጮኹት በላይ ጮሆ።
ሌሎች ተረባረቡበት፡፡
«አንተ! ያው አባትህ ከብቶቹን እያሰማራ ...ያቻት እናትህ ስጥ ስታሰጣ ... ያው ታናሽህ ጡጦ እየጠባ..ያው ቤታችሁ ...ሰፈሬ አይደለም ይላል እንዴ? ብትክድ ብትክድ ሰፈርህን ትክዳለህ ? ምናይነቱ ውሸታም ነህ?»
«ውረድ፤ በል ውረድ።» አለ ሾፌሩም።
«በናትህ ጋሽ ሾፌር በእግሬ እመለሳለሁ፣ በናትህ ስንመለስ የነበርንበት ቦታ ላይ ስትጥለን ያኔ በእግሬ ወደዚህ እመጣለሁ።» አለው
ሾፌሩ የፈጠረለትን ደስታ ሊነጥቀው አልፈለገም። መኪናውን አስነሳና ጉዞውን ቀጠለ። ገፅ 208
***
በሰከርናት የደስታ ጌሾ ባጠፋናት የወረት እርሾ እየተገፋን፣ የሚያይ የዐይናችንን መስኮት ዘግተን፣ የልባችንን በኩር እምነት ያልካድን ማነን? ለሚታይ የግምባር ስር ስጋ የማልን የተገዘትንስ? በማታረጅ የልጅነት ለጋ ነብሳችን የሰጡንን፤ ያስጋለቡንን፤ እየጠባን አንቀልባዎቻችን ውስጥ በመሆን ያልገላመጥንስ?
ጅልነት ባጠቃው መንገዳችን አውቀን የጨፈንናቸው እውነቶች ስንት ይሆኑ? በመኪና እየሄድን የረሳናትን ሀገር በእግር እየመጣን እናስታውሳታለን። ሌላም ሌላም... ለእኔ ትርጉም የሚሰጥ ቆንጆ ማህበራዊ ተሀዝቦት መሆን የሚችል ሒስ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ደግሞም ብዙ የሚመነዘሩ ተረኮችን በድፍንነቷ ድፍን ሲጥልን አካላ ይዛለች። ተግታችሁ ፈልጉ፤ እንደምርቃትም እንደጥቆማም ቀደምት ታሪካዊ የታሪክ አጋጣሚዎችን በተመለከተ፣ በገፅ 39 አፄ ምሊኒክና ጥቁሯ ድመትን እንዲሁም በገፅ 126 የቀብሪ ደሃር ሰዎች የገጠማቸው የዝናብና የሬሳውን ገጠመኝ ከዚህችው ጋር አያይዛችሁ እዩልኝ።
በባህላዊ የእምነት ኪስ
አሁን በቅርብ በንጉሱ ዘመን ጎጃም በራስ ሀይሉ በሚተዳደርበት ወቅት ኮከብ ቆጣሪና ጠንቋዮች በግዛቱ ምን ያህል ስልጣን እንደነበራቸው «ህይወቴ» በሚለው የህይወት ታሪኩ ላይ የፃፈልን ተመስገን ገብሬ ምስክር ነው። እንደ ተመስገን ገብሬ ገለፃ፤ በግዛቱ የሚኖሩ ኮከብ ቆጣሪና ጠንቋዮች፣ አራሹን ገበሬ ግብር ካላሳገባህልኝ ሰብልህን በአመዳይ አደባየዋለሁ፣ እጅህ ላይ የሚቀረው ገለባ ብቻ ይሆናል እያሉ ስንት እንዳርበደበዷቸው አትቶ፣ ኋላ መንግስት ባለበት ሀገር እንዴት እንዲህ ይሆናል በሚል አስተኳሽ ቃል መቀጣታቸውን ያትታል። ከገፅ 36 እስከ 39 ገፅ ባለው ሰፊ ሀተታ ያየውን የሚተርክልን ተመስገን፤ ራሱም ከዚህ ገፈት እንዴት እንዳመለጠና በአውራጃው የሚገኙ ጥንቁልና ጠቀስ መፅሐፍት በሞላ እየተሰበሰቡ እንደተቃጠሉ ይጠቁማል። የጥንታዊውን የደስክ ባህላዊ እምነት በተመለከተ የረባ ንባብ ባይኖረኝም እንደ ወንድሜ ቢንያም ገዛኽኝ ገለፃ፤ ከደስክም ባሻገር ደራሞ እና ዚኖ የሚባሉ ባህላዊ እምነቶች በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ እንደሚኖሩ ለማወቅ ችያለሁ። በተለያዩ ጊዜያትም ይህን እምነት ሲያራምዱ የተገኙ ሰዎችን ማሰር፣ ማሰቃየትና ባስ ሲልም መግደል የሚበዛበት የታሪካችን አንጓ፤ ዛሬ ላይ ከትዝታና ተረት ያላለፈ እምነቱ በስነ ጥበቡ ላይ እንኳን ታሪክ እንዳይኖረው እንዳደረገ ይሰማኛል።
እንዲህ ከመሰለው ማህበረሰባዊ መገፋት ያደቀቀው ይህ የባህላዊ እምነት ዳርቻ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሀሜት እየሆነ ከመቅረት አልዳነም። በዘመናዊው የፊልም ሳይንስ ባደጉት ሀገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ረብጣ ገንዘቦችን የሚሰሩበት ይህ ዘርፍ፤ በእኛ ሀገር እንዲህ ያለውን ቦታ ሊያገኝ ቀርቶ የእዳና የስም ሸክሞችንም ማራገፍ ከብዶት ሲፍገመገም እንመለከታለን።
