Saturday, 31 August 2024 19:57

በሰገራ የሚሰጥ ህክምና እንዳለ ያውቃሉ?

Written by  ሎዛ ደረጀ ጌታቸው
Rate this item
(1 Vote)

አይበለውና በጠና ታመው ወደ ሀኪም ቤት ሲሄዱ፣ ሀኪሙ ለመትረፍ የሌላ ሰው ሰገራ መውሰድ እንደሚያስፈልግዎ ቢነግርዎት ምን ይላሉ! አሻፈረኝ ይሉ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ምርጫም የላቸውም።
ራያን ስኒደርን ተዋወቁት፤ እንደ ማንኛውም ጤነኛ የ25 አመት ወጣት፣ የራሱ ህልምና ተስፋ ነበረው፡፡ ያልታሰበ ድንገተኛ ክስተት ግን ህይወቱን ወዳልተቀደ አቅጣጫ ወሰደው፡፡ ”በመጀመሪያ chronic pelvic pain የሚባለው በሽታ ነበረብኝ፤ ዮሮሎጂስቶች ዘንድ ስሄድ፣ በSTD ወይም በUTI ዳያግኖስ እያደረጉ፣ በአንቲባዮቲክ ላይ አንቲባዮቲክ ያዙልኝ ነበር። በጊዜው አንቲባዮቲኩ በእኔ ላይ ምን ያህል ጉዳት እያደረሰ እንደነበር አላወቅኩም።” ይላል ራያን።
በየቀኑ ማስመለስ፣ ክብደት መቀነስና ሌሎችም ምልክቶችም ያሳይ ጀመር። የሰገራ ምርመራ ሲያደርግ፤ c.diff እንዳለበት ተነገረው። C.diff (clostridium defficlie) በአንጀታችን ውስጥ ያለው ጠቃሚ እና “ጎጂ” ባክቴርያ፣ ተፈጥሮአዊ ሚዛን፣ በመድሀኒትና ሌሎች ነገሮች ምክንያት ሲዛባ፣ ለዚህ ባክቴርያ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
Microbiome በአንጀታችን ውስጥ ያለው ብዝሀ ህይወት ሲሆን፤ በሰውነታችን ውስጥ የምግብ መፈጨት፣ በሽታ መከላከል፣ ስሜቶቻችን ጭምር ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው።
ራያን ከዚህ በፊት የሞከራቸው ህክምናዎች ስላልሰሩለት፣ ፊቱን ወደ ኤፍኤምቲ (FMT) አዙሯል። FMT (Fecal micro biome transplant) የመጀመሪያው FDA ያፀደቀው የማይክሮ ባዮም ህክምና ሲሆን፤ በሚያስደንቅ ሁኔታ 90 በመቶ ስኬታማ ነው። አሰራሩም እንዲህ ነው፡፡ የጤናማ ሰው አንጀት ባክቴርያ በመውሰድ፣ የባክቴርያ መዛባት ወዳለበት ሰው ማዘዋወር ነው። በዚህ እንግዳ ህክምና፣ በጥንቃቄ የተጣራና የተፈተነ የሰገራ ናሙና፣ ከጤናማ ለጋሽ ወደ ተቀባዩ አንጀት ይገባል። ይህ ጠቃሚ ህክምና፣ ባክቴርያዎችን እንደገና በመሙላት የተፈጥሮ ሚዛንን ለመመለስ ይረዳል።
FMTን ለማከናወን ጤናማ ናሙና፣ በቂ ምርመራና ትክክለኛ አወሳሰድ ያስፈልጋል። በማሳቹሴትስ የሚገኘው ኦፕን ቦዮም የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት፣ በመላ ሀገሪቱ ከሚገኙ ሃኪሞች ጋር በመተባበር፣ የተጣራ የሰገራ ናሙና በማቅረብ፣ እንደ ራያን ያሉ ታካሚዎችን ተስፋ ያለመልማል። የሰገራ ባንክ በሉት።
ኦፕን ቦዮም፣ ለጋሾች መለገስ ከመጀመራቸው በፊት የተለያዩ ምርመራዎችን እንደሚያደርጉና ክፍያም እንደሚከፈላቸው ገልጸዋል። በአማካይ ለጋሾች 40 ዶላር ለናሙና የሚከፈላቸው ሲሆን፤ በሳምንት ለ5 ቀናት ከመጡ የ50 ዶላር ጉርሻ ያገኛሉ፤ ይህም ማለት በሳምንት 250 ዶላር ወይም በአመት 13,000 ዶላር ነው። ሰዎች በየእለቱ ለሚያደርጉት ተግባር፣ የሰውንም ህይወት እያተረፉ፣ 13,000 ዶላር ማግኘታቸው የማይታመን ነው።
FMT በተለያየ መልኩ ሊሰጥ ይችላል፤ በኮለኖስኮፒ (ቀጥታ ወደ አንጀት ቱቦ) እንክብሎች እንዲሁም በአፍንጫ መተላለፊያ ቱቦና በሌሎችም። FMT በአንፃራዊነት አዲስ ህክምና ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን ተስፋ ሰጪ ነው። ተመራማሪዎች ከFMT ከc.diff ባሻገር የተለያዩ በሽታዎችን (allergies, autoimmune diseases) በስፋት ለማከም የFMTን አቅም እያጠኑ ነው። ራያን ከህክምናው በኋላ ለc.diff ኔጌቲቭ ውጤት አሳይቷል። ቀሪ ክትትሎች ቢኖሩትም፣ ሲያሰቃየው የነበረውን በሽታ ተሰናብቷል።
የራያን ታሪክ፣ ዘመናዊ ህክምና፣ ወደ ተፈጥሮ አስደናቂ ጥበብ እየተመለሰ ለመሆኑ ምስክር ነው። FMT ለህመማችን መፍትሄ የምናገኘው በመድሀኒት ጠርሙስ ውስጥ ሳይሆን፤ በዙሪያችን ባለው የተፈጥሮ አለም ውስጥ መሆኑን ያስታውሰናል።

 

Read 92 times