በተፈጥሮና በተለያዩ ምክንያቶች ለአካል ጉዳት ለተጋለጡ፣ የእግር መቆልመም፣ የወገብ መጉበጥና ልዩ ልዩ ችግሮች ላገጠሟቸው ልጆችና የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ችግር ለደረሰባቸው ልጆች ከቀላልና ውስብስብ ቀዶ ህክምናዎች ጀምሮ የተለያዩ ህክምናዎችን በነጻ በመስጠት የሚታወቀው ኪዩር ሆስፒታል፤ ሐምሌ 19 የሕዝብ መናፈሻ አጠገብ በሚገኘው የድርጅቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማውጣት የሚያካሂደውን የማስፋፊያ ግንባታ በይፋ አስጀመረ።
በዚሁ የማስፋፊያ ግንባታ የማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የኪዩር ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አደይ አባተ እንደተናገሩት፤ የማስፋፊያ ሕንፃ ግንባታው ተቋሙ ያለበትን የተደራሽነት ችግር በተወሰነ ደረጃ የሚያቃልልና የአገልግሎት አሰጣጡን አቅምና ጥራት ለማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ሆስፒታሉ በአጠቃላይ ሕክምና ድጋፍ ሊስተካከል የሚችል ችግር ያለባቸውን ሕፃናት፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመቀበል ነፃ የሕክምናና የመድሃኒት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ክራ አስፈጻሚዋ፤ የሕክምና ባለሙያዎችን ማሰልጠንና ማብቃት በሆስፒታሉ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል።
የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱና፤ ሆስፒታሉ የሚሰጠው አገልግሎት ከታካሚዎች ቁጥር ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ከፍተኛ ችግር አጋጥሞናል ያሉት ስራ አስኪያጇ፤ የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራት ለማሳደግና የስልጠና አቅሙን ለመጨመር ይረዳ ዘንድ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሚተገበር ግምቱ ከ10 ሚሊዮን ዶላር የሚልቅ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ማስጀመሩን ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ ባለፉት 15 የአገልግሎት ዓመታት፣ ከ118 ሺ 100 በላይ የሚሆኑ አካል ጉዳተኛ ልጆች፣ ሆስፒታሉ ከሚሠጠው አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ከ33 ሺ 800 በላይ ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ከመላ አገሪቱ ለመጡ ልጆች መሰጠቱን ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል፡፡
በ2001 ዓ.ም የተከፈተውና አዲስ አበባን ማዕከሉን ያደረገው ኪዩር ኢትዮጵያ የልጆች ሆስፒታል፤ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ባገኘው ህጋዊ ፍቃድና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በገባው የፕሮጀክት ስምምነት መሠረት፣ ለአካል ጉዳተኛ ልጆች ነፃ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ለትርፍ ያልተቋቋመ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