Saturday, 24 August 2024 00:00

ደበበ ሠይፉ እና ደብዳቤዎቹ

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(1 Vote)

‹‹ነፋሱ - ሣር ቅጠሉን አዋከበው፤
ሞገዱ - ባሕሩን አናወጠው፤
ግን የኔን ልብ፣ ምን አራደው?
ምንም የለ - ‘ሚታወሰኝ፤
ድንገት እንጂ፣ ሆድ የባሰኝ።
ለምን አልኩኝ - ተጨብጬ፤
እንባዬን ባፌ መጥጬ፤
ሳውቅ ጥያቄ፣ መልስ እንዳይሆን፤
የለምን ለምን፣ ለምን ሊሆን?!››
(‹‹የለምን ለምን››፤ ገጽ 12)
የግጥም መድበል ጣጣ የማያጣው ነው፤ መድበሉ መሠየም ያለበት ውስጥ ከሚካተቱ ግጥሞች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካለው እና ወካይ በሆነ ርዕስ ነው፤ በአጭሩ፣ በአንድ መድበል ውስጥ የሚካተቱ የተለያዩ ግጥሞች የመድበሉን ርዕስ/ሥም መጮኽ ይጠበቅባቸዋል፤ የግጥም መጻሕፍ ርዕስ/ሥም ውስጥ ላይ ከሚነሱ እና ከሚቀነቀኑ ግጥሞች ጋር መግጠም እና መስማማት ይጠበቅበታል።
በጓድ ሰለሞን ደሬሳ ብሒል ተመርተን ግጥም የመሆን/የመነካት ነው (Poetry to be) ካልን (የወለሎ ግጥም እንዳለ ሆኖ ማለት ነው)፣ በመድበል ውስጥ የሚካተቱ ግጥሞች የገጣሚውን አሁናዊ/ዐውዳዊ ሥሜት እና የግጥም መጻሕፉን ርዕስ/ሥሙን መምሰል አለባቸው። ሥም እና ሃቲት በተቻለ መጠን ዕኩል መሄድ ይጠበቅባቸዋል፤ አለያ፣ መሳ ለመሳ የሚጓዙ ከሆነ አንባቢን ከመጠሪያው ያፈነገጠ፣ ወይም ያልተግባባ ሀሳብ ውስጥ ሊከትቱ ይችላሉ። የሀገሬ ሰው ‹‹ሥምን መላእክ ያወጣዋል›› ያለው በከንቱ አይደለም፤ ሥምና ሥራ መግባባት መቻል አለባቸው፤ በዚህ ዐውድ ደግሞ፣ የመጻሕፍ ርዕስና ውስጥ ላይ የሚነሳ ሀሳብ መግባባት መቻል አለበት እንደማለት ነው።
ወግ በአጭሩ ሲሆን ጣዕምና አይናጠበውምና፣ ይኼንን ካወጋን ዘንድ ወደ ገጣሚ፣ መምሕር፣ ተውኔት ጸሐፊ እና ተርጓሚ ደበበ ሠይፉ ሥራ ወደሆነው ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ፣ የብርሃን ፍቅር›› እንስከንተር…
…ይኼ መድበል (‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ፣ የብርሃን ፍቅር››) የደበበ ሠይፉ ደብዳቤዎች የታጨቁበት የግጥም መጻሕፍ ነው፤ ደበበ ሠይፉ በርካታ የተነካባቸውን ጉዳዮች በደብዳቤ መልክ ሰንዶ አቅርቧል፤ ደበበ ሠይፉ ከምንም በላይ ለኪነ-ጥበብ ታማኝነቱን እና ተጠቃሽነቱን አስመስክሮ አልፏል፤ መድበሉ ውስጥ ገጣሚው ጨረቃን ሲያወጋት፣ ፀሐይን ሲናፍቃት፣ መዓዛን ሲያድን፣ ነጻነትን ለመቀዳጀት ሲውተረተር እና በሌሎች ጉዳዮች ተሰቅዞ ለማፈትለክ ሲፍጨረጨር እናስተውላለን፤ ታዲያ፣ እነዚህን ሀሳቦች በደብዳቤ መልክ ሰንዶ እና ከእራሱ ጋር ያወጋውን በውሎ ማስታወሻው አኑሮ ለመነበብ በቅቷል።