ይህ እንደኛ ላለው እምነት ላይ ከራራ ነኝ ብሎ ለሚያስብ ማህበረሰብ የማያወላዳ ቢሆንም፣ በስነ ፅሁፉ ዘርፍ እምብዛም ትኩረት እንዳይኖረው፣ በፍርሃት ቆፈን ታቅፎ እንደሆነ እገምታለሁ። ሆኖም ግን ድርሻው እምብዛም ነው አልኩ እንጂ ጨርሶ የተሞከረ ጅምር የለም ማለቴ እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ። ሲጥል አዲስ ይዞልን የመጣው ስነ ፅሁፋዊ ፍካሬ ይሄ ነው። ከገፀ ባህሪ መረጣ ጀምሮ ጥንቅቅ ያሉ ሙሌቶችን ልብ በሚሰቅል የታሪክ ነገራ እያጀበ አቅርቦልናል ብዬ አምናለሁ። በዚህች ሀገር ታሪክ የሁለት ዐይናማዎች ብቻ ሳይሆን፣ የአንድም ዓይናማና የዐይነ ስውራንም ሀገር እንደሆነ ሊገልፅልን መድፈሩን ሳላመሰግን አላልፍም። እንዲመረመር እንዲጠና የማሪያም መንገድን በመፍጠር ረገድ ይህ ስራ ደህና መጠቆም እንዳለው መናገር እወዳለሁ። ሆነም ቀረ እንደ ላስብ አርዝሜና መሪጌታ ሐብቱ ያሉ ብርቅዬ ገፀ ባህሪያትም ለሀገሪቱ ስነፅሁፋዊ እድገት የበኩላቸውን መነቃቃት እንደሚፈጥሩ አልጠራጠርም።
መ. ማጠቃለያ
ሊጥል በሽብሻቦው ውስጥ ሀገራዊ መንፈስን አሰፍስፎ የለገሰን የጊዜው አንድ እርምጃ ስራ ነው። ብዙ ኪስ እንዳለበት ውብ ልብስ መስዬዋለሁ። ብዙ ኪስ ያለው ልብስ የለበሰ ሰው፣ በኪሱ ብዙ ነገሮች አብረውት እንዲሻገሩ የማድረግ እድል ይኖረዋል።
እናትነትና ሀገር፣ አባትና ዘመን፣ መገፋትና ብቻ መቅረት፣ ቅሬታና ፍቅር፣ የተስፋ ጀምበርን ከስክሶ በቀቢፀ ተስፋ መደነስና ማለፍ፣ ጥላና ጥላሞት፣ ሀገራዊ ውጥንቅጥና ትውልድ እንዲሁም ብዙ ብዙ መፅሐፉ ከለበሰው ሀሳባዊ ልብስ ላይ የተገጠሙ ኪሶች ናቸው። ኪሶቹም የሀገር መከራን በከንፈራቸው ዳር የሚያነበንቡ፣ የትውልድ ጉብጠትን በጣቶቻቸው ጉበን የሚደረድሩ የዘለሰኛ ውልብታ ወጨፎ ያረሰረሳቸው ናቸው።
ድምፃቸውን ዝግ በማድረግ ትሁት የምህላቸውን ትንፋሽ በታሪክ ነገራው ላይ ሰቅለው እየደረደሩ ጊዜን፣ ዘመንን፣ ሰውንና ጀምበርን የሚታዘቡም ጭምር... “ሲጥል” ከሸኚነቱ ባሻገር በመቋጫው ላይ እንደተደመደመበት ቃልም ምናልባት ቀጣይ መፅሐፍ የሚኖረው ይመስለኛል። አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል.. እንዲሉ ምናልባትም አንተነህ ወይ እዩኤልን ስቦ ወደ ራሱ እምነት ይጠቀልለው ይሆናል አልያም እዩኤል በያዘው እምነት ተጠምዶ የራሱንም ሊያጣ ይችላል።
ምናልባትም መሪጌታ ከሄዱበት የሚመለሱ፤ አቶ ስዩምም ወደ ትጥቅ ትግሉ ባይመለሱም ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙ ይመስለኛል። ላስብ አርዝሜም ምን አይነት ቀጣይነት ያለው ህይወት ሊኖረው እንደሚችል እናውቅ ይሆናል፡፡ ምናልባት ሀ ሁ ተብሎ ተጀምሮ፣ በ ነ ኑ ኒ የፊደል ስድራት ውስጥ ኖ ሲል የተዘጋው ምዕራፍ፣ ቅጥያ ኖሮት እስከ ፐ ይሄድ ይሆን ይሆናል። ባይሄድም አልቋል ብለን ለመደምደም የሚያግደን አይኖርም። መጻሕፍት ዋጋቸው አንድም መቆስቆስ አንድም ማዳፈን ነውና! (ለተደራሲ ሜዳውን ጠቁሞ ፈረስ መሆንንም ይጨምራል!)
የነ ኑ ኒ ስድራት በሄደው ምዕራፍ ውስጥ ኖ ብሎ ሲያልቅ፣ አላለቀም የምትሉ በፈረንጅኛው አፍ ኖ (No) እያላችሁ ጠብቁ አልያም ዝቅ ብላችሁ አበቃ! የሚለውን አንብቡ፡፡ እኔም አበቃሁ፡፡
Saturday, 31 August 2024 19:44
ዘለሰኛ ኪሶች (ሀገር፣ ጥላና ዘመን)
Written by ሲራክ ወንድሙ
Published in
ጥበብ