ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ በመላው አለም እድሜያቸው ከ2-17 ዓመት ያሉ አንድ ቢሊዮን ልጆች የተለያዩ ጥቃቶች ይደርስባቸዋል፡፡ የጥቃቶቹ መገለጫዎች ደግሞ አካላዊ፣ ፆታዊና ስነልቦናዊ ናቸው፡፡
ማንኛውም ሰው፣ በማንኛውም ስፍራ በልጆች ላይ ጥቃት ሊፈጽም ይችላል፡፡ ጥቃቱ በቤተሰብ፣ በቅርብ ዘመድ፣ በባል፣ በወንድም፣ በመምህራን፣ በቢሮ ሃላፊዎች፣በመሪዎችና በባለስልጣናት፣ በሃይማኖት አባቶችና በማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ሊፈፀም ይችላል፡፡ ይህም በቤት፣ በትምህርት ቤት፣ በስራ ቦታ፣በመንገድና በማንኛውም ቦታ ማለት ነው፡፡ እጅግ ልብ የሚሰብረው በልጆች ላይ ጾታዊ ጥቃት በአብዛኛው የሚያደርሱት የቅርብ ሰዎች መሆናቸው ነው፡፡ ለአብነትም የቤተሰብ አባላት፣ ጎረቤት፣ ጓደኛና ወዳጆች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አጥቂዎች ብዙውን ጊዜ ያላቸውን እምነትና ቅርበት ተገን በማድረግ፣ የልጆችን ህይወት ገና በማለዳው ያጨልሙታል፡፡
በልጆች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ይዞ ይመጣል፡፡ ከእነርሱም መካከል አካላዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ማህበራዊና የጤና ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ችግሩን ይበልጥ ውስብስብ የሚያደርገው ደግሞ ይህን ከባድ ችግር ልጆች የመከላከልም ሆነ የመቋቋም አቅም ማጣታቸው ነው፡፡ የልጆቹም ጤና ይታወካል፡፡ ለአብነትም ለተላላፊ በሽታዎች ፣ ላልታሰበ እርግዝና፣ ለተለያዩ ስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ይጋለጣሉ፡፡
ጥቃቱ ለደም መፍሰስ አደጋ፣ ለኢንፌክሽን፣ ኤችአይ ቪ እና ሌሎች ከወሊድ ጋር የተያያዙ እስከ ሞት የሚያደርሱ ጉዳቶች ያስከትልባቸዋል፡፡ ጥቃት የደረሰባቸው ልጆች በቂ ክትትልና ድጋፍ ካልተደረገላቸው እንግዳ የሆነ ባህርይ ይስተዋልባቸዋል፡፡ ከችግራቸው ለመደበቅ በሱስና መጠጥ ውስጥ ሊሸሸጉ ይችላሉ፡፡
ብርቅዬ የልጅነት ጊዜያቸውን በድንገት ሲነጠቁ፣ ትላንት የተስፋ ብርሃን ይፈነጥቅ የነበረው ፊታቸው ሰማይ የተደፋበት ይሆናል፡፡ እነዚያ የሚቧርቁ ልጆቻችን ከነፃነት ወደ ቀንበር ተሸካሚነት የህይወት መዘውር ውስጥ ተገደው ይገባሉ፡፡ በስነልቦናቸውና በስሜቶቻቸው ላይ እንግዳ ባህሪ ይታይባቸዋል፡፡
ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ መቃዠት፣ ፀፀት፣ ራስን ማግለል፣ ብቸኝነት፣ ብሶት፣ አለመረጋጋትና በራስ አለመተማመን ይስተዋልባቸዋል፡፡ በተለይም በማህበረሰባችን ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸውን ልጆች የማግለልና መጠቋቆሚያ የማድረግ አዝማሚያ ይታያል፡፡
