“የጨነቃት አይጥ ከድመት ትዋጋለች”
ጀግንነት ከባህል ጅረት የሚቀዳ የአስተሳሰብ/የአመለካከት ውጤት ይሆን? ማንኛውም ሰው በትንሹም በትልቁም ጉዳይ ተነስቶ ሌላውን ጀግና ወይም ፈሪ ሲለው ይገርመኛል፡፡ ደፋርነትና ጀግንነት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
ጀግኖች ሁሉ ደፋሮች ናቸው፤ ደፋሮች ሁሉ ግን ጀግኖች አይመስሉኝም፡፡ “ጀግንነት” የተሰኘው ንድፈ ሃሳብ (አስተሳሰብ) ከታሪክ አተራረክ ቃና አና ከባህል ጋር የተሰናኘና አንድ ሕዝብ “የሚኮራባቸውን ግዳጆች/ሥራዎች ፈጽሞ በመገኘት” ላይ የሚያተኩር ጉዳይ ተደርጎ በመቅረብ ለረጅም ጊዜያት ሲሠራበት ቆይቶ እንደነበረ አውቃለሁ፡፡
“ጀግንነት” በብዛት ተደጋግሞ የሚወሳው በታሪክ ውስጥ ነው፡፡ በተለይ በጦርነት ታሪክ ውስጥ፣ ጀግንነት በስሜት ተቀነባብሮ ጭምር ይነሳል፡፡ በዚህም ሳቢያ አንድ ሕዝብ/ሕብረተ-ሰብ የግሉና የጋራ ጀግኖች እንዳሉት ማየት ይቻላል፡፡ ይህንን የምታውቁት እያንዳንዱ ታሪክን የሚያነብ ሰው፣ በሚያነበው የታሪክ መጸሐፍ ውስጥ የየራሱን ብሔረ-ሰብ “ጀግና” ሲፈልግ የምታገኙት በመሆኑ ነው፡፡
ማነው ጀግና መባል ያለበት? ብሎ መጠየቅ እንደ ቀላልና የማይረባ ጥያቄ ተደርጎ ሊወሰድብኝ ይችላል ብዬ እሰጋለሁ፡፡ ይህ ጥያቄ ለእኔ ቀላል ሆኖልኝ አያውቅም፡፡ ጀግንነት ምን እንደሆነና ጀግና ለማሰኘትም መስፈርቶች ካሉ እነርሱን በዝርዝር ማቅረብ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ዛሬ ዛሬ (በግምትም ቢሆን ከመቼ ጀምሮ ይህ አስተሳሰብ ተቀባይነት እንዳገኘ ማወቅ ተገቢ መሆኑን በማመን) በአስተዳደርም፣ በዲፕሎማሲውም፣ በልማቱም መስኮች ጀግንነት እንዳለ ግንዛቤ ተጨብጧል፡፡
በዘመነ ደርግ ሚኒስትርና በኤኮኖሚ ሙያ አማካሪ የነበሩት አቶ ፋሲካ ሲደልል፣ ጀግንነት በጦር ሜዳ ተሳታፊነት ብቻ ተለክቶ መታየት የለበትም፤ በየሙያ ዘርፎችም ውስጥ አኩሪ ተግባር የሚፈጽሙ ሁሉ ጀግኖች ናቸው በማለት ኒሻንም ይሁን ዕውቅና እንዲሰጣቸው ጥረት አድርገው እንደነበረ ሰምቼ ነበር፡፡ በጦርነት አውዶች ዜና ጆሯቸው ጭው ያለው የደርግ አባላት የሰሟቸው አልመሰለኝም፡፡
በአመዛኙ ጀግንነት ከጦርነት አዋቂነትና ከጦር ሜዳ “ጀብዱ”ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ዝና ሆኖ የቆየውን ያህል፤ በዚህ ዘመን ደግሞ የልማት ጀግና፣ የአስተዳደር ጀግና፣ የሰላም ጀግና፣ የምርምር ጀግና፣ የስፖርት ጀግና፣... በመባል የትኛውም መልካም የሆነ ሕዝብንና አገርን (ዓለምን) የሚጠቅም ሥራ ሁሉ ጀግንነት በመሆን እውቅና እየተሰጠው ይገኛል፡፡
የጦር ተዋጊ ብቻ ጀግና ከተባለ፣ አንዳንዴ በህብረተሰቡ መለኪያ ፈሪ የተባለ ሰው ጀግና ተብሎ ለመጠራትም ይችል ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ለምን ብሎ መጠየቅ ግን አግባብ ነው፡፡ ኋላ ላይ እመለስበታለሁ፡፡
