ሕልፈተ ሕይወቱ ድንገተኛ መሆኑ ለበርካታ ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ አስደንጋጭ ነበር። የቴአትር እና የፊልም ባለሞያው ኩራባቸው ደነቀ በሚመጡት ዓመታት በርካታ የኪነጥበብ ስራዎችን ለመስራት አቅዶ ሲንቀሳቀስ መክረሙን የሚያውቁ ሁሉ ሐዘናቸው ከባድ ሆኗል።
አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ የተወለደው በ1957 ዓ.ም. በሐረር ከተማ፣ ልዩ ስሙ ሸንኮር በሚባለው መንደር ውስጥ ነበር። አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ በትወና በመድረክ ቴአትሮች ላይ ከ1982 ዓ.ም. ጀምሮ ከተሳተፈባቸው ስራዎች መካከል፤ በሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ‘የዝናቧ እመቤት’ እና ‘የገንፎ ተራራ’ ቴአትሮች፤ በአገር ፍቅር ቴአትር ‘የጨረቃ ቤት’፣ ‘ዓይነ ሞራ’፣ ‘ንጉሥ ሊር’፣ ‘ፍሬሕይወት’፣ ‘ጥሎሽ’፣ ‘አሉ’፣ ‘ጣውንቶቹ’፣ ‘ከራስ በላይ ራስ’ እና ‘የሸክላ ጌጥ’ ቴአትሮች፤ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባሕል አዳራሽ ‘የጫጉላ ሽርሽር’ ቴአትር፤ በራስ ቴአትር ‘ቅርጫው’ ቴአትር ይገኙበታል።
ኩራባቸው ተዋናይ ብቻ ሳይሆን ዳይሬክተርም ጭምር ነበር። ከዳይሬክቲንግ ስራዎቹ፣ ይልቁንም ካዘጋጃቸው የመድረክ ቴአትሮች በአገር ፍቅር ቴአትር ‘ስጦታ’፣ ‘ጥሎሽ’ እና ‘መዳኛ’ ቴአትሮች፤ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባሕል አዳራሽ ‘ሶስና’፣ ‘አንድ ክረምት’፣ ‘ጥቁሩ መናኝ’ እና ‘የጫጉላ ሽርሽር’ (ዝግጅቱ በቴአትሩ ተዋንያን ነበር) ቴአትሮች፤ በራስ ቴአትር ‘ትንታግ’ የተሰኘ ቴአትር በማዘጋጀት ተሳትፏል።
በሌላ በኩል፤ ካዘጋጃቸው ሙዚቃዊ ድራማዎች መካከል፣ በተለይ በአንጋፋዋ አርቲስት አስናቀች ወርቁ ህይወት ላይ ተመስርቶ የተፃፈውና ያዘጋጀው ‘አስናቀች ኢትዮጵያ’ የተሰኘው ስራ በጉልሕ ይጠቀሳል። በበርካታ የራዲዮ ድራማዎች ላይ በተለይም፣ ደራሲ ሃይሉ ጸጋዬ በጻፋቸውና በቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም በተላለፉት በአብዛኛዎቹ ላይ ተሳትፏል።
በእነዚህ የኪነጥበብ ስራዎች ሳይወሰን፤ የቴሌቪዥን ድራማዎች ‘ገመና 1’ እና ‘ገመና 2’፣ እንዲሁም ‘እረኛዬ’ ድራማዎች በርካታ አድናቂዎችን ያፈሩለት ስራዎች ናቸው። አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ ከወይዘሮ አስቴር ታደሰ ጋር በ1985 ዓ.ም. በጋብቻ ተጣምሮ፣ ሁለት ወንዶች እና አንዲት ሴት ልጆች አፍርቷል።
ባሳለፍነው ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በድንገት ሕይወቱ ያለፈው አርቲስት ኩራባቸው፣ በነጋታው ማክሰኞ የቀብር ስነስርዓቱ ጓደኞቹ፤ የስራ ባልደረቦቹ እንዲሁም ሌሎች አርቲስቶች፣ ብሎም በርካታ ሕዝብ በተገኘበት በቀጨኔ መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
Published in
ህብረተሰብ