”ለተፈናቃዮች በቂ እርዳታ እየቀረበ አይደለም”
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ስልጤ ዞን በደረሰው የጎርፍ አደጋ ከአንድ ሺህ በላይ አባወራዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ። ለተፈናቃዮች እየቀረበ ያለው ዕርዳታ ከብዛታቸው ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑም ተጠቁሟል።
የዞኑ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ወሲላ አሰፋ፤ የጎርፍ አደጋው የደረሰው በሁለት ወረዳዎች፣ በስምንት ቀበሌዎች ላይ እንደሆነ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። ችግሩ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ መፍትሔ ለማምጣት ርብርብ እየተደረገ ነው ያሉት ሃላፊዋ፣ ሰዎቹን ከአደጋ ቀጣና የማውጣትና እንዲጠለሉ የማድረግ ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።
ከአንድ ሺህ በላይ አባወራዎች የጎርፉ አደጋ ከደረሰባቸው አካባቢዎች እንዲወጡ የተደረጉ ሲሆን፤ ተፈናቃዮቹ በትምሕርት ቤቶች፣ በአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋምና ዘመዶቻቸው ዘንድ እንዲጠለሉ መደረጉን ሃላፊዋ ገልፀዋል። ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ከክልል ጀምሮ የዞን፣ የወረዳና ሌሎች አካላትን በማስተባበር ለተፈናቃዮቹ እየቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
“ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ስራዎች ተጀምረዋል። የችግሩ መነሻ የመኸር ዝናብ መጠን እጅግ በጣም ስለጨመረ ደለል የሚወርድበትን አቅጣጫ ውሃ ሞልቶታል። ጥናት የማጥናትና የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ቦታውን እንዲያዩ የማድረግ፣ ቀጣይ የዕቅዳቸው አካል እንዲያደርጉ እየሰራን ነው” ብለዋል፣ ወይዘሮ ወሲላ።
የተፈናቃዮቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ሃላፊዋ ያስረዱ ሲሆን፣ “አስፈላጊውን ዕርዳታ ለተፈናቃዮቹ ማቅረብ ያስፈልጋል” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም፣ “ከተፈናቃዮች ብዛት ጋር የምናቀርበው ዕርዳታ በቂ አይደለም፤ የተለያዩ አካላት እንዲያግዙን ጥሪ አቅርበናል።
የባንክ ሀሳብ ተከፍቶ ዕገዛ እንዲሰባሰብ እየተደረገ ነው። ክልሉ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን እያቀረበ እያገዘን ነው” ብለዋል።
ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረሰናይ ድርጅቶች ዕርዳታ እያቀረቡ እንደሆነ የተጠየቁት ወይዘሮ ወሲላ ሲመልሱ፣ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ድጋፋቸውን እየለገሱ ነው።
ሌሎችም ሁኔታውን እያዩ ሊለግሱን ይችላሉ” ብለዋል።
በዞኑ በደረሰው የጎርፍ አደጋ በበልግና መኽር የለማ አንድ ሺህ ሄክታር ላይ የነበረ ሰብል በውሃ መጥለቅለቁን የጠቆሙት ሃላፊዋ፤ “ዝናቡ በዚሁ ከቀጠለ ሰብሉ ከጥቅም ውጭ ይሆናል።” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
Sunday, 01 September 2024 20:14
Published in
ዜና