ወጣት በነበርኩበት ጊዜ ካነበብኳቸው ታሪኮች፣ በቤተ ሰብና በሌሎች የአገሬ ሰዎች ከተነገሩኝ የጀብድ ሥራዎች በመነሳት፣ ጀግንነት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ብርቅዬ ተግባር እንደሆነ አድርጌ እቆጥር ነበር፡፡ “ዘራፍ” ብሎ መሸለል በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረና ያለ መሆኑንም አውቃለሁ፡፡ ግን ሌሎች አገሮች የሚሸልሉበት ጀብዱ ይኖራቸዋል ብዬ ጠይቄ አላውቅም፡፡ የሚገርመው ለአቅመ አዳም ከደረስኩም በኋላ ይኸው አስተሳሰቤ ከኔ ጋር ተጣብቆ ለብዙ ዓመታት መቆየቱ ነበር፡፡ ታዲያ ጀግንነትን ያቆራኘሁት ከጦርነት ፍልሚያና ከውጤታቸው ጋር ብቻ እንደ ነበረ አልሸሽግም፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከድፍረት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው ለጀግንነት የሚያሳጩት፡፡ ሁሉም ሕዝብ (ብሄረ-ሰብ) የራሱ የጀግና መግለጫ አለው፡፡ መግደልም መሞትም እንደየሁኔታው በጀግንነት ሊያስጠራ ይችላል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር ውስጥ ወደ ውጭ ለመውጣት ዕድል ያገኘሁት ወደ ቡልጌሪያ ነበር፡፡ በ ዩኒዶ (UNIDO) ስኮላርሺፕ ከሁለት ወራት በላይ በቡልጌሪያ ቆይታ አድርጌአለሁ፡፡ ጀግንነት በኢትዮጵያ ብቻ በሞኖፖል ያልተያዘ መሆኑን እዚያ እንዳለሁ ነበር የተረዳሁት፡፡ የቡልጋሪያ ዜጎች ከኦቶማን ቱርኮች ጋር ያደረጉትን ለምዕተ ዓመታት የዘለቀ ፍልሚያ (የቅኝ ግዛት ታሪክ) ይተርኩላችኋል፡፡ የቡልጌራውያንን ጀግንነት እና መስዋዕትነት ብቻ አይደለም የምትሰሙት፡፡ ማንም ሊደፍራቸው የማይችል መሆናቸውንም ጭምር ነው እስኪሰለቻችሁ የሚነግሯችሁ፡፡
ቡልጌራውያን በኦቶማን ቱርኮች ለአራት መቶ ዓመታት ያህል መገዛታቸው አንገታቸውን ያስደፋቸው ሕዝቦች አይደሉም፡፡ ይልቁን በታሪካቸው ያሳዩትን ተጋድሏቸውን (መግደልና መሞታቸውን) በፓናሮማ ውስጥ በሚታይ ትንግርት በሚመስል የስዕል ጥበብ ለመጣው ጎብኚ በሙሉ ያስጎበኛሉ (የዚህ ዓይነት የስዕል ጥበብ፣ በአድዋ የጦርነት ታሪክ ላይ የተመሠረተ ፓናሮማ፣ ኢትዮጵያም ቢኖር እያልኩኝ ለረዥም ዓመታት ተመኝቻለሁ፡፡ አሁንም ድረስ ያ ምኞቴ አልሞተም)፡፡
ሌሎች አገራት፣ ሁልጊዜ በአሸናፊነት መታየትን ብቻ ሳይሆን ላለመሸነፍ መጋደልንም (መሞትንም) የአንድ ታሪክ ክፍል አድርገው ያቀርቡታል፡፡ ፓናሮማው የቱሪስት መስህብም ነው፡፡ በፓናሮማው የምታዩት የጦርነት የተጋድሎ ታሪክ ልክ ትኩስ ደም እየፈሰሰው ያለ ቁስለኛ ያያችሁ እስከሚመስላችሁ ድረስ አፍዝዞ እንዲያቅለሸልሻችሁ ያደርጋቸኋል፡፡ ፓናሮማውን ሰልችታችሁ ሳይሆን፣ ትኩስ ደምና በሜዳ የወደቁ ሬሳዎችን ደጋግማችሁ “በማየታችሁ” የሚደርስባችሁ የማቅለሽለሽ ስሜት (nausea) ነው፡፡ የጀግንነታቸውን ታሪክ በጦርነት የስዕል አውድማ ውስጥ እንደ ጉድ ሲያበራዩት ትመለከታላችሁ፡፡ ይህንን አንድ በሉልኝ፡፡