በሰላሳ ሀገራት በተጠና ጥናት፤ አስገድዶ ደፈራ ከገጠማቸው ልጆች መካከል ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ያደረጉ አንድ በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየን በበርካታ ሀገራት ጥቃቱን ሪፖርት የማድረግ ባህል አለመዳበሩን ነው፡፡
ጤና ቢሱ አካላዊ ንክኪ
ጤና ቢስ አካላዊ ንክኪ የምንለው አንድ ሰው በማንኛውም ወቅት የልጆችን ያልተፈቀዱ የግል አካላቸውን በመነካካት የሚያስጨንቅ፣ የሚያስፈራራ፣ የሚያበሳጭ፣ ግራ የሚያጋባና ምቾትን የሚነሳ ስሜት ሲፈጥርባቸው በተለይም ፆታዊ ትንኮሳን ሲያካትት ነው::
ይህ አጀንዳ በተለይ ለእኛ ሀገር ከባድ ርዕስ ጉዳይ ነው:: ጉዳዩን ከባድ የሚያደርገው ደግሞ በወላጅና ልጆች መካከል በግልፅ የመወያየት ልማድ አለመኖሩ ነው፡፡ ይሁንና ልጆችን በጤናማና እና ጤና ቢስ ንክኪ መካከል ያለውን ልዩነት ማሰልጠን፤ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ መወያየት፤ በተለይም አሁን በልጆች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ዝምታውን ሰብረን፣ የመፍትሄ አካል መሆን ግድ ይለናል፡፡ :
በወላጅና በልጅ መካከል ግልፅ ውይይት ያለመኖሩ የልጆቻችንን ችግር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርግባቸዋል፡፡ የውይይት እጦቱን እንደ ሽፋን የሚጠቀሙበት አጥቂዎች ናቸው:: እነዚህ የእኩይ ስራ አቀንቃኞች፣ ልጆች ባላጠፉት መልሰው፣ ይህንን ሚስጢር ²እናገራለሁ ² ብለው እንደ ማስፈራሪያ ይጠቀሙበታል::
ወላጆች ይህንን በመረዳት ክፍተቱን ለመሙላት፣ ከልጆቻቸው ጋር በግልፅ የመወያየት ባህል እንዲያዳብሩ ይመከራል:: ልጆች ካልተነገራቸው፣ እንዲያውቁ እድሉ ካልተሰጣቸው ያልተገባ ንክኪን ችግር እንደማያመጣ የተለመደ ድርጊት አድርገው ሊያስቡት ይችላሉ፡፡ አንዲት ወጣት የሰጠችውን ልብ የሚሰብር ምስክርነት ለአብነት ማየት እንችላለን፡፡ ፊቷ በእንባ ረስርሷል፤ የልጅነት ጠባሳ ታሪክ ለመናገር ተቸግራለች፤ “ጎልማሳ ነው ጎረቤታችን፤ በጨቅላ እድሜዬ በዚያ ክፉ ልምምድ ህይወቴን እንዳበላሸ የተረዳሁት በኋላ ላይ ነው፡፡²
ንክኪ፤ ቃላት አልባ ተግባቦት ሲሆን፤ በጤናማ እና ጤና ቢሱ አካላዊ ንክኪ መካከል ስላለው ልዩነት ልጆችን ስናስተምር :
ልጆች ያልተፈቀዱ የግል አካላቸው እንዳይነካ ይጠብቃሉ
ያልተገባ ንክኪ የመለየትና ለወላጅ የማሳወቅ ልምድ ያዳብራሉ
የስሜት አቅጣጫውን የመለየት አቅም ይኖራቸዋል
ለብዙዎቻችን ትልቁ ራስ ምታት፣ ይህንን ጉዳይ በየትኛው እድሜያቸው እናሳውቃቸው የሚለው ነው:: በዘርፉ ያጠኑ የስነልቦና ምሁራን፤ ²ልጆች ይህ ጉዳይ አይገባቸውም የሚለው አመለካከት ሊቀረፍ ይገባል² ይላሉ::