ደብዳቤዎቹ ንቡር ጠቃሽ ናቸው፤ የታለመላቸው ተቀባይ አላቸው፤ የሚወጋባቸው፣ የሚነገርባቸው ናቸው፤ ግልጽ እና አካል ያለው ተቀባይ ተሰጥቷቸዋል፤ ከማን ወደ ማን እንደተጻፉ አድራሻቸው በቀጥተኛ መንገድ ይታወቃል፤ የደበበ ሠይፉ ቋንቋው የተመጠነ፣ ስንኝ አዘጋገኑ የተቆጠበ ቢሆንም በጥንቃቄ መነበብ አለበት፤ በዚህ መልክ አድራሻውን መያዝ፣ መገንዘብ ይቻላል ባይ ነኝ፤ በደብዳቤዎቹ ውስጥ የሚንዠቀዠቅ እንባ አለ፤ ከነፍሱ ጋር ሲጋጭ የተየበው ደብዳቤ አለ፤ ዕጣ-ፈንታውን ባሰበ ቁጥር ሰማይ ጠቀስ ሥጋት ጫንቃው ላይ ሲወድቅ ያሳያል፤ ሕልም እና ትልሙም ካነበብናቸው ደብዳቤዎቹ መካከል ናቸው፤ ቅርቡ ነውና ላይደንቀው ይችላል እንበል…
…እኛ ጋር ሲደርስ ግን ደብዳቤው ግጥም ሆኖ ቀርቷል፤ ያውም ከታላላቆቹ ገጣሚያን እና ከማይዘነጉ መድበሎች ተርታ የሚሰለፍ ነው፤ ሥነ-ጽሑፋዊ ዳሰሳ ወይም ትንታኔ ላይ ከሕግጋት እና ከኅልዮት ባለፈ የተንታኙ ሥሜት ሊንጸባረቅ ይችላል፤ ኀዘን የሥጋ ዘመዴ ነው መሰል ነፍስያዬ በኀዘን የጠየመች ስለሆነች፣ የደበበ ሠይፉን መድበል ባነሳሁ ቁጥር ጥፍራም ኀዘን ጠልጣላዋ ነፍሴን ይቧጥጣታል፤ እንግዳውስ ልቤ ድንጋይ አይደለምና ኀዘን ቅልቅል ሀሳቤን እንደሚከተለው ላቀርብ እወዳለሁና ብትቀየሙኝም እችለዋለሁ!
ደበበ ሠይፉ ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ፣ የብርሃን ፍቅር›› በተሰኘ መድበሉ ለፀሐይ፣ ለጨረቃ፣ ለብርሃን፣ ለአቢዮቱ፣ ለሶሻሊዝም፣ ለቅኔ፣ ለሙዚቃ፣ ለጣዕም እና በአጠቃላይ ሥነ-ውበታዊ ለዛ ለተላበሱ ጉዳዮች የጻፈውን ደብዳቤ እያነበብን ልናነባ፣ ልንጠይቅ፣ ልንገረም፣ ልንቆዝም ሆኖአል፤ ደበበ ሠይፉ በ‹‹ሩቅ ነው ጉዟችን›› እና ‹‹የክረምት ማገዶች›› ግጥሞቹ ሶሻሊስታዊ ጽናቱን መስክሯል፤ በ‹‹እኔና ጨረቃ›› ደግሞ አንድ አጥቶ፣ ከአንዱ ጋር ሲቧደን አስተውለናል…
የትውልድ ቀዬውን ናፍቆት፣ እሸት እና ማር ያጣጣመበትን ውለታ፣ የቤተሰብ፣ የአባት ፍቅሩን አውስቶ አይጠግብም፤ ደበበ ሠይፉ ሞራላዊ ልዕልና ላይ ተንተርሶ የወል ግድፈታችንን የሚኮንንበት ግጥምም አልታጣም፤ ግጥም በጊዜ ሂደት ጉድባ ውስጥ ተሰንቅሮ ያልተሰናከለ መሆን እንዳለበት ዕሙን ነው፤ ታዲያ፣ ደበበ ሠይፉ ጊዜ ያልገነተራቸው፣ ነገ የታያቸው ግጥሞቹን ነው ለንባብ ያበቃው፤ አብዛኞቹ ግጥሞች እጅግ በጣም ተወዳጅና ተጠቃሽ በመሆናቸው ምክንያት እንደ ሥነ-ቃል የምንላቸው/የምንወርዳቸው ናቸው፤ ለምሳሌ፡-
‹‹የጣልኩብሽ ተስፋ፤
እኔን ይዞ ጠፋ፤››
የሚሉ ከ‹‹ጠብቄሽ ነበረ›› ግጥም ገላ ውስጥ የተቀነጨቡ ስንኞችን በንግግር መሃል ሰዎች ሲጠቅሱ መስማት የተለመደ ነው፤ ከዚህ በተረፈ ‹‹የተስፋዬ ዛፉ›› ከተሰኘ ግጥም ውስጥ፡-