አላማዬ በዓለም የዞርኩባቸውን ሥፍራዎች ማስቃኘት ሳይሆን፣ በሁሉም አገር በታሪኮቻቸው (እንደ ቋንቋውና ባህሉ) ላይ የተመሰረቱ የጀግንነት “ታሪኮች” መኖራቸውንና ሁሉም ራሱን እንደ ብቸኛ ጀግና የሚቆጥር መሆኑን ለማሳየት ብቻ ነው፡፡ በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩት እንደ ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አንጎላ፣ ማሊ፣ ግብፅ፣… ጀግኖች ነን፣ ነበርንም የሚሉ የጀግንነት ታሪክ በልበ-ሙሉነት ይተረኩላችኋል፡፡
የአንዲት ጊዜ ወይም ቅጽበት ክንዋኔ ብትሆንም እንኳን የሚንቋት አይደሉም፡፡ ጀግንነትን ከምን መለኪያ አንጻር አይተውት ይሆን ብላችሁ ራሳችሁን መጠየቅ አታቆሙም (ኢትዮጵያውያን ካለን የጀግንነት ግንዛቤ አንጻር)፡፡
የምትነግሩኝን ታሪክ ከየት አመጣችሁት የምልና የምጠይቅ እኔ ማነኝ? ብዬ ራሴን ወቅሻለሁ፡፡ “እንዴት ተደፈርኩ” ባህል በአፍሪካውያን ዘንድም አለ፡፡ አውሮፓም እንደዚያው ነው፡፡ አሜሪካን ጀግኖችዋን የምትዘክርበትን ወቅት የወሰነችና ለጀግንነትም ከፍተኛ ሥፍራ የምትሰጥ አገር ናት፡፡ እኔ ያየኋቸውን አገራት ጠቀስኳቸው እንጂ፣ በምድር ያሉት አገራት በሙሉ ጀግኖች እንደሆኑና የጀግንነትን ታሪክ የሚተርኩ የታሪክ ድርሳናት ያሏቸው ስለመሆኑ መፈተሽ ትችላላችሁ፡፡ ሁሉም የየራሱ ጀግና’ና ድርሳናት አሉት፡፡
በሽንፈት ውስጥ እንኳን አንድን ጀግና ፈልጎ ማግኘት ታሪክን ለማሳመር እንደ ጌጥ ይውላል፡፡ ጀግንነት ካልተወሳና ካልተወደሰ ጀግና ለመሆን የሚነሳሳ ትውልድ አይቀጥልማ! ወታደር ለመመልመልም ሆነ ጦርነትን ለመዋጋት/ለማሸነፍ መጀመሪያ የሌሎችን ጀግኖች ወኔ በዘማቹ ልብ ውስጥ ማስታጠቅ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ተዋጊ የሌሎችን ጀግኖች ዝና ሰምቶ ለመጀገንና ጀግና ተብሎ የሚያስጠራ ሥራ ለመሥራት በወኔ ይነሳሳል፡፡ በአገራችንም ሆነ በሌሎች አገሮች የምናየው ያንን ነው፡፡
ልቡ የፈራበት ወታደር እንኳን፣ በድንገት በጎኑ ተሰልፎ ባገኘው ደፋር ተዋጊ ወኔው ሊነሳሳ ይችላል፡፡ በዚያች ድፍረትን በተላበሰባት ቅጽበት በሠራት “ጀብዱ” ጀግና ሊባል፣ እሱን ያደፋፈረው “ልበ ሙሉው” ወይ በሞት አለያም በለስ ስላልቀናው ጀግና ላይባል ይችላል፤ እንደውም እንደ ሁኔታው ተገምግሞ ፈሪ ሊባልም ይችላል፡፡
ከጦርነት ፍልሚያ የአፈጻጸም መመዘኛ አኳያ፣ የጀግንነት መስፈርት አንድ ዓይነት መስሎ ቢታይ ብዙም አያስደንቅም፡፡ በጦርነት ውስጥ ፈሪው ጀግና፣ ጀግናው ደግሞ ፈሪ የሚባልባቸው “ቅጽበቶች” መከሰታቸው ያጋጥማል፡፡ ታሪክም የዚያ ውጤት ይሆናል፡፡