የስነ ልቦና ምሁራኑ እንደሚሉት፤ የሦስት አመት ህፃን አካላዊ ንክኪን የመረዳት አቅም አለው:: እናም ትክክለኛ ጊዜውን መጠበቅ አያስፈልግም:: ለሦስትና ለአራት አመት ህፃን በጥቅሉ ማስረዳት ይቻላል:: ይሁንና መሠረቱ የሚጣለው ግን ልጆች በሁለት አመታቸው የሰውነት ክፍላቸውን እንዲለዩ በማስተማር ነው፡፡ በዚህ ወቅት ያልተፈቀደ የግል አካላቸው ክፍል መሆኑንና በትክክለኛ ስያሜው መጥራት ይመከራል:: አሁን ጉዳዩ የሚመጣው ወላጆች ለልጆችቸው ሲያስተምሩ የልጆችን እድሜና የብስለት ደረጃ እንዲሁም እንዴት መግለፅ እንዳለባቸው ሊረዱ ይገባል ፡፡
ለወላጆች ምክረ ሃሳብ
ይሄ ነውር ነው፤አይነገርም፤ያሳፍራል የሚለውን አመለካከት መቅረፍ
ወላጆች፤ ልጆቻቸውን ያልተገባ (ምቾት የማይሰጣቸውን) አካላዊ ንክኪ፣ “እምቢ” የሚሉበት አመለካከት እንዲገነቡ ማሰልጠን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ወቅት እምቢ ማለታቸው አመፀኝነት ሳይሆን መትረፍያቸው መሆኑን ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ ከአመፀኛና ጉልበተኛ ለመዳን አንዱና ዋነኛ አዋጭ መንገድ መሆኑን ደጋግሞ ማስታወስ ይገባል፡፡
ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው፣ ወላጆች በጉዳዩ ዙርያ ልጆቻቸውን ሲያስተምሩ፣ ልጆች ራሳቸውን እንዴት እንደሚከላከሉና የእርዳታ ጥሪን እንዴት ማሰማት እንዳለባቸው ነው፡፡ ለምሳሌ አቁም (ሚ)፣አትንካኝ፣አልፈልግም፣እንዲሉ አልያም እንዲጮሁ እና እንዲሮጡ፣ ለእርዳታ እንዲጣሩ ማበረታታት ይገኝበታል:: በዚህ ወቅት የሚደረግ የእርዳታ ጥሪ የፍርሃትና የደካማነት መገለጫ ሳይሆን የጀግንነት አልያም የአሸናፊነት ምልክት እንደሆነ ማስረዳት ይጠበቃል::
ከቤተሰብ ጋር ሚስጥር እንደሌለ ማሳወቅ፡- የስነልቦና ባለሙያዎች፣ በወላጅና በልጅ መካከል ምንም ሚስጥር ሊኖር እንደማይገባና የውይይት መድረኮችን በመፍጠር ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ:: ጤና ቢሱ አካላዊ ንክኪ አንዱ መገለጫው፣ በአብዛኛው በሚስጥራዊ መልክ መያዙ ነው:: ተንኳሹ አካል ጉዳዩ በሚስጥር እንዲያዝ ፍላጎት አለው፡፡ እናም ወላጆች ይህንን ለመስበር ከልጆቻቸው ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባትን ሊፈጥሩ ይገባል::
ጤናማ እና ጤና ቢሱን አካላዊ ንክኪ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያስተምሩ፣ ልጆች በፍርሃት ውስጥ እንዲገቡ በሚያደርግ መልኩ አልያም አክብደውት ሳይሆን፣ በቀላልና በጫወታ መልክ ሊያደርጉት ይገባል:: ልጆች ስለ ጉዳዩ የሚማሩበት መንገድ፣ የምንፈልገውን ውጤት ያህል ወሳኝነት አለው፡፡ የትምህርቱ ዋነኛ አላማ፣ ልጆችን ከዚህ ክፉ ድርጊት በሚገባቸው ቃላትና እንደ የእድሜያቸው፣ በፍቅርና በርህራሄ በእውቀት ማስታጠቅ ነው፡፡ ወላጆችም ታዲያ ከሚያዩትና ከሚሰሙት ተነስተው፣ በፍርሃት ስሜት ውስጥ ተዘፍቀው ሳይሆን፣ ራሳቸውን ከዚህ ስሜት ገዝተው በተቻለ መጠን በመረጋጋት ቀለል አድርገው መግለፅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የልጆችን አካላዊ ክፍል እንዴት እናስተዋውቅ ?
ወላጆች የልጆችን አካላዊ ክፍል ሲያስተዋውቁ ስያሜውንና የግል በሌሎች ሊነኩ ያልተገቡ አካላቸውን ለይተው እንዲነግሯቸው ይጠበቃል፡፡ ወላጆች ገለፃውን በተለያየ መንገድ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡
የመጀመሪያው የልጆችን አካላዊ ክፍል የማስተዋወቂያ መንገድ፣ የሰውነት ክፍላቸውን በምስል በታገዘ መልኩ ገለፃ ማድረግን ይመለከታል፡፡ በዚህ መልኩ የሚሰለጥኑ ልጆች ሊነኩ እና ሊነኩ የማይገቡ አካላቸውን በደንብ እንዲለዩትና እንዲረዱት አቅም ይሰጣቸዋል::
ሁለተኛው ቀላሉ የገለፃ መንገድ ደግሞ በአሻንጉሊት መጠቀም ነው፡፡ ልጆች ከአሻንጉሊት ጋር ያላቸው ጥብቅ ትስስር ጉዳዩን ይበልጥ ለመረዳት እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ ወላጆች አሻንጉሊት በመጠቀም ገለፃ ሊያደርጉ ይችላሉ:: ወላጆች በጣቶቻቸው በመጠቀም ጤናማ እና ጤና ቢሱን አካላዊ ንክኪ ገለፃ ያደርጋሉ:: ወላጆች በሚያስረዱበት ወቅት የሚሳዩት ስሜት፣ የፊት ገፅታ እንዲሁም የድምፅ አወጣጥ፣ ልጆች ይበልጥ እንዲረዱትና መቼ እና የቱ ቦታ ሲነኩ ምን ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው እንዲረዱ ያግዛቸዋል፡፡
የወላጆች የፊት ገፅታ አንዱ የማስተማሪያ ስልት ነው:: ምቾት ለማይሰጡ ንክኪዎች “እምቢ” የሚሉበትን አኳኋን እንዲረዱ መሰረት ይጥላል:: በተመሳሳይ ደግሞ ጤናማ ንክኪው ደስታ፣ እረፍት፣ፍቅርና ርህራሄ ያለው መሆኑን፣ ወላጆች በሚያሳዩት የፊት ገፅታ፣ ልጆች በቀላሉ እንዲረዱ ያደርጋቸዋል፡፡
ሦስተኛው መንገድ የተረት መፃሕፍት በመጠቀም ገለፃ ማድረግን ይመለከታል፡፡ በአካላዊ ንክኪ ዙርያ የተፃፉ የተረት መፅሐፍትን በመግዛት ማስተማር ሌላኛው አማራጭ ነው፡፡ ይህ መንገድ በተለይ ልጆች ከተረት ጋር ያላቸውን ጥብቅ ትስስር በመጠቀም የሚቀርብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ልጆች ይበልጥ በቀላሉ እንዲረዱት ያግዛል፡፡
ይህንን ነውረኛ ድርጊት ለመከላከል እንደ ማህበረሰብ የአመለካከት ለውጥ ያስፈልገናል፡፡ በዚህም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ለቤተሰብ፣ ለጤና ባለሙያዎች፣ ለትምህርት ቤት ማህበረሰብ ሊሰጥ ይገባል፡፡ የመገናኛ ብዙሃን እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳትፎ ሊያድግ ይገባል፡፡ በተለይም ልዩ የልጆች ፆታዊ ጥቃት ማገገሚያ ማዕከላት በበቂ ሊገነቡ ይገባል፡፡ በመንግስት በኩል ደግሞ የህግ ማዕቀፉን በማጠናከር ቁርጠኛ አስፈጻሚ አካላትን ማብቃት ይጠበቃል፡፡
ከአዘጋጁ፡-
ጸሃፊው፤ ”የክቡር ልጆች የልጆችን ስነልቦና ለመገንባትና የስሜት ስብራት ለመጠገን የሚረዱ ቁልፍ መንገዶች“ አዲስ የቤተሰብ መጽሐፍ ደራሲ ሲሆን፤ በኢሜይል አድራሻው፡-
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ማግኘት ይቻላል፡፡
Saturday, 24 August 2024 00:00
ልብ ሰባሪው የልጆች ሰቆቃ
Written by ብርሃኑ በላቸው አሰፋ
Published in
ህብረተሰብ