‹‹የልቤን ልበ-ባሻነት ገሠፅኩኝ፤
ተስፋ መቁረጥን ተስፋ አረኩኝ፤››
የሚሉትን ስንኞች አንዳንድ ሰዎች ተስፋ ያለመቁረጥ ማሰሪያ አድርገው ሲጠቅሱ እንሰማለን፤ ይኼ በመሆኑ፣ ደራሲ ወይም ገጣሚ ማድረግ ያለበት የሚታወስ እና ከእሱ ይልቅ ሥራው ትልቁን ድርሻ የሚይዝበትን መጻሕፍ ማበርከት እንደሆነ ይታመናል።
የሆነው ሆነና፣ ጓድ ደበበ ሠይፉ የእሣት ላንቃ ላይ ጥዶን ሄዷል፤ ግጥሞቹ የሚፈሉ፣ የጠበቁ እና እንደ ለበቅ የሚፋጁ ናቸው፤ እኛ ውስጥ ነው ደበበ፤ ሂሳችንን እንድንውጥ መንገድ አበጅቷል፤ ራስን የመውቀስ ዕድል ማግኘት ትልቅነት ነው፤ ለአብነት እንኳን በደበበ ሠይፉ ‹‹አይደለም የዘወትር ምጤ›› ግጥም በኩል ወደ ሰብዕና እና ወደ ሰውነት ክብር እንድንመለስ ተደርገናል፤ ገጣሚው ከቁጭት ቀጥሎ እርማት የተከተላቸው እና የሚያበቁ ግጥሞችን እንኩ ብሎን አልፏል፤ እንቆጭ፤ እንብቃ!
ልብ እና አንጀት ከሚመዘምዙ ግጥሞቹ አንዱን እንጥቀስ በዚህ፡-
‹‹አደን››
‹‹አሣዳጄን አመለጥኳት፤
አመለጠችኝ ያሣደድኳት፤
ኗሪ ሆንኩኝ እንደፍየል፤
በነብርና ቅጠል መሀል።
አቤት አለች ያልጠራኋት፤
የጠራኋት ድምጽም የላት።
ራቂኝ ‘ምላት ጎኔ ወድቃ፤
ቅረቢኝ ‘ምላት ከኔ ርቃ።
አንዴ ስታደን አንዴም ሳድን፤
ዕረፍት አጥቼ ስባክን፤
የዕድሜዬን ጀንበር ብታዘባት፤
ልትጠልቅ ምንም አልቀራት።››
(‹‹አደን››፣ ገጽ 9)
በዚህ ግጥም ደበበ ሠይፉ በተቃርኖዎች ተከብቧል፤ የዕጣ-ፈንታ ጉዳይ ነው ሀሳቡ፤ ልቡ ያሻው ሌላ ነው፤ የሆነው ግን ሌላ፤ በሕይወቱ ፉርጉ ውስጥ መዛነቅ ተወዝፏል፤ የመሰናከያ ጉድባ ገጥሞታል፤ ነፍሱ ሠርክ ስትወራከብ እናስተውላለን፤ ሰናይ መንገድን መርጦ ኖሯል፤ ነገር ግን ዕኩይ ነገሮች ተግተልትለው ከሕልም እና ትልሙ ሲያናጥቡት ይታያል፤ ታዲያ፣ ሊያቸንፋቸው እየታገለ፣ ዕድሜውን ሲባጅ ደብዳቤው ይጠቁመናል።
‹‹ለምን ሞተ ቢሉ››
ለምን ሞተ ቢሉ፤
ንገሩ ለሁሉ፤
ሳትደብቁ ከቶ፤
“ከዘመን ተኳርፎ
ከዘመን ተጣልቶ”
(‹‹ለምን ሞተ ቢሉ››፣ ገጽ 73)
ዓለማየሁ ገላጋይ ‹‹ማዕበል ጠሪ ወፍ›› በሚል መጻሕፉ ስለዚህ ግጥም ሲያወጋ፣ ደበበ ሠይፉ መነሻ አድርጎ የተጠቀመው፡-
‹‹እኔ እዘጋዋለሁ፣ ቤቴን እንዳመሉ፤
ሰዎች ከጠየቁ፣ ከፍቶት ሄደ በሉ፤››
ከሚል የሕዝብ ሥነ-ቃል እንደሆነ ነግሮናል፤ ግጥሙ ልብ ያጠፋል፤ ደበበ ሠይፉ ሲታክት እናስተውላለን፤ ዘመን የፈረስ ጀርባ ላይ እንደተጫነ፣ ውሃ እንደነካው ጨው መላ ሰውነቱን ሸነታትሮታል፣ ገሸላልጦታል፤ ኩርፊያው ከእኛ ጋር ነው፤ አስከፍተነው ጣጥሎን የሄደበትን ምክንያት አትቷል፤ ተነጋሪዎቹም ነጋሪዎቹም እኛው ነን። ከስንብት ጎን ለጎን ተስፋውን በሚመለከተው በግጥሙ ውስጥ እንመልከት…
‹‹በመንፈቀ ሌሊት››
በመንፈቀ ሌሊት፤….
