Sunday, 01 September 2024 20:11

የአዲስ ዓመት ባዛርና ኤክስፖ ተከፈተ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አስመጪዎች እና አምራቾች ከሸማች ሕብረተሰቡ ክፍል እንደሚያገናኝ የታመነበት የአዲስ ዓመት ባዛር እና ኤክስፖ ተመርቆ ተከፍቷል። ባለፈው ሐሙስ ነሐሴ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. የተከፈተው ባዛር እና ኤክስፖ እስከ አዲስ ዓመት ዋዜማ እንደሚቆይ ተነግሯል።
በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልመሃዲን፣ የባሮክ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ብርሃኑን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች ተገኝተዋል። ሚኒስትር ደኤታዋ ወይዘሮ ነፊሳ ባደረጉት አጭር ንግግር፤ “ንግግር ለማድረግ ሳይሆን ለሸመታ ነው የመጣሁት” ያሉ ሲሆን፣ የባዛሩ መሪቃል “ስለሰላም” መሆኑን አመልክተው፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በሰላም ዙሪያ ከሚሰሩ አካላት ጋር በትብብር ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህ የአዲስ ዓመት ባዛር እና ኤክስፖ ሸማቹ የሕብረተሰብ ክፍል በዓልን ምክንያት አድርጎ ከሚገጥመው  የዋጋ ንረት በተመጣጣኝ እና በቅናሽ ዋጋ ከራሱ ከአምራቹና ከአስመጪው የሚገበያይበት እንደሆነ ተጠቅሷል። የተለያዩ የመዝናኛ፣ የምግብ እና የመጠጥ ፕሮግራሞች እምደሚገኙበት በተነገረለት በዚህ ባዛርና ኤክስፖ፣ ከ2 ሺህ በላይ አስመጪና ሻጮች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።
በባዛርና ኤክስፖው ላይ በቀን ከ7 ሺህ እስከ 10 ሺህ ሸማቾች እንደሚገኙ የተገመተ ሲሆን፣ ዕውቅ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ለታዳሚዎች ያቀርባሉ ተብሏል። ኢትዮ ቴሌኮም እና ዳሽን ባንክን ጨምሮ፣ በርካታ ተቋማት ባዛር እና ኤክስፖው አጋር እንደሆኑም ተጠቅሷል።

Read 462 times