ጀግንነት የልብ (የደፋር ሀሳብ) መለኪያ ሳይሆን የድርጊት መለኪያ ይመስለኛል፡፡ ልብና ድርጊት ብዙም የሚነጣጠሉ ባይሆንም፣ የልብን ሀሳብ ማወቅ እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ ልብ ሁሌም በቋሚነት ይሠራል፤ ድርጊት ግን የአጋጣሚ ነገር ሆኖ አንዳንዴ በድክመት ወይንም በጥንካሬ የመደምደም ዕድል አለው፡፡ ሃሳቤ፣ ጀግንነት በጦርነት ወይም እልህ በቀላቀለ ጸብ ውስጥ የሚበቅል ማስፈራሪያ ወይንም መኮፈሺያ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ መሆንም አይገባውም ለማለት ነው፡፡
አንድን ሰው በቡድን ሆነው ዘራፍ እያሉ ቢገድሉ ጀግንነት ሊባል ነው? የራሱን ክብር ከፍ ለማድረግ ሲል የሌላውን ክብር የሚያሳንስና፣ ሌላውን ለማኮሰስ የሚደፍርን ደፋር ሰው ጀግና ልንል ነው? ይህ ሁሉ በእውንም፣ በሶሻል ሚዲያም ሲከወን አያለሁ፣ እሰማለሁ፡፡ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ማስተዋል፣ ትዕግሥት፣ ትህትናም በየራሳቸው ጀግንነት ናቸው፡፡ ሰው ያለውን እንጂ የሌለውን አይሰጥም፡፡ በባዶ የሚፎክርና የሚያስተጋባ ባዶነቱን ለሌሎች ይሰጣል፡፡ በማስተዋልና በትዕግስት የሚናገር ደግሞ ማስተዋልን ለሌሎች ያቀርባል፡፡ ይኸው ነው፡፡ ሰው የሌለውን ከየት አምጥቶ ይሰጣል?
ጀግንነት ምንጊዜም ያለንን ሳንቆጥብ በቅንነት ለሌሎች መስጠት ነው፡፡ ደፋርነት ግን ጠንካራ “የደም ፍላት” ስሜት ወይንም ከጭንቀትና ከቁጭት የሚነሳ፣ በምክንያት የማሰብን ቀልብ የሚፈታተን ድርጊት በመሆን ሊከሰት የሚችል ስሜት ነው፡፡ ደፋርነት ለመልካም ነገር ሲውል ራስንና ሌሎችን ለመከላከል ይጠቅማል፡፡ ያስመሰግናል፡፡ ደፋርነቱ ለመልካም ነገር ካልሆነ ደግሞ ውድቀትና ጸጸት ላይ ይጥላል፡፡ ጀግና ምንጊዜም ደፋር ነው፡፡ ድፍረት ሁሉ ግን ወደ ጀግንነት ጎራ አያደርሱም፡፡ እስቲ በየሜዳውና በየሶሻል ሚዲያው “ጀግና” እየተባሉ የሚጠሩትንና እንዲባሉም የሚሹትን አጢኗቸው? እውን ጀግኖች ናቸው ወይንስ ደፋር?
ጀግንነት ከአንድ አቅጣጫ አመለካከት (በጦርነት ውስጥ ከመሞትና ከመግደል) ወጣ ተደርጎ መታየት እንዳለበት ከማመን ጋር፤ ለጀግንነት ዝርዝር መለኪያዎችን ሰይሞ/አስቀምጦ ጀግኖችን ማፍራት የታሪክን ሚዛን ከፍ እንደሚያደርገው ግልጽ ነው፡፡ ደፋሩ ሁሉ ጀግና እየተባለ ሲጠራ ቢደንቀኝ ነው፤ ጀግናው ጀግና፤ ደፋሩ ደግሞ ደፋር እንዲባል ካለኝ ምኞት ይቺን ልጽፍ የተነሳሳሁት፡፡ ጀግንነትና ድፍረት ለየቅል ናቸው፡፡ ሰውም ሆነ እንስሳት ሲጨንቃቸው ደፋር የሚሆኑባቸው ሁኔታዎች በርካታ ናቸው፡፡
“የጨነቃት አይጥ ከድመት ትዋጋለች” (“driven into a corner, even a mouse can fight a cat”) የሚል አባባል ያነበብኩ ይመስለኛል፡፡ ሰላም፡፡
Sunday, 01 September 2024 20:09
ደፋር ሁሉ ጀግና ነው?
Written by ስንታየሁ ገ/ጊዮርጊስ
Published in
ህብረተሰብ