በመንፈቀ ሌሊት፣ ጨለማ ቱቢቱን፣
ለፍጡር ባደለበት፤
የሚያይ ዓይንን ሁሉ፣ ዙሮ ባወረበት፤
ፅልመቱ ሲያስፈራ፤
ከቀኝ ከግራ፤
አንቺ ድል ሳትሆኚ፣ ጨለማን ጥሰሽ፤
እፊቴ የቆምሽው፣ በብርሃን ታጥረሽ፤
ፍቅሬ ሆይ ዓለሜ፣ እንኳን የመጣሽ፤
በይ ነይ ወደሕልሜ፣ ልሂድ ታቅፌሽ።
(‹‹በመንፈቀ ሌሊት››፣ ገጽ 10)
ዙሪያውን የባጀውን ጨለማ በሕልም ዓለም እንኳን የምታበራ ተስፋ አለቺው፤ ናፋቂ ነው፤ ወዳድ ነው፤ የከበበውን ደንዳና ጨለማ ጥሳ የምታበራ፣ በእንቅልፍ መሃል የተገኘች ንቃት ልቡ ውስጥ አለች፤ ጭላንጭል ብርሃን ታድለዋለችና ትጠጋው ዘንድ ይማጠናል፤ በሕልም ነው ታዲያ! ደስታ እና ሐሴት ከልቡ አይንጠፉ እንጂ የሕልም እና የዕውን ኬላ አይገዱትም! አንድ ግጥም ልመርቅና ላብቃ፡-
‹‹ለአንዲት ቅጽበት ብቻ››
እስቲ የማነው ጉልበት፤
የሰው የአማልክት፤
ሊሰጠኝ የሚችል፣ የደቂቃ ዕረፍት?
ከእውነት - ፍቅር - ውበት እማወጋበት?
ለአንዲት ውብ ሙዚቃ፣ ሀሳቤን ሰውቼ፤
ለአንዲት መልካም ቅኔ፣ ባርነት ገብቼ፤
ሕሊናዬን፣ ቀልቤን፣ አካሌን ሰጥቼ፤
ለአንዲት ቅጽበት ብቻ!
የአዕምሮዬ መርከብ፣ ከማዕበል አምልጣ፤
ከሕይወት ስንክሣር፣ አምርራ ፈርጥጣ፤
በዕፁብ - ውበት ቅኝት፣ እጅግ ተመስጣ፤
ሌላው ሌላው ነገር፣ ባፍንጫዬ ይውጣ!
(‹‹ለአንዲት ቅጽበት ብቻ››፣ ገጽ 77)
በዚህ ግጥም ውስጥ ደበበ ሠይፉ የነፍሱን ጥያቄ፣ ቁስ እንደማይመልስ ይናገራል፤ ያመነው ጥበብ እንደሚያድነው ከፍ ባለ ስፍራ ተደላድሎ ያትታል፤ ዝናው በልቡ ውስጥ የሚንተገተግ የጥበብ ሻማ ነው፤ መዳኛውም ጥበብ፤ የሚዋጀውም ጥበብ! አንድ የሚፈልጋትን ነገር ሊያገኝ ከቤቱ ወጣ፤ ጥበብን ፈለገ፣ አገኛትም! ጥበብን፣ ብርሃንን፣ አመክንዮን፣ ተስፋን፣ መልካም መዓዛን፣ ቁርጠኝነትን…አስረክቦን አለፈ! ነፍስህ በሠላም ትረፍ!
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር /ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።

Read 